>
5:18 pm - Sunday June 16, 1393

ተከበሩ ዶ/ር ዐብይ ዛሬ ከፓርቲም ከአንድ ጎሳም በላይ ሆነዋልና ላጠቃላይ አገሪቱ ያስቡላት! (ደግፌ አስረስ)

ለተከበሩ ዶ/ር ዐብይ ዛሬ ከፓርቲም ከአንድ ጎሳም በላይ ሆነዋልና ላጠቃላይ አገሪቱ ያስቡላት !  
ደግፌ አስረስ
ብዙ ነገር አያምርባችሁም ሲሉን አምነን ያላማረብንን መተው አለብን ብየ ከወሰኑት ሰዎች አንዱ ነኝ። እርስዎም መለስን መምሰል አያምርብዎትም ይተዉ! ኦህዴድም ህወሀትን መምሰል አያምርበትም ይተው!
በአከታታይ በርካታ ግቦች አስቆጥረው ብዙ ነጥብ ስለያዙ በከንቲባ ጉዳይ ላይ በአዲስ አበባ በአንዲቷ ጨዋታ ብዙ ግብ ቢገባቦትም ያልተጎዱ ሊመስልዎ ይችላል። በፓለቲካ ውስጥ ጨዋታው ዙር ይሁን ጥሎ ማለፍ ስለማይታወቅ በአንድ ጨዋታ መሸነፍ ከጨዋታ ውጪ ሊያረግዎት ይችላልና እጅግ ይጠንቀቁ!
የዘር ፖለቲካ መጨረሻው አያምርም። በርስዎ ዘመን እንኳ መጀመሪያው ማስጠላት ጀምሯል። አዲስ አበባ ህዝብ ፊት ቆሞ መመረጥ የሚፈራው የማን ዘር ነው? እኛ ኦሮሞ ያልሆንን የለማ መገርሳን ዘር፣ የዐብይ አህመድን ዘር አንመርጥም? የደገፍናችሁኮ በናንተ ሂሳብ ከዘራችሁ ስለሆንን አይደለም! በርስዎ ላይ የተጣለውን ቦምብ በደም፣ በአጥንትና በህይወት ክፍያ ያከሸፉት ኦሮሞዎች ብቻ አይመስሉኝም።
በተለይ ሰፊ የሆነውን ኦሮሞ ወክለው እንደጠባቡ ህወሀት ከሰሩ በግል ለራስዎ ከዚያ በላይ ግን ሰፊ ትከሻ አለው ብለን ላመነው የኦሮሞ ህዝብ ታላቅ ውድቀት ነው። በዘር መሰጋሰግ ሀያ ሰባት አመት ለወያኔ ቢሰራ ሌላ ሀያ ሰባት አመት ለኦሮሞ አይሰራም። ቢሰራስ የተላ ዘረኛ መሆን ምኑ ነው የሚመረጠው? የኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ መለስና ህወሀት ያላቸውን ቦታ እያዩ ነው። ለርስዎም ሆነ ለኦሮሞ ህዝብ ከዚህ የከፋ ነግር አይኖርም። አንዳንዴም እናትዎ አማራ እንደነበሩ በህዝብ ፊት መናዘዙ ሊጠቅምዎት ይችላል። ከፓርቲም ከአንድ ጎሳም በላይ ሆነዋልና ላጠቃላይ አገሪቱ ያስቡላት!
Filed in: Amharic