>
1:21 am - Saturday December 10, 2022

የስርአቱን አስብቶ አራጅነት ከማንም ቀድሞ የተረዳና ራሱን ከመንጋው የለየው ታማኝ!!! (ጌታቸው ሽፈራው)

የስርአቱን አስብቶ አራጅነት ከማንም ቀድሞ የተረዳና ራሱን ከመንጋው የለየው ታማኝ!!!
ጌታቸው ሽፈራው
በታማኝ ጉዳይ ለአማራው ሕዝብ የሚታገሉ ወገኖች የሚነሱትን ቅሬታና ጥርጣሬ በላይ፣ ቅሬታ ያነሱትንና ታማኝን ለማራራቅ  የሚጥሩትም በርካቶች ናቸው። አንዳንድ ወንድሞች ታማኝ ለአማራው ሕዝብ ትግል የሚገባውን ያህል አላበረከተም ብለው ሲተቹት እሰማለሁ። በእስር ላይ እያለሁ ምን እንደተፈጠረ አላውቅም።
 ያም  ሆኖ!
የታማኝን ያህል በአማራው ላይ የተፈፀመውን ድብቅ ወንጀል ሕዝብ በሚገባው መልኩ ሲያስረዳ የሰማሁት ሰው አለ ለማለት ይከብደኛል። የአርባጉጉ፣ የበደኖና ሌሎች ጭፍጨፋዎችን ሕዝብ እንደዚህ ጆሮ ሰጥቶ መስማት ባልቻለበት፣ ባልተመቸ ሰዓት ለማስረዳት ጥሯል።
የትህነግ/ህወሓትን ሴራ፣ የብአዴን አሽከርነትና የአማራን ሕዝብ ላይ የተፈፀመውን በርካታ በደለ አጋልጧል።
በቅርቡም ቢሆን ከቤንሻንጉል ለተፈናቀሉት ወገኖች 800 ሺህ ብር በላይ እገዛ እንዲደረግ አስተባብሯል። በተጨማሪም የአማራ ተጋድሎ ምልክት የሆነው እና  ኮ/ል ደመቀ መኖርያ ቤት የነበረውን ቤት ሙዝየም እንዲሆን ለማድረግ ትልቁን ድርሻ     የወጣው  ታማኝ በየነ ነው።
ታማኝ የእኛን ሀሳብ ፊት ለፊት ላይናገርልን ይችላል። ሁሉም ወገናችን በተመሳሳይ ግንባር ላይሰለፍ ይችላል። የእኛ ሚና መሆን የሚገባው ያ ሰው ባለበት አቅሙን በተቻለ መጠን ለመጠቀም መጣር ነው።
 አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ፊት ለፊት እኛ የምንፈልገው አቋም ላይዝ ይችላል። ወይንም ታማኝ ካለው ትልቅ ተቀባይነት እና አቅም አንፃር የምንፈልገውን ያህል ያበረክታል ብለን የጠበቅንበትን ባያደርግ ከሰው ውስንነት፣ እኛም እንደ ታላቅ ወንድም ከሰጠነው  እጅግ  የገዘፈና ተደራራቢ ኃላፊነትና ግምት ሊሆን ይችላል። ይህ የእኛም ለታማኝ በሰጠነው አክብሮት፣ የለውጥ ፍላጎት እንጅ የእሱም የእኛም ስህተት ላይሆን ይችላል።
ዛሬ ዛሬ ከየጎጡ ብቅ ብቅ ያሉ የብአዴን ቡችሎች ድንገት ተነስተው “ነፃ አውጭ ነን” ብለው ያዙን ልቀቁን ሲሉ ማየት ያሳፍራል። ታማኝ ማለት አዳሜ “ኢህአዴግ ማሬ ማሬ!” እያለ በየወጣት ፎረሙ ለወያኔ እስክስታ ሲደልቅ የስርአቱን አስብቶ አራጅነት ከማንም ቀድሞ የተረዳና ራሱን ከመንጋው የለየ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው። ይሄ ሁሉ ወፈ ሰማይ የድል አጥቢያ ዓርበኛ ተሰብስቦ አንድ ታማኝ አይወጣውም። ቢመራችሁም ዋጡት። ትልቅን በመሳደብ ትንሽነታችሁን ለማከም አትዳክሩ። ታማኝ ታማኝ ነው!
ታማኝ አጥፍቷል ከተባለ እንኳ እንደታላቅ ወንድማችን ቀርበን ልንጠይቀው፣ እንደታናሽ ወንድምና እህቶቹ ልንወቅሰው እንችላለን እንጅ ታማኝን ከሕዝብ እንዲርቅ የሚፈልጉ አካላት ለፕሮፖጋንዳ በሚጠቀሙበት መንገድ ሊሆን አይገባም!
“አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ”  ብላችሁ ቆማችሁ ታማኝ የሚባል ግዙፍ እና ለአማራው ሲጮህ የኖረን ሰው የሚገባውን ክብር አለመስጠት ከመርህ ማፈንገጥ ነው።  ለተቀናቃኝ ምቹ የርካሽ ፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያ መሆን ነው! ሽንፈትም ነው!
Filed in: Amharic