>

“ወይ ተለወጥ ወይ ተፈጥፈጥ” (ፋሲል የኔአለም)

“ወይ ተለወጥ ወይ ተፈጥፈጥ”
ፋሲል የኔአለም

የህወሃት ዋና ዋና መሪዎች “ወደ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመራችን እንመለስ” እያሉ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ ከእንግዲህ ከለውጥ አራማጅ የኢህአዴግ መሪዎች ጋር አብረው ሲቀጥሉ አይታየኝም። በአባል ድርጅቶች ውስጥ ሰፊ የርዕዮት አለም ልዩነት ተፈጥሯል። ህወሃቶች ይህን ልዩነት ይዘው  ከሌሎች የኢህአዴግ መሪዎች ጋር አብረው ለመቀጠል ቢወስኑ እንኳን፣ “ለጥቅማቸው ሲሉ አላማቸውን የሸጡ” ተብለው በደጋፊዎቻቸው መወገዛቸውና ተቀባይነት ማጣታቸው አይቀሬ ነው። ከኢህአዴግ ጋር አንቀጥልም ካሉ ደግሞ ለብቻቸው ድርጅት አቋቁመው ለማዕከላዊ መንግስት ስልጣን መታገል አለባቸው። ይህን ማድረግ ዳገት ከሆነባቸውም፣ ነባሮቹ አመራሮች፣ የለውጡን አላማ ለሚደግፉት አባሎቻቸው ድርጅቱን አስረክበው ፖለቲካን “ ቻው” ማለት አለባቸው ። የህወሃት ነባር አመራሮች ከገቡበት አጣብቂኝ በቀላሉ ሊወጡ የሚችሉት፣ ሌሎች የኢህአዴግ ድርጅቶች “ወደ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመራችን እንመለስ” ብለው ከወሰኑላቸው ብቻ ነው፤ ይህ ደግሞ በፍጹም የማይታሰብ ነው። የለውጡ አራማጅ ኢህአዴጎች እንኳንስ ወደ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ሊመለሱ ቀርቶ ስሙንም ለመጥራት  እየቀፈፋቸው እንደመጣ ታዝቤያለሁ። እውነት ለመናገር እንደ ህወሃት ኮንፓሱ የጠፋበት ድርጅት አላየሁም። ደብረጺዮን በየሳምንቱ እርሱ በርሱ የሚጣረስ መግለጫ የሚሰጠው ወዶ ሳይሆን ጨንቆት ነው። አሁን ግን ፈትለወርቅ የምትባል ሰው፣ ደብረ ጺዮን በየሳምንቱ እያምታታ እንዳይቀጥል መንገዱን ዘጋችበት።  ደብሬ ከእንግዲህ የፈትለወርቅን አቋም በይፋ ከማራመድ ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም፤ መሙለጭለጭ አከተመ።  አቅጣጫ የጠፋበት ህወሃት የትግራይንም ህዝብ አቅጣጫ አስጠፍቶበት ከርሟል፤ አሁን ግን እድሜ ለፈትለ ሁሉም ነገር ግልጽ ሆኗል። የትግራይ ህዝብ   ከህወሃት ምርኮኛነት ካልተላቀቀ በስተቀር፣ ሌሎች ኢትዮጵያውያን የሚያገኙትን ነጻነት ሊያገኝ አይችልም። የትግራይ ህዝብ እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነቱን ካላገኘ ደግሞ ነጻነታችንን ሙሉ አይሆንም። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ እንደ ሶማሊ ክልል ህዝብ ቆርጦ በመነሳት ህወሃትን “ወይ ተለወጥ ወይ ተፈጥፈጥ” ማለት አለበት። ጊዜውም አሁን ይመስለኛል።

Filed in: Amharic