>

የለውጡ ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ አንጂ የተወሰኑ ቡድኖች ወይንም ግለሰብ አይደለም ! (አበጋዝ ወንድሙ)

የለውጡ ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ አንጂ የተወሰኑ ቡድኖች ወይንም ግለሰብ አይደለም !

አበጋዝ ወንድሙ

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የተፈጠረውን ሃገራዊ የተስፋ ጭላንጭልና፣ ወደፊት ለዴሞክራሲ መንገድ ጠራጊ ሊሆን ይችላል የሚባለውን ሁኔታ አመጣጥ በቅጡ ካለመረዳትም ሆነ ለራስ የተጋነነ ድርሻ ለመውሰድ ወይንም አጋጣሚዉን በመጠቀም የበላይነት ለመቀዳጀት የሚደረግ እሽቅድምድም፣ለውጡን ከሚቃወሙ ሃይሎች ጋር ተዳምሮ  ተስፋውን እንዳያጨልመው ስጋት እየፈጠረ ይገኛል።

ዛሬ ሁሉም በየፊናው በሀገራችን ውስጥ  ለተፈጠረው ሁኔታ የኔ ቡድን አስተዋጽዖ ከከሌ በላይ ነው ያለኔማ ተሳትፎ ፈቅ አንልም ነበርወዘተ አንዳንዱ ደግሞ ይባስ ብሎ ለለውጡ መምጣት የአንበሳው ድርሻ የኔ ነውና ላመጣሁላችሁ ለውጥ እጅ ልትነሱ ይገባል ለማለት የሚዳዳው ሁኔታ ላይ አንገኛለን።

በመሰረቱ እንዲህ ያለ የተሳሳተ ዕይታ የሚፈጠረው ስለ ህዝባዊ ትግልና አካሄድ የተዛባ አመለካከት ስላለ ነው የሚል እምነት አለኝ ።አንዳንድ አካላት እነሱ ለውጡን ለማምጣት በተደረገው ትግል የተቀላቀሉበትን ቀን ብቻ ታሳቢ በማድረግ በሚያቅርቧቸው ትርክቶች  እንደ የሁኔታው ሶስትም አራትም ዓመት የፈጀው ትግል…  ወዘተ በሚል ሲዘግቡ ማየት የተለመደ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ለተፈጠረው የተስፋ ጭላንጭል የሚታይበት ሁኔታ እንዲፈጠር፣ ትላንት ከትላንት ወዲያ ህይወታቸውን የገበሩ፣የታሰሩ የተንገላቱ፣ ሰልፍ የወጡ ወይንም ድንጋይ የወረወሩ ብቻ ሳይሆኑ፣ ባለፉት 27 ዓመታት ህይወታቸውን የገበሩ፣የታሰሩ የተንገላቱ ሺዎች እንደነበሩ ላፍታም ቢሆን ሊዘነጋ አይገባም።

ኢህአዴግ አዲስ አበባ እንደገባ የቡትሮስ ጋሊን ጉብኝት አስመልክቶ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ተማሪዎች ላይ ከተካሄደ ግድያ ጀምሮ   2009 አሬቻ በዓልና አሁንም በመገፋትና በመገደል ላይ  ያሉ ወገኖች መስዋአትነት፣  ዛሬ ላለንበት ሁኔታ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዳበረከቱ ማወቅ ተገቢ ነው። ህዝባዊ ትግልን አስመልክቶ እንዲህ ያለ ግንዛቤ ከተጨበጠ ደግሞ የለውጥን ሂደት በቅጡ ለመረዳት ስለሚረዳ ራስን ከግብዝነት ቆጥቦ ካላስፈላጊ አጉል ፉክክርና ጉራ ያድናል።

ባለፈው ስድስት ዓመት በላይ በስፋትና በቀጣይነት ሃገራዊ በሚባል መልኩ፣ ድምጻችን ይሰማ ከሚለው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግል እስከ ኦሮሚያ፣ አማራ ክልልና ኮንሶ  የተካሄደው ህዝባዊ ትግል አንደኛው ከአንደኛው ልምድ በመማር ሚሊዮኖችን ያሳተፈ፣ የህዝብን የትግል ወኔ ያነሳሳ፣ ልምድን ያጋራና ያዳበረ ፣አጋርነትን የፈጠረ ህዝባዊ እንቢተኝነቱንም አጎልብቶ በገዥው ክፍል ውስጥ ክፍፍልን በመፍጠር  አሁን ያለንበት የለውጥ ምዕራፍ  ያደረሰ መሆኑ እሙን ነው።

ሆኖም ህዝባዊ ትግሉ  ይሄ ነው የሚባል የተቀናጀ አመራር የሚሰጥ ድርጅት ስላልነበረው፣ በኔ አተያይ የህዝብ ትግል ራሱን እንዲጠይቅ ያደረገውና፣በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የህዝብንም ጥያቄዎች መልስ ካልሰጠ ስርዓቱ በሙሉ አደጋ ላይ መውደቁን የተረዳ ቡድን በገዥው ፓርቲ  ውስጥ ተፈጥሮ ስልጣን ላይ እንዲወጣ አስችሎታል።

ባጭሩ አሁን በሀገራችን የተፈጠረውን ሁኔታ አስመልክቶ በየክልሉ ከተካሄዱ ህዝባዊ ትግሎች ጎን ለጎን፣ ወይንም ምናልባት በሱ ምክንያት፣በገዥው ፓርቲ ውስጥም የተካሄዱ ትግሎች የየራሳቸው አስተዋጽዖ እንዳላቸው መገንዝብ፣ ያለንበትን ወቅት በቅጡ ለመረዳት ይጠቅማል።

በኢህአዴግ ውስጥ ጊዜያዊ የበላይነት የተቀዳጀውና የለማ ቡድን ተብሎ የሚታወቀውን የኦህዴድ፣ የብአዴንና  ሌሎችም ስብስብ መረዳት ያለብን በዚህ ማአቀፍ ውስጥ መሆን ይኖርበታል። ማለትም የህዝብን ጥያቄ በተወሰነም ደረጃ ቢሆን ለመመለስ ፍቃደኝነት ያለውና፣ በህወሃት የበላይነት ይሽከረከር ከነበረው ኢህአዴግ የተለየ፣ ለዴሞክራሲ ሽግግር ለሚያስፈልገው ጉዞ (የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋትም ሆነ ሌሎች  እርምጃዎች) አዎንታዊ ሚና ለመጫወት በሚያደርገው ጥረት እንደ አጋዥ የሚታይ ሃይል መሆኑን መገንዝብም ያስፈልጋል ለማለትም ጭምር  ነው።   

ከዚህ ውጭ ግን ለሁሉም ለተገኘው ድልና ስኬት ራስን ብቸኛ ተዋናይ አድርጎ መመልከት ወይንም ራስን እንደ አድራጊ ፈጣሪ ማየት፣ ስህተት ከመሆኑም በላይ ለአጠቃላይ ትግሉ እንቅፋትና በለውጥ ሃይሎች መሃልም አላስፈላጊ ንትርክ በመፍጠር ትግሉን የማደናቀፍ ሚና ሊጫወት ስለሚችል መጠንቀቅ ያሻል። ማንም መሪ ሚና ይጫወት አይጫወት ዋናው የትኩረት አቅጣጫ መሆን ያለበት የተገኙትን ህዝባዊ ድሎች አጎልብቶ እንዴት ወደፊት መራመድ ይኖርብናል የሚለው ጉዳይ መሆን ይኖርበታል።   

 

Filed in: Amharic