>
5:13 pm - Thursday April 19, 2959

አክሱም እንደየሩሳሌም  (ዮናታን ተስፋዬ)

አክሱም እንደየሩሳሌም 
ዮናታን ተስፋዬ
የአክሱም ሙስሊሞችን የመብት ጥያቄ በተመለከተ አንድ የማይገባኝ ነገር አለ። ብዙ ሰዎች የመንግስት ሀላፊዎችን ጨምሮ በአክሱም መስጊድ መስራት የማይታሰብ ነው ሲሉ ይደመጣል። መከራከሪያቸው ደግሞ “በመካ መዲና ቤተክርስቲያን እንደማይሰራው ሁሉ በአክሱምም መስጊድ መስራት አይቻልም” የሚል ነው። ይሄ መከራከሪያ በምን አመክንዮ ተቀባይነት እንደሚኖረው አልገባኝም።
ሳኡዲ፣ ኢራን፣ ካታር ወዘተ እስላማዊ መንግስታት ናቸው በዛ ላይ አብዛኞቹ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የላቸውም። በአንፃሩ ኢትዮጵያ ሰኪዩላሪዝምን የተቀበለች በህዝብ አስተዳደር እና በሀይማኖት መካከል መስመር የለየች ሀገር ናት። ታዲያ በምን መመዘኛ ነው አክሱም ከከተማነት አልፋ “የክርስቲያን ከተማ” በሚል ለሙስሊሙ ማህበረሰብ መስጊድ የምትከለክለው?
እንደኔ እየሩሳሌምን የመሰለች ከተማ በላይ ለሶስት ሃይማኖቶች ቅድስት ከተማ የለችም። ይህችን ከተማ ተምሳሌት ማድረግ የተገባ ነገር ነው። የአይሁድ፣ እስልምና እና ክርስትና ሃይማኖቶች እኩል ቅድስት ከተማቸው ነች። የኛዋ አክሱም ይሄን የመሰለ ከተማ የማትሆንበት ምክንያት ያል አይመስለኝም። በሸገር አንዋር እና ራጉኤል በህዝባችን የጋራ ስነ ልቦና የፈጠሩት መልካም ባህልም ሊሰፋ እንጂ የአምባገነን እና ሃይማኖታዊ መንግስታት ምሳሌን ወስዶ “እከሌ ገደል ስለገባ እኔም መግባት አለብኝ” ማለት የሚጠቅም አይሆንም።
ከዚህ አንፃር የአክሱም ከተማ አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና ፌደራል መንግስት ከቱሪዝም ባለስልጣናት ጋር በመሆን ለአክሱም ሙስሊሞች መፍትሄ መፈለግ የሚኖርባቸው ይመስለኛል።
ኢትዮጵያ ለሁሉም ሁሉም ለኢትዮጵያ!
ፍትህ ለአክሱም ሙስሊሞች
Filed in: Amharic