>

እምዬና የቆሎ ተማሪዎች ትዝታ (አበበ ሀረገወይን)

እምዬና የቆሎ ተማሪዎች ትዝታ
የብላታ መርስኤ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ትዝታ
አበበ ሀረገወይን
አጤ ምኒልክ በ1896 አዲሷን እንጦጦ ማሪያም ሲያስገነቡ በቦታው በመገኘት ስራም ላይ በመሳተፍ ሱራተኛውን ያበረታቱ ነበር።
አንድ ቀን ለዚሁ ስራ ጥድ ሊያስቆርጡ አሽከሮቺቸውን አስከትለው ሲሄዱ ሕጻናት ተሰብስበው የሚማሩበት አንድ ተማሪ ቤትደረሱ። ሕጻናቱ ትምህርታቸውን አቋርጠው እንዳይነሱ ስለ ታዘዙ ቁጭ ብለው ትምሕርታቸውን ቀጠሉ። ጃንሆይም ወደ ሕጻናቱ ቀርበው የእያንዳንዱን መጽሐፍ እየተመለከቱ ዜማውን ያዳምጡ ጀመር። አስተያየታቸው ሁሉ በርህራሄና በፈገግታ ነበር። ተማሪዎቹም ጃንሆይን ከእግር እስከ ራስ ድረስ ለማየት ስለ ቻሉ እጅግ ደስ አላቸው። ጫማቸው ጥቁር ነው ፣ እጀ ጠባባቸው አብደልካኒ ቀሚስ ኑው ባለጥበብ ኩታ ለብሰዋል። በኩታቸው ላይ ላይ ባለወርቅ ጥብጣብ ጥቁር ካባ ደርበዋል። በእጃቸው ሰንደቅ መቋሚያ ከመሐረብ ጋር ይዘዋል።
ከቆሎ ተማሪዎቹ አንዱ — መርስኤ ኀዘን ነበሩ። ይህ የሳቸው ትዝታ ነው።
እንዲህ ነበሩ የእኛ አባት ፣ እምዬ ምኒልክ
 
እምዬ ደስተኛ ነበሩ- ብስክሌት እየነዱ አሜሪካኖችን ያስደንቁም ያዝናኑም ነበር
 
እምዬ ምኒልክ ጥዋት የሚነሱት ገና ሳይነጋ ከሌሊቱ 10 ሰአት ነበር። መጀመሪያ ጸሎት ቤታቸው ገብተው አንድ ሰአት ያህል በጸሎት ከቆዩ በኋላ ቀለል ያለ ልብስ ለብሰው ሀኪማቸው ቪታልየን እንደመከራቸው ባሽከሮቻቸው ተከትለው ፈጠን ብለው በመራመድ ወደ አንድ ሰአት የሚፈጅ ጊዜ ያሳልፋሉ። የሚከተሏቸው ብርድ ፈርተው በቡልኮ ሲሸፋፈኑ እሳቸው ካለ ምንም ድርብ ሲሄዱ ያዩ በሽታ እንዳይዛቸው እያሉ ይፈሩ ነበር።  በኋላም ስትሮክ የያዛቸው በጥዋት ስለ ነበር ብርድ መቷቸው ነው ይባል ነበር።
እምዬ አልፎ አልፎ በበቅሎዋቸው ሆነው በከተማ ይዘዋወሩና ከህዝብ ይገናኙ ነበር። በገበያውም ፣ ባደባባዩም ይዞራሉ። ሱቆች ከበቅሎ ወርደው ይገባሉ። የህዝብን ስሜት ለማወቅ ከማንም ጋር ያወሩ ነበር። ጨዋታ የሚያውቅ ሰው ካለ እየሳቁ ተጨዋውተው አመስግነው ያልፋሉ።
ምንም የእምዬ ቀን ብዙ ስራ ያለበት ቢሆንም ፣ መዝናናትም የጨመረ ነበር። ጨዋታ አዋቂዎችና አዝናኞች በቤተ መንግስት መተው እሳቸውንና መኳንንቶቻቸውን አስቀው ይሄዱ ነበር። አለቃ ገብረ ሀና ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው። እምዬ በአጼ ቴዎድሮስ ቤት እንደአለቃ ዘነብ አይነት አዋቂና በሳል ጎንደሬዎች ጋር ስላደጉ የሰሜኑንም የመሀል አገሩንም አማርኛና ፈሊጦች በደምብ ስለሚያውቁ የቋንቋ ጨዋታዎችን ይወዱ ነበር።  እምዬ የመዝናናት ለኑሮና ለስራ ስኬታማነት ጠቃሚነቱን ስላወቁ ያገርን ብቻ ሳይሆን የባህር ማዶውንም ለሕዝባቸው እንዲመጣ ይጥሩ ነበር። ለዚህ ነው ሲኒማ ቤትና የፎኖግራፍ ሙዚቃ እንዲስፋፋና እንደ ነጋድራስእሸቴን አይነት ወጣቶች የአርት ጥበብ እንዲቀስሙ ወደ አውሮፖ የላኳቸው።
እምዬ አዳዲስ ነገር በተለይ ላገር ይጠቅማል የሚል ቴክኖሎጂ አፍቃሪ ነበሩ። ይህን የተማሩት ከአጼ ቴዎድሮስ ነበር።  በጥረታቸው የፈረንጆችን አሻጥር በመቋቋም የአጼ ቴዎድሮስን ህልም ባቡሩንም ፣ መኪናውንም ፣ ሰአቱን ፣ ካሜራውን ፣ ብስክሌቱን ወዘተ ያስመጡት። የመጣውን ሁሉ ደሞ ራሳቸው መርምረው ማወቅ ይፈልጋሉ።  ለምሳሌ የጅ ሰአት ሲያስመጡ ፣ ቢበላሽስ ማን ይጠግነዋል በማለት ከስዊስ ባለሙያ አስመጥተው ጥገናውን እራሳቸው ተምረው የተበላሸበት ሰው ሰአቱን ለእደሳ እሳቸውጋ ያመጣ ነበር። ቢስክሌት ሲያስመጡም ንጉስ ነኝ ሳይሉ እየወደቁ እየተነሱ ተለማምደዋል።  ወደኩ ብለው አያፍሩም።  ቢስክሌት የተማሩ አካባቢ የአሜሪካን ልኡካን መተው ቢስክሌታቸውን ነድተው በማሳየት እዝናንተዋቸዋል።
እምዬን አንዱ ልዩ የሚያደርጋቸው ርህሩህነታቸው ነበር። ለምሳሌ በሩሲያው ሆስፒታል በዚያን ዘመን ኦፕራሲዮን ሲደረግ ማደንዘዣ ስላልነበረ እምዬ እዚያ ተገኝተው በሽተኛው በስቃይ ሲያለቅስ እጁን ይዘው አይዞህ እያሉ የሱንም የራሳቸውንም እምባ ያብሱ ነበር።
እምዬ የተሟላ ስብእና የነበራቸው ያገራችን አባት ናቸው።
የእምዬን ነፍስ አምላካችንይማር።
 
በዘመኑ ባሜሪካ እንኳን ያልተለመደ ዘመናዊ የመድሃኒት ስርጭት ሕግ!!!
በ1888 የመጀመሪያው የሩሲያ ሆስፒታል በኋላ ምኒልክ ሆስፒታል የተባለው ከተከፈተ በኋላ የተለያዩ የመዳህኒት መሸጫ መደብሮች ወይም ፋርማሲዎች ባዲስ አበባ ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። እነዚህንም መርቀው በመክፈትም አንዳንዴም በድንገት እምዬ ምኒልክ ይጎበኙ ነበር።
በዚያን ዘመን የሚመጡት የመዳሕኒት ቢልቃጦችና እሽጎች የውጭ ቋንቋ ምልክት ብቻ ነው የነበራቸው።  ይህን ካስተዋሉ በኋላ የሚከተለውን የመድሂኒት ሕግ አስተላለፉ…..እያንዳንዱ ቢልቃጥ ወይም እሽግ ፣ የመዳሕኒቱ ስም ፤ ለምን እንደሚወሰድ ፤ አጠቃቀም ፣ ወይም አደራረግ ፤ በአማርኛ እንዲለጠፍ….ብለው አዘዙ ብሎ ዲ ካስትሮ ዘግቧል።
ይህ የእምዬ ዘመናዊ ሕግ ይህን በሚመለከት በአሜሪካን በነሱ 1913 ከእምዬ ሕግ ከአስር አመት በኋላ እሳቸው በሞቱበት አመት ነበር የወጣው።
ኧረ ማን እንደ እምዬ
Filed in: Amharic