>

ማልኮም-ኤክስ - እና የአፍሪካውያን አንድነት ድርጅት! (አሰፋ ሀይሉ)

ማልኮም-ኤክስ – እና የአፍሪካውያን አንድነት ድርጅት!
አሰፋ ሀይሉ
— ከአዲስ አበባ እስከ መካ – ከሚችጋን እስከ ሐርለም 
በቅድሚያ ግን — ማልኮም ኤክስ ማነው? የሰብዕናውስ ጡቦች ከምን ከምን ተሠሩ?
ዛሬ ላይ ብዙው የዓለም ኗሪ — «ማልኮም-ኤክስ» በሚል መጠሪያ ስሙ የሚያውቀው — ትንሹ ማልኮም — «ማልኮም ሊትል» — ከአባቱ ከኧርል ሊትል — እና ከእናቱ ከልዊስ ሊትል — የዛሬ 93 ዓመት — በዕለተ ማክሰኞ — በኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር — በግንቦት 11 ቀን 1917 ዓመተ ምህረት— በአሜሪካ ካርታ ላይ እምብርት ሆና በምናገኛት — በነብራስካ ክፍለ ሀገር — በ ኦማሃ ከተማ — ፒንክኒ ተብላ በምትጠራ ክፍለከተማ ተወለደ፡፡
ማልኮም ኤክስን ያፈራችው የነብራስካ ዋና መቀመጫ — «ኦማሃ» — በታሪክ መጠሪያ ስሟን ያገኘችው — ከሲዮክስ፣ አዮዋ፣ ሚሱሪ ቀደምት ‹‹ቀይ ህንድ›› ሠፋሪዎች ነው፡፡ ለዘመናት የኖረው የቀይ ሕንዳውያኑ መግባቢያ ቋንቋ — ‹‹ኦማሃ›› ይሰኝ ነበርና — ይህቺው የቀደምት ሲዮክሶች መናኸሪያ የነበረች ሀገር — በዚያው በቀደምት ሠፋሪዎቿ ቋንቋ — «ኦማሃ» የሚለውን መጠሪያዋን ይዛ የቀረች ነች፡፡
እነዚያስ የሲዮክስ ቀይ ሕንድ ነገዶች — ማልኮም ኤክስ ሲወለድ — በዚያ ነበሩ ወይ? ብሎ የሚጠይቅ ካለ — መልሱ — ከጥቂት ቅሪቶቻቸው በቀር — በማልኮም ኤክስ ጊዜ ሲዮክሶቹ አልነበሩም፡፡ ምክንያቱስ? ካልን — ምናልባትም እነዚያው ምክንያቶች — ኋላ ላይ ለተፈጠረው — እና ለጥቁሮች ነፃነት እስከሞት መስዋዕትነት ለመክፈል — እና ያን መብትም ለመከላከል እስከማናቸውም እርምጃ ድረስ ለመውሰድ ቆርጦ ለተነሣው — ለኋለኛው የጥቁሮች ነፃነት ታጋዩ ማልኮልም ኤክስ መፈጠር — ምናልባትም ዋነኛ የሰብዕና መሠረቱን የጣለለት ምክንያት ሊሆንም ይችላል — የሚል ግምት ያሳደሩ አንዳንድ የታሪክ አጥኚዎች አልታጡም፡፡
እውን በዚያ የማልኮምል ኤክስ መፈጠሪያ ከተማ — በነብራስካ ኦማሃ — የነበቱት ቀይ የሲዮክስ፣ የአዮዋ፣ የሚሱሪ፣ እና የሌሎችም ቀይ ሕንዳውያን ነገዶች ቀደምት የመኖሪያ ሥፍራቸውን መልቀቅ — ዋነኛ ምክንያቱ ምንድን ነበረ? ካልን — ዋነኛውና ብቸኛው ምክንያቱ — ቀይ ህንዳውያኑ ቀደምት ሠፋሪዎች — በትውልደ ትውልደ-አውሮፓውያኑ ሠፋሪዎች — ማለትም በትውልደ እንግሊዛውያኑ፣ ጀርመናውያኑ፣ ሩሲያውያኑ፣ አሜሪካውያኑና ካናዳውያኑ ነጭ ሠፋሪዎች — በተከታታይ የተካሄዱባቸውን ብርቱ ወታደራዊ የግዛት ማስፋፋት ዘመቻዎችና — ብርቱ ተከታታይ ውጊያዎችንና ምንጠራዎችን — በዚያ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እበለጸገ ከመጣባቸው ዘመነኛ የውጊያ ሥልቶችና መሣሪያዎች ጋር ተደማምሮባቸው — የነጮቹን ሠፋሪዎች ብርቱ ወረራዎች መቋቋም ስለተሳናቸው ነበር ቀይ ህንዶቹ — ከማልኮም ኤክስ መወለድ 60 እና 70 ዓመታት አስቀድመው — ከዚያች የማልኮም ትውልድ ሥፍራ — ከኦማሃ ግዛት — ነቅለው የመውጣታቸውና በነጮች ነዋሪዎች የመተካታቸው ምክንያት፡፡
«ቡፋሎ» የተሰኙት  ቀደምት ቀይ ሕንዳውያን ነገዶች፦
በተለይ በተለይም — በኃይለኛ ተዋጊነታቸው ዛሬም ድረስ ስማቸው በጀግንነት የሚወሣላቸው — «ቡፋሎ» የተሰኙት የሥፍራው ቀደምት ቀይ ሕንዳውያን ነገዶች — ዕጣ-ፈንታ አሳዛኝ ነበረ፡፡ በቡፋሎዎቹ ምድር — ድንገት የተከሰተባቸው የፈንጣጣ በሽታ አደገኛ ወረርሽኝ — ክትባትና መድኃኒት የሚሉ ነገሮች ገና ባልታሰቡባቸው በእነዚያ ዓመታት — አብዛኞቹን ቀይ ህንዳውያን የቡፋሎ ነገዶች — ትርግርግ አድርጎ ጨረሳቸው፡፡ ከፈንጣጣው በኋላ ደግሞ — እስከዛሬም ድረስ — ስሙ የተለያዩ ምርቶች መጠሪያ ሆኖ የምናገኘው — ዊሊያም ክላርክ በተሰኘው የጦር መሪ የሚመሩት — አዲሶቹ አሜሪካውያን ነጭ ሰፋሪዎች — ከፈንጣጣው ወረርሽኝ የተረፉትን — እና እነ ክላርክስን የሚመክቱበት የረባ ብርታት ያልተረፋቸውን ቡፋሎዎች — ማልኮም ከመወለዱ ግማሽ ክፍለዘመን በፊት — ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ድል አድርገው ቀይ ህንዶቹን ከአብዛኛው የነብራስካ ግዛት አባረሯቸው፡፡
ቀይ ህንዶቹም — ለተረኞቹ ነዋሪዎች — ለነጮቹ አውሮፓውያን ሠፋሪዎች ግዛታቸውን አስረክበው — ዛሬ ላይ እንደዋነኛ መኖሪያቸው ተቆጥሮ ወደተከለለላቸው — ሽቅብ ወደሚገኘው «ቡለቬል» ግዛት አፈግፍገው — ይኖሩ ጀመር፡፡ ያ ከማልኮም ኤክስ ግንዛቤ ሊሰወር የማይችል የቀይ ሕንዶች ዕጣፈንታ — በአንዳንዶች ግምት — ምናልባትም ኋላ ላይ በጥቁሮችም ላይ ተመሣሣይ ዕጣ ፈንታ ይደርሳል በሚል ኃይለኛ ሥጋት «ፍሬንዚ» ውስጥ ለወደቀው — እና በማናቸውም ዓይነት መንገድ ቢሆን አጥብቆ ነጮችን ለመዋጋት ዝግጁ ለነበረው — ለዚያ የማልኮልም ኤክስ — «ቫዮለንት» ሊባል የሚችል የትግል ፍልስፍናና ጠንካራ («ፅንፈኛ») አቋም — ምናልባት — ከፍተኛውን አበርክቶት ያደረገለት — ሁነኛ ታሪካዊ እርሾ ሣይሆንለት አልቀረም፡፡
ከታዋቂው የፕላት ወንዝ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቃ — በሚሱሪ ወንዝ አናት ላይ የተቆረቆረችው — የማልኮም ኤክሷ የትውልድ ከተማ — ኦማሃ — የቀይ ህንዶቹን ከአካባቢው ርቀው ማፈግፈግና — የነጮችን ቋሚ ኑሮ መመሥረት ተከትሎ — ከጊዜ ወደ ጊዜ — ከአቅራቢያዎቿ ከሚቺጋን፣ ሚኔሶታ፣ አዮዋ እስከ ኒውዮርክ ድረስ የተዘረጋ — ዋነኛ የነጭ ሰፋሪዎች እንስሳት ንግድ መናኸሪያ እየሆነች መጣች፡፡ እናም በዚያች የኦማሃ ከተማ — የሰዎች ጉልበት እጅጉን ተፈላጊ ነገር ሆነ፡፡ በዚህም የተነሣ — በከብቶች ማቆያ በረቶቹ («ስቶክያርድስ») ውስጥ — በጉልበት ሠራተኝነት ለመሥራት ፍላጎት ያደረባቸው በርካታ ጥቁሮች — ወደ ከተማዋ መፍለስ ጀምረው — ቁጥራቸውም ከሌሎቹ አጎራባች ከተሞች ይልቅ ተበራክቶ ነበር፡፡
የዘር አናሳነት «ዜኖፎቢያ» 
እና — በዚያ እያደገ የመጣ የጥቁር ነዋሪዎች ምክንያት — ብዙ ነጭ ሰፋሪዎች — ከባድ ሥጋት (የዘር አናሳነት እንዳይፈጠር ፍራቻ ሥጋት! እንበለው? ወይስ «ዜኖፎቢያ» ዓይነት ብሔርተኝነት ስሜት) ውስጥ ወድቀው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ግን ከተማዋ — የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ ተከትሎ — የሚጎርፉ በርካታ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች — እና በርካታ የቀንድ ከብት አዘዋዋሪ ነጋዴዎች የሚርመሰመሱባት ከተማ ከመሆን አልዳነችላቸውም ነበር፡፡
እንዲያውም አንዳንዶች ባለትልልቅ በረቶች — ጥቁሮችን በማስታጠቅ — በረቶቻቸውን በጥቁር ጠባቂዎች ማስጠበቅ በመጀመራቸው — እነዚያ ጥቁሮች በአጋጣሚ ከሌሎች ነጭ ወጣቶች ጋር ተጣልተው በነጩ ላይ ጉዳት ካደረሱ — በነጮቹ ነዋሪዎች ዘንድ ባጠቃላይ — ትልቅ ቁጣና ሥጋት ይቀሰቅሱባቸው ነበር፡፡ እና ነገሮች በዚህ ዓይነት ቀጥለው — ልክ ማልኮም ኤክስ ከመወለዱ ከ6 ዓመታት በፊት — ማለትም በጎርጎሮሣውያኑ የዘመን አቆጣጠር — በ1919 ዓመተ ምህረት ላይ — አንድ ስለኦማሃ ከተማ በተነሣ ቁጥር — እስከዛሬም ድረስ ሳይጠቀስ የማይታለፍ — የማይረሳ ክስተት በከተማዋ ሊስተናገድ በቃ፡፡ ማልኮም ኤክስ ከመወለዱ 6 ዓመታት በፊት — በነብራስካዋ መዲና በኦማሃ የተከሰተው «ሬስ ራየት» («የዘር አመፃ») ነበረ፡፡
ምንድን ነበር ያ የኦማሃ የዘር አመፅ? 
ያ — ማልኮም ኤክስ ከመወለዱ 6 ዓመት በፊት በትውልድ ከተማው በኦማሃ የተቀሰቀሰው — እና «የ1919ኙ የኦማሃ የዘር ዐመፃ» እየተባለ የሚጠራው ከፍተኛ የነጮችን ነዋሪዎች ቁጣ የተነሣ የተፈጠረው ክስተት — መነሻ ምክንያቱ — አንድ ዊል ብራውን የተሰኘ የጥቁር «ስቶክያርድ ጋርድ» — ማለትም የከብት ማቆያዎችን የሚጠብቅ ታጣቂ የሆነ ጥቁር ጎልማሣ — አንዲትን ዕድሜዋ ላቅመ ሔዋን ያላደረሰች ነጭ ታዳጊ ልጃገረድ — አስገድዶ ደፈራት — የሚል ዜና መሠራጨቱ ነበር፡፡ ደሞ ያ ዜና የተሠራጨው በቃል ብቻ ሣይሆን — ሆነ ብለው ገበያ ለማግኘት ሲሉ — እንዲያ ዓይነት ትኩስ፣ ስሜት-ቀስቃሽ፣ በዘር-ልዩነት ላይ የተመሠረቱ ንዴትን የሚያጭሩ ዜናዎችን በሚያናፍሱት ጋዜጦች አማካይነት የተሠራጨ አሳዛኝ ዜና ነበር፡፡
ልክ የዚያ ዊል ብራውን የተሰኘ ጥቁር ነዋሪ የታዳጊዋን ነጭ መድፈር ዜና በምድረ ነብራስካ እንደተሰራጨ — ከደቡብ ጫፍ ጀምሮ እስከ መሐል ሀገር ወደ ኦማሃ ከተማ የሚኖሩ ነጭ ወጣት ነዋሪዎች «መች ሰማንና – ይለያል ገና!» የሚል የመሠለ መፈክር አንግበው — በከፍተኛ ቁጣ — ቶም ዴኒሰን በተባለ ነጭ አመፀኛ ፊታውራሪነት እየተመሩ መጥተው — በኦማሃ በመንገዳቸው ሁሉ በሕይወት ባገኙት የጥቁር ዘር ሁሉ ላይ — ያለርህራሄ በመተኮስ ወይ ቋንጃና ብሽሽቱን በመቁረጥ — ንዴትና በቀላቸውን መወጣት ያዙ፡፡
በመጨረሻም በቁጣ የነደዱት አመፀኞች በቀጥታ ወደከተማዋ ፍርድ ቤት አመሩ፡፡ እና በፍርድ ቤቱ ጉዳዩ እየታየ ያለውን — ያን ዊል ብራውን የተሰኘ ሰው — አሣልፋችሁ ስጡን ብለው ፍርድ ቤቱን ወረሩት፡፡ የሕግ አስከባሪዎች ለጥቂት ጊዜ ያን ሊከላከሉ ሞከሩ፡፡ እንዲያውም አመፀኞቹ ያ እጅጉን ስሜታቸውን በንዴት ስለፈነቀለው — ማቆያ ቤቱን ሰባብረው ተከሣሹን ዊል ብራውንን በእጃቸው ካገቡ በኋላ — ፍርድ ቤቱን እንዳለ እሣት ለቀቁበት፡፡ ያን ጥቁር ጎልማሳ —  ዊል ብራውንን ግን — በከተማው አደባባይ ወስደው አካሉን ካኮላሹት በኋላ — በያዙት ነገር ሁላ እንደ እባብ ቀጥቅጠው — አስከሬኑ እስኪበጣጠስ ጎዳና ለጎዳና በተሽከርካሪ እንስሳ ጀርባ አስረው መሬት ለመሬት ሲጎትቱት ዋሉ — መቀጣጫ እና እልህ መወጫ መሆኑ ነው፡፡
በወቅቱ — ያ ሁሉ የጭካኔ ተግባር ሲፈጸም — የተከማው ከንቲባ የነበረው ትውልደ አውሮፓዊ አሜሪካዊ ባለሥልጣን — ድርጊታቸውን ለማስቆም ጣልቃ ሊገባ ሲሞክር — ወዲያው እዚያው በዚያው በንዴት የተጋጋሙት ነጭ ወጣቶቹ — እርሱንም ባንገቱ ገመድ አጥልቀው በአደባባይ እንደሰቀሉት — ነገር ግን በመሐል የፌዴራሉ መንግሥት ታጣቂዎች ገብተው ነፍሱ ሳትወጣ ሊያተርፉት እንደቻሉ፡፡ ያ የኦማሃ የዘር ዐመፃም የሚያበርደው ጠፍቶ — የፌዴራሉ ጦር በመጀመሪያዎቹ ቀናት ሊያደርግ የቻለው ነገር ቢኖር — ወደሰሜናዊ ነብራስካም ያ ድርጊት ተቀጣጥሎ — የብዙ ሰዎች ነፍስ እንዳይጠፋ — በሌሎቹ ሰሜናዊ ግዛቶች ገና ከመነሻው አመፅ እንዳይጀመር ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጦር አስፍሮ መጠባበቅ ብቻ ነበር፡፡ ያሳዝናል በእውነቱ፡፡
እስካሁንም ድረስ ግን —ያ የማልኮም ኤክሷ መገኛ ከተማ — የኦማሃ — የዘር ዐመፃ ክስተት — ከብዙዎች ዘርን-መሠረት ያደረጉ በአሜሪካ ምድር ጠባሳቸውን ጥለው ካለፉ አሳዛኝ ክስተቶች መሐል — እንደ አንዱ ተደርጎ — እስከዛሬም በታሪክ ድርሳናት በሃፍረት ሲወሳ ይኖራል፡፡  እንግዲህ — ለኋለኛው እጅግ ፅንፈኛ የሚባለውን አቋም ለተላበሰውና — ለጥቁሮች መብት — በአሜሪካ ምድር — ነፍጥን እስከመምዘዝና እስከማስመዘዝ ለሰደረው — ለማልኮም ኤክስ አደገኛ ሥጋትና ቁጣ የተሞላ ‹‹ፅንፈኛ›› ማንነት — እነዚህ እነዚህ ሁሉ — በትውልድ መንደሩ እና ከዚያም በኋላ ገና በጨቅላ ዕድሜው — በትንሹ ማልኮም ዙሪያ የተከናወኑ — መራር የታሪክ ክንዋኔዎች — የትንሹን ማልኮም ለስላሳ ሰብዕና — ወደ ደመመራሩ ማልኮም ኤክስ መራር ስብዕና ለመቀየር — ትልቁን ሚና ተጫውተዋል የሚሉን — በአንዳንድ የታሪክ አጥኚዎች የሚነሳው እነዚህን ነባራዊ ክስተቶች በመመርመራቸው የተነሣ ነው፡፡
እናም ዛሬ ላይ ሆነን — ትናንት ስለተፈጠሩ መሰል አሳዛኝ ክስተቶች ስናወሳ — ቢያንስ ማንኛውም ጤናማ ህጻን — ወይም ማንኛውም ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖረው የሚፈልግ ሰው — ከልጅነቱ እስከ ዕውቀቱ ድረስ — ከዘር ጥላቻ ነፃ የሆነ መኖሪያ ሥፍራ እስካልገጠመው ድረስ — እና ከዘር ጥላቻና ግጭት ነጻ የሆነ ሀገር እስካልተፈጠረለት ድረስ — ያ የዘር ጥፋት ሥጋት — ያ የበላይነትና የበታችነት ልክፍት — ያ የሚያደርስበት የዐዕምሮ ቀውስና የስሜት ጉዳት — የቱን ያህል ያን ሰው ዕድሜ ልኩን ሲከተለውና ሲያሳድደው እንደሚኖር — እና ደግሞ — እንዲህ ዓይነት የዘር መቀናቀን የሞላባቸው አካባቢዎች — ምን ያህልስ በእኛ ሰብዓውያን ፍጡራን ላይ — በተፈጥሮ አምላክ ያልፈጠረብንን ከባድ ጥላቻ — እና በሥጋትና ጥርጣሬ የተሞላ ቁስለኛ ሰብዕና —በውስጣችን የመፍጠር ኃይል እንዳላቸው — ከእነዚህና ከሌሎች መሰል እልፍ አዕላፍ ታሪኮች መማርና መገንዘብ ብንችል — በበኩሌ — ብልህ ከሰው ስህተት ይማራል እንዲሉ — ይህ የማልኮም ኤክስን መኖሪያ ከተማና ክፍለሀገር የከበበው አስከፊ ተሞክሮ — እና በጨቅላ ማልኮምና በቤተሰቦቹ ላይ ተክሎ የቀረው ጠባሳ — በቂ ትምህርትና ተሞክሮ የሚሰጥ ይመስለኛል፡፡
በነገራችን ላይ — የማልኮም ቤተሰቦች ሁሉ መጠሪያ ሆኖ የምናገኘውን — ያንን «ሊትል» የሚል ስም ለምሣሌ ብንወስድ — ያ ‹‹ሊትል›› የሚል የቤተሰብ ስም ለእነ ማልኮም ቤተሰቦች መጠሪያነት የተሰጣቸው ከዘራቸው ‹‹ሊትል›› የሚባል ቅደመአያታቸው ኖሮ አልነበረም፡፡ ለራሳቸው ያወጡት ስምም አልነበረም፡፡ «ሊትል» በወቅቱ — ራስህ ለራስህ የምታወጣው የቤተሰብ ስም ሣይሆን — የበታች ማንነትህን አጥርተህ እንድታውቅ — እና መቼም ቢሆን ያንተ ትውልዶች ትንሽነታቸውን ከቶውን በዘመን ብዛት እንዳይረሱት — በ«ስሌቭ ማስተርህ» (ማለትም በጌቶች!) የሚወጣልህ — ስትሸማቀቅበት የምትኖርበት ስምህ ነበር (ቀድሞ ነገር አንተ «ሸምቃቃ» ከሆንክ እንደማለት ነው በእርግጥ!)፡፡
ለምሳሌ የቤተክርስቲያን ሰባኪ ከነበረው — ከማልኮም ትንሹ ወላጅ አባት — ከ«ኧርል» ከራሱ ብንጀምር — ወደላይ የሚቆጠሩ ወላጆቹ በመጠሪያ ስማቸው ላይ «ሊትል» («ትንሹ» «ትንሿ») የሚል የቤተሰብ ስም አላቸው ሁሉም፡፡ የወጣላቸው ግን — እነርሱን እንደንብረቱ እያስቆጠረ ባስመዘገባቸው — በባርያ አሳዳሪያቸው ነበር፡፡
አንዳንዴ እነዚህን ሳስብ — የእኛዎቹ አያት ቅድመ-አያቶች — ለትልዶቻቸው — ግዛቸው፣ ጌታቸው፣ በለው፣ ጌታነህ፣ ጌታሁን፣ አንበሴ፣ ጎሹ፣ ንጉሡ፣ መሥፍን፣ መሣፍንት፣ የምሥራች፣ ላቀው፣ አስታጥቃቸው፣ ሸዋን ግዛው፣ ሠፊሀገር፣ አዝማች፣ አበጋዝ፣ ወዘተ ወዘተ የሚሉ የነፃ ህዝቦች የጌትነት ስሞችን ለትውልዶቻቸው መጠሪያ አድርገው መሠየማቸው ለካ — ለካንስ ነፃ ህዝቦች መሆናቸውን መቼውኑም ቢሆን እንዳይረሱት —ትውልዶቻቸውን ለማስታወስ ነበረ — እያልኩ አስባለሁ!!! አይ ይቺ ዓለም! እኛኮ ያለንን፣ የተሰጠንን ጸጋ አናውቅም! የራሳችንን ስም ተጠይፈን — የባርነት ስም እናወርሳለን ለልጆቻችን — አይ የእኛ ነገር!!
እና ለዚህ ነበር — ማልኮም ኤክስ ነፍስ ሲያውቅ — እና ምራቁን ዋጥ ሲያደርግ — «ሊትል ማልኮም» የሚለውን ከቤተሰብ የወረደለትን መጠሪያ ስሙን ቀይሮት — «Malcolm ‘X’» ተብሎ መጠራትን የወደደው፡፡ በአንድ — እስካሁንም በሚጠቀስለት — ታዋቂ ንግግሩ — ማልኮም ኤክስ በነጭ የባርያ አሳዳሪዎች — ለጥቁር ባሮቻቸው የሚወጡላቸውን መጠሪያ ስሞች — ጥቁሮች አሻፈረኝ ሊሉት እንሚገባ እያስረገጠ በሚናገርበት ንግግር እንዲህ ሲል የሚደመጠው በዚሁ በራሱ ላይ በደረሰበት ሥር የሠደደ ምክንያት ነበር፡፡ እንዲህ ነው የሚላቸው ማልኮም ኤክስ ጥቁሮቹን ሰብስቦ ‹‹ስምህ ማን ነው?›› በሚል ስሜት ቀስቃሽ ንግግሩ፡-
«እስቲ ንገሩኝ? እናንተ ማን ናችሁ? አታውቁትም ማንነታችሁን? ‹ባርቾ› ነኝ እንዳትሉኝ፡፡ ያ የመጨረሻው የከንቱ ከንቱ ስም ነው እኮ፡፡ ነጮች መጥተው ከእነርሱ ከለር ጋር አስተያይተው እናንተን ‹ባሮች› ‹ጥቁሮች› ‹ባርቾች› ከማለታቸው በፊት ግን እናንተ ማን ነበረ ስማችሁ? የት ነበራችሁ ለመሆኑ? እና ምንድንስ ነበራችሁ? እነርሱን ከመሆናችሁ በፊት የእናንተ የሆነው ምንድነበር? የምትናገሩት አንደበት ምንድን ነበር ለመሆኑ? ስማችሁስ ማን ይባል ነበር? ስሚዝ ነበር ስማችሁ? ወይ ጆንስ ነበር? ወይስ ቡቺ ነበር?› ወይስ ፓውል ነበር? ንገሩኝ እንጂ!? ያ አልነበረም ስማችሁ? እኔና እናንተ ከበቀልንበትና ከመጣንበት ሥፍራ እንዲያ ዓይነት ስሞች የሏቸውም፡፡ ፈጽሞ፡፡ እና ማን ነበር ስማችሁ? እና አሁንስ ያኔ ስማችሁ ማን ይባል እንደነበር እንዴት ልትረሱት ቻላችሁ? እንዴት እንዲህ ድራሹ ሊጠፋባችሁ ቻለ? የት ቦታ ላይ ነው የጣላችሁት? ማን ወሰደባችሁ? እንዴትስ አድርጎ ነው የወሰደባችሁ? በምን አንደበት ነበር የምትግባቡት? ታሪካችሁስ የት ነው ያለው? እንዴት አንድ ሌላ ሰው ታሪካችሁን ሁላ ሙልጭ አርጎ እንዲህ እርቃናችሁን ሊያስቀራችሁ ቻለ? እንዴትስ እና ምንስ ቢያደርግ ነው እንዲህ አሁን እንደሆናችሁት እናንተን ስለራሳችሁ አንዳችም ነገር የማታውቁ ዲዳዎች አድርጎ ሊቀርጻችሁ የተሣካለት?»
«Who are you? You don’t know? Don’t tell me “negro” that’s nothing. What were you before the white man named you a negro? And where were you and what did you have? What was yours? What language did you speak then? What was your name? It couldn’t have been Smith or Jones, or Butch or Powell. That wasn’t your name. They don’t have those kind of names where you and I came from. No. What was YOUR name? And why don’t you NOW know what your name was THEN? Where did it go? Where did you lose it? Who took it? And how did he take it? What tongue did you speak? How did the man take your tongue? Where is your history? How did the man wipe out your history? What did the man do to make you as dumb, as you are right now?» (— MALCOLM X SPEECH – “Who are you and whats your name?)
የማልኮም ኤክስ ዕድገትና ማንነት መነሻ ታሪክ አበቃ፡፡ አስደማሚ ታሪኩ ግን ይቀጥላል፡፡ ለዛሬ አበቃሁ፡፡ አምላክ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አብዝቶ ይባርክ፡፡ የብዙሃን እናት ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ መልካም ጊዜ፡፡  ቻው፡፡
Filed in: Amharic