>
5:13 pm - Friday April 19, 1630

አይዲዮሎጂ ጥንሰሳ (በታምራት ነገራ)

አይዲዮሎጂ ጥንሰሳ
 በታምራት ነገራ፡ 
 
የኦሮሞ ልሂቃን በመገንጠል  ሀሳብ ዙሪያ የሰሩአቸውን ትንንሽ ኩሽናዎች ትተው አይናቸውን ቤተመንግስት መቆጣጠር ላይ ያደረጉ ቀን የአፍሪካ ቀንድ መልክ በወሳኝ በሆነ መልኩ ይቀየራል፡፡ እራሳቸውንም ኢትዮጵያንም ከአላስፈላጊ መወላወል ነጻ ያወጣሉ፡፡ 
***
      ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዴት ኦሮሞ ተኮር የሆነ በግቡ ግን ጠቅላይ (Hegemonic) ኢትዮጵያዊ የሆነ አይዲዮሎጂ መቅረጽ እንደሚቻል በማውጠንጠን ላይ ነኝ፡፡ ይህን አይዲዮሎጂ ለመቅረጽም  ከኦሮሞ፤ ታሪክ ፤ባህል ሐይማኖት ፤ቋንቋ ፤ መልክአምድር ፤ኢኮኖሚ ምን ምን እሴቶች ሊውጣጡ እደሚችሉ ማሰባሰብ ከጀመርኩ ሰነባበትኩ፡፡  ይህ ስራ በርካታ ጥያቄዎች እና ተገዳዳሪዎችን እንደሚያስነሳ እያወኩኝ ነው የጀመርኩት፡፡
    እንደእኔ ግምት እስከአሁን የኦሮሞን ፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚዘውሩት አይዲዮሎጂዎች በዋነኛነት የተቀዱት  ከኦሮሞ ሕዝብ መንፈስ (Ayyana Oromo) ፤ መልክዓ ምድራዊ እና ፖለቲካዊ እውነታዎች ላይ በመመስረት አይደለም፡፡ የኦሮሞን ትግል 40 ዓመት በላይ በምድረበዳ እንዲንከራተት ምክንያት የሆኑት በርካታ ሀሳቦች በዋነኛነት የተቀዱት  በሚገባ መልኩ እንኳን ለአካባቢያቸው በሚመጥን ማለኩ  ባልተተረጎሙ የግድ ለኦሮሞ እውነታ እንዲውሉ በተጠመዘዙ  ፍልስፍናዎች  እና ፖለቲካዊ ትንታኔዎች ነው፡፡
       እነዚህም አይዲዮሎጂዎች የኦሮሞን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በአብዛኛው በሁለት መስመር እያንቀሳሱ ይገኛል፡፡  አንደኛው እና እስከአሁን በበርካታ ኦሮሞ ልሂቃን ዘንድ የልብ ትርታ የሚያሞቀው መስመር ኦሮሚያን ከኢትዮጵያ  “ኢምፓየር” በመገንጠል ኦሮሚያ የምትባል አዲስ አገር የመመስረት ሕልም ያለው አይዲዮሎጂ ነው፡፡ ይህ አይዲዮሎጂ ኦሮሚያ በኢትዮጵያ ቅኝ የተገዛች  ጭቁን አገር ነች ብሎ ያምናል፡፡ ስለዚህም የኦሮሞ ጥያቄ ሙሉ ቡሉ እናም አጥጋቢ በሆነ ምለኩ  መፍትሄ የሚየገኘው ኦሮሚያን ከኢትዮጵያ በመገንጠል  ለኦሮሞን ነጻ አገር በመስጠት ነው ብሎ ያምናል፡፡
       ሁለተኛው መስመር ደግሞ ኦሮሞ በኢትዮጵያ ተጨቋኝ አንደነበር ያምናል፡፡ በዚህም ከመጀመሪያው መስመር ጋር ይስማማል፡፡ ነገር ግን ለኦሮሞ ጥያቄ መፍትሄ ነው ብሎ የሚያስበው ኦሮሚያን ከኢትዮጵያ መገንጠልን ሳይሆን ኦሮሞ በኢትዮጵያውያን መካከል እኩል  ሕዝብ ሆኖ ጥቅሙን እንዲያገኝ ይመኛል፡፡
    እኔ የማቀርበው እና  እስከአሁን በሚገባ መልኩ አልተሞከረም የምለው መስመር ኦሮሞ በኢትዮጵያ የነበረው ተሳትፎ የተጨቋኝነት ብቻ ሳይሆን የጨቋኝነትም ነበር ብሎ ይነሳል፡፡  ይህ የኦሮሞ ጨቋኝነት እና ጠቅላነት ታሪክ ኦሮሚያን ከኢትዩጵያ ለመገንጠል በሚፈልጉ እና የኦሮሞን ጉልበት በሚፈሩ ተፎካካሪዎቹ ምክንያት ተሸፋፍኗል ብሎ ያምናል፡፡ ከዚህ በኋላም የኦሮሞ ፖለቲካዊ ግብም ሆነ ምኞቱም መሆን ያለበት ከኢትዮጵያ መገንጠልም በኢትዮጵያ ውስጥ እኩል መሆንም አይደለም ይላል፡፡
    እኔ የማቀርበው መስመር ለኦሮሞ ህዝብ ክብር ትክለኛው ርስት፤   ለኦሮሞ ግርማ የሚመጥነው ግብ፤ ለኦሮሞ መንፈስ መንፈስ (Ayyana Oromo)  ትክለኛው ምስ ፤ኢትዮጵያን ሲልም የአፍሪካ ቀንድን ጠቅልሎ መግዛት እንጂ  ከኢትዮጵየ መገንጠልም ሆነ በኢትዮጵያ  እኩል መሆንም አይደለም ብሎ ያምናል፡፡
     ከልገንጠል ባዩ እና አኩል ልሁን ባዩ  አይዲዮሎጂዎች በዋነኛነት ከኦሮሞ ታሪክ ፤ብሂል፤ ስብዕና፤ አፈር እና ውኋ አልተቀዳም እያልኩ የምከሰው ልገንጠል ባዩን ኤዲዮሎጂ ነው፡፡ ሌላው ሌላውን በሙሉ ለጊዜው  እንተወው እና የኦሮሞን መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ብቻ ስናየው ከሞያሌ እስከ ራያ ፤ ከአሶሳ እስከ ጅጅጋ በኢትዮጵያ አቀማመጥ ውስጥ  አከርካሪ ይመስል ተሰንጎ ይገኛል፡፡ በዚህም የተነሳ ከ95% በላይ  ኦሮሞ በኢትዮጵያ “ኢምፓየር” ውስጥ ተጠቅልሏል፡፡ የኦሮሞ  መልክአምድራዊ አቀማመጥ  አንደኛ ከመከመሪያውኑ  ያለ ኦሮሞ ወሳኘ ተሳትፎ ሊፈጠርም እልቻለም ሁለተኛ ኦሮሞ በኢትዮጵያ ያለው ወሳኘወ አቀማመጥ ደግሞ ለረጅም ዘመን ያለኦሮሞ ጥረት  እንዳለ  ሊጠበቅ  ፈጽሞውንም አልቻለም፡፡
      ኦሮሞ ከሌሎች ጋር በእኩልነት ይኑር ከሚሉት ጋር ያለኝ ችግር የስትራቴጂ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ አንደኛ ኦሮሞ ካለው በርካታ ንዋይ (Resource) አንፃር እኩልነት አይመጥነውም ባይ ነኝ፡፡ የእኩልነት ፖለቲካ ተገቢ የሚሆነው ያላቸው ነዋያት እኩል ሊሆኑት ከሚያስቡት ሕዝብ ጋር ሊመጣጠነላቸው  ላልቻለ አናሳዎች (minorities) ነው፡፡ እስቲ ጥቁር አሜሪካውያን በምን አቅማቸው በምን ሕልማቸው የአሜሪካንን ነጮች በሙሉ እንግዛ ሲሉ ይመኛሉ ? ኦሮሞ በባሕል ቢባል ፤በታሪክ ቢባል ፤በቋንቋ ቢባል፤ በተፈጥሮ ሀብት ቢባል ብቻ በማንኛውም መለኪያ  አናሳ አይደለም! አልነበረምም!
  ሁለተኛ በፖለቲካ ውስጥ እኩልነት ግብ እንዲሆን ቢያስፈልግ እንኳን  ለኦሮሞ አይነት ግርማ ላለው ሕዝብ እኩልነት የሚገኘው እኩልንትን በመፈለግ አይደለም፡፡ እኩልነት የሚገኘው ሌላውን ለማስገበር በሚደረግ ሽኩቻ ውስጥ አሸናፊም ተሸናፊም ሲጠፋ ዘለቄታዊ ሰላም ለማግኘት ሲባል  በሚደረግ የመጨረሻ ድርድር ውስጥ ነው፡፡ ተፎካካሪን  ሙሉለሙሉ  ለማንበርከክ ነጠላ አንኳ ሳያረግፉ  ተራኒ ወገን በር ላይ ሄዶ እኩል አድርገኝ ብሎ መጠየቅ እኩልነትን አያስገኝም አስገኝቶም አያውቅም፡፡
ይህን  የጠቅላይ ኦሮሞነት አይዲዮሎጂ በመመር ሳለሁኝ  በገዳ ዶት ኮም ላይ የወጣ አንድ ፎቶግራፍ ትዝ አለኝ፡፡  ፎቶግራፉ  ኤሮል ሞሪስ Believing  is Seeing;  Observations on the mysterious of photography በተሰኘ መጽሀፉም ላይ በጥልቀት የዳሰሰው አንድ ጸንሰሀሳብ  ትዝ አለኝ፡፡ ፎቶግራፉ የጥሩነሽ ዲባባ ሲሆን ፎቶግራፉ በኦሪጂናል መልኩ የተነሳው በቤጂንግ ኦሎምፒክ ላይ ሲሆን ገዳ ዶትኮም  በሌላ ወቅት ይህንኑ ፎቶ ጥሩነሽ ያነገበችውን የኢትዮጵያ  ባንዲራ በመግፈፍ በፋንታው  የኦሮሚያን ባንዲራ እንድትሸከም አድርጓታል፡፡
በጥሩነሽ ፎቶ ላይ የደረሰው ገፈፋ በአይዲዮሎጂ እና ፕሮፖጋንዳ  ግብ ግብ ታሪክ ውስጥ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ሌሎች በብዛት የተለመዱ ፖለቲካዊ የፎቶ አርትኦት  ዘይቤዎች አሉ፡፡  ጆሴፍ ስታሊን በ1930 ዎቹ ገደማ ፤ ስልጣኑን ያረጋጋለትን ፤ተቀናቃኞቹን  ሁሉ የደመሰለትን ፤ የሶቪየት ህብረት የደህንነት ሚኒስትር የነበረው  ኒኮላይ  ዪዦቭ ነበር፡፡  ስታሊን ዩዦቭን በሚገባ ከተገለገለበት በኋላ ከዚህ በመቀጠል የዩዞቭ መኖር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚበዛ ሲያምን ዩዦቭን አገለለው ብሎም አስገደለው፡፡  ካስገደለውም በኋላ በታሪክ መዝገብ ውስጥ ኒኮላይን  ከስታሊን ጋር ተማጣኝ ማንነት እነደነበረው እንዳይመዘገብ ሲባል እስታሊን እና ኒኮላይ አብረው የተነሷቸው ፎቶዎች እየተለቀሙ እንድገና ኤዲት ተደረጉ፡፡ የግብፁ የቀድሞውን መሪ ሁስኒ ሙባረክ ያየን እነደሆነ ደግሞ ከዓለም መሪዎች ጋር የተነሱት ፎቶ ስትመለከቱ የእሳቸውን ክብር ለማስጠበቅ ሲባል ከኦሪጂናሉ በእጅጉ በተለየ መልኩ እሳቸው ከኋላ ሲጎተቱ  ሳይሆን  የዓለም መሪዎቸን ሲመሩ  በሚያሳይ መለኩ አርትዖት ተደርጓል፡፡
  በዋነኛነት እንድትይዙልኝ የምፈልገው ነገር  በስታሊንም ሆነ በሁስኒ ሙባረክ ፎቶዎች ዙሪያ  የተደረገው ኤዲቲንግ በዋነኛነት የተካሄደው በመንግስት ተቋማት መሆኑን ነው፡፡ በጥሩነሽ ላይ የተካሄደው ኤዲቲንግ ግን መንግስት ባልሆነ የግል ተቋም አካል የተደረገ  ነው፡፡  የጥሩነሽ የዘመናት ልፋት እና ድካም ውጤትም፤  ትርጉምም የሚያገኘው በዚያች የባንዲራ የማውለብለብ ቅጽበት ነው፡፡ ነገር ግን ኦሮሞ ሲጀመር ኢትዮጵያዊ አይደለም ብሎ የሚያምን ሌላ አካል ኦሮሞነቷ ሆነ ኢትዮጵያዊነቷ ያልተጣረሱባት ጥሩነሽ ስብዕና፤ ህልውና ፊት ለፊቱ እያየ እሱን እያየ ከማመን ይልቅ  ቀድሞውንም ያመነውን ለማየት ሲል ብቻ  ካሜራውን መጠምዘዝ ቢያቅተው በኤዲቲንግ በኩል መጣ፡፡
ይህ በጥሩነሽ ፎቶ ዙሪያ የተከሰተ የአይዲዮሎጂ ጨዋታ  ነው  ማማን ማየት ነው የሚለውን የኤሮል ሞሪስ የፎቶግራፍ ትንታኔ እንዳስታውስ ያረገኝ፡፡ ኤሮል በአብዛኛው የሚያተኩረው ፎቶ ከመነሳቱ በፊት ባለው ሂደት ላይ እና ፎቶው ከተነሳ ባኋላ በተነሳው ፎቶግራፍ ዙሪያ ስለምናመርተው ትርጉም ነው፡፡  በጥሩነሽ ፎቶ ላይ የተከሰተው ከተፋ ኤሮል ካሰበውም በላይ ይሄዳል፡፡
እና ምን ይጠበስ?    
የአይዲዮሎጂ ግብ ግብ ዋነኛት የሚካሄድበት ትልቁ መድረክ የታሪክ ትርጓሜ ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ ደግሞ በኢትዩጵያ ከየትኛውም ታሪክ ትልቁ የግብ ግብ መድረክ ነው፡፡  የእኔ አይነቱ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀንድ ጋር ካልጠቀለልኩኝ የሚለው እብሪተኛ ኦሮሞም  (Were Ajesa) ሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ  እኩልነት ይበቃኛል የሚለው ኦሮሞ ልገንጠል የሚለውን ኦሮሞ ሕልውናም ሆነ መነሻ ምክንያቶች  አይክዱም፡፡  ለጊዜውም ቢሆን ልገንጠል ባዩ ነው አይኑ የሚያየውን እውነታም እንኳን መቀበል ያቃተው፡፡
ኦሮሚያን የመገንጠል መንገድም ሆነ አጀንዳ ፖለቲካዊ ኪሳራ ከደረሰበት ሰነባብቷል፡፡ ይህ ኪሳራ የገባቸው የመገንጠል ጠንሳሾች እና አቀንቃኞች አንዳንዶቹ  ነገር አለሙን ትተው  አገር ቤት መግባት ጀምረዋል፡፡ በተጨማሪም አዲስ እየተቋቋሙ ያሉ የኦሮሞ ፓርቲዎች እና እንቅስቃሴዎች መገንጠልን እየረሱት ይገኛሉ፡፡   ነገር ግን የመገንጠል ናፍቆት  ወሳኝ የሚባለውን  የኦሮሞ ልሂቅ ልብ አሁንም አሸፍቶታል፡፡   ይህ ሃሳብ ቀላል የማባል የኦሮሞ ልሂቅ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ኦሮሞ  ያለውን የአከርካሪነት ሚና እንዲገነዘብ እንደአከርካሪም እንዲተውን እንዲችል  ይልቅ በየትኛውም ቀን እና ስፍራ ተቆርጦ መጣል   ትርፍ አንጀት ይመስል መገንጠልን እነዲናቅ አድርጎታል፡፡
ስለዚህ ልገንጠል ባዩ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለውን ኦሮሞ ያየዋልን ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛው መልስ ልገንጠል ባዩ ኦሮሞ እራሱን ማየት ይቻለዋልን የሚል ሌላ ጥያቄ ይሆናል፡፡ የኦሮሞ ልሂቃን በመገንጠል  ሀሳብ ዙሪያ የሰሩአቸውን ትንንሽ ኩሽናዎች ትተው አይናቸውን ቤተመንግስት መቆጣጠር ላይ ያደረጉ ቀን የአፍሪካ ቀንድ መልክ በወሳኝ በሆነ መልኩ ይቀየራል፡፡ እራሳቸውንም ኢትዮጵያንም ከአላስፈላጊ መወላወል ነጻ ያወጣሉ፡፡ ፊንፊኔ ይባል ሸገር ይባል አዲስ አበባ ብቻ ቤተመንግስት ለመገናኘት ያብቃን፡፡
2014 የተጻፈ
Filed in: Amharic