>

የኢትዮ-ሱዳን የደንበር ውዝግብና፤በየወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ መንግስታት ምላሽ!!! (ቹቹ አለባቸው)

የኢትዮ-ሱዳን የደንበር ውዝግብና፤በየወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ መንግስታት ምላሽ!!!
ቹቹ አለባቸው
1. መንደርደሪያ
የሱዳን ጦር በተደጋገሚ እያደረገ ያለውን የአማራ ገበሬዎችን ወረራ በመቃወም በኢትዮጵያ የስአት አቆጣጠር ዛሬ ከ11/11/ 2010 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡00 ጀምሮ በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ እንደሚደረግ በማህበራዊ ሚዲያ ጥሪ እየተደረገ ነው፡፡ መጀመሪያ ሳየው እንዲሁ የግለሰቦች መስሎኝ ነበር፤ነገር ግን መልእክቱ በተደጋጋሚ ሲደርሰኝ አመንኩ፡፡ ስለሆነም በቲንሹ የግሌን አስተዋጽኦ ለማድረግ ብየ ይችን መረጃ ይዠ ወጥቻለሁ፡፡
2. የኢትዮጵ-ሱዳን ደነበር ውዝግብ ታሪካዊ አጀማመር፤
የኢትዮ-ሱዳን ደንበርን ውዝግብ ለመፍታት ስራ የተጀመረው በሚኒሊክ መንግስት ዘመን ሲሆን፤ እርሳቸውን የተኩት ንጉስ ኃ/ስላሴም የራሳቸውን ሙከራ አድርገዋል፡፡ ደርግም የተወሰነ እርምጃ ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳቸውም ጉዳዩን ከፍጻሜ አላደረሱትም፡፡ ግን ለምን ?የዚህን ዝርዝር ጉዳይ እኔ ባለችኝ ቲንሽ መረጃ መሰረት ቀጣይ የመጽሀፌአካል ስለማደርገው ያኔ መረጃውን በጥቂቱም ቢሆን ታገኙታላችሁ፡፡ ለዛሬው ግን የኢህአዴግ መንግስት ከኢትዮ-ሱዳን ደንበር አኳያ እየተከተለ ያለውን ነገር በአጭሩ መረጃ ለመስተት ነው፡፡
3. የኢህአዴግ መንግስትና የኢትዮ-ሱዳን ደንበር ጉዳይ
ኢህአዴግ በ1983 ዓ.ም ግንቦት ወር ስልጣኑን ከያዘ በኃላ፤ በሀገሪቱ የነበረውን አጠቃላይ የዴሞክራሲና ሰላም ጥያቄ ለመፍታት፤ መንግስታዊ መዋቅሩን ለመዘርጋት፤ የህዝብ ስልጣን ባለቤትነትን ለማረጋገጥ ወዘተ… ለመሳሰሉት ጉዳዮች ቅድሚያ ትኩረት በመስጠቱ እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ በነዚህና በመሳሰሉት ጉዳዮች ተወጥሮ ስለነበር፤ ሱዳን ደንበር እየገፋ መሆኑን ልብ ልብ ካለው ዋል አደር ያለ ቢሆንም ፤ ለችግሩ ግን ያን ያክል ትኩረት ሳይሰጠው ቆየ፡፡ ይህን የኢህአዴግ እንዝህላልነት የተረዱት የሱዳን ባለ ስልጣናት፤ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ ወደ ኢትዮጵያ ለም መሬቶች ( በተለይም አርማጭሆ፤መተማ፤ ማጠቢያና ቋራ አካባቢዎች)፤ እያስገቡ ዜጎቻቸው በስፋት እንዲያርሱ ሁኔታዎችን አመቻቹላቸው፤ ለደህንነታቸውም በርካታ የሱዳን ሰራዊት በከባድ መሳሪያ ታጅበው በተለይም በመተማ፤አርማጭሆና ቋራ፤ የእርሻ ቦታ ሰራዊት አሰፈሩ፡፡ የኢትዮጵያን ገበሬዎች ማሳደድና መግደል ጀመሩ፡፡ በተለይም ይህ ችግር ከ1986 -1987 ዓ.ም ድረስ ተባብሶ ቀጠለ፡፡ የችግሩ እየተባባሰ መሄድ ያስጨነቀው የኢትዮጵያ መንግስትም፤ በደንበር ያለው ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት ማድረግ ጀመረ፤ ሁኖም በሱዳኖች አሻፈረኝ ባይነት ሙከራዎች ሁሉ ሳይሳኩ ቀሩ፡፡ የሱዳን መንግስት ከአቅም በላይ በመሆን በሰላማዊ ሰው ላይ ጉዳት ማድረሱን ቀጠለበት፡፡ የሱዳን መንግስት ችግሩን በሰላማዊ መንገድም ለመፍታት ፈቃደኛ ሆኖ አልተገኘም፡፡
4. የኃይል እርምጃ የመውሰድ አስፈላጊነት፤
ሱዳን አስቸግራለች፡፡ ስለሆነም በ1988 ዓ.ም ታህሳስ ወር ላይ የኢትዮጵያ መንግስት በህገ-ወጥ መንገድ የተወሰደበትን መሬት ለማስለቀቅ በሱዳን ላይ ጠንከር ያለ ጦርነት ከፈተ፡፡ ጦርነቱ የተካሄደው በሁመራ ግንባር፤ በአብደራፊ፤በመተማና በቋራ አካባቢዎች በጠረፍ ቦታዎች አካባቢ ሲሆን ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኛው ድል አድራጊነት ተደመደመ፡፡ በሱዳን ተይዘውብን የነበሩትን መሬቶቻችንን ለማስመለስ ተቻለ፡፡ ይህንን ሁኔታ ተከትሎ በመንግስታችን በኩል ተላልፎ የነበረው መመሪያ( ያው ቃል ቢሆንም) ሱዳኖች፤
1. በቋራ በኩል- ከፋዝራ ወዲህ እንዳይሻገሩ፤
2. በመተማ በኩል- የጓንግ ወንዝን እንዳይሻገሩ፤
3. በአርማጭሆ በኩል ደግሞ ጓንግ ወንዝን፤አንገረብና ሱፍ ውሀ መገናኛውን ወንዝ እንዳይሻገሩ፤
4. በሁመራ በኩል- እስከ ልጉዲ ድረስ ተከብሮ እንዲጠበቅ፤ የሚል ነበር፡፡
5. የመወጠርና የማላለት አስፈላጊነት
ሱዳን አይታመንም፤ ክፉኛም ተበሳጭቶ ነበር፡፡ ስለሆነም ነቅቶ መጠበቅ አስፈላጊ ነበር፡፡ ስለሆነም ከዚህ ጦርነት በኃላ የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ መከላከያ ሰራዊት ከዘመናዊ መሳሪያ ጋር አስፈላጊ ከሆኑ የጠረፍ ቦታዎች ላይ በማስፈር ጥበቃውን አጠናከረ፡፡ በዚህም መሰረት የኢትዮጵያና ሱዳን ግንኙነት ከ1988 ከታህሳስ ወር ጀምሮ እስከ መጋቢት ወር 19992 ዓ.ም ድረስ ተበላሽቶና ተቋርጦ ቆየ፡፡ በ1992 ዓ.ም ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር( መለስ ዜናዊ) ወደ ሱዳን ሀገር ተጓዙ፡፡ ከወራት በኃላ ደግሞ የሱዳኑ ፕሬዝዳንት( ሀሰን አልበሽር) ወደ ኢትዮጵያ ጥሪ ተደርጎላቸው መጡ፡፡ ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፤በካርቱምና በገዳሪፍ ጉብኝት አደረጉ፡፡ ከዚህ በኃላ በሁለቱ አገሮች በፈረቃ ተከታታይ ስብሰባዎችና ውይይቶች ተካሄዱ፤ከነዚህ መካከል የሚከተሉት ዋናዋናዎቹ ነበሩ፡፡
5.1. የገዳሪፍ ስብሰባ- 1993 ዓ.ም ፡
§ በ1993 ዓ.ም በሱዳን ገዳሪፍ ክልል ልዑካን ቡድን አማራ ክልል ባለስልጣናት መተማ ሸከዲ ላይ ለ3 ቀን ያክል ስብሰባ ተደረገ፡፡ በመቀጠልም አንድ ቡድን ወደ ገዳሪፍ ተጓዘ፡፡ የዚህ ስብሰባ ( ገዳሪፍ ) ዋና አጀንዳ ነበረው፤ የሁለቱ አገር መሪዎች በተለያዩ ወቅቶች ተገናኝተው በሁለቱ ሀገር የተውጣጣ ኮሚቴ፤እንዲዋቀርና ስራ እንዲጀምር ስምመነት ስለተደረሰ የተለያዩ ኮሚቴዎችን ማዋቀር አንዱና ዋናው አጀንዳ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት የተለያዩ ኮሚቴዎች ተዋቀሩ፡፡ የተዋቀሩት የኮሚቴ አይነትና ብዛት( በገዳሪፍ መድረክ)፤
1. ደንበርና የፖለቲካ ጉዳይ ኮሚቴ፤
2. የንግድ ፤የመሰረተ ልማት ኮሚቴ፤- ከበሁለቱ መንግስታት ተውጣጣ 8 ኮሚቴ አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁ ሞ ነበር፡፡
3. የጤናና የግብርና ጉዳይ ኮሚቴ፤ ከሁለቱ አገራት የተወከሉ 6 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር ፡፡ በአጠቃላይ የገዳሪፉ ስብሰባ የተጠናቀቀው ኮሚቴዎችን በማቋቋምና ስራና ተግባራቸውን በማስቀመጥ ነበር፡፡
5.2. የባህርዳሩ ስብሰባ-1994 ዓ.ም፡
§ የገዳሪፍ ስብሰባ በተደረገ ከ3 ወር በኃላ ነበር የተካሄደው፡፡ የስብሰባው አላማ ቀደም ሲል በገዳሪፍ ላይ የተዋቀረው ኮሚቴ ወደ ስራው እንዲገባ የመወያያ ርዕሶችን መነሻ በማድረግ የደረሰበትን ድምዳሜ ለቡድን አባላት የጋራ ኮሚቴ እንዲቀርቡ በሚል ለኮሚቴዎቹ ርጭስ ተሰጠ፡፡ ኮሚቴው በየስራ ድርሻው ስብሰባ ጀመረ፡፡ በዚህምመሰረት የፖለቲካና የድንበር ኮሚቴውም ስብሰባውን ጀመረ፡፡ በሱዳን በኩል ቀረበው ሃሳብ፤ መሬታችን በኢትዮጵያ ተወሰደብን በተለይ ደግሞ በ1988 ዓ.ም በኢህአዴግ መንግስት ጦርነት ተከፍቶብን በርካታ ዜጎቻችን ከእርሻቸው ተፈናቅለዋል፤የእርሻ መሳሪያዎቻቸው ተወስዶባቸዋል፤ ለአንድ ምዕተ አመት ያክል ተወሰደብን መሬት እንዲመለስልን ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ አላገኘንም፤ ስለዚህ ይህ እልባት እስኪያገኝ ድረስ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1988 ዓ.ም ስናርሰው ነበረው መሬታችን እንዲመለስልን፤ ሌላው መሬት ጥያቂያችንም እንዲፈታልን፤የሚል አጀንዳ አቀረቡ፡፡ በኢትዮጵያ ኮሚቴ አጀንዳው ተቀባይነት እንደሌለው ተነገራቸው፡፡ ስምመነት ባለመደረሱ በቀጠሮ ታለፈ፡፡
5.3. የገዳሪፍ ስብሰባ፡ የዚህ ስብሰባ ዋነኛ አጀንዳ የንግድና የመሰረተ ልማት ንዑስ ኮሚቴ ሪፖርት ማዳመጥ ነበር፡፡
5.4. በሱዳን የደማዚን ከተማ ስብሰባ- 1994 ዓ.ም አጋማሽ፡
§ ከባ/ዳር ውጤት አልባ ስብሰባ በኃላ በደማዚን ከተማ ስብሰባ ተጀመረ፡፡ በዚህ ስብሰባ የፖለቲካና የደንበር ን/ኮሚቴ በሱዳን በኩል ያቀረበው አሁንም በድጋሚ የመሬት ጥያቄ ነበር፡፡ ሱዳኖች ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ጠንካራ ሃሳብ ያራምዱበት መድረክ ነበር፡፡ መግባበት ተፋ፤ስብሰባ ው ተቋረጠ፡፡ በማግስቱ የሁለቱ ሀገር መሪዎች የተስማመሙበት መልስ መጣ፤ “የደንበር ውዝግቡና የመሬት ጥያቄው ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆም፤ በሚፈታበት መንገድ እንዲፈታል” ፡፡
የኢትዮ-ሱዳን ግንኙነት እየተሸሻለ መምጣቱ
§ የሱዳን መንግሰት ከኢትዮጵያ መንግሰት ጋር የነበረውን ተቃርኖ ለመለወጥ ከተቅላይ ሚኒስትር መለስ ዛናዊ ጋር ግንኙነት ፈተረ፡፡ ግንኙነቱም እተተናከረ መጣ፡፡ የኢትዮ-ሱዳን መንግስታ ግንኙነት በመተናከሩ እንዲሁም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በመነሳቱ ሱዳን ተቃዋሚ ድርጅቶችን ሚያግዝ ሀይል ጠፋ፡፡የሁለቱም አገር መንግስታት በተለያዩ ጊዚያት በመገናኘት ስለ ሀገራቸው ውስጣዉ ጉዳይ ሲነጋገሩ ቆይተዋል፡፡
5.5. የአዲስ አበባው ስብሰባ- በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት
§ በዞህ ስብሰባ ተሳታፊ የነበሩት- የአማራ ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ፤ የሰ/ጎንደር አስተዳደር፤የመተማ ወረዳ አስተዳደር፤እንዲሁም ከትግራይ በኩል ደግሞ የክልሉ አስተዳደርና ጸጥታ ፤የሁመራ አስተዳደሪ፤ በጋራ የከፌደራል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ነበሩ፡፡ የአዲስ አበባው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዳራሽ ስብሰባ ዋነኛ አላማ የደንበር ውዝግቡን ለመፍታት የሚያስችል የጋራ ኮሚቴ መቋቋም ነበር፡፡ በዚህም መሰረት 3 አጀንዳዎች ውይይት ተደረገባቸው፡
1. የስፔሻል (Specila) ኮሚቴ ማቋቋም፤
2. የቴክኒክ ( Technique) ኮሚቴ ፤
3. ወደ ጥናት የሚያስገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን ማማቻቻት( Research History for future harmony) የሚል ነበር፡፡ በእነዚህ አጀንዳዎች መሰረት ኮሚቴው እንዲቋቋም በቀጠሮ ተይዞ ስብሰባው ተጠናቀቀ፡፡ ወድያውኑ ኮሚቴዎቹ ተቋቋሙ ወደ ስራ ገቡ፡፡
5.6. በሱዳን አፐር ናይል (ማላካን)ስብሰባ- 1995 አጋማሽ፡
§ የደንበር የጋራ ልማት ኮሚቴ ከአሶሳ ስብሰባ በኃላ በሱዳን ማላካን ላይ ስብሰባ ተጀመረ፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ ትኩረት ያደረገው አሶሳ ላይ ተደረሰው ስምምነት በተግባር ዋሉና ያልዋሉትን መገምገም ነበር፡፡ በዚህ ላይ የጠረፍ የፀጥታ ኮሚቴ እንቅስቃሴ ፤የጠረፍ ንግድ ፈቃድ እየተሰጠ ያለ መሆኑን ሪፖርት ቀርቦ ከተገመገመ በኃላ የነጭ አባይ ወንዝ ጉብኝት ተደርጎ ስብሰባው ተጠናቀቀ፡፡
5.7. የመቀሌው ስብሰባ -1996 ዓ.ም መጀመሪያ፤
§ የደንበርና የልማት ኮሚቴው ስብሰባ መቀሌ ላይ ሲጀመር ዋነኛው አጀንዳው የነበረው በመሰረተ ልማት ንኡስ የጋራ ኮሚቴ የቀረበውን ሪፖርት መገምገም መነበር፤ አደረገው፡፡ይሁን እንጅ በሱዳኖች በኩል ነገሩን እንደ አዲስ በማንሳት እልባት እስኪገኝ ከ1980-1988 ዓ.ም ስናርሰው የነበረው መሬታችን ይመለስልንና እንድናርስ እንሁን የሚል ነበር፡፡ ይሁን እንጅ በዚህ ነጥብ ስምምነት ሳይደረስ ቀረ፡፡
5.8. በሱዳን ስናር ከተማ ስብሰባ- 1996 ዓ.ም አጋማሽ፡
§ ከመቀሌው ስብሰባ በኃላ ሱዳን ውስጥ ስናር ከተማ ውስጥ የተደረገው ስብሰባ በአይነቱ ካሁን በፊት ከተደረጉት ስብሰባዎች የተለየ ነበር፡፡ በቀጥታ በሱዳን በኩል የቀረበው ሃሳብ ለ10 አመታት ያክል ስናርስው የነበረው መሬታችን ይመለስልን፤ በስፔሻል ኮሚቴ ከተጠና በኃላ ጥናቱ ወደ ኢትዮያ የሚል ከሆነ ለኢትዮጵያ ይሆናል፤ ወደ ሱዳን ከሆነ ደግሞ ወደሱዳን ይሆናል፤ እስከዛው ድረስ ግን እኛ ማረስ አለብን የሚል ነበር፡፡ አሁንም ስምመነት አልተደረሰም፡፡
6. የቴክኒክ ኮሚቴው ስራውን እንዲጀምር ስለመታዘዙ፤
በካቲት ወር 1995 ዓ.ም ስፔሻል ኮሚቴ ካርቱም ላይ ስብሰባ ካደረገ በኃላ ወድያውኑ የሁለቱ ሀገሮች ቴክኒክ ኮሚቴ ስራውን እንዲጀምር ታዘዙ፡፡ በመጀመሪያው ምእራፍ አወዛጋቢ በሆነው መሬት ላይ ማን እንደሚያርሰው ፤ከመቸ ጀምሮ እንደሚያርሰው፤መሬቱ ምን አይነት ምረት ያመርታል…ወዘተ ሚል መጠይቅ ሲኖው ፤ይህ መጠይቅ በሱዳንና በኢትዮጵያ ቴክኒክ ኮሚቴ በጋር የሚሞላ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ቴክኒክ ኮሚቴው በመተማ ምእራብ በኩል በቲሀ፤ በጀበል ስኳር፤ በመርትርሀድ፤ በአስከኒት፤ምዝገባ ተካሂዶ፤95% የሚሆነው አወዛጋቢ መሬት በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች እጅ መሆኑ ተመዘግቦ ተያዘ፡፡ 5 % ሚሆነው አወዛጋቢ መሬት ደግሞ በሱዳን ገበሬዎች እጅ እንደሚገኝ ተመዘገበ፡፡ ሱዳኖች ስራውን ለማደናቀፍ ሰበብ መፈለግ ጀመሩ፡፡ሁኖም ሁለቱ መንግስታት መመሪያ ሰጥው ስራው ቀጠለ፡፡
በዚህም መሰረት በሎሚናት፤ማሪያምና መተማ ዩሀንስ ዳር ያለው እርሻ መሬት ጥናት ተካሄደ፡፡ በዚህ አካባቢ ካለው ሰፊ እርሻ መሬት 96% ያህሉ ኢትዮጵያ አ/አደሮች መሬት መሆኑን ከተሟላ መረጃ ጋር በማቅረብ በኢትዮጵያ አ/አደሮች ስም፤4% የሚሆነው ደግሞ በሱዳን አ/አደሮች ስም ተመዘገበ፡፡ አሁንም በሱዳን ቴክኒክ ኮሚቴ የፈለጉትን ያክል መሬት ሳያገኙ መቅረታቸው የተለያዩ ምክንያቶች እያቀረቡ ስራው እንዲቋረጥ ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን አልተሳካላቸውም ጥናቱ ተጠናቀቀ፡፡
7. አባይ ፀሀየና የደለሎ መሬት
ይህ አካባቢ ከአብደራፊ መሬት ጋር ተያያዘ ሲሆን በጣም ሰፊና ገና ያልተነካ፤ድንግል መሬት ነው፡፡ ከዚህ ቦታ ቀደም ሲል ከ1980-1988 ዓ.ም መጀመሪያ ድረስ ሱዳን ባለሀብት በሱዳን መከላከያ ሰራዊት ታጅቦ በህገ ወጥ መንገድ ገብተው ሰፋፊ እርሻ መሬት ይዘው ሲተቀሙበት ቆይተው፤በ1988 ዓ.ም ታህሳስ ወር መጨረሻ እንዲወጡ ተደርገው ነበር፡፡ ከ1988-1995 ዓ.ም የኢትዮጵያዊያን ባለሀብቶችና ከ 5 ሽህ በላይ አ/አደሮች በዚህ አካባቢ ያርሱ እንደነበር ይታወቃል፤ከነዚህ መካል ንብረተንቱ የብአዴን የነበረው ዘለቀ እርሻ ልማት ከ23 ሽህ ሄ/ር በመሬት በላይ ይዞ ከ1988-1995 ዓ.ም ሲያለማ ቆይቷል፤ በኃላ ድርጅቱ ዘግቶ ወጣ፡፡ ከዚህ ውጭ ከ10 ሽህ ሄር በላይ የሚሆነው መሬት በደን የተሸፈነ ነበር፡፡ በዚህ መሬት ምዝገባው ሲጀምር፤ በሙሉ በኢትዮጵያዊያን አ/አደር እጅ ያለ መሆኑን ሲያውቁና መረጃ ሲቀርብላቸው በሱዳን ቴክኒክ ቡድን ያቀረቡት ሃሳብ ይህ መሬት በኢትዮጵያዊያን ገበሬዎች ብቻ መመዝገብ የለበትም፤ከ1980-1988 ዓ.ም በዚህ አካባቢ የሱዳን ባለሀብቶች ሲያርሱ ነበር የሚል መከራከሪያ አቀረቡ፤ለምሳሌ የሚከተሉትን ዘረዘሩ፤
1. አቶ ጀባር፤
2. ሙሀማድ- አቶ ጀባር ወንድም ፤
3. አቶ ሀምዛ፤
4. አቶ ኑርሁሴን፤
5. አቶ ከማልአረቢ፤
6. ድፋሻ ሻቢያ ማህበር፤
7. ሱዳን አረቢክ ሸሪክ ማህበር ፤
8. እንዲሁም እስከ 100 የሚደርሱ የሱዳን ተራ ገበሬዎች ለ10 አመት ያክል በእጃቸው የነበረውን መሬት የኢትዮጵያ መንግስት ያላግባብ ስላፈናቀላቸው፤እነዚህ መሬት መመለስና በራሳቸው ስም መመዝገብ አለበት፤ ይህ ካልሆነ ግን ስራውን አቋርጠን መውጣታችን ነው የሚል ሃሳብ አቀረቡ፡፡ ችግር ተፈጠረ፡፡ ሁለቱ መንግስታ ሰስራው ለጊዜው ይቁም አሉ፤ ስራው በቋራ ተጀምሮ ጥሩ እየሁደ ቆይቶ ደለሎ ሲደርስ ቆመ፡፡
8. ከገላባት እስከ ደለሎ በሄሊኮፕተር- 1995 ዓም መጨረሻ፡ 
 
ሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ 5 ያህል የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በሄሊኮፕተር ከሱዳኗ ከተማ ገላበት ይገባሉ፤ ከዚያ ወደደለሎ፡፡ እንዲሁም 5 ያህል የሱዳን ባለስልጣናት በተመሳሳይ ሁኔታ በሄሊኮፕተር ደለሎ ደረሱ፡፡ ከቡዙ ውይይትና ጭቅጭቅ በኃላ፤ አቶ አባይ ፀሀየ “ደለሎ ቁጥር 2፤ 3፤4 እና 5 የሚባለው ቦታ ለጊዜው የሱዳን ገበሬዎች እንዲሰጥና እንዲያርሱት ይሁን፤የሚል ቀጭን ትእዝ ሰጠ ተፈጸመ፡፡
ደለሎን መሬት እንስጥ ተከትሎ የመተማ ካቢኔ ውይይት፤
1. እኛ እጃችንን መስደድ አይገባንም ፤የታሪክ የታሪክ ተጠያቂ አንሆንም ይሉ ነበር፡፡
2. ዘመቻ “ማጤ ቀደም” በደለሎ በረሀ!ማስፋፈት፤ይህ ማለት አ/አደሩ ወደ ደለሎ በመዝመት መሬቱን ቀድሞ የያዘ ገበሬ እንዲጠቀምበት የማድረግ ዘዴ ነው፡፡
የሰ/ጎንደር ዞን አስተዳደር በመተማ አመራር ድርጊት ስለመቆጣቱ፤
§ ለሱዳን ይሰጥ የተባለውን መሬት ለአ/አደሮች የሰጠው አካል በአስቸኳይ ይጣራ!
§ የበርካታ የዞን አመራሮች ዘመቻ ወደ መተማ ፤
§ የሙሉአለም ካቢኔ መፈረካከስና ሙሉአለምን አጋልጦ የመስጠት ሁኔታ መፈጠሩ፤
§ አሳፋሪው የሙሉአለም ገሌ ክስና የ7 አመት እስራ ቅጣት፤
የነ አቶ አባይ ፀሐየ ውሳኔ በአማራ አ/አደሮች ላይ ጥሎት ያለፈው ጦስ ፤
§ ህውሀት አማራን ለተደጋገሚ በደል ዳርጎታል ፡፡ ለምና ታሪካዊ መሬቶቹን(ወልቃይትን፤ ሁመራን፤ጠለምትን፤ ራያን፤መተከልንና ሌሎቹን የአማራ እርስቶች) ከአማራ ቆርጦ ወደ ትግራይ ወስዷል፤ ወይም ወደ ሌሎች ክልሎች አስወስዷል፡፡ ህወሀት ይህ አልበቃው ብሎ አማራ ከሱዳን ጋር በሚዋሰንባቸው ቦታዎች ሁሉ የአማራን መሬት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት ተንቀሳቅሷል፡፡ በዚህ በኩል አባይ ጸሀየ ዋነኛው መሀንዲስ ነው፡፡ አቶ አባይ ተክሎብን የሄደው ጦስ ይሄው ዛሬ ለአ/አደሮቻችን መቅሰፍት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡
9. የአርማጭሆ ነገር፤
የአርማጭሆ አማራ ለመሬቱ ሟች ነው፡፡ አርማጭሆን ዳር ደንበር ከጥንት ጀምሮ አስከብሮ ኖሯል፡፡ ስለሆነም የአርማጭሆ ህዝብ በሱዳን በኩል የቀረበው መሬት አምጡ ጥያቄ፤ እንደ እግር እሳት እየፈጀውም ቢሆን ፤ጉዳዩን በንቃት መከታተል ጀመረ፡፡ ይህ አሁን ጓንግ ወዝን በመሻገር ሱዳን የይገባኛል ጥያቄ ሚያነሳበት መሬት ፤ለረዥም ጊዜ በኢትዮጵያዊያን አ/አደሮች እጅ የኖረ፤መሆኑን አ/አደሩ ከልምዱ ያውቀዋል፡፡ ይሁን እንጅ ሱዳኞች በአርማጭሆ ግንባር ያነሱት የመሬት የይገባኛል ጥያቄ ልክ እንደ መተማና ቃራው ሁሉ በጥናት ላይ ተመስርቶ መፈታት ነበረበትና፤ ልክ በመተማና በቋራ አካባቢዎች እንደተከናወነው ሁሉ በአርማጭሆም በተመሳሳይ መንገድ ተተገበረ፡፡
በሂደት እንደተረዳሁት በአርማጭሆ ግንባር በተካሄደው የማካለል ስራ፤ በአርማጭሆ ግንባር በ1988 ዓ.ም በጦርነት ያስከበርናቸውን አንዳንድ ቦታዎች አሁንም አስከብረን የቀጠልን መሆኑን አውቂያለሁ፤ ይህም ጓንግ ወንዝን ተከትሎ ከአሲራ እስከ ሱፍ ውሀ ያለውን መሬት እንደሚሸፍን ተገንዝቢያለሁ፡፡ ይሁን እንጅ በእጃችን ገብቶ የነበረ በርካታ መሬት ግን እንደገና በሱዳኖች እጅ መግባቱን ሰምቻለሁ፡፡ በዚህ በኩል ለጊዜው በሱዳኖች እጅ መልሶ የገባውን የመሬት ስፋት መረጃ ባላገኝም፤ሰፊ መሬት እንደተሰጠ ግን መረጃዎች አሉ፡፡ የተሰጡት መሬቶችም በዋናነት በስናር፤ኮር ሁመር፤ኮረደም አካባቢዎች ናቸው፡፡ ይህም ማለት ጓንግ ወንዝን እያካለለ ወደ ኢትዮጵያ ገባ በማለት፤ ከአሲራ እስከ ስናር( ደለሎ ቁጥር 1 ድረስ ያለውን ያካትታል) ማለት ነው፡፡
የአርማጭሆ ህዝብ መሬቱን አሳልፎ ላለመስጠት ያደረጋቸው ዋና ዋና ተጋድሎዎች፤
1. መሬታችንነ አሳልፈን አንሰጥም የሚል ተደጋገሚ ቁጣ፤
2. በዞን አመራሮች ፊት ጥይት በመተኮስ ቁጣን መግለጽ፤
3. የከሸፈው የሱዳን ከተሞችን የማቃጠል ዘመቻ፤
10. የጥምር ኃይል (Joint Force)፤ ማቋቋም ሌላው የአማራን መሬት ለሱዳን አሳልፎ የመስጠት ዘዴ፤
በኢትዮ-ሱዳንን ደንበር አካባቢ ያለው ውዝግብ አንዴ ሞቅ፤ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ ዘልቋል፡፡ አንዳንዴ በሚከሰቱ የደንበር ላይ ግጭቶች፤በሁለቱም ወገን ከባድ ጉዳቶች ተስተናግደዋል፡፡ በተለይም በሱዳን በኩል ጥቃቱ በመደበኛ ወታደርና በካባድ የጦር መሳሪያ ተደግፎ ስለሚፈጸም በአማራ አ/አደሮች ላይ ተከታታይና ከባድ ጉዳቶች ተስተናግደዋል፡፡ የግጭቱን እየተባባሰ መሄድ ተከትሎ የሁለቱ መንግስታት በደንበሩ አካባቢ ከእንቅስቃሴ ነጻ የሆነና ቦታ እንዲመረጥ፤ በተወሰኑ ቦታዎችም የሁለቱ መንግስታ ሰራዊት በመስፈር የፀታውን እንዲቆጣጠር ስምምነት ተደረሰ፡፡ በዚህም መሰረት በመጀመሪያ ላይ የጥም ጦሩ ሚሰፍርባቸው አራት ቦታዎች ተመረጡ፡
1. በአርማጭሆ ግንባር— አቡጢርና የመሰረት መቅረጫ( በረከት ኑሪ አጠገብ)፤
2. በመተማ ግንባር—-ቲሀ፤
3. በቋራ ግንባር ——-ሰኞ ገበያ( ሱዳኖች ጀበል ከለዋ እንደሚሉት ሰምቻለሁ)፡፡
በዚህ መሰረት ፕሮፖዛሉ ከተሰራ በኃላ ወደ ተግባር ለመግባት ይቻል ዘንድ የሚመለከታቸው አካላት መፈረምና ስምምነት መግለጽ ነበረባቸው፡፡ ይህም ተደረጋው ሱዳን ውስጥ ገዳሪፍ ከተማ በተደረገው ስብሰባ ላይ ነበር፡፡ በዚህ ወቀት የአማራ ክልል ተወካዮች ( የአሁኑ ፕሬዝዳንታችን እንደመሩት አውቂያለሁ)፤ የተለያዩ ጥያቄዎችን አነሱ፡ አንደኛ ነብስ ገበያና ጀበል ከለዋ የሚባሉት ሁለት ቦታዎች አንድ ናቸው፤ ትክክለኛ መጠሪያውም ነብስ ገበያ ነው የሚባልና ይስተካከል፤አንድ ቦታ መሆኑ ይታወቅ አሉ፡፡ ሱዳኖች አይደለም ሁለቱ ቦታዎች የተለያዩ ናቸው አሉ፤በዚሁ ታለፈ፡፡ ሁለተኛው ነገር ደግሞ፤- አቡጢር፤ የመሰረት መቅረጫ እንዲሁም ቲሀ የተባሉት ቦታዎች በኢትዮጵያ መሬት ውስጥ የሚገኙ እንጅ ቦረደር ላይ ስላልሆኑ እነዚህ ላይ የጥምር ኃይል ሊሰፍር አይገባም፤ በተለይም አቡጢር የሚባለው ቦታ ከደንበራችን እስከ 30 ኪ.ሜ ገባ ብሎ እንደሚገኝ፤ለማስረዳት ተሞከረ፡፡ በወቅቱ ለፊርማ ቀርቦ ነበረው ሰነድ በአማራ ክልል ተወካዮች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ጉዳዩ እንዲያድር ተደረገ፤ ማታ ለገድሻ ነገሩ በደንብ ተነግሮታል፤አሁን ነገሩ በደንብ ገብቶታል፡፡ ገድሻም በበነገታው ይህን ጉዳይ አሁን አልፈርምም በጥናት ይታይና እንደገና እናየዋለን በማለቱ ለጊዜው መሬታችንነ አሳልፎ ለመስተት ታስቦ የነበረውን ሙከራው አከሸፈ፡፡ በዚህም መሰረት፤አቡጢር፤ መሰረት መቅረጫና ቲሀ አካባቢ ታስቦ የነበረው የጥምር ሀይሉን የማስፈር እቅድ ሳይሳካ ቀረ፡፡ ሁኖም ወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ እና ኢታማጆር ሹሙ የነበሩት ጀኔራል ሳሞራ የኑስ የጥምር ሀይሉ ስለሚሰፍርባቸው ቦታዎች ሰምምነት መፈረማቸው ታውቋል፡፡
ይሁን እንጅ ሰኞ ገበያ ላይ ታስቦ የነበረው የጥምር ኃይል የማስፈር እቅድ ለሱዳኖች በሚያመች መልኩ ተከናዋነ፡፡አስቀድሞ የተፈራው የነብስ ገበያ ነገር ተደራራቢ ሁኖ ተገኘ፡፡ ሁለቱ ሰራዊት ሰፈሩ፤የኢትዮጵያ ሰራዊት ከነብስ ገበያ እንዲወጣ ተደረገ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ይሄው ይህ ከባቢ የግጭት ማእከል ሁኖ ቀጥሏል፤አ/አደሩ ተረጋግቶ አያርስም፤ የአማራ ገበሬዎች ይገደሉበታል፡፡
11. የኢትዮ-ሱዳን የደንበር ውዝግብና
 የብአዴን ሚና፤
እውነት ነው በሁለት አገሮች መካከል የሚነሳ የደንበር ውዝግብ ባለቤቱ የፌደራል መንግስት ነው፡፡ ይሁን እንጅ ክልሎችም ድርሻ ነበራቸው፡፡ በዚህ በኩል የብአዴን መንግስት በኢትዮ-ሱዳን የደንበር አፈታት ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበረው፡፡ በስፔሻል ኮሚቴ፤በቴክኒክ ኮሚቴ፤ወዘተ ተሳትፏል፡፡ አባይ ፀሀየ የደለሎን መሬት ለሱዳኖች ሲሰጥ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች አብረው ነበሩ፡፡ ስለሆነም በዚህ በኩል ለሚነሳ ጥሩም ሆነ ጥሩ ያልሆነ ነገር የብአዴን አመራር፤ ለጥሩ ስራው ምስጋና፤ እንዲሁም ጥሩ ላልሆነው ስራው ሙሉ ሀላፊነት አለበት፡፡
12. መፍትሄ
 
§ ዘለቄታዊ መፍትሄ ያስፈልገናል፡፡ ለዚህ ደግሞ መፍትሄው በ1988 ዓ.ም በጃችን አስገብተነው የነበረውን መሬት መልሰን በእጃችን ማስገባት ነው፡፡ እኔ ከልምዴ እንዳየሁት በተለይም በአርማጭሆ ግንባር፤ የአርማጭሆ ህዝብ ኳንግ ወዲህ ሱዳን ተሸግሮ እንዲያርስ ይፈቅድለታል ብየ አልገምትም፤ ምን አልባት መሬቱ በሱዳናዊ ገበሬ ስም ሁኖ ተጠቃሚው ግን የኛ ገበሬ ሊሆን ይችላል( በኪራይ)፡፡ ከዚያ ውጭ ሱዳን ጓንግ ወንዝን ተሸግሮ ያመርታል ብሎ መገመት እጅግ ከባድ ነው፡፡ በመተማና ቋራ ያለው ስሜትም ተመሳሳይ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡
§ ስለሆነም በ1988 ዓ.ም ለምን ወደ ጦርነት ገባን? መሬታችን ማስመለስ የሚለው ዋነኛ አጀንዳችን አልነበረንም? ታድያ ዛሬ ምን ተፈጠረና ደም ገብረን ያስመለስነውን መሬት አዙረን እንመልሳለን? ሲሆን -ሲሆን ውዝግቡን በሰላም እንፍታው፤ ካልሆነና መሞታችን ካቀረስ መሬታችንን ይዘን መሞቱ አይሻለንም?
§ በዚህ በኩል ኢህአዴግ መሰረታዊ ስህተት ፈጽሟል፤ከኤርትራና ከኢትዮጵያቂያን አማፂያን የሚመጣን ተቃውሞ፤ በሱዳን አማካኝነት ለመመከትና ለማርገብ ሲል ያልተገባ ተግባር ውስጥ ገብቷል፡፡ ስለዚህ ማስተካከል ይገባል፡፡ ባለኝ መረጃ መሰረት የደለሎ ጉዳይ በጊዚያዊነት ነው የተሰጠ ስለሚባል፤ በቃ ጊዜው አልፏል ይመለስ፡፡ እንዲሁም በ1988 ዓ.ም በጃችን ከገቡ በኃላ ዙረው በሱዳን እጅ እንዲገቡ የተደረጉት መሬቶች በህውሀት ሰዎች ሴራ የተፈጸመ በመሆኑ፤ አንቀበለውም፡፡ ይህን ጉዳይ ብአዴን ለዶ/ር አብይ በተገቢው ማስረዳት አለበት፡፡ እኔ ባልኩት አቅጣጫ ችግሩ እንዲፈታም ብአዴን በግንባር ቀደምትነት መንቀሳቀስ አለበት፡፡
Filed in: Amharic