>
11:18 am - Sunday May 22, 2022

የኢትዮጵያ ወጣት ሆይ ሰከን በል! (ታዬ ደንደአ)

የኢትዮጵያ ወጣት ሆይ ሰከን በል!
ታዬ ደንደአ
በተለያዩ ቦታዎች ህገ-ወጥነት ይታያል። አንዳንዴም ከባህላችን ያፈነገጠ አስነዋሪ ድርጊት ይፈፀማል። ይህ ወደነበርንበት እንዳይመልሰን ያሰጋል።
ወጣቱ ብዙ ችግር እንዳለበት ይታወቃል። ችግራችን ከምናስበዉ በላይ ይከፋል። ሆኖም መረጋጋት ግድ ይሆናል። በስሜት እና በብሶት መንቀሳቀስ አቅጣጫ ያስታል። በዝህ ላይ የ1966ቱን አብዮት ማስታወስ ይጠቅማል። አብዮቱን ያመጣዉ የወጣቱ ትግልና መስዋዕትነት መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን ከስሌት ይልቅ ስሜት ስለበዛ አብዮቱ ከሸፈ።
አሁን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። ወጣቱ ባደረገዉ ትግል መንግስትን አስገድዶ ወደ ተሀድሶ አስገብቷል። የዶር አብይ አስተዳደር ሊካዱ የማይችሉ ተጨባጭ ለዉጦችን አሳይቷል። ለዝህ ለዉጥ ኢትዮጵያዉያን በዉስጥም በዉጭም  ከፍተኛ ድጋፍ ሰጥቷል። ለዉጡን ለማስቀጠል ድጋፉን መሬት ማስነካት ይገባል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ስክነት ያስፈልጋል። ወጣቱ ሦስት ነገሮችን ማድረግ አለበት።
አንደኛዉ ሰላም ማስፈን 
ያለሠላም የለዉጡ ባቡር ወደፊት ሊሄድ አይችልም። አመራሩ በእሳት ማጥፋት ስራ ይጠመዳል።
ሁለተኛዉ የህግ የበላይነት
  ህግና ስርዓት ከሌሌ ምንም ሊኖር አይችልም። ወጣቱ ከምንም በላይ ለህግ የባላይነት ዘብ መቆም አለበት።
ሦስተኛዉ ስራ ነዉ
ለዉጥ የአንድ ሰዉ ወይም የጥቂት ሰዎች ተአምራዊ ስራ አይደለም። የሁሉንም አስተዋፅኦ ይፈልጋል። ስለዝህ ሁሉም በተሰማራበት ስራ ዉጤት በማምጣት ለለዉጡ አስተዋፅኦ ማድረግ አለበት!
ወጣት ሆይ፣ ተረጋጋ! የሚጠቅምህን እና የሚጎዳህን ለይ! ግርግር የሚበጀዉ ለሌባ ነዉ! ሰላም ዋሉ!
Filed in: Amharic