>

ከሁዋላ ቆንጆ ምን ይመራርጡ! (አሰፋ ሃይሉ)

ከሁዋላ ቆንጆ ምን ይመራርጡ!
አሰፋ ሃይሉ
በቅርቡ ከውጭም ከውስጥም የሠማይና የምድርን ያህል የሚራራቁ አጀንዳዎችን ያነገቡ የሚመስሉ –  የተለያዩ አንጃዎችና ቡድኖች – በትዕምርተ ጥቅስ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች›› – ለሀገራዊው የፖለቲካ ድግስ መጋበዛቸውና ድግሱንም እየተቀላቀሉ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ታዲያ እነዚህ እርስ በርስ የሚጣረሱ አጀንዳዎችን ያነገቡ የሚመስሉ ‹‹ፓርቲዎች›› ባለው ሀገራዊ አዳራሽ ውስጥ ታድመው – ምርጫና ፖለቲካውን ‹‹የጨረባ ተዝካር›› እንዳያደርጉት የሰጉ የሚመስሉ ብዙ ሰዎች – ብዙ ዓይነት ይበጃሉ የሚሏቸውን አስተያየቶች (ወይም ምክሮች) – ለወዳጅም ለጠላትም ብለው ሲሰነዝሩ ይታያሉ፡፡ 
 
ከእነዚህ መሐል ከውጭ ለሚመጡ ከ‹‹ዘውግ›› ወይም ከ‹‹ጎሣ›› ወይም ደግሞ ከ‹ዘር›› ወይም ከ‹‹ብሔር›› ላፈነገጡ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲሰጥ የምናየው የወዳጅም የውስጥ አዋቂም ምክር ይገኝበታል፡፡ ይህም እባካችሁ – በአሁኑ ሰዓት በብሔር ፖለቲካ ያልተሳበ እና ያልገባበት – እና ከብዙው የአንዱ ጎራ ያልጎበኘው ኢትዮጵያዊ አይገኝምና፡- 
 
‹‹እናንት በዘውግ ፖለቲካ አናምንም የምትሉ የፖለቲካ ቡድኖች – ወደሀገርቤት ስትመጡ – እባካችሁ – መርሃችሁን ለጊዜው ወደጎን ብላችሁ – ከብሔር ፓርቲዎችና ቡድኖች ጋር ህብረትን ፍጠሩ፣ እባካችሁ ስትራቴጂያችሁን ከልሱና እናንተም የብሔርን ወይም የዘውግን አስተሳሰብ በማኒፌስቷችሁ አካትቱ – ምክንያቱም ወደዳችሁም ጠላችሁም አሁን እዚህ ሀገር የምታገኙት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ – ላለፉት 27 ዓመታት – ያው ያንኑ እና ያንኑ – አንድን የዘውግ ፖለቲካ ብቻ – በተለያዩ መጠሪያ ስሞች – በተለያዩ ዓይነት ቅርፆች – በተለያዩ ዓይነት አምሳሎች – ሲቀርብለትና እና ሲታደም እና ሲጋት የኖረ ሕዝብ ስለሆነ – እናንተ የምታመጡትን ከብሔር አስተሳሰብ የዘለለ – በአስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ አጀንዳ የሚቀበላችሁ ላታገኙ ትችላላችሁ – ስለዚህ እባካችሁ – አጀንዳችሁን ሀገር ቤት ካለው እውነታ ጋር አስተካክሉት…!››
 
 – የሚሉ ብዙ ምክሮችና አስተያየቶች – በተለይ በወገናዊ ስሜት ሲሰነዘሩና – ሲደመጡ እየሰማን ነው፡፡ 
 
ግን ግን ለመሆኑ አሁን በሀገራችን ያሉት የደም ምርመራን፣ ወይም ጂኦግራፊ ምርመራን፣ ወይም የቋንቋ ምርመራን፣ ወይም ደግሞ የመልክና የተክለቁመና ምርመራን፣ ወይም ደግሞ የአፍንጫ መሰልከክና የፀጉር ዞማነትና ከርዳዳነትን፣ ወይም ሌሎች ባዮሎጂያዊና ክህሎታዊ የደምና የስፐርም ምርመራዎችን መሠረት አድርገውአባሎቻቸውን ያሰባሰቡ፣ እነዚያንም የምርመራ ውጤቶች እንደቡድን ለመሰባሰብ ብቸኛ መስፈርት አድርገው እየተንቀሳቀሱ ያሉ – የተወላጅነት ስብስቦች – እውን – ቀድሞ ነገር – በዘመናዊው ዓለም – ‹‹የፖለቲካ ፓርቲ›› ለሚለው የሰዎች ስብስብ ዓለማቀፋዊ ትርጉሙንና መስፈርቱን የሚያሟሉ ናቸው ወይ?? ብለን እንጠይቅ እስቲ? – መልሱ ‹‹ኔንቼ!›› ነው!! አያሟሉም፡፡ እነዚህ ባዮሎጂያዊ ስብስቦች – የፖለቲካ ፓርቲ ተብለው ሊጠሩ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም እነዚህን ባዮሎጂያዊና ጂኦግራፊያዊ ስብስቦች ያሰባሰባቸው – ለሁሉም ሰው አባልነት ክፍት የሆነ የጋራ ሀሳብ ሳይሆን – በቃ – የላብራቶሪ ወይም የጎግል ኧርዝ ወይም የትኦፍል ምርመራ ውጤት ብቻ ስለሆነ፡፡ 
 
የፖለቲካ ፓርቲ በትርጉም ደረጃ ማንን ወይም የትኞቹን የሰዎች ስብስቦች ለመግለጽ ድፍን የሠለጠነው ዓለም የሚገለገልበት ቃል ነው? ያልን እንደሆነ የፖለቲካ ፓርቲ የሚለው ቃል የሚያመለክተው አባልነት ለማንኛውም ዜጋ ክፍት የሆነበትን፣ በሀሳብ እና በአስተሳሰብ አብሮነት ላይ መሰባሰቢያ አጀንዳውን በሚቀርፀው፣ እና ሥልጣንን ለመያዝ ወይም የያዘውን ሥልጣን ለማቆየት ሲተጋ – ብቸኛና ብቸኛ ግቡ – በሀሳብ ዙሪያ ተሰባስበው የመጡ አባላቱና ደጋፊዎቹ – ለአጠቃላይዋ ሀገር ይበጃል ያሉትን – ሀገራዊ የሆኑ አጀንዳዎችንና ፖሊሲዎችን በተግባር ለማዋል ፈልጎ – እና አስቦ – በሕዝባዊ ምርጫ እና በምርጫ ውድድር አማካይነት ብቻ የአብዛኛውን ሕዝብ ይሁንታ አግኝቶ ወደሀገራዊ የፖለቲካ ሥልጣን ለመምጣት የተነሣ፣ የሚፎካከር፣ እና ሥልጣንን የሚይዝ፣ ከያዘም በሥልጣኑ ለመቆየት የሚተጋን የሰዎች ስብስብ የሚመለከት ቃልና ፅንሰ-ሃሳብ ነው ‹‹የፖለቲካ ፓርቲ›› ተብሎ የሚጠራው ቃል መሠረታዊ ትርጓሜ፡፡ ይህ የትኛውም የሠለጠነ ሀገር ላይ የምናገኘው የፖለቲካ ፓርቲ ‹‹ኤ ቢ ሲ›› ወይም ‹‹ሀ ሁ›› ነው፡፡ ምንም ማስተባበያ የሌለው ሃቅ ነው፡፡
 
እና ታዲያ በደም አንድነት፣ በስፐርም ዝምድና፣ ወይም በባዮሎጂካዊ ምስስሎሽ፣ ወይም በአካላዊና ጂኦግራፊያዊ ንቡርነት፣ ወይም በቋንቋ ተናጋሪነት ስብስብ- አንድ በመሆናቸው ብቻ – ‹‹ፖለቲካ ፓርቲ›› ነን ብለው በሀገራችን የፖለቲካ ዐውድ ዕውቅና ተሰጥቷቸው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሰዎቸ ስብስቦችን ወይም የተለያዩ ቡድኖችን ምን ልንላቸው ነው? ዘመናዊው ዓለም እነዚህን መሠል በጎሣ፣ ውይም በዘውግ፣ ወይም በጎጥ፣ ወይም በብሔር፣ ወይም በቋንቋ፣ ወይም በአንድ ሥፍራ በመገኘት – አንድ ነን፣ የሚያስተሳስረን ነገር አለ ብለው – በአንድነት ተሰባስበው የቆሙ ማህበራትን የሚቀበላቸው – ወይም የሚመለከታቸው- ልክ እንደ ዕድር ነው – ወይም ደግሞ እንደ የአባሎቻቸውን ነገዳዊ መብቶች ለማስጠበቅ እንደቆሙ – የመብት ተከላካይ ማህበራት ነው የሚመለከታቸው፡፡ 
 
ማለትም ልክ ለምሳሌ የኮካ ኮላ ተጠቃሚዎች ማህበር – የኮካ ተጠቃሚዎችን መብት የሚጎዳ ነገር እንዳይኖር ለአባላቱ እንደሚቆመው፣ አሊያም ከሁሉ ቀድመው በመዲናችን የተቋቋሙ የዶርዜ ዕድሮችና የአንዳንድ ብሔሮች የልማት መረዳጃ ማህበራት አባላቶቻቸው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲያገኙ፣ በችግር ጊዜ ደራሽ ለመሆን፣ አሊያም ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ የበረከተ እንዲሆን፣ ወይም ከሌሎች የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ በጋራ ለመከላከልና ለመበልፀግ – የሚቋቋሙ ማህበራት ናቸው፡፡ ወይ በደም ወይ በተለያዩ መነሻዎች አባል እንዲሆኑ የተደረጉ መሰሎቻቸውን ጥቅም ይከላከላሉ፣ አሊያ ለጋራ ደራሽ የሆነ አጋርነት ይመሰርታሉ፡፡ ይህ ነው በምዕራቡ ዓለም ዘርን መሠረት አድርገው ለሚመሠረቱ የሰዎች ስብስቦች የሚሰጣቸው ትንታኔና ትርጓሜ፡፡
 
እውነታው ይህ ከሆነ – አይደለም የሚል ካለ እልፍ አዕላፍ መጻሕፍትንና የምሁራንን ትንታኔዎችን ለመጠቆም ይቻላል – እና እውነታው ይህ ከሆነ ታዲያ በሀገራችን እስከዛሬ ብዙ የዘመናዊ ፖለቲካ ፓርቲ ምንነትና ሚና ወይም አወቃቀርና ዓላማ አሊያም የመሰባሰቢያ ምክንያቶችን ጠንቅቀው የሚያውቁ በርካታ ኢትዮጵያውያን – ስለምን በእነዚህ ‹‹ፖለቲካ ፓርቲ›› ሊሰኙ የማይችልን ‹‹ዘውጋዊ›› አጀንዳን ባነገቡ የሰዎች ስብስቦች ወይም ቡድኖች ውስጥ ገብተው መሣተፍን፣ መንቀሳቀስን፣ እና የሀገሪቱን ፖለቲካ በገዢነትም ይሁን በተፎካካሪነት መዘወርን ለምን መረጡ? የሚል ጥያቄ ሊከተል ይችላል፡፡ እውነት ነው – መጠየቅም አለበት፡፡ እነርሱ ራሳቸው መልሱንና ማብራሪያውን (ወይም ‹‹ጀስቲፊኬሽናቸውን›› ቢሰጡበት ይሻላል፡፡ 
 
በበኩሌ ግን ያለኝ ግምት – ሀገራዊ ፖለቲካዊ አጀንዳ እያላቸው፣ እና በሀገሪቱ ፖለቲካ ሚና አለን ብለው ወስነው – ነገር ግን በሀገሪቱ ሕገመንግሥታዊ ጥላ-ከለላ ተችሮት ዋናው እና (ኦልሞስት!) ብቸኛው የፖለቲካ መሮጫ መም – ለዘውግ ስብስቦች እና ባዮሎጂካል ምርመራን ማዕከል ላደረጉ ቡድኖች መላወሻነት የተተወ በመሆኑ – ያላቸው አዋጪ አማራጭ – በዚያው የዘውግ ፖለቲካ ገብቶ ያላቸውንና የቻሉትን ማበርከት ስለሆነባቸው ሊሆን እንደሚችል ሰፊ ግምት አለኝ፡፡ 
 
ከብዙዎችም እንዲህ የመሰለው አስተያየት ስለሚደመጥም ጭምር፡፡ ለምሳሌ ከብዙ በኢህአዴግ ግንባር ሥር ህብረት ፈጥረው ከተሰባሰቡ የዘውጌ ድርጅቶች – ‹‹በሂደት ራሳችንን ወደ ፓርቲነት የመለወጥ ዕቅድ›› አለን ሲሉ የምናደምጠው – በበኩሌ – እውነታውን ተረድተው – ለጊዜው በሌላኛው በቀለላቸው መንገድ እየተጓዙ መሆኑን ያውቁታል እንድንል ያስገድዱናል፡፡ 
 
ይህ ማለት ምን ማለት ነው? አንደኛ በኢትዮጵያ ውስጥ – ላለፉት ዓመታት ሲቀነቀኑ የነበሩት አጀንዳዎች በትክክል ‹‹ፖለቲካዊ›› አጀንዳዎች አልነበሩም፡፡ ሁለተኛ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት አብዛኞቹ (ዋነኞቹ) ሀገራዊ ቡድኖች ፈጽሞ ‹‹ፖለቲካ ፓርቲ›› የሚለውን ድፍን የሠለጠነው ዓለም የሚጠቀምበትን ቅቡል መሥፈርቶች አያሟሉም፡፡ 
 
እና ስለዚህ ሦስተኛ ብዙ ይህንን ከማናችንም በላይ ጠንቅቀው የሚያውቁ ግለሰቦችና ቡድኖች እነዚህን ‹‹ፖለቲካ ፓርቲ›› የሚለውን ዓለማቀፋዊ መሥፈርት የማያሟሉ ባዮሎጂካል፣ ዘውጋዊ፣ ጂኦግራፊያዊ ወይም ሌላ ቀደም ሲል የጠቀስናቸውን – በሀገራችን የሠፈኑትን የሰዎች ስብስቦች – አንዱን የቀረባቸውን መርጠው ሲሳተፉ የነበሩት – ያው ‹‹ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ›› በሚል እሳቤ ነው ማለት ነው፡፡ እንጂ ፖለቲካ ፓርቲ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ላያውቁት ስለማይችሉ ማለቴ ነው፡፡ 
 
ቆይ ምሳሌ እንውሰድና – ዘመድ ቤት ሠርግ ተጠርተህ – ቢፌ ዝረፍ ትባልና – ወደቢፌው ስትደርስ – ሁሉም ድስት – አንድ ዓይነትን ምግብ ይዞ ብታገኘውስ? ሁሉም ውስጥ ክትፎ ቢኖር፣ ወይም ሁሉም ውስጥ አሳ በአትክልት ቢኖር – ምን ታደርጋለህ? – ብዙው ሰው አንዱን ብቻ አንስቶ ቁጭ!! በቃ – የሀገራችንም ነቄ (ባለንቃተ ህሊና) ፖለቲከኞችም ያደረጉት ያንኑ ይመስለኛል፡፡ አንዱን መርጠህ – በል ግባ በሞቴ !! ምክንያቱም – ብልሀቱ – ያው – ‹‹ከሁዋላ ቆንጆ – ምን ይመራርጡ›› ነውና!!!!!!    
 
ምክረ ሃሳብ፡-
 
ከውጭ የሚመጡም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች›› (በትዕምርተ ጥቅስ!) – ብዙው ሰው ላለፉት አስርት ዓመታት ‹‹ይህ ነው!›› እየተባለ ሲነገረው፣ ሲሳብ፣ ሲንቀሳቀስበት፣ ሲሰማው፣ ሲያየው፣ እና ጧት ማታ በሚዲያውም በመንገዱም በመኝታውም ሲያላምጠው የኖረው – ወይም የኖርነው – ይህ የዘውጌያዊ ኃይሎች ስብስብ – ከላይ በጠቀስናቸው ዝርዝር ምክንያቶች የተነሣ – ዘመናዊ የፖለቲካ ፓርቲ የሚሰኘውን በዘመናዊው ዓለም ዲሞክራሲን ለማስፈን ጥቅም ላይ የዋለውን የፖለቲካ ፓርቲ ትርጉምና ፅንሰ-ሀሳብ –   እንደማያሟላ ግልጽ ነው፡፡ ብዙዎች ራሳችንን እንፈትሽ – እና በርግጠኝነት ብዙዎች ፖለቲካ ፓርቲ ለመሰኘት እንደማንበቃ ግልጽ ነው፡፡ 
 
ስለሆነም – አሁን በሀገራችን ፖለቲካ ገብተው ለመንቀሳቀስ የሚሹ እዚህ ያሉት (ገዢዎቹና ተፎካካሪዎቹ) እንዲሁም ከውጭ ወዳገርቤት የሚገቡት የፖለቲካ ስብስቦች – ራሳቸውን በአፋጣኝ ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት ለውጠው – ሕዝባቸውንም  በዘመናዊ ፖለቲካ አስተሳሰብ አደራጅተው – እና አሰባስበው – ለሚያምኑበት ሀገራዊ አጀንዳና አስተሳሰብ – የበኩላቸውን ሚና ቢወጡ – መልካም ነው፡፡ 
 
መደምደሚያ፡-
 
በስህተት ጎዳና በዘውጌያዊ ስብስብ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ብዙሃን የፖለቲካ ቡድኖች – አባልነታቸውን ለሁሉም ዜጋ ክፍት ወደሚያደርግ – ሀገራዊ ሀሳብን ማዕከሉ ወዳደረገ – ወደ ትክክለኛው የፖለቲካ ጎዳና መምጣት ይገባቸዋል፡፡ እንጂ – በትክክለኛው ጎዳና የሚጓዙትን ህዳጣን የፖለቲካ ፓርቲዎች – በስህተት ጎዳና ወደሚመላለሱት ብዙሃን የዘውግ ስብስቦች ራሳችሁን ቀይሩ ብሎ መምከር – ጤነኛውን ሰው ጨርቅህን ጣል እንደማለት ያለ – በመልካም እሳቤ የተሰነዘረ – ነገር ግን ለስልታችሁ ስትሉ የአላዋቂነትን ካባ ደርቡ የሚል – አስገራሚ ምክር ይመስለኛል፡፡ 
 
መሰናበቻ፡-
 
ቆይ ግን… ማን ነው ግን ለመሆኑ የሠለጠነውን የምዕራቡን ዓለም ለኛ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲ›› …. ‹‹ዓለማቀፋዊ ትርጉም ሰጪ›› ያደረጋቸው??
 
እኔ እንጃ!! በምን አውቄ!!! ትርጉሙ ግን – የእነሱ ነው!! እውነታውም እንደዚያው – መ ሠ ለ ኝ ! ! ! ! አይ አይደለም ካልክ – እንግዲህ ምን እንልሃለን? – ሐረሮች ካንተ ጋር መከራከር ሲሰለቻቸው እንደሚሉህ – ‹‹ካንተ አናውቅም!›› ከማለት በስተቀር፡፡ አዎ ማንም ለማንም አያውቅም! አናውቅም! እንደራስ! ቻው አቦ!!!!!!    
 
አምላክ ኢትዮጵያ ሀገራችንን ይባርክ፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም – በፍቅር – ትኑር፡፡
ፎቶግራፉ (ከምስጋና ጋር)፡-
Filed in: Amharic