>
3:19 pm - Sunday August 7, 2022

አስገድዶ የመሰወር ወንጀል ሕግ በኢትዮጵያ- የሌለውን ፍለጋ!!! (ዉብሸት ሙላት)

አስገድዶ የመሰወር ወንጀል ሕግ በኢትዮጵያ- የሌለውን ፍለጋ!!!
ዉብሸት ሙላት
የኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብት አያያዝን በተመለከተ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ይሁኑ አገራት በርካታ ጉዳዮች ላይ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ እንዳለበት በተለያየ መድረክና ሚዲያ ሲገልጹ ኑረዋል፡፡
 የሰብኣዊ መብት ጥበቃን በሚመለከት መንግሥት ማሻሻያን እንዲያደርግና ሌሎች እርምጃዎችን እንዲወስድ በየጊዜው ከሚጠየቁት ውስጥ የእስረኞች አያያዝ፣ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተወሰዱ ያልተመጣጠነ ኃይል እንዲሁም በየጊዜው የሚጠፉና የሚሰወሩ ሰዎችን ጉዳይ ይገኙበታል፡፡ በተለይ ስለአስገድዶ መሰወር ከሚቀርቡት አስተያየት መካከል እንዱ በግዳጅ የሚሰወሩ ሰዎችን በሚመለከት በቂ የሕግ ማእቀፍ እንዲኖር የሚጠይቅ ነው፡፡
ከዓለም አቀፍ ተቋማትና አገራት በተጨማሪም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ መኖራቸውም መሞታቸውም የማይታወቁ ሰዎችን በሚመለከት መረጃዎች በተለያዩ ሚዲያዎች ይፋ በመሆን ላይ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን በሚመለከት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድም በተለያዩ መድረኮች ጥያቄዎች መቅረባቸው ተዘግቧል፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግም ሁኔታዉን እንደሚያጠራ ይፋ አድርጓል፡፡
ተገደው የተሰወሩ ሰዎች ብዛትን እንዲሁም ከየትና መቼ ለሚሉት ጥያቄዎች የተማላ መረጃ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ እ.አ.አ. በ2009 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ 119 የተሰወሩ ሰዎች መኖራቸውን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ተደርጓል፡፡ አሁን ላይ ተገደው የተሰወሩ ሰዎች በሕይወት ይኑሩ ወይም አይኑሩ፣ የተሰወሩት ሰዎች አድራሻም የት እንደሆነ አይታወቅም፡፡
በአገራችን በውል ተለይተው የማይታወቅ ቁጥር ያለው ሰው የተሰወረ በመሆኑ እንዲሁም አሁን ላይ ለመንግሥትም በተለያዩ ሁኔታ ጥያቄዎች በመቅረባቸው አስገድዶ መሰወርን ለመከላከልና ለእስካሁኑ ድርጊትም እልባት ማበጀት ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ሰዎችን ከአስገድዶ መሰወር ድርጊት ለመጠበቅና ለመከላከል የሚረዱ ሕግጋት ፍተሻ በማድረግ  ለሚጎድለው ነገር መፍትሔ ማመላከት ነው፡፡
#በግዳጅ_መሰወር_ማለት
አስገድዶ የመሰወር ድርጊት ተፈጽማል ለማለት መሟላት ያለባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ የጠለፋ ወይም የእስራት ተግባር መኖሩ የመጀመሪያው ጉዳይ ነው፡፡ ተጠልፎ የታገተ ወይም የታሠረ ሰው መኖር ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ጠለፋ በባሕርይው ሕገወጥ ነው፡፡ የሚጠለፈው ሰው ሳይፈቅድ የሚደረግ ነው፡፡ በሕግ መሠረት የሚፈጸምም አይደለም፡፡ ሕጋዊ የሚባል ጠለፋ የለም፡፡ እስራቱም ቢሆን ሕገወጥ ሲሆን ነው ስወራ የሚያስበለው፡፡
ስወራውን የሚያከናውነው አካል መንግሥት፣የፖለቲካ ድርጅት ወይም ሌላ አካል (ግለሰብ) ሊሆን ይችላል፡፡ ቁምነገሩ ያለው ማን ሰወረው የሚለው ላይ አይደለም፡፡ ይልቁንስ የመንግሥት ሚና ነው ወሳኙ፡፡ የግዳጅ ስወራ ተፈጽሟል ለማለት የመጀመሪያው ስወራውን መንግሥት የሚያውቀው ራሱ የፈጸመው ሲሆን ነው፡፡ በተለያዩ አገራት ‘ቆሻሻ ጦርነት’ (Dirty War) ውስጥ ሲገቡ ተስተውሏል፡፡
ሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት የፖለቲካ ባላንጣ የሚላቸውን፣ ባላንጣም ባይሆኑ ሕዝቡን እንዲነቃ እንዲጠይቅ እንዲቃወም ሊያነሳሱ ይችላሉ ብሎ የሚገምቷቸውን ሰዎች መሰወር ተለምዷል፡፡ ስለዚህ አስገድዶ ስወራን በዋናነት የሚፈጽሙት ሥልጣን ላይ ያሉ መንግሥታት ናቸው፡፡
 መንግሥታት በቀጥታ የስወራ ተግባር ውስጥ ባይገቡም ሌሎች አካላት ሊፈጽሙም ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ አስገድዶ ስወራ ተፈጽሟል ለማለት የሚሰውሩት ሌሎች አካላት ሆነው መንግሥት በድርጊትም ይሁን በዝምታ ለስወራው ድጋፍ ካደረገ ነው፡፡ አንድም መንግሥት ለሰዋሪ አካላት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር፣ስወራውን እንዲሳካ ማገዝ አለበት፡፡
አልበለዚያም ስለስወራው መረጃ ቢኖርም ዝም በማለት መደገፍ ሊኖር ይችላል፡፡ የተሰወረ ሰውም መኖሩን መረጃ ቢደርሰውም ምርመራና ክትትል ባለማድረግ ሰዋሪዎቹን ሊያግዝ ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ይኼም ያው ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡
አንድ ሰው ተሰውራል የሚባለውም የተሰወረው ሰው ዕጣፋንታውም ሆነ  አድራሻ (ያለበት) የማይታወቅ ሲሆን ነው፡፡ መንግሥትም ይሁን ሌሎች አካላት ስለተሰወረው ሰው ዕጣፋንታም ይሁን አድራሻ እንደማያውቁ መካድ የተለመደ ነው፡፡ ምንም ዓይነት መረጃ ለመሥጠት እምቢተኛ መሆንም የድርጊቱ መገለጫ ነው፡፡
ሰዋሪዎች የሚፈለጉትና ዓላማቸው የሚሰወረውን ሰው ከሕግ ጥበቃ ውጭ ማድረግ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ሕግን መሠረት ያደረገ ጥበቃና መፍትሔ እንዳያገኝ ማድረግ ነው፡፡ ሁሉ ነገር የሚፈጸመው በሰዋሪዎች ፍላጎትና ፍቃድ እንጂ በተሰወረው ሰው መብት መነሻነት አይደለም፡፡
ተገድዶ የተሰወረ ሰው ብዙ ጊዜ ዕጣፋንታው ሞት ነው፡፡ ከተሰወረበት የሚለቀቅ እና ነጻ የሚሆን ከሆነ የሰወሩት አካላት በወንጀል እንዳይጠየቁ ስለሚሰጉ ነው፡፡ የተሰወረው ሰው ቃል ሲሰጥም በማሰቃየት ሊሆን ይችላል፡፡ በስቃዩም የተነሳ ሊሞት ይችላል፡፡ የተሰወረ ሰው ሲሞትም አስከሬኑም ጭምር ይሰዋራል፡፡ ይደበቃል፡፡ ስለአሟሟቱም ማስረጃም እንዳይኖር ማድረግ የተለመደ ነው፡፡
#አስገድዶ_መሰወር_ከዓለም_አቀፍ_የሰብኣዊ_መብት_ሕግ_አንጻር
አስገድዶ መሰወር በዓለም አቀፍ ደረጃ አጀንዳ ከሆነ ሃምሳ ዓመታት ሊሞላው ነው፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ድርጅቶች ትኩረት ከሰጡት ቆይተዋል፡፡ ስወራን ለመከላከል  ሕግጋት ወጥተዋል፡፡ ድርጅቶችና ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፡፡ የበይነ-አሜሪካ ስለሰዎች በግዳጅ የመሰወር ስምምነት (Inter-America Convention on Forced Disappearance of Persons)፣ ሁሉን ሰው ከአስገድዶ ስወራ ለመጠበቅ የወጣው ዓለም አቀፍ ስምምነት (International Convention for the Protection of All Persons from Enforced Disappearance)፣ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ፣ እንዲሁም የቬና መግለጫና የድርጊት መርሃ ግብርን በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም የሁኔታውን ዓለም አቀፋዊ ይዘትና አሳሳቢነት በመገንዘብ እንዲሁም በዓለም አቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት፣ አገራትን ስምምነቱን በመተግበር የሰብኣዊ መብትን ማክበራቸውን የመከታተል በአንቀጽ 28 መሠረት ኃላፊነት ስላለበት  እ.አ.አ. በ1980 ዓ.ም. አስገድዶ የመሰወርን ጉዳይ የሚከታተል አንድ ቡድን አቋቁሞ ነበር፡፡ ይህ ቡድን ስለተሰወሩ ሰዎች ሁኔታ የሚያጣራ፣ የተጎጂዎችን ቤተሰብም የሚደግፍ ነበር፡፡
ቡድኑ ከተቋቋመ እና ሃያ አምስት ዓመታት ገደማ ከሠራ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.አ.አ. በታሕሳስ 2006  ሰዎችን ካስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የሚረዳ ስምምነት ተቀብሎ በዚሁ ዓመት በወርሃ የካቲት የሃምሳ ሦስት አገራት ተወካዮች በተገኙበት ፈረንሳይ፣ፓሪስ ላይ ተቀባይነት  ዘንድ በማገኘቱ እየፈረሙ እንዲያጸድቁት ለፊርማ ክፍት ሆነ፡፡
ስምምነቱ አስገዳጅ የሚሆነው ሠላሳ ሁለት አገራት ሲያጸድቁት ስለሆነ ይሄው ቁጥር ሲሟላ እ.አ.አ. ታሕሳስ 2010 ላይ ሥራ ላይ ውሏል፡፡ አሁን ላይ ሃምሳ ስምንት አገራት አጽድቀውታል፡፡ ዘጠና ሰባት አገራት ደግሞ ፈርመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ተቀብላ አላደቀችውም፤ፈራሚም አይደለች፡፡
ስምምነቱ አስገድዶ መሰወርን በሰብእና ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች (Crimes against humanity) አንዱ እንደሆነ እውቅና ሰጥቷል፡፡ የተሰወረው ሰው ቤተሰቦች ከመንግሥት ካሳ የመጠየቅ መብት እንዳለቸው አረጋግጧል፡፡ ከገንዝብ ካሳ በተጨማሪ የተሰወረው ሰው ቤተሰቦችን እንዲያገግሙና የሞራልና የመንፈስ ተሃድሶ እንዲያደርጉ ማመቻቸት፣ ከብራቸው እንዲመለስ ማድረግ፣ ተጨማሪ ስወራ በቤተሰባቸው ላይ እንዳይከሰት ዋስትና መስጠትን ይዟል፡፡
ስለተሰወረው ሰው ሁኔታ እውነታው እንዲነገራቸው የመጠየቅ መብት እንዳለቸው ገልጿል፡፡ ሰዎች ለስወራ እንዳይጋለጡ የማድረግ መንግሥት ላይ ግዴታ ጥሏል፡፡አገራት ስወራ ሲኖር የመመርመር እና ሰዋሪዎቹን ለፍትሕ የማቅረብ፣ አስገድዶ መሰወርን በወንጀል ሕግ ማካተት፣ አስገድዶ የመሰወር ወንጀል ሲፈጽም መዳኘት እንዲችሉ ለፍርድ ቤት ሥልጣን መስጠት፣ ሰዎች ነጻነታቸው የሚገደብባቸውን ሁኔታዎች በሚኖርበት ጊዜ ዝቅተኛ የአያያዝ መሥፈርት ማውጣትና ማክበር፣መንግሥት የታሠሩ ሰዎችን ስም ዝርዝር መያዝ እና በዘመድና በአማካሪ እንዲጎበኙ ማድረግን ይጠይቃል፡፡
በግዳጅ መሰወር በኢትዮጵያ ሕግ
አስገድዶ መሰወርን በሚመለከት በቀደማነት የምንመለከተው ሕገ መንግሥቱን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28 ላይ በአሰገዳጅነት ሰውን መሰወር በሰብእና ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች አንዱ አንደሆነ ተገለጿል፡፡ ስለሆነም የአስገድዶ ስወራ ወንጀል የፈጸመ ሰው መቼም ይሁን መቼ ክስ ሊቀርብበት ይችላል፡፡ በሌላ አገላለጽ ይርጋ የለውም፡፡ የሆነ ያህል ጊዜ አልፎታል ተብሎ ወንጀለኞች ከመከሰስ ሊድኑ አይችሉም፡፡
እንዲሁም አስገድዶ መሰወር ወንጀል የፈጸመን ሰው ከወንጀል ኃላፊነት ነጻ ለማድረግ፣ ተጠያቂ እንዳይሆን ምህረት ማድረግ አይቻልም፡፡ በምንም ዓይነት ሕግ ቢሆን ምህረት አይደረግም፡፡ ይቅርታም አይሰጥም፡፡ የሚቻለው ነገር ቢኖር በዚህ ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ የሞት ፍርድ የተፈረደበትን ፍርደኛ በአገሪቱ ርእሰ ብሔር የሞት ፍርዱን ወደ ዕድሜ ልክ እሥራት ሊቀየር ይችላል፡፡
አስገድዶ የመሰወር ወንጀል በሰብእና ላይ ከሚፈጸሙ ምህረትም ይቅርታም ከማያሰጡ አሰቃቂ ወንጀሎች አንዱ መሆኑን ሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ከዚህ ሌላም ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብኣዊ መብት ስምምነቶችም ላይ በሰብእና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ምህረትና ይቀርታ እንደሌላቸው ብሎም በይርጋ እንደማይታገዱ ይገልጻሉ፤ እነዚህን አጽድቃለች፡፡
አትዮጵያ በሰብእና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመዳኘት፣ ወንጀለኞችን ለፍትሕ ለማቀረብ የተቋቋመውን ዓለም አቀፉን የወንጀል ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ አልተቀበለችም፤ አልፈረመችምም፡፡ እንደውም ሌሎች የአፍሪካ አገራት ፈራሚ እንዳይሆኑም ስትሠራ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡
 ምክንያቱ ደግሞ ፍርድ ቤቱ አፍሪካን ለመጎዳትና ዘረኛም ነው የሚል ነው፡፡ በሰብእና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን እንደማይፈጽም የሚተማመን መንግሥት የፍርድ ቤቱ ዘረኝነት አያሳስበውም፡፡ ወንጀሉን ካልፈጸመ ቀድሞውን ስለማይከሰስ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሰዎችን  ካስገድዶ መሰወርን ለመጠበቅ ሲባል የወጣውን ዓለም አቀፍ ስምምነት ፈራሚም አልሆነችም፡፡ መንግሥት በእሱ መሠረት ስወራን የመከላከል ፍላጎት የለውም ማለት ነው፡፡
እንግዲህ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት መመሥረቻንም ሆነ አስገድዶ መሰወርን ለመከላከል ሲባል የወጣውን ዓለም አቀፍ ስምምነት ካልተቀበለች የሚቀረው አማራጭ አገራችን ሰዎችን ከአስገድዶ መሰወር ሊታደግ የሚችል፣ ከተፈጸመም ሰዋሪዎቹን ለፍትሕ ለማቀርብ የሚያስችል፣ የተጎጂ ቤተሰቦችንም ካሳና ሌሎች መሰል መፍትሔዎችን የሚሰጥ የሕግ ማእቀፍ ሊኖራት ይገባል ማለት ነው፡፡
በዚሁ ልክ እንደ ሕገ መንግሥቱ ትኩረት ሰጥቶ ማንኛውም ሰው በተለይም ዜጎችን ከአስገድዶ ስወራ መጠበቅ የሚያስችል ሕገ መንግሥቱን ሥራ ላይ ለማዋል የሚረዳና የሚያግዝ ዝርዝር ሕግ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28 ላይ እንደተቀመጠው አስገድዶ መሰወርን ወንጀል የሚያደርግ ሕግ ሊኖር ይገባል፡፡ አንድን ድርጊት ወንጀል ነው ለማለት ወንጀል መሆኑን የሚደነግግ ሕግ መኖርን ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም ወደ ወንጀል ሕጉ ማማተር ይጠበቅብናል፡፡
አሁን በሥራ ላይ ያለውን የወንጀል ሕግ በምንፈትሽበት ጊዜ ራሱን ችሎ አስገድዶ መሰወርን ወንጀል የሚያደርግ አንቀጽ አናገኝም፡፡ ከአስገድዶ መሰወር ጋር በትንሹም ቢሆን ሊቀራረቡ የቢችሉም  በትክክል አስገድዶ መሰወርን የሚሸፍኑ ሆነው አናገኛቸውም፡፡
ከዚህ አንጻር መጀመሪያ ላይ ስለመሰወር የምናገኘው የዘር ማጥፋት ድርጊትን ወንጀል የሚያደርገው አንቀጽ 269 (ሐ) ላይ ሲሆን በዚህ አንቀጽ እንደተገለጸው አስገድዶ መሰወሩ የዘር ማጥፋት መሆንን ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም በዚህ አንቀጽ ተመርኩዞ አስገድዶ መሰወርን ራሱን ችሎ ወንጀል በማድረግ ክስ ማቅረብ አይቻልም፡፡
አሰገድዶ መሰወሩ ዉጤቱ የዘር ማጥፋት መሆንን ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም ይህ ድንጋጌ ሰብእና ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች መካከል አንዱን ማለትም የዘር ማጥፋትን የሚመለከት ቢሆንም አስገድዶ መሰወርን ግን አይሸፍንም፡፡
አስገድዶ የመሠወር ወንጀል ተፈጽሟል ለማለት ከላይ እንዳየነው የመንግሥት ትብብር መኖር እንዳሚያስፈልግ ተመልክተናል፡፡ የተሰወረው ሰው ዕጣ ፋንታ በሚያዝበት ጊዜ የሚሰወረውም ቤተሰቦቹም የማያውቁ መሆን አለበት፡፡ እንግዲህ ከምርመራ በኋላ ግን ይህ ሁኔታ ሊደረስበት ይችላል፡፡ እነዚህንና ከላይ የተገለጹ ነጥቦችን የሚያካትት አስገድዶ መሰወርን ወንጀል የሚደርግ ካል እንመልከት፡፡
ራሱን ችሎ ስሙ ተጠቅሶ ወንጀል ካልተደረገ ከአስገድዶ መሰወር ጋር ሊገኛኙ የሚችሉ ወንጀሎችን ደግሞ እንመልከት፡፡ አስገድዶ መሰወር በርካታ መብቶችን የሚያሳጣ ቢሆንም ዋናው ግን ነጻነትን (liberty) ያሳጣል፡፡ በተለይ ደግሞ የመንቀሳቀስ ነጻነትን ማሳጣት መለያ ጠባዩ ነው፡፡
የወንጀል ሕጉ ነጻነትን አላግባብ ማሳጣት ወንጀል ያደረገበትን አንቀጾች ከ580 ጀምሮ እናገኛለን፡፡ ከዚህ አንጻር ከያዝነው ጉዳይ ጋር የሚቀራረቡ ሁለት አንቀጾችን እናገኛለን፡፡ አንደኛው አንቀጽ 585 ሲሆን ከሕግ ውጭ የሰውን ነጻነት ማሳጣት፣ማገት፣መሰርን ይመለከታል፡፡
ማንም ሰው፣የመንግሥት ሠራተኛ ያልሆነ ሰው ከሕግ ውጭ ካሰረ እጅግ በጣም ቢበዛ አስር ዓመት በሚደርስ እስራት ሊቀጣ ይችላል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ ከፈጸመው ደግሞ አሁንም በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 423 መሠረት ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ከፍተኛው የቅጣት መጠንም ያው አስር ዓመት ነው፡፡
እንግዲህ አስገድዶ መሰወርም ያው ሕገ ወጥ እስራት ነው ተመሳሳይ ነው ካልን ነው በእነዚህ አንቀጾች ክስ ማቀረብ የሚቻለው፡፡ ሌላው የምናገኘው ጠላፋን የሚመለከተው አንቀጽ ነው፡፡ እንደ ሕጉ ጠለፋ አድራጊውን እና የተጠላፊውን የት እንደተወሰደ የሚታወቅ ይመስላል፡፡ የቅጣት መጠኑም ከፍተኛው የሰባት ዓመት እስራት ነው፡፡
 ይሄ የታሰረው ሰው የት እንዴታሰረ፣ማን እንዳሰረው ሲታወቅ ነው፡፡ ጠለፋውም ቢሆን እንዲሁ፡፡  እንግዲህ አስገድዶ መሰወር የሚፈጽሙ ሰዎችን ለፍትሕ ለማቅረብ የሚሆን ራሱን የቻለ ስሙን ጠርቶ ባሕርውን ገልጾ ወንጀል የሚያደርግ ሕግ ከሌለ አማራጩ ከላይ በጠቀስናቸውና ሌሎች ተያያዥ አንቀጾች ክስ ማቅረብ ይሆናል፡፡
አሰገድዶ የመሰወር ድርጊት የተሰወረውን ሰው በርካታ መብቶች ስለሚጥስ የተጣሱትን መብቶች  ወንጀል በሚደርጉ አንቀጾች ክስ ማቅረብ ይሆናል አሁን ላይ ያለው መፍትሔ፡፡
በጥቅሉ ሲታይ የወንጀል ሕጉ ለዚህ ከባድና ሰብእና ላይ ለሚፈጸም፣ምህረትና ይቅርታ ለሌለው በይርጋ ለማይታገድ ወንጀል ትኩረት አልሰጠውም፡፡ በምትኩ ሊያገለግሉ የሚችሉ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንም መንግሥት አልተቀበለም፡፡
 ሌሎች አገራትም ኢትዮጵያን ሁለቱን ስምምነቶች እንድትቀበል በተባበሩት በየጊዜው የሚቀርቡ ሁሉን አቀፍ የሰብኣዊ መብት ግምገማ ላይ ለአብነት አርጀንቲናና ካናዳ ከላይ የተገለጹትን ሁለቱን ስምምነቶች እንድትቀበል ቢጠይቁም ስለ አስገድዶ መሰወር የወጣውን ስምምነት በሚመለከት መልስ መስጠት አልፈለገችም፡፡ እቀበላለሁም ወይም አልቀበልም አላለችም፡፡ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤቱን ግን እንደማትቀበል አሳውቃለች፡፡ በግልጽ ወድቅ አድርጋለች፡፡
አስገድዶ መሰወር በአገራችን በሰፊው ተንሰራፍቶ ኖሯል፡፡ ሕዝብ በየቦታው ስለሁኔታቸው ከሚጠይቀው መካከል ሁለት ብቻ እንጥቀስ፡፡ በ1984  ዓ.ም. ነዲ ገመዳ ከባሌ እንዲሁም በ1986 ዓ.መ. መሪጌታ እንደሥራቸው ከጎንደር ተሰውረዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውም ሆነ ሕዝቡ መኖራቸውንም መሞታቸውንም አያውቅም፡፡ ሕዝቡ ግን አሁንም ጥያቄውን አላቆመም፡፡
መንግሥትም በዓለም አቀፍ ሰነዶች ላይ እንደተደነገገው (ከላይ እንዳየነው) ለቤተሰቦቻቸው ምንም ነገር ሲደርግ አልተስተዋለም፡፡ ይሄንን እንዲያደርግ የሚሰገድደውም ለተጎጂዎች መብት የሚያደርግ በግልጽ የተቀመጠ ሕግ የለም፡፡
የተሰወሩት ሰዎች ላይ ከደረሰው በደል ባሻገር ቤተሰብ ላይ የሚደረሰውም ከባድ ስለሆነ ነው ይርጋም፣ምህረትም፣ይቅርታም የሌለው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ወንጀል እንደሆነ ቢገለጽም አገራችን ግን አስገድዶ መሰወርን ወንጀል ያደረገ ሕግ የላትም፡፡
ስለሆነም የመሰወር ፍላጎት የሌለው መንግሥት ሰውን ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ ዝርዝር ሕግ ያወጣል፡፡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶቹንም ይቀበላል፡፡ የዶክተር ዐቢይ አስተዳደርም ይኼንኑ ያደርጋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
Filed in: Amharic