>
5:18 pm - Thursday June 15, 0575

ወቅታዊ ትዝብት (ከይኄይስ እውነቱ)

ወቅታዊ ትዝብት

ከይኄይስ እውነቱ

አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሕይወት/ከኑሮ ይልቅ ለሞት የሚጨነቅ ነው ብንል ስህተት ወይም ማጋነን አይመስለኝም፡፡ ምናልባትም የአብዛኛው ሰው ሕይወት ከሞት ስለማይሻል ይሆን? ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል፤ ተኖረና ተሞተ ወዘተ እያለ የሚተርተው ይህንኑ የኑሮ ፍልስምና መግለጫው ይሆን? የሃይማኖታዊ አስተምሕሮዎች ተጽእኖ ይሆን? ወይስ ጨካኝ አገዛዞች እየተፈራረቁበት ቀቢፀ ተስፋ ውስጥ ከተዉት ይሆን? ወይስ ፍትሕ ርትዕ የሚኖረው ኹሉን በሚያስተካክለው በሞት ብቻ ነው ብሎ ስላመነ ይሆን? ለማንኛውም ይህ ምውታንን የማግዘፍ ባህል አግባብ ባላቸው የትምህርት ዘርፎች በወጉ መጠናት ያለበት ይመስለኛል፡፡

በአግባቡ ሳይኖር ስለሞቱ እንዲጨነቅ ያደረገው ምክንያት የትኛውም ይሁን ይህ አስተሳሰብ ምድራዊ ሕይወቱን በትምህርት÷ በዕውቀት÷ በጥበብ ታግዞ እንዳያቀል፣ እንዳያሻሽል፤ ለራሱ ተደላድሎ ላገር ለወገኑ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብትና ቅርስ ትቶ እንዳያልፍ በእጅጉ እንቅፋት የሆነ ይመስለኛል፡፡ ጫንቃውን ለግፍና ለጭቆና አመቻችቶ እንዲኖርም በተወሰነ ደረጃ ምክንያት የሆነ ይመስለኛል፡፡ በቁሙ ያላከበርነውን፣ ሲቸገር ያልጎበኘንውን ሰው ሲሞት ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት አዛኝ ቅቤ አንጓች እንሆናለን፡፡ በቂ መረጃ ሳንይዝ ጨካኙን ርህሩህ፤ ንፉጉን ለጋስ፤ መሠሪውን የዋህ፤ ሌባውን ታማኝ፤ ዕቡዩን ትሁት፤ ሰነፉን ጎበዝ፤ ፈሪውን ጀግና፤ ባንዳውን አገር ወዳድ ወዘተ ለማድረግ ወደ ኋላ የማንል ግብዞች ነን፡፡ በሥራው በምግባሩ ያልጻፈውን ታሪክ በሐውልትና በዜና ዕረፍት ጽሑፍ ለማድመቅ የምንጥር ግብዞች፡፡

ሰሞኑን አንድ ‹ታዋቂ› ወንድማችን በመዲናችን ያውም በመስቀል አደባባይ በመኪናው ወስጥ ሞቶ እንደተገኘና የሞተውም በጥይት ተመትቶ እንደሆነ በብዙኃን መገናኛ ሰምተናል፡፡ በሰማነውም ዜና ተደናግጠናል አዝነናል፡፡ ሟቹን ‹ታዋቂ› ያደረገው የዐባይ ግድብ ፕሮጀክት ዋ/ሥራ አስኪያጅ መሐንዲስ መሆኑ ነው፡፡ ዝርዝር መረጃ ባለመኖሩ፣ ነገሮችን ኹሉ ምሥጢራዊ ማድረግ ባህልም ስላደረግነው፣ በምሥጢራዊነቱም የሚጠቀሙ ወገኖች እንደሚኖሩ በመጠርጠር ሁሉም የመሰለውን ግምት እየሠነዘረ ይገኛል፡፡ የሞቱ ምክንያት ተጣርቶ እስኪታወቅ (የሚጣራና የሚታወቅ ከሆነ፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሳይጣሩና ሳይታወቁ የታለፉ በመኖራቸው /ለአብነት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥ/አስኪያጅ ሞት፣ የሰኔ 16ቱ የቦንብ ፍንዳታ አደጋ/፡፡ ባሁኑ ጊዜ ጠ/ሚ ዐቢይ በሚመራው ‹አስተዳደር› ውስጥ  የመሐንዲሱን ሞት ጨምሮ ከላይ የጠቀስናቸውን ዓይነት ክስተቶች በገለልተኛነት የሚያጣራ አካል ያለ አይመስለኝም፡፡ እውነትን የሚፈልግና የሚያጣራ ባለሞያተኛም እንደዚሁ፡፡ ወይ ዶ/ር ዐቢይ ከሚመራው ግንባር ውጭ ባለሞያዎች ካሉ በጊዜያዊነት ማደራጀት ወይም ለጊዜውም ቢሆን ከአገር ውጭ አግባብነት ያላቸውን ባለሞያዎች ካልጋበዝን)

እውነቱን ለመናገር ሟቹን ከዚህ ቀደም በስምም ይሁን በመልክ አላውቀውም፡፡ ይህም የሆነበት በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው ላለፉት 14 ዓመታት ገደማ ወያኔ ትግሬ የተቆጣጠረውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከፍቼ የማላውቅ በመሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛውና ዋናው ምክንያት ገና የዐባይ ግድብ ፕሮጀክት ጉዳይ ሲነሳ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በጠላትነት የፈረጀና ለአቅመ መንግሥትነት ሳይበቃ የውንብድና ጠባዩን እንደያዘ ወደ ታሪክ ቆሻሻ ቅርጫት ሊጣል የታቃረበው መንደርተኛ ቡድን ይህንን ታላቅ ፕሮጀክት ለመሥራት በየትኛውም መመዘኛ ብቃት አይኖረውም ከሚል የፀና አቋሜ የተነሳ ነው፡፡ ገና ከጅምሩ የፕሮጀክቱ ሥራ ያለምንም ጨረታ ሳሊኒ ለተባለው ኩባንያ ሲሰጥ፣ ሜቴክ እና የኤፈርት ኩባንያዎች በብቸኝነት የግንባታ ቁሳቁሶች አቅራቢ ሲሆኑ፣ ወያኔ ሁነኛ ባለሙያዎችን ሳያማክር ባዘጋጀውና ‹‹የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን›› ብሎ በሰየመው ዕቅድ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን ግዙፍ ፕሮጀክት ሳይካተት ሲቀር፣ ባጠቃላይ በፕሮጀክቱ ዙሪያ እስካሁንም የሚታየው ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር፣ ወዘተ በፕሮጀክቱ ላይ ከመነሻው ተዐቅቦ (reservation) እንዲኖረኝ አድርጎኛል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ በነበርኩበት ጊዜ ወያኔ በካድሬዎቹ አማካይነት በግድ መዋጮ ሲሰበስብ (በጉልበት ቢወስደውም) በምሠራበት መ/ቤት ብቸኛ ተቃዋሚ እንደነበርኩና በዚህም ምክንያት በወያኔ ሎሌዎች ክትትል ውስጥ እንደነበርኩ አስታውሳለሁ፡፡

በነገራችን ላይ ዐባይን ገድቦ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም የማዋሉ ጉዳይ ከላሊበላ ነገሥታት አንዱ የሆነው ንጉሥ ሐርቤ ጀምሮ ይታሰብ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ይህ ታላቅ ወንዝ ተገድቦ ላገር ጥቅም መዋሉን የማይመኝ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ ከወያኔና ግብረ በላዎቹ በስተቀር፡፡ ወያኔ ማናቸውንም አገራዊ ፕሮጀክት የሚያሰላው ከዝርፊያ ምንጭነት አኳያ እንደሆነ ያለፉት 27 ዓመታት ገሀድ ምስክሮች ናቸው፡፡

ወያኔ ትግሬ ኢትዮጵያ ጥንታዊ መሠረት እንደሌላት ቆጥሮ በኹሉም መስክ ‹ሀ ብሎ የሚጀመር› አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ሞክሯል ግን አልተሳካለትም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብና መጪው ትውልድ ዘመነ ወያኔን ዘመነ ተዋርዶ ወ ድንቁርና በሚል በጥቁር መዝገብ ጽፎ ሲዘክረው ይኖራል፡፡ ደግሞ ‹‹ዐባይን የደፈረ ጀግና›› ይባልልኛላ!!! ስም አይጠሬውና ተከታዮቹ ምናምንቴዎች ‹የደፈሩት› ኢትዮጵያን እንጂ ዐባይን አይደለም፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአቶ ለማና በዶ/ር ዐቢይ በኩል የተስፋ ፍንጣቂ እያየን ቢሆንም ኢትዮጵያችን በአራቱም ማዕዘናት ጅምር ለውጡን ለመቀልበስ በሚታገሉ የጥፋት ኃይሎች ከፍተኛ ሥጋት አንዣቦባታል፡፡ በእነ ዐቢይ በኩል ያለውን ሂደት ስመለከት በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን የማስቀመጥ ሥራ ላይ የተጠመዱ ይመስላል፡፡ ከ14 ዓመታት በኋላ የከፈትኩት ቴሌቭዥን ባንፃራዊነት ነፃ ቢመስልም በአቀራረብ ፎርማት፣ በቋንቋ አጠቃቀም፣ ከሞያው ከሚጠበቅ ብቃት ወይም ክህሎት (professionalism) አኳያ፣ መረጃ ለማግኘት አሁንም በሩ ወለል ብሎ የሚከፈትላቸው ፋና÷ ዋልታና ሪፖርተር መሆናቸው፣ ቃለ መጠይቅ የሚያደርጉት የሚፈልጉትን መልስ ከሚሰጧቸው ግለሰቦች መሆኑ፣ ባለሥልጣናትን የመጠየቅ ድፍረቱና በቂ ዝግጅቱ ያለመኖር፣ ቃለ መጠይቅ የሚደረግላቸው ባለሥልጣናትም የለመዱትን አራቂ ገጽታ ተላብሶ መገኘት፣  ወዘተ በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን ላልኩት ጥሩ ማሳያ ይመስሉኛል፡፡ ለውጥ ተቋማዊ ካልሆነ ሥር አይሰድም፤ በቅብና ገጽታ ታይታ የተወሰነ ይሆናል፡፡

በቢሮክራሲው ውስጥ አንድ ለአምስት የተባለው የፖርቲው የአፈና መዋቅር ቀጥሏል፡፡ ደርግ መሠረታዊ ድርጅት ብሎ በየመንግሥት መ/ቤቱ እንዳስቀመጣቸው የኢሠፓ ካድሬዎች ወያኔም በተመሳሳይ መልኩ በረከት ስምዖን ይመራው በነበረው የኮምውኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስቴር መ/ቤት ሥር ካድሬዎችን አደራጅቶ በየመንግሥት መ/ቤቱ አሠማርቷል፡፡ እነዚህ ‹‹የኮምውኒኬሽን ክፍሎቹ›› እያንዳንዱ የመንግሥት መ/ቤት ከተቋቋመበት ዓላማ ወይም መደበኛ ሥራ ጋር አንዳች ግንኙነት አልነበራቸውም፡፡ አሁንም የላቸውም፡፡ (አልፎ አልፎ የሕዝብ ግንኙነት ዓይነት ሥራ የሚሠሩ ለማስመሰል ቢሞክሩም ተልእኳቸው ይህ እንዳልሆነ፣ ለዚህም አብዛኞቹ ብቃቱም እንዳልነበራቸውና እንደሌላቸው ታዝበናል ፤ በየመ/ቤቱ ለዚህ ዓላማ የተመደቡ ባለሞያች አስቀድሞም መኖራቸው አገር ያውቀዋል)፡፡ በዋናነት ተግባራቸው የሕወሓት ፕሮፓጋንዳና ደኅንነት ክንድ ሆኖ ማገለግል ነበር፡፡ ይህ የካድሬዎች ምደባ የ1997 ዓ.ም አገር አቀፍ ምርጫንና የምርጫው በወያኔ መጭበርበርን ተከትሎ የተናጋውን አገዛዝ ለማስቀጠል በየክፍላተ ሀገሩ ከፍተኛ ወንጀሎችን በመፈጸም ለሚጠረጠሩ ካድሬዎች በሽልማት መልክ የተበረከተ ሥጦታ ነው፡፡ ይህ አደረጃጀት አሁንም ቀጥሏል፡፡ ወደ ማኅበራዊው ጉዳይ ወረድ ስንልም የኤሌክትሪክና ውኃ አገልግሎት ጨርቅ ሊያስጥለን ደርሷል፡፡ እኔ በምኖርበት የቂርቆስ ክ/ከተማ ውስጥ ላለፉት 12 ዓመታት መፍትሄ ያልተገኘለት ጉዳይ ሆኗል፡፡ በየቦታው በኃላፊነት የተቀመጡት ግለሰቦች ባብዛኛው ከቅንነትና ሞራላዊ ልዕልና እንዲሁም ከብቃት የተራቆቱ ሲሆኑ፣ ሳይገባቸው (ጠብቆ) እና ሳይገባቸው (ላልቶ) በሕዝብ ወንበር ላይ ተቀምጠው ዋናው ተግባራቸው ሕዝብን ማማረር አድርገውት ዘልቀዋል፡፡ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ንቅዘቱ ጣሪያ ከነካበቸው የመንግሥት መ/ቤቶች አንዱ በተለምዶ መብራት ኃይል (አሁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን) የሚባለው ነው፡፡ ኢትዮጵያችን በየቦታው ያለ የቆሸሸ ኅሊናና አእምሮ ለማጽዳት የሚጠብቃት ፈተና ቀላል አይመስለኝም፡፡

ያለንበት አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታ በቀላላ ፍርክስክሱ ሊወጣ የሚችል (fragile) እንደሆነ ምድር ላይ ያለው እውነታ በግልጽ ይመሰክራል፡፡ በመሆኑም አዲሱ ‹አስተዳደር› ከሁሉም አስቀድሞ የአገር ደኅንነትንና ፀጥታ የማረጋጥ ሥራ ቅድሚያ መስጠት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የገጠመን ባላጋራ አጥፍቶ ጠፊ መሆኑን ዛሬ ሥልጣኑን ባጣበትና የዝርፊያ ፍሬውን ለማስጠበቅ የሞት ሽረት ሽብር በሚያደርግበት ጊዜ ሳይሆን በሙሉ ሥልጣን ላይ በነበረበትም ሰዓት ደናቁርት አለቆቹ ሲያናፉና ሲደነፉ የከረሙበት ጉዳይ ነው፡፡ ሕዝብ ተባብሮ አገዛዙን እንዳይነቅል መያዣ አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡ በመሆኑም ወደድንም ጠላን የዐቢይ መንግሥት የፖሊስ ኃይሉን ተጠቅሞ የሽብር አስተባባሪዎቹን በቊጥጥር ሥር ማዋል የግድ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ እነዚህን የጥፋት ኃይሎች በሕግ ጥላ ሥር ማምጣት ሜዳ ላይ ለቆ ከሚያስከትሉት አደጋ በየትኛውም መመዘኛ የሚነፃፀር አይደለም፡፡ ጥያቄው ዶ/ር ዐቢይ ሠራዊቱንና ደኅንነቱን የማዘዘ ተግባራዊ አቅም ካለው፣ በሕዝብ ኃይል የሚተማመን ከሆነ ሁኔታዎች ከቊጥጥር ውጭ ሳይወጡና ሥርዓተ አልበኝነት ሳይነግሥ ፈጣን ርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ በሃይማኖት አባቶችና በባህላዊ መንገድ የሚደረገው የማግባባት/የማስማማት ሂደት ከሕጋዊው መንገድ መሳ ለመሳ ሊካሄድ ይችላል፡፡

በሌላ በኩል አገርን ከማረጋጋቱ ጎን ለጎን የሚካሄዱት የለውጥ እንቅስቃሴዎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፉን በኹሉም መስክ ማስቀደም ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚቻለው ደግሞ ዐቢይ ከሚመራው የፖለቲካ ግንባር ውጭ በማሰብ የአገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉና ለውጡን የሚደግፉ ኃይሎችን በተለይም በአገር ቤትና በውጭ ያሉ ምሁራንን እንዲሁም ተቃዋሚ የፖለቲካ ማኅበራትን እና የማኅበረሰብ (ሲቪክ) ድርጅቶችን በለውጡ ሂደት በማካተት መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት – የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታን፣ አዲስ ሕገ መንግሥት ማቆምን ጨምሮ መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ለውጦች ማካሄድን – በጋራ መወያየትና መመካከር ሲቻል ነው፡፡ እነዚህ የለውጥ ኃይሎች (አብዛኛዎቹ ሲታገሉ የቆዩት ነፃነት፣እኩልነት፣ ማኅበራዊ ፍትሕና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ እውን ሆኖ ለማየት እንደሆነ ስለሚታመን) የዐቢይ መንግሥት ከንግግር ባለፈ በተግባር ‹የሚደምራቸው› መቼ ነው? የማስታመም የሚመስል/በሁለት ልብ የማነከስ አካሄድ ብዙ እንዳያስከፍለን አጥብቀን ልናስብበት ይገባል፡፡

Filed in: Amharic