>

"የሚኒልክ ሃዉልት ይፍረስ" 27 አመት ያስቆጠረው አሮጌ የወያኔ መፈክር (እስራኤል ሶቦቃ)

የሚኒልክ ሃዉልት ይፍረስ”
27 አመት ያስቆጠረው አሮጌ የወያኔ መፈክር
እስራኤል ሶቦቃ
 
ይህ የሚኒልክ ሃውልት ጉዳይ አዲስ ሳይሆን 27 አመት በፊት መጀመሪያ ሲነሳ ኦነግም ኦህዴድም ሸገር ነበሩ። ይህን መፈክር አንግባ ቀድማ አደባባይ የወጣቺው ግን አዴት ላይ ተወልዳ በዴራ በኩል ወደ ኦሮሚያ የዘለቀቺውና በወያኔ ኣንቀልባ ትታዘል የነበረቺዋ ጩጨዋ Dh.D.U.O.ነበረች።
 
ያኔም ቢሆን ኦነጎች የወያኔን ፍላጎት ያውቁ ስለነበር በኦሮሞና በሌሎች ህዝቦች መሃከል ግጭት እንዳይፈጠር ጠንክረው ይስሩ ነበር። ግባቸው እርሱ አልነበረምና። ለእንዲህ አይነቱና የፓለቲካ ጠቀሜታው ጎልቶ ለማይታይና ለተራ የፕሮፖጋንዳ ፍጆታና እርባና ቢስ ጋጋታም ቦታ አልነበራቸውም። ወቅቱ የሚጠይቀው በርካታ ስራዎች ነበሩትና።
 
ያቺ አሮጌዋ Dh.D.U.O ገና የበረሃ ነጠላ ጫማዋን ሳትቀይርና ጨበረ ጸጉሩዋን ባግባቡ ሳትከረከም ነበር ካርቶኒ ላይ “የሚኒሊክ ሃውልት ይፍረስ” የሚል መፈክር ለጥፋ የአራዳን አደባባይ በሰልፍ እንድታቋርጥ በወያኔ የታዘዘቺው…. የዛሬን አያርገውና። “ለሰፊው ህዝብ ጥቅም” ወያኔ በተቆጣጠረቺው “የደርግ ኢሰፓ” ሚዲያዎች የዜና ሽፋን ተሰጠው። 
 
ህዝቡ ገና ኦህዴድንና ኦነግን ባልለየበት ወያኔዎች ቅምና በቀል የማስረጽ እኩይ ተግባራቸውን በሰፊው ተያያዙት። ወያኔ ደፋሯ ካድሬዎቿን፣ ሚዲያዎቿን፣ ነጭ ለባሾቿን፣ ስላምና መረጋጋት ብላ የመለመለቻቸዉን ሁሉ ሳይቀር ለዚህ መጠነ ሰፊ ዘመቻ ታጥቀው እንዲሰማሩ ኣዘዘች። አማራና ኦሮሞ እሳትና ጭድ እንደሆኑ በመግለጽ ቤንዚን ማርከፍከፍ የጀመረቺው ያኔ ነበር።
 
የሚኒልክ ሃውልት እንዲፈርስ ከሩቅ የገጠር መንደሮች ጭምር ህዝቡ ጥይቄዎችን ማቅረቡን የወያኔ ሚዲያዎች ስፊ የዜና ሽፋን በመስጠት ዘገቡት። ሸገር ላይ የሚኒሊክ ሃዉልት ስለመኖሩ እንኳን የማያውቀው የዳር ሃገር ሰዉ ይህን ጥያቄ ስለማቅረቡ ግን እርግጠኞች አልነበርንም።
ብዙም ሳይቆይ “ዲማ ጉርሜሳ” የሚል የወያኔ ስያሜ በተሰጠው የጦር አዛዥ የሚመራው የወያኔ ጦር አርባ ጉጉና ባካባቢው በሰፈሩ ያማራ ተወላጆችና በኦሮሞ ህዝብ መሃል ሁከት በመፍጠር ደም ማፋሰሳቸውን ዛሬም ህዝቡ በጥልቅ ሃዘን ያስታውሰዋል።
 
አሮጌዋ የነኩማ Dh.D.U.O አሁን የለቺም። ኣሁን ያለዉ ግፍና ጭቆና የወለደዉ የለዉጥ ሃይል በመሆኑ የነዚያን አሮጌ መፈክር ማንሳት እየተሰራ ካለዉ ተግባር ኣኩዋያ ህዝባዊ ጠቀመታው እምብዛም ነዉ። እኔን ግን የአቶ ገዱ ንግግር ተስማማኝ። ከትናንት ጋር መፋታት። ስለመጪው ዘመን ብሩህ ተስፋ መስራት። ነጌያችንን ማሰብ…..። 
በኦሮሞና በአማራ መሃከል የነበረውን ሰላም በማደፍረስ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ ለነበረው ለዚያን ዘመኑ ጥቁር ጠባሳና ግጭት የመጀመሪያው ክብሪት የተለኮሰው በሚኒልክ ሀውልት ዙሪያ ነበርና አሁን ላይ ያንን ያረጀ መጥፎ ትውስታ ብንተወዉስ ለማለት ነው። ጊዜው የሚጠይቀው ብዙ የምንሰራዉ አለና።
በዝህ ጉዳይ ላይ ታዋቂው ፖለቲካኛ ኦቦ ሌንጮ ለታ በዘመኑ ያሉታን ላካፍላችሁ ወደድሁና በሚቀጥለው ጽሁፌ ጀባ ልላችሁ ፈቀድሁ። እስክዚያው ግን ሰላም ክረሙልኝ።
Filed in: Amharic