ከይኄይስ እውነቱ
የጠ/ሚር ዐቢይ አስተዳደር በጅምር የለውጥ ሂደት ላይ ያለ እንደመሆኑ መጠን በርካታ አደጋዎች ተጋርጠውበት ይገኛሉ፡፡ ግዙፍ የሆነው አደጋ አገራችን ባራቱም ማዕዝናት ያለመረጋጋቷ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ መንበረ ሥልጣን እስከ መጨረሻው ተጣብቆ ለመኖር ያለመውና ይህ ሕልሙ ቅዠት የሆነበት ወያኔ ትግሬ ቀዳሚው የአገር ደኅንነትና ፀጥታ አደጋ መሆኑ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ሲሆን፤ ከሕወሓት ባልተናነሰ የለውጡን ሂደት ለማስተጓጐል በሽፋን እየተንቀሳቀሱ ያሉት ለእነ አቶ ለማ ቡድን ቅርብ የሚመስሉ÷ በፓርቲያቸው ወይም በ‹ግንባሩ› ሥር የተጠለሉ እና በኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ድርጅቶቸና ግለሰቦች ናቸው፡፡ እነዚህን ነው ተረፈ-ወያኔዎች የምላቸው፡፡ ወያኔ ትግሬም አገር ለማወክ መሣሪያ አድርጎ እየተጠቀመባቸው ያለው እነዚህኑ ሆድ አደር አድርባዮችን ነው፡፡ አቶ ለማም ሆኑ ጠ/ሚር ዐቢይ በቅርባቸው ያሉና ሕዝብን ከሕዝብ የማቃቃር አፍራሽ ሥራ ላይ የተጠመዱ ግለሰቦችን ወይ አላስተዋሏቸውም ወይም የቅድሚያ ትኩረታቸው አልሆኑም አሊያም አፍራሽ ድርጊታቸውን በዝምታ ተቀብለውታል፡፡ አደፍ ጉድፍን ማጥራት ከራስ/ከቤት ይጀምራል፡፡ አጋንንታዊ ተግባር ከሩቅ ብቻ ሳይሆን ከቅርብም ከመጣ መወገዝ ብቻ ሳይሆን በጊዜው መቀጨት ይኖርበታል፡፡ ለአጋንንት ‹የቤትና የጎረቤት› የሚባል የለውም፡፡ የበጎ ለውጥ ደጋፊዎችን እሺ በጄ በርቱ እንደምንለው ኹሉ፤ የለውጡ እንቅፋቶችን እምቢ ወግዱ ማለት ይኖርብናል፡፡ ስለሆነም እነ አቶ ለማ ቤታችሁን (ኦሕዴድን) በሚገባ አጽዱ፡፡ ጠ/ሚር ዐቢይ የሚመሩት ‹ግንባር› አባል ድርጅቶችን እንቅስቃሴ በቅርበት መከታተል ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ለውጡን ተቀብለናል ወይም ‹ተደምረናል› በማለት አገር ቤት የገቡትን (በተለይም የኢትዮጵያ ስምና አንድነቷ ሲነሳ አጋንንት እንዳደረባቸው የሚንዘፈዘፉ ወገኖች) የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች እንቅስቃሴ በጥንቃቄ ማስተዋል ይገባል፡፡
በዛሬው አስተያየቴ ጠ/ሚር ዐቢይ እና አቶ ለማ ትኩረት ሰጥተው እንዳስፈላጊነቱ የማስተካከያ ርምጃ እንዲወስዱ የማሳስበው ጉዳይ አቶ አዲሱ አረጋ የሚባል የናንተ ተሿሚ የኢትዮጵያ መዲና ስለሆነችውና እንደ ትንሿ ኢትዮጵያ (macrocosm) የምናያትን አዲስ አበባ ከተማ አስመልክቶ ‹‹የአዲስ አበባ ሕዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት የለውም›› በማለት ያለዕውቀት በድፍረት የሰጠው አስተያየት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ለሕዝብ ንቀት ያላቸውና ከዕውቀትና ልምድ ‹ጨዋ› የሆኑ ባለሥልጣናት በለውጥ ሂደት የሚገኝ አስተዳደርዎን ትዝብት ውስጥ የሚያስገቡ ብቻ ሳይሆን የለውጥ እንቅፋቶች ባጠገብዎም መኖራቸውን አመላካች ነው፡፡ በተለይም በጅጅጋ የተፈጠረው አስደንጋጭ ክስተት ባልተረጋጋበትና ሕዝቡም በሐዘን ላይ በሚገኝበት ባሁኑ ሰዓት በቊስል ላይ እንጨት መስደድ ሆኖ የሚታይ ነው፡፡ ግለሰቡ ከሕወሓት በቀሰመው ተንኮል መሠረት ይህንን ርእሰ ጉዳይ ያነሳው የነገር አጥንት ወርውሮ ሰዉ ኹሉ በዚህ ዙሪያ እንዲነታረክና የወቅቱን አንገብጋቢ የትኩረት አቅጣጫ ለማሳት (diversion) አስቦ ከሆነም አይሳካለትም፡፡ ይህም አስተያየት ለግለሰቡ መልስ የመስጠት ዓላማ የለውም፡፡ ከጽሑፉ እንደምንረዳው ከሆነ የግለሰቡ ዓላማ የትኩረት አቅጣጫን ከማስቀየር የዘለለ ይመስላል፡፡
ዛሬ በአቶ ለማና በርስዎ በጠ/ሚሩ መሪነት የለውጡ ብሥራት የተጀመረውና አሰባሳቢ የሆነው ቃል የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመስማት ሲናፍቅ የቆየው ኢትዮጵያዊነትና አገራዊ አንድነት ነው፡፡ ይህ ግለሰብ ግን ወደ ኋላ ሊመልሰን ወደመንደርተኝነት ወርዶ ባዲስ አበባም ጎሠኝነት እንዲሠለጥን የወያኔ ትግሬ ግርፍነቱን አስመስክሯል፡፡ የሚገርመው ደግሞ ላለፉት 27 ዓመታት መንግሥታዊ ሽብር ሲፈጽም የቆየው ወያኔ ትግሬ ያወጣቸውን ሕገ ወጥ ‹ሕጎች› መሠረት አድርጎ ስለ አዲስ አበባ ባለቤትነት የሚያቀርበው መከራከሪያ ነው፡፡ አዲሱ ‹አዲስ› አልመሰልከኝም፡፡ ባሮጌው የወያኔ ‹ክልላዊ/ጎጣዊ› አስተሳሰብ የምትኖር አሮጌ ነህ፡፡ ኢትዮጵያ አሁን የምትፈልገው ዕውነተኛ አዲስ ሰው ነው፡፡ ሕፃናት ሳይቀሩ ለተሠዉለት ሁላችንን በዕኩልነት እንድንታይ ወደሚያደርገን ዴሞክራሲያው ሥርዓት ለመሸጋገር የበኩሉን አዎንታዊ እገዛ የሚያደርግ አዲስ ሰው፡፡ እንደ ‹አዲሱ› ያሉ አሮጌ አቁማዳዎች አዲሱን የለውጥ ወይንጠጅ የሚሸከሙበት አቅም የላቸውም፡፡
ስለ አዲስ አበባ ከተማ በርካታ ምሁራን ታሪክን መሠረት አድርገው የተለያዩ አስተያየቶች በተለያየ ጊዜ አቅርበዋል፡፡ መናገሻ ከተማችን የኢትዮጵያውያን በሙሉ በመሆኗ በዚህ ረገድ ከይስሙላ ‹ሕገ መንግሥቱ› ጀምሮ አግባብነት ያላቸውን ድንጋጌዎች በማሻሻል፣ ጥናት የሚያስፈልገውም ከሆነ ባለድርሻ ነን የሚሉ ባለሙያዎችን ያካተተ አንድ ቡድን ሰይሞ ማስጠናት ይቻላል፡፡
በሥራው አነስተኛው የአስተዳደር ዕርከን (ቀበሌ) ድረስ ወርዶ መገናኘት የሚችል የሕዝብ ግንኙነት ባለሥልጣን ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ያሻውን ሲዘባርቅ እንደ ተራ ግለሰብ አስተያየት መመልከት በየትኛውም መመዘኛ ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡
ስለሆነም ተገቢውን አስተዳደራዊ ርምጃ መውሰዱ እንደተጠበቀ ሆኖ ግለሰቡ የአዲስ አበባንና የኢትዮጵያን ሕዝብ በይፋ ይቅርታ እንዲጠየቅ ይደረግ ዘንድ (ያብዛኛው አዲሳቤ ድምፅ እንደሆነ በማመን) በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ስም ይህንን አቤቱታ ለአቶ ለማና ለጠ/ሚር ዐቢይ በታላቅ አክብሮት አቀርባለኹ፡፡
ኢትዮጵያችን በአሁኑ ሰዓት ከበቂ በላይ ተግዳሮቶች አሏት፡፡ ከአእምሮአችንና ከኅሊናችን ጋር ከሆንን ወያኔ በየቦታው የለኮሰው እሳት ላይ ቤንዚን አቀባይ መሆናችንን ባስቸኳይ ማቆም ይበጀናል፡፡ ልቦናውን ይስጠን፡፡