>
5:13 pm - Wednesday April 19, 3848

ታሪከ ነገሥት!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ታሪከ ነገሥት!!!
አሰፋ ሀይሉ
    — የግራኝ አህመድ ቃጠሎዎች፤ ከሽምንብራ ኩሬ እስከ ወይና ደጋ !
*”ግራኝ፤ ማለት የሰው ስም ፤ ቅፅል ስሙ ነው ፤ በሐረርጌ አውራጃ የተወለደ መሐመድ ገራድ ኢትዮጵያን በዐፄ ልብነ ድንግል ጊዜ ፲፭ ዓመት በጦር ያስጨነቀ ፤ ቤተክርስቲያን መጽሐፍ አቃጣይ፡፡”
— ደስታ ተክለ ወልድ (አለቃ)፤ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፡፡
‹‹ነገር ግን የሀገራችንን በጠላት እጅ መውደቅ በዐፄ ናዖድ ልጅ በንጉሥ ልብነ ድንግል ልጅ ተጀመረ፡፡ ስመ መንግሥቱም ወናግ ሰገድ ነው፡፡ ወናግ ሰገድ ማለት አንበሳ ነው፡፡
‹‹ልብነ ድንግል በነገሠ በ፲፱ኛው ዐመት መልአከ ኃይሉ (የጦሩ አዛዥ) ዴገልሀን ወደ አዳል ምድር ኼዶ ንብረታቸውን ዘረፈ፤ ሴቶቻቸውንም ማህረከ፡፡ ከዚህ በኋላ ግራኝ* ተከትሎ ምርኮውን ኹሉ አስመለሰ፡፡ ከዚያም በ፪ ዐመት በልብነ ድንግል በ፳፩ኛው የመንግሥቱ ዘመን ሲኾን ግራኝ እስከ ሰመርማ መጥቶ ንጉሥም ከሠራዊቱ ጋር ተጣላ (ተዋጋ)፡፡ እስከ ንጉሡ መዲና ሽምብራ ኩሬ* ድረስ አሳደደው፡፡ /*”ሽምብራ ኩሬ ደብረ ዘይት እና ናዝሬት አጠገብ የሚገኝ ቦታ ነው፤ መዲና ሲል ንጉሡ ለጊዜያዊም ጊዜ ዋና ከተማቸው አድርገዋት ነበር ማለት ነው፡፡ የተሸነፉበትም ቦታ ይኸው ነው፡፡”/
‹‹በዚያም (በሽምብራ ኩሬ) በመጋቢት ፲፩ ቀን ውጊያ አደረጉና፤ ብዙ መኳንንት አለቁ፡፡ እነ እዱግ ራስ መኅዘንቶ፣ ገብረ መድኅን፣ ሸዋ ራስ ጻፈ ላም ሮቤል እና አሴር እና ሌሎች ብዙዎች ሞቱ፡፡ ከዚህ በኋላ በ፪ ዐመት በጥር ፲፯ ተመልሶ ከአዳል ሀገር ተነሥቶ የዚያው ሀገር ሰዎችም እንደነገሩን የካቲት ፲፪ ደዋሮ ደረሰ፡፡ በአይፈረስም ሚያዝያ ፭ ቀን ውጊያ አደረገ፡፡ ራስ እስላም ሰገድ እና ተክለ ኢየሱስ እና ብዙዎች መኳንንትም ሞቱ፡፡ ሻዋንም ገዛት፡፡* /* ስለዚሁ የግዕዙ ቃል በቃል ትርጓሜ፡- “ንብለ ድንግልንም ከእስላም የተወለደ ግራኝ የሚሉ ሰው ተነሥቶ ከሸዋ እስከ ምጽዋ አሳደደው ቤተክርስቲያኑን ሁሉ ተኮሳቸው በሸዋ ባማራ በበጌምድር በደንቢያ እስከ ተከዚ ድረስ ያሉትን የክርስቲያን ልጆች ሁሉ ፈጃቸው፡፡”/
‹‹የቤተ ክርስቲያን መቃጠል (“ውዕየተ ቤተ ክርስቲያን”)፥ “ግራኝ” በሐምሌ ፳፬ ቀን ደብረ ሊባኖስን አቃጠላት፡፡ ነሐሴ ፭ ቀን ራስ ወሰን ሰገድ ሞተ፡፡ ከዚህ በኋላ በ፪ ዐመት ንጉሥ ወደ ምድረ ዐምሐራ* አለፈ፡፡ /*”አምሐራ ወሎ የሚገኘው ሳይንት ነው፡፡”/ በሐጓ ተቀመጠ፡፡ ጥቅምት ፳፪ ቀን ከዚያ ተሰደደ፡፡ ኅዳር ፯ ቀን ግራኝ መካነ ሥላሴን፣ ደብረ ነጎድጓድን፣ አትሮንስ ማርያምን በእሳት አቃጠላቸው፡፡ በ፲፪ ገነተ ጊዮርጊስ ተቃጠለ፡፡ ታኅሣሥ ፯ ደብረ እግዚአብሔር ተቃጠለ፡፡ ታኅሣሥ ፲ ሐይቅ መካነ እስጢፋኖስ ተበረበረች፡፡ ይህንን አድርጎ ወደ ሀገሩ ኼዶ ዐመት ተቀመጠ፡፡ በሚያዝያ ወርም ተመልሶ ወርወርን በረበራት፡፡ በዚያም ከረመ፡፡ ያም የልብነ ድንግል የመንግሥቱ ፳፭ ዐመት ኾኖ ነበር፡፡
‹‹ዳግመኛ በ፳፮ኛው የመንግሥቱ ዐመት በጥቅምት ወር ግራኝ ወደ ትግሬ ወረደ፡፡ሲሬ እና ሠራዌም ተላልፈው ተሰጡት፡፡ ንጉሥም በደምቢያ ከረመ፡፡ ከዚም በጥቅምት ወር ተነሣ፤ ወገራም ደረሰ፡፡ ከዚያም በታኅሣሥ ወር መንገዱን በጸለምት* አደረገ፡፡ /*”ጸለምት፣ ድሮ የጎንደር ክፍል፤ አሆን ትግራይ፡፡”/ አክሱምም ደረሰ፡፡ በዚያም የጥምቀትን በዓል አከበረ፡፡ ከዚያም ተመልሶ መንገዱን በጸገዴ* በኩል አደረገ፡፡ /*”ጸገዴ፣ ድሮ፣ የጎንደር ክፍል፤ አሆን ትግራይ፡፡”/ ግራኝም በኋላው ተከተለው፡፡ በጥር ፳፫ም የአባ ሳሙኤልን መቅደስ አቃጠላት፡፡ ከዚያም አለፈ፡፡ መዘጋም ደረሰ፡፡ ከመከትርም ጋር ተገናኘ፡፡ ተመልሰውም እስከ ደምብያ መሩት፡፡ ንጉሥም መንገዱን ወደ ደራ* በኩል አደረገ፡፡ /*”ደራ፣ ደቡብ ጎንደር የሚገኘውን ቦታ ይጠቁማል፡፡”/ መለሳይም በኋላው ተከተለው፡፡ በዐባዊ ወንዝም የካቲት ፳፪ ተገናኙ፤ ዐቃቤ ሰዐት ነገደ ኢየሱስ እና ልጁ ብእሴ እግዚአብሔር፣ ቀኝ ጌታ ወሰንጌ እና ሌሎች ብዙዎች ሞቱ፡፡ ቁጥር የሌለው ገንዘብ (ንብረት) ጠፋ፡፡ ተስፋ ልዑልም የተማረኩም ነበሩ፡፡
‹‹በዚቺው ዐመት… ከሰራዌ ሰዎች መካከል ብዙዎች ሞቱ፡፡ …አክሱምም ተቃጠለች፡፡ …ሚያዝያ ፲፪ ቀን ሳውል ተሸነፈ፡፡ አዝማቻቸው ዮሐንስ እና ገንዘይ እና ቡላ ሞቱ፡፡ ስሜንን*፣ ደምብያን እና ቤገምድርን ገዛቸው፡፡ ተቀመጠም፡፡ /*”ስሜን፣ በሰሜን ጎንደር ያለው ደባርቅን ማዕከል ያደረገው ምድር፣ ስሜን እና በጌምድር እንዲሉ፡፡”/ እዚህ ላይ የግዕዙ ዝርዝር ትርጓሜ እንዲህ ይላል፡- “ዐፄ [ልብነ ድንግል] ከደንቢያ በመልዛ በኩል ወደ ትግሬ ሄዱ፡፡ እስከ ምጽዋም ሄዱ፡፡ ወንድሙ [የግራኝ] ምስአለ ማርያምን አቃጠላት፤ እና ደንግጾ ሞተ፡፡”
‹‹በ፳፰ኛው ዐመተ መንግሥቱ ወደ ጎዣም ምድር ተሻገረ፤ ብዙዎችን ገደለ፡፡ ወደ ሰራዌም ወረደ፡፡ የሰራዌ ሰዎችንም ገደለ፡፡ ፈጃቸውም፡፡ አምኃም ፈረሻ እስላምን ገደለው፡፡ በ፳፱ኛው የመንግሥቱ ዐመት መስከረም ፳፩ ቀን ወሰንን ገደለው፡፡ ግንቦት ፳፫ ቀን በዚያው ዐመት ማዕከለ ደሴት ገሊላ ተቃጠለች፡፡ መለሳይ ወደ ምድረ ደዋሮ ኼደ፡፡ ፰ ወር ተቀመጠ፡፡ ከዚያ በዚያ ተመልሶ በ፴ኛው የመንግሥቱ ዐመት ያ መለሳይ ወደ ንጉሥ እንዲህ ሲል ላከ፡- «ፍቅርን እናደርግ ዘንድ ሴት ልጅህን ሚስት ትኾነኝ ዘንድ ስጠኝ ይህንን ነገር ካላደረግህ የምታመልጠኝ ነገር የለም፡፡» ንጉሥም እንዲህ ሲል መልእክትን መልሶ ላከለት፡- «አንተ አረማዊ ስትኾን እንዴት እሰጥሀለሁ? አልሰጥህም፤ በእጅህ ከምወድቅ በእግዚአብሔር እጅ ብወድቅ ይሻለኛል እንደ ችሎታው እንዲሁ የምሕረቱ መብዛት ነውና እሱ ለደካሞች ኀይልን ለጽኑዓን ድካምን ይሰጣል፡፡» [ብሎ ላከበት]፡፡ ያን ጊዜም ለንጉሥና ሠራዊቱ ታላቅ መከራ ብዙ ስደት ረኀብ እና ጦርነት ኾነ፡፡
‹‹ሚያዝያ ፯ ቀን ዕለቱ ረቡዕ ሲኾን በሰሙነ ሕማማት ባላሰቡት እና ባልጠረጠሩት ኹኔታ መንገድ ቀጭን አቦከር ወጋቸው፡፡ አዛዥ ተክለ ጊዮርጊስ፣ አዛዥ አምኃ እና ሚካኤል፣ ዳረጎት፣ ያዕቆብ፣ ጋድ የደብረ ሰማዕት መምህር አባ ተንሥአ ክርስቶስ ዘቢዘን* እና አመተ ልዑል ሌሎች ብዙዎችም ሞቱ፡፡ /*”ቢዘን፣ ኤርትራ ውስጥ የሚገኝ ታላቅ ገዳም፡፡”/ ጌዴዎን እና ሐመተ ንጉሥ (የንጉሥ አማት) ዮዲት እና ብዙ የንጉሥ ሠራዊት ከእነሱ ጋር ተማረኩ፡፡ ስፍር ቁጥር የሌለው ገንዘብ (ንብረት) ጠፋ፡፡ በዚያ ዘመን ከስደት ብዛት የተነሣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለ ፋሲካ ተጠራጠረ (ተለያየ)፡፡ ፋሲካ ሚያዚያ ፲፰ ቀን ይውላል (ይኾናል) የሚሉም ነበሩ፡፡ የእግዚአብሔርን ሕግ ያወቁትስ ከንጉሥ ጋር በሀይማኖት ተባበሩ፤ ሚያዝያ ፲ ቀን ደስታን አደረጉ፡፡ ፋሲካንም በ፲፩ “በፍስሐ” አከበሩ፡፡
‹‹…ዳግመኛም እመር (“ኡመር”) ተከተለው [ልብነ ድንግልን]፡፡ በአንድ መውጊያ ተወጋ፡፡ እንደ ነገሩን መሞትንስ አልሞተም፡፡ ይህም የኾነው ጥቅምት ፩ ቀን ነው፡፡ በዚህ ወር ከደምብያ ከተነሣ ወዲህ እመር ወደ ሲሬ ወርዶ የቀሩትን አብያተ ክርስቲያን አፈረሰ፡፡ መዘበረ፡፡ ተኅሣሥ ፲ ቀን መጥበቢላን አቃጠላት፡፡ በ፲፭ ጉትማን አጠፋት፡፡ ብዙዎች መነኮሳት ሞቱ፡፡ ከዚያ ተመልሶ በጥር ወር ዘና ደረሰ፡፡ የክብርቶን ቤተ ክርስቲያንን ንዋይ ወሰደ፡፡ በ፲፫ የደብረ ከርቤን ቤተ ክርስቲያን ንዋይ ወሰደ፡፡ ወደ ሲሬ ተመልሶ ጥቂት ጊዜ ተቀመጠ፡፡ ከዚያም ተነሥቶ ወደ በላይጢጎ ኼደ፡፡ እግዚአብሔር ኀይሉን ለማሳየት በወደደ ጊዜ ስሙ ያልታወቀን አንድ ደሀ ምስኪን ላከ፡፡ ያም ደሀ [እመርን] ከሚስቱ ጋር ተኝቶ ሳለ ወደ እሱ ገብቶ ከእንብርቱ በላይ ወጋው የከዝር መጠን ያህልም ቀደደው፡፡ ያዩ ሰዎች እንደ ነገሩንም ይህ የኾነው የወላዲተ አምላክ እመቤታችን ማርያም የኪዳኗ ዕለት በኾነበት በየካቲት ፲፮ ነው፡፡
‹‹… የትዕቢትን ሸለፈት/ሸንኮፍ ከክርስቲያን እና ከእስላም ልብ ያስወግድ ዘንድ ይህንን ያደረገው የእግዚአብሔርን ኃይሉን አድንቅ፡፡ እንደዚህ ያለውን ድል/ስጦታ ከክርስቲን መኳንንት መካከል አንዱ አግኝቶ ቢኾንስ ኖሮ በእግዚአብሔር ኃይል ሳይኾን እራሴ በኃይሌ አደረግኩት ባለም ነበር፡፡ የኢትዮጵያም ኹለንተናዋን ይልቁንም የትግሬ ሹማምንትን አሳልፋ ባልሰጠችውም ነበር፡፡ ማእምረ ኅቡኣት/የተሸሸገውን የሚያውቅ እግዚአብሔር በአልጠረጠሩት በ፩ ነዳይ ከደዋሮ እስከ.. የሰደደንን …ኀያልን አሳፈረው፡፡
‹‹በዚቺ ወር በየካቲት ፫ ቀን አምባ ነገሥት ግሼ ተሻረ* ፤ ተበረበረ፡፡ /*”ተሻረ፣ ተስዕረ፣ የሚለውን የግእዝ ቃል ስለሚጠቀም፤ ጥሶ መግባትን ያመለክታል፡፡”/ በዚያም ከይኹኖ አምላክ እስከ መንግሥተ ልብነ ድንግል ድረስ የተሰበሰቡ መዛግብተ ነገሥት እና ብዙ ልብሰ ሐሪር ተገኘ፡፡ ሌሎችን መዛግብት ግን ያለ እግዚአብሔር (ብቻውን) የሚያውቅ የለም፡፡ ያን ጊዜም ወርቅ እንደ ድንጋዮች ልብሰ ሐሪር (ከሐር የተሠረራ ልብስ) እንደ ቅጠል ኾነ፡፡ የኅልቅ ዋጋ ፴ አሞሌ እና ወቄት ለ፩ በሬ ነበር፡፡ በዚያ የነበሩ እስራኤላውያንን በሰይፍ ገደሏቸው፡፡ በሀይማኖታቸው ወደ ባሕር የተወረወሩ ነበሩ፡፡ ይህንንም ወዚር ሙጃሂድ እና አምጁስ አደረጉ፡፡ ከዚህም በኋላ መስከረም ፭ ቀን በዘመነ ማቴዎስ ንጉሣችን ልብነ ድንግል ዐረፈ፡፡ ከአባቶቹ ጋርም አንቀላፋ፡፡ የመንግሥቱ ዐመትም ፴፪ ነው፡፡ በአባ አረጋዊ ደብር በዳሞ* ተቀበረ፡፡ /*”ዳሞ፣ ትግራይ ውስጥ ይገኛል፤ የአቡነ አረጋዊ ገዳም፤ መሥራቹም አቡነ አረጋዊ ናቸው፤ ታላላቅ አባቶች ተገኝተውበታል፤ በገብረ መስቀል ዘመን፡፡”/
‹‹ከዚህ በኋላ ስመ መንግሥቱ አጽናፍ ሰገድ የተባለ ልጁ ገላውዴዎስ ሕፃን ሳለ ነገሠ፡፡ ተነሥቶ በቡርከሎ መከዳ መካከል ደረሰ፡፡ ድንገትም ከወዚር ዓሣ እና ገራድ እስማን፣ ድልበ ኢየሱስ፣ ዮራም እና ሌሎች ብዙዎች መለሳይ ጋር ተገናኝቶ ከእነሱ ጋር ታኅሣሥ አንድ ቀን ውጊያ አደረገ፡፡ ብዙዎችንም ገደለ፡፡ እንደ አራስ ድብ* እና የሚያስፈራ አንበሳ አስፈራቸው፡፡ /*”ድብ፤ በቁሙ አውሬ የዥብ ወገን፤ የሚያደባ እና የሚሸምቅ አድብቶ የሚይዝ የሚነጥቅ ጥላው የሚያፈዝ የሚደብት ጸጉራም ዐመድማ፡፡”/ ከፊቱ መቆም አልቻሉምና ኼዱ (ሸሹ)፡፡  እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና ሊዋጋው የሚችለው ማን ነው? አሉ፡፡ ይህንንም አድሮበት ባለ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል አደረገ፡፡ ውጊያን አልተማረም፤ ያለዚች ቀን ከውጊያ ዘንድም አልዋለምና፡፡ ከዚያም ተነሣ ምድረ ስሜንም ደረሰ፡፡ የስሜን፣ የለዋሬ፣ የኆፃ፣ የጸለምት አገውም ተቀበሉት፡፡ ዳግመኛ ወዚር ሙጃሒድ ገረድ እስማን ገንዘ ገራደ፣ ነስረዲን እና የሲሬ እና የሠራዌ ሹማምንት እና ብዙዎች መለሳይ በላዩ ላይ ተሰባሰቡበት፡፡ ሊወጉትም አልተቻላቸውም፡፡
‹‹… ከዚያም ተነሥቶ ወደ ተከዜ አለፈ፡፡ ወደ ምድረ ሰርድ ደረሰ፡፡ የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የትንሣዔውን መታሰቢያ ፋሲካን አከበረ (አደረገ)፡፡ በዚያሳለ ገራድ እመር ወደ እሱ መጣ፡፡ በሰልፍ ገጠሙት (ቀረቡት)፡፡ ሚያዝያ ፳፱ ቀን ውጊያ አደረጉ፡፡ እንደዚህ ያለ ኃይል አላየንም፤ አልሰማንም አሉ፡፡ ሕፃን ሲኾን በብዙ ሳይኾን በጥቂት (ተዋጊዎች) ሞትን የማይፈራው ተዋጋቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ስሜን ምድር ኼደ፡፡ በዚያው ዐመት ግብጣናቸው ድንግስቶቡ የኾነ ከፖርቱጋል ሀገራቸው ሠራዊት መካከል ፈረንጆች መጡ፡፡  አባ እስማን ኑርንም ገደሉት፡፡ በድርባዋም* ከረሙ፡፡ /*”ድርባዋ፣ ኤርትራ ውስጥ የምትገኝ ታላቅ ቦታ፤ ድርባዋ/ሩአ ይላሉ፣ የድምፅ ለውጡን ይመለከታል፣ ወ ከፊል አናባቢ ስለሆነ፡፡”/
‹‹ … ግራኝም በታህሣሥ ወር ተነሣ፡፡ ወደ ምድረ ትግሬም ኼደ፡፡ ፈረንጅም ከድባርዋ ወጣ፡፡ ከእነሱም ጋር የንጉሥ እናት እቴጌ ሰብለ ወንጌል ስትመግባቸው በገንዘብ ስትረዳቸው በጥበብ እና በምክር ስታፅናናቸው ነበር፡፡ መጋቢት ፳፱ ቀን ሲኾን በምድረ አነጻ ከግራኝ ጋር ተገናኝተው ተዋጉ፡፡ በነፍጥም ነደፉት፡፡ አልሞተም፡፡ ግራኝም በዞብል ከረመ፡፡ ንግሥት ሰብለ ወንጌልም በአፍላ ከፈረንጆች ጋር ነበረች፡፡ በነገሠ በ፪ኛ ዐመት መስከረም ፫ ቀን ውጊያን አደረገ፡፡ ግብጣንም በጥቅምት ወር ሞተ፡፡ ንጉሥ አጽናፍ ሰገድም መጣና ከተረፉት (ከቀሩት) ፈረንጆች እና እናቱ ጋር በምድረ ስሜን ተገናኘ፡፡ በሽዋዳ* ተማክረው ኅዳር ፲፫ በወገራ ውጊያን አደረጉ፡፡  /*”ሸዋዳ፣ በለሳ፡፡”/ ሲድ መሐመድን እና እስማንን እና ጠሊላን ገደላቸው፡፡ የተረፉት እንደጢስ በነኑ፡፡ ድንጋይ ተሸክመው [ለምሕረት] የገቡ ነበሩ፡፡ በ፲፱ ወደ ደረስጌ ወረደ፡፡ ቤቶቻቸውን በእሳት አቃጠለ፡፡ ንብረታቸውንም ማረከ፡፡ ወደ ሽዋዳ ተመልሶ ፪ ወር ኖረ፡፡ ግራኝም ከዘብለ ተነሥቶ ደመብያ ገባ፡፡ ንጉሥም ከሽዋዳ ተነሥቶ የካቲት ፭ ቀን ወይና ደጋ ደረሰ፡፡ በዚያ ተቀመጠ፡፡ ግራኝም ከደረስጌ ተነሥቶ ሳለ የግራኝ ሠራዊት ለንጉሥ ቅርብ ነበሩ፡፡ የንጉሥ ሠራዊትም በ፩ ቦታ ዋሉ፡፡
‹‹ንጉሣቸውም ሕፃን አጽናፍ ሰገደን እና አገልጋዮችን ያጸናቸውን የእግዚአብሔርን ምሕረቱን ተመልከቱ፡፡ ቀድሞ ስሙን በመስማት ሲፈሩ እና ሲርዱ ነበርና፤ ይቃረቡና ፊት ለፊት ይተያዩ ዘንድ አደረጋቸው፡፡ እሱ [ግራኝ] በሸዋ ክርስቲያን በትግሬ ሳሉ የደረሰባቸው እየመሰላቸው ድንጉፃን ነበሩ፡፡ የእግዚአብሔር ምሕረት በጎበኛቸው ጊዜ [ግን] ይስቁበት ይሳለቁበት ያዙ፡፡ [ግራኝም] የካቲት ፲፯ ቀን በመድፍ እና በነፍጥ እና በትርኩ እየተማመነ በእግረ ትዕቢት ተነሣ፡፡ ይህን ያህል ዐመታት ተጋደልኳቸው፤ አሳደድኳቸው፤ ዛሬ በፊቴ ይቆማሉን? አለ፡፡ (በማለት ደነፋ)፡፡ ንጉሥም በወላዲተ አምላክ በእመቤታችን ጸሎት እና በእግዚአብሔር ታምኖ መለሰለት፡፡ ቀረበው፡፡ ገጠመው፡፡ የቀደሙት የንጉሥ ወታደሮች ግን ንጉሥ ከመድረሱ በፊት ግራኝን ገደሉት፡፡ በዛንተራ* ተራራም ወደቀ፡፡ /*”ዛንተራ፣ ጎንደር የሚገኝ፡፡”/ በዕለተ ረቡዕ በ፫ ሰዓት በትእዛዘ እግዚአብሔር ሞተ፡፡ ሠራዊቱም እንደጢስ እና እቶን ዐመድ ተበተኑ፡፡ ከብዙ ፍርሃት የተነሣ ከሚስቱ ከድል ወንበራ ጋር እስከ አትበራ የሸሹ አሉ፡፡ ፈረስን እና ሰይፍን ትተው (ጥለው) በአንገታቸው ገመደ አስረው የገቡም (ምሕረት የጠየቁ፣ እጅ የሰጡ) አሉ፡፡ … አጽናፍ ሰገድ በነገሠ በ፪ ዐመት በ፭ ወር ከ፳፪ ቀን ግራኝ ሞተ፡፡ ግራኝ በሞተ በ፪ ዐመት አባስን ገደለው፡፡
‹‹…ከዚህ በኋላ በ፲፱ኛው ዐመት እስላም ኑር ከአዳል መጣ፡፡ እሱም የግራኝ የእኅቱ ልጅ ነው፡፡ የመምጣቱ ምክንያትም ተባለ፡፡ ግራኝ ባሏ በወደቀበት ዕለት ድል ወምበራ ስትሸሽ ኑርም ከእርሷ ጋር ሸሽቶ ወደ ሀገራቸው አደል ደርሰው ሳለ ለእስላሞች ልማዳቸው ነው እና ያገባት ዘንድ ኑር ወደደ፡፡ እሷም እኔን ልታገባ ከወደድክ የባሌን ገዳይ ያንን የክርስቲያን ንጉሥ ኺድ ግደለው አለችው፡፡ ስለዚህም ኑር መጣ፡፡ ንጉሥም መምጣቱን በሰማ ጊዜ ሠራዊቱን ሰብስቦ ከኑር ጋር ይዋጋ ዘንድ ኼደ፡፡ ፊት ለፊት በሚተያዩበት (በተፋጠጡበት) ጊዜ መነኮሳት ወደ ንጉሥ ገላውዴዎስ ዘንድ ደረሱ፡፡ መልክአ አባ ተክለ ሀይማኖትን የደረሰው የደብረ ሊባኖስ መምህር አባ ዮሐንስ፣ አባ መቀ/ቃርስም እና ሌሎች ብዙዎች መነኮሳት መጡ፡፡ ንጉሥንም ከመንግሥተ ምድርና ከመንግሥተ ሰማይ ምረጥ፤ ካደርክ ታሸንፋለህ ካላደርክ ዛሬ ትሞታለህ፤ ወደ መንግሥተ ሰማይም ትገባለህ አሉት፡፡
‹‹ስለ መንግሥተ ሰማያት መሞት ይሻለኛል አላቸው፡፡ በዚያው ቀን መጋቢት ፳፯ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለቱ ዕለት በኾነበት ቀን መኳንንቱ ንጉሥ ገላውዴዎስን ለመኑት ጌታችን ሆይ ይህንን ፋሲካ ትውልልን ዘንድ ከአንተም ጋር በመብል ደስ ይለን ዘንድ ተማጽነንሀል አሉት፡፡ በልቼ ለምፀዳዳበት ጠጥቼ ለምፀዳዳበት ለዚህ [ምድራዊ መብሉን ለማለት ነው] ፋሲካ አላየውም አልውልም፡፡ ነገር ግን መፀዳዳት በሌለበት በሰማያዊ ፋሲካ እውላለሁ፤ በዚያም ከጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በዚያ እደሰታለሁ አላቸው፡፡ ይህንን ብሎ በውጊያው መካከል ገባ፡፡ ተንባለት (እስላሞችም) በብዙ ጦር ወጉት፡፡ ራሱንም ቆርጠው ወደ አዳል ወሰዱት፡፡ በእንጨት ላይም ሰቀሉት፡፡… ከዚህ በኋላ ነጋድያን የተቆረጠውን ራሱን ወስደው ወደ ሀገረ አንጾኪያ አደረሱት በታላቁ ሰማዕት በቅዱስ ገላውዴዎስ መቃብርም ቀበሩት፡፡የቀረው ሥጋው እስከ ዛሬ ድረስ በተድባበ ማርያም አለ፡፡ ወደ ነገራችን እንመለስ ንጉሥ ገላውዴዎስ በሞተበት ዕለት ብዙዎች መነኮሳት ሞቱ፡፡ እጨጌ* ዮሐንስም በዚቺ ቀን ሞተ፡፡ /*”እጨጌ፣ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ በደብረ ሊባኖስ መንበር የሚቀመጡ አባት፡፡”/ ከሊቃውንትም ዐቃቤ ሰዐት እና ቄስ ሐፄ ከእሱ ጋር ሞቱ፡፡†
/†”ዐፄ ገላውዴዎስ ሲሞት የተገጠመለት፡፡ በዚህ ጊዜ አማርኛ አድጎ ነበር ማለት ነው፡፡ ከእነ ዐፄ ዐምደ ጽዮን ዘመን ይሄ የግእዝ ተጽዕኖ የለበትም፡-
«ዐፄ ገላውዴዎስ ጌታን ተከተለ
ፋሲካን ሳይውል ዐርብ ተሰቀለ፤
ጌታውም ሳይረሳው የፋሲካ ለታ
አስጠርቶ አበላው ከጧት እስከ ማታ፤
ዐፄ ገላውዴዎስ እንደ ዮሐንስ
ባሕር ዳሩን ዞሮ ሸዋ ሲመለስ
አንጾኪያ ታየ ብርሃንን ሲለብስ፡፡»”/
‹‹… ሚናስ ወንድሙንም ብዙ ወርቅ ለእስላሞች ሰጥተውከተሸጠበት አምጥተው አነገሡት፡፡ ሺሜ* የይቴጌ ምን ይቻሌ ልጇ አቤቱ ዮናኤል ከአገባት ስሟ ሰበነ ጊዮርጊስ ከተባለው ከአንዲት ልጅ በቀር ወንድ ልጅ ለንጉሥ ገላውዴዎስ አልነበረውም፡፡… /*”ሺሜ፣ በአፈረዋናት የምትገኝ ጥንታዊት ባለታሪክ ቦታ ናት፣ ሺሜ ስትነሣ የነገሥታቱ ዋና ቤተ ሰብእ የሆነችው እቴጌ ምንይቻሌ አብራ ትነሣለች፣ ልጇ አቤቶ ዮናኤልም በጀግንነቱ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ ጀግንነቱም በድጓው ውስጥ ሥራው በዜማ ምልክትነት ተጠቅሷል፡፡”
‹‹ሠርፀ ድንግል በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ፲፫ ዐመት ከ፮ ወር ኾኖት ነበር፡፡ በዚያው ዐመት ሠራዊቱ ከእስላም ጋር ሆነው ዐመፁ፡፡ ከከተማም ከተማም ንብረትን ዘረፉ፡፡ … በዚያው ዐመት የንጉሥ እናት ይቴጌ ሰብለ ወንጌል ሞተች፡፡… በ፱ኛው ዐመት ወደ ደምብያ መጣ፡፡… ከእነርሱም ብዙ የእጅ መንሻ ወሰደ፡፡ መዲናውንም በጾቢት አደረገ፡፡ በዚያው ዐመት ወደ ዝዋይ ምድር ኼደ ሉባሁ አምቢሳ ሲኾን ቦረንን ወጉት፡፡… በዚያው ዐመት ንጉሥ የዘርዐ ዮሐንስ ተከታዮችን ቆጥሮ ጭፍራ አደረጋቸው፡፡ ወደ ደምብያ መጣ፤ አህጉሩንም ኹሉ በእጁ አስገባ፡፡ ጨዋ ሠራለት፡፡ በ፲፫ኛው ዐመት መሐመድ መጣ፡፡ የይስኸቅ ዐመፃው በረታ፡፡ ዳረጎትን በትግሬ ሾሙት እና ከይስሐቅ ጋር ተዋጋ፤ አሸነፈውም፡፡ በ፲፬ኛው ዐመት ወደ መሐመድ ኼደ፡፡ በወቢ ወንዝ ወጋው፤ አሸነፈውም፡፡ በዝኆን ዱር ከረመ፡፡ በ፲፭ኛው ዐመት በመጆ ወንዝ ቦረንን ወጋው፤ አሸነፈውም ወደ ደምብያ ተመለሰ፡፡ አበጢን በወይና ደጋ አገኘው፡፡ ያለ ማስቀረትም ያለማትረፍም ገደለው፡፡››
«እኚህ ጦቢያዎች ያምላክ ሥጋ ነፍሥ
ካፍሪቃ አልፈው-ተርፈው በባሕር በየብስ
ገና ይሰፋሉ እንደግዜር መንፈስ፡፡»
ከእነዚህ — ለሀገር ለትውልድ ለታሪክ ብለው — ዘመናቸውን ሁሉ ካገር ሃገር ሲንከራተቱ ከኖሩ — ከእነዚህ ባለታሪክ፣ ሀገር-ወዳድ፣ ባለታላቅ ራዕይ፣ ሥልጡን ያፍሪቃ ህዝቦች፣ ከእነዚህ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን በመፈጠሬ — ታላቅ ክብርና ኩራት ይሰማኛል፡፡ አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ሁሉ አብዝቶ ይባርክ ዘንድ ተመኘሁ፡፡ የብዙሀን እናት — እምዬ ኢትዮጵያችን — ለዘለዓለም ትኑር፡፡ አበቃሁ፡፡
ከላይ የቀረበው ጽሑፍ የተወሰደው (እጅግ ልባዊ ከሆነ፣ እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር)፡-
«ታሪከ ነገሥት … ከምኒልክ ፩ይ እስከ ምኒልክ ፪ይ»፣ አዘጋጂ መ/ር ደሴ ቀለብ (አ.አ.ዩ.)፣ ታተመ በኢት/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን፣ ፪ሺ፯ ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፡፡
«ይህ የመምህር ደሴ መጽሐፍ ታሪክን፣ ቋንቋንና ሃይማኖትን አገናዝቦ የያዘ የምርምር ውጤት ነው፡፡ የጥንት የግእዝ ጽሑፎችን ተርጉሞ፣ የየዘመኑን ነገሥታት ታሪክ ያቀረበ ስለሆነ በሙያው ለተሰለፉ ሁሉ ጥሩ መረጃ ሊሆን ይችላል፡፡… መምህር ደሴ… ይህን መጽሐፍ ‹ታሪከ ነገሥት› በሚል ርዕስ ለአንባብያንና ለተመራማሪዎች አበርክቷል፡፡ ይህም ሌሎችን የሚያበረታታ ጥሩ ተግባር ነው፡፡»
— ባየ ይማም (ፕሮፌሰር)፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፡፡
«ኲሎ አመክሩ ወዘሠናየ አጽንዑ፡፡» («ኹሉን መርምሩ፤ መልካም የኾነውንም ያዙ፡፡») — ፩ኛ ተሰ ፭፥፳፩
Filed in: Amharic