>

''ወጣቱን የአገሪቱም ሆነ የተጀመረው ለውጥ አድራጊ ፈጣሪ አለመሆኑን ማስረዳት/ማሳየት ያስፈልጋል።'' (መስፍን ነጋሽ)

የማናውቀው፣ ያልጠበቅነው፣ ያልፈራነው አልሆነም። በሻሸመኔም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የሚሆነውን አውሬያዊ የሰው ድርጊት ስንመለከት ማዘን እንጂ ደርሶ እንግዳ መሆን የለብንም። የሻሽመኔው ድርጊት እስካሁን ከታዩት ሁሉ የመንጋውን አደገኛ አውሬነት የሚያሳይ ነው። ሁለት መሠረታዊ ገፊ ምክንያቶች አሉ። የዘውግ ፖለቲካ እና ከአቅሙ በላይ እየተወጠረ፣ መረን እየወጣ ያለ ወጣት ኀይል።

የዘውግ/ብሔር ፖለቲካ በእያንዳንዱ ተፈጥሯዊና የማይቀርበት ፌርማታው ሲደርስ እንዲህ እርቃኑን እየቆመ ያባንነናል። መርዶው ሌላ ነው፤ እስካሁን ያየነው ገና የመጀመሪያዎቹን ፌርማታዎች ትእይንት ነው። እነበረከት ስምኦን፣ እነመለስ ዜናዊ ወዘተ እንደተነበዩልን የመጨረሻ ፌርማታችን የዘር እልቂት (ኢንተርሃሙዌ) ነው፤ ፕሮጀክቱን አስበው ካስጀመሩት ሰዎች በላይ መዳራሻውን እናውቃለን አንልም። መፍትሔው ይህን ፕሮጀክት ማዳከም ነው፤ ሐዲዱን መስበር ነው። የቡድን መብቶችን ያለማመንታት እያከበርን፣ የብሔር ፖለቲካን ተፈጥሯዊ የመለያየትና የማባላት አዝማሚያ ማዳከም ያስፈልጋል።

ያለንበት ወቅት አንዱ መገለጫ፣ ወጣቱ የሁሉ ነገር አድራጊ ፈጣሪ ተደርጎ መቅረቡ ነው። ወጣቱም ይህን አምኖ በከፍተኛ የድል አድራጊነት ስሜት እየጋለበ ነው፤ ይህም ለጋላቢዎቹ የሚመረጥ ምቹ ፈረስ አድርጎታል። ከጋላቢዎቹ ቁጥጥር ውጭ እየወጣም ነው። የብሔር ፖለቲካ ነጋዴዎች ወጣቱን ከሆነው በላይ እያጀገኑ፣ የብሔሩ ብቸኛ ባለመብት ጠባቂ፣ የማይሳሳት ዘበኛ እያደረጉ የራሱን ምስል ይኩሉለታል። ወጣቱ በቡድን እየሰከረ ነው። የወጣቱን አስተዋጽኦ ለማኮሰስ አልፈልግም፤ የአገሪቱም ሆነ የተጀመረው ለውጥ አድራጊ ፈጣሪ አለመሆኑን ማስረዳት/ማሳየት ግን ያስፈልጋል። (እዚህ ላይ ኅይለ ማርያም ደሳለኝን የመሰሉ ቂል አታላዮች “ጠያቂ ትውልድ ፈጥረናል” ያሉትን ቀልድ አስታውሳለሁ። ጠያቂ ትውልድ?! ህምም)

Filed in: Amharic