>
5:13 pm - Thursday April 19, 5240

አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ፍኖተ ካርታ ምን ይዞልን ምንስ ይዞብን ይመጣ ይሆን?!? (ዳንኤል ተስፋዬ)

አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ፍኖተ ካርታ ምን ይዞልን ምንስ ይዞብን ይመጣ ይሆን?!?
ዳንኤል ተስፋዬ
አባ ተስፋ ገ/ስላሴ ዘ -ብሔረ ቡልጋ “እውቀት ይስፋ፤ድንቁርና ይጥፋ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ” በሚለው ፍልስፍና ወጋቸው ሀሁን ፣ አቦጊዳን ፣ መልህከተ ዮኃንስን በአንድ የፌደል ገበታ በማቅረብ ለትውልድ አበርክተው አልፈዋል። ታዲያ ይህ ትውልድ ይማርበት ዘንድ ለአገራችን ህዝቦች እንካችሁ ያሉትን ገፀበረከት ዛሬ ላይ ደብዛው ጠፍቷል ሊያስብል በሚችል ደረጃ ላይ ተደርሷል።
ትናንት ድንጋይ እና መደብ ላይ ቁጭ ብሎ ግብረ-ገብን ከቄስ ትምህርት ጋር አሰናስሎ ሲቀስም የነበረው ማህበረሰብ ዛሬ የባህዳን አጅ ገብቶበት የቄስ ትምህርት ቦታውን በመልቀቅ ዛሬ በአብዛኛው የአገሬቱ ክፍሎች ኬጂ እየተባለ በሚጠራው ከእፃናት ማቆያ ጀምሮ የሚሰጥ የትምህርት ዘይቤ አገሬቱን በቅኝ ግዛት መልኩ ተቆጣጥሮ፤ ያለንን ድልብ የትምህርት ዘይቤ አሽቀንጥሮ በመጣል ስንዴውንም እንክርዳዱንም ይዞ ጉዞውን እየገሰገሰ ይገኛል።
  ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እየተካሔደ በሚገኘው  አገር አቀፍ የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታ ፎረም ላይ ከሚመለከታቸው የባለድረሻ አካላት ጋር በመሆን ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ለ24 ዓመት ሲሰራበት የቆየውን የትምህርት ፖሊሲ ብዙ ክፍተቶች የነበሩበት መሆኑን ፣ ብቁ ዜጋን ለመፍጠር አለመቻሉን ተጠቅሶ የትምህርት ማሻሻያ አዲስ ፍኖተ-ካርታ እንደሚያስፈልግ በመድረኩ መገለፁን ተከትሎ ነው።
 ትምህርት የብቁ ዜጋ መፍጠሬያ መሳሬያ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ማጥቂያ መሳሬያም መሆኑንም ሳንዘነጋ ማለት ነው።ይህ በአንድ እንጨት ላይ ያለ ሁለት ባላ የሆነ መሳሬያ አገራችን ወደፌት ወይስ ወደኃላ ስትአስወነጭፍ ቆየች? የሚለውን አፅኖት ሰጥተን ልንመለከተው የሚገባ ጉዳይ ነው። ትምህርት በቀዳማዊ አፄ ሃይለ ስላሴ የአስተዳደር ዘመን ግብረ-ገብን መሰረትን ያደረገ ፣ ባህልን እና ወግን ያልለቀቀ ፣ ለምህራብዊያን ሕቡያን እጅ ያልሰጠ ተቋም በመሆን፣ ማህበራዊ አላፌነቱን የሚወጣ አገሩን የሚወድ ብቁ ዜጋ ትውልድ በመፍጠር ፣ በወቅቱ ቀ.ኃ.ስ የትምህርት ጥራት እንዲያድግ ትምህርት ለምርምር፣ ትምህርት ለምርት እንዲሆን በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥጥር በማድረግ ትምህርት ላይ ትኩረት በማድረግ አስከ ዛሬ ሲያስመሰግናቸው የሚችል በትምህርት ዘርፍ ትልቅ ሊባል የሚችል ስራ ሰርተዋል።የራሳቸውን መኖሬያ ቤት (ቤተ-መንግስት) ለትምህርት ካላቸው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ መኖሬያቸውን ለብቁ ዜጋ ማፍሪያ ይሆን ዘንድ በስጦታ አበርክተዋል። አፄ ኃይለ ስላሴን ከመንበረ ስልጣናቸው በዓይል ገርስሶ መንበረ ስልጣኑን የተቆናጠጠው ወታደራዊ መንግስት ደርግም ቢሆን የትምህርት ፖሊሲ ለመደብ ትግል ቢያውለውም አገሩን የሚወድ ብቁ ዜጋ ከመፍጠር አኳያ የሚታማ እና የሚወቀስ ነው ብሎ መናገር አይቻልም።
 ኢህአዴግ እና ትምህርት…
ትምህርት በኢህአዴግ መሳሬያ ነው። ማጥቂያ መሳሬያ። የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ማጥመቂያ ፣ የምህራብዊያን እጀ ሰብ መፈንጫ የእርካሽ ባህል ማራገፌያ ነው። ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ለ24 ዓመታት ሲሰራበት የቆየው የትምህርት ፖሊሲ በአገዛዙ ምክንያት የትምህርት ጥራት አገሩን የሚወድ ብቁ እና ታታሪ፣ ለማህበራዊ የአኗኗር ዘይቤ ባይተዋር የሆነ ፣ ለብሔር-መደብ ቅድሚያ የሰጠ ፣ ነጭ አምላኪ የሆነ ትውልድ በመፍጠር አቻ የሌለው አቻ የአገዛዝ ስርዓት ሆኖ ላለፉት 27 ዓመታት በመንበሩ ስልጣኑ ቆይቷል።
 በዚህ የአገዛዝ ስርዐት ውስጥ በትምህርት መስክ አንቱታን ያተረፉትን መምህራንን ሳይቀር አገዛዙ በሚፈልገው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍና መስመር አልተጓዙም በሚል በርካታ መምህራንን የማስተማር አቅም የላችውም የሚል ታፔላን በመለጠፍ ከከፍተኛ ትምህርት ደጃፍ እንዲርቁ በማድረግ ዛሬ ላይ እየታየ ያለውን መረን የለቀቀ ትውልድ በአገሩ የማይኮራ ፣ ምህራብዊያንን የሚናፍቅ ትውልድ እንዲፈጠር በር ከፍቷል። እነዚህ መምህራን ገበሬው በግብርናው አርሶ እና ለፍቶ የአስተማራቸውን ማህበረሰብ እንዳያገለግሉ  በሩን ጠርቅሞ በመዝጋት ዛሬ በተለያዩ የምህራብ አገሮች በሚገኙ አጅግ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በማስተማር የነጭ አገልጋይ ሆነው እንዲቀሩ አገዛዙ የተቻለውን ለፍቷል። ተሳክቶለታልም። የነጭ አገልጋይነት ብቻም ሳይሆን አገር እንደ ሀገር ያላትን ባህል እና ወግን ፣ ግብረ-ገብነትን አጣምሮ የያዛውን የትምህርት ልህልና እንድታጠም ተደርጓል።
 እነዚህ ጉምቱ መምህራን ዛሬ በአገራችን ባሉ የትምህርት አውዶች ኖረው ቢሆን ኖሮ ዛሬ በጤና ተቋሞቻችን  እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች ፣ በሃይማኖት በኩል ያለ የጎሬጥ መተያየት፣ በማህበረሰቡ ውስጥ አሁን የተከሰተው የእርስ በእርስ መጠራጠር እንደዚህ ተንሰራፍቶ እና ጥግ ድረስ ተለጥጦ ባልታየ እና ሁኔታዎች ሁኔታዎችን እየፈጠሩ ዛሬ የደረስንበት የቁልቁለት መንገድ ባልደረስን ነበር።
 የሉል-አቀፋዊነት ወረራ በትምህርት ላይ…
ሉል-አቀፋዊነት(ግሎባሌዜሽን) ድንበር የለሽ ቁርኝት በመፈጠር አንድ ወጥ ባህል አንድ ወጥ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለመፈጠር እየታገለ የሚገኝ ርዕዮት መሆኑን ግልፅ ነው፤ የዚህ ግዙፍ አለም አቀፍ እንቅስቃሴ የመጨረሻው ግቡ አለም  በአንድ ወጥ ኢኮኖሚ ፣ አንድ ወጥ የትምህርት ዘርፍ፣ አንድ ወጥ ወታደር እና የሃይማኖት ዕዝ ቀለበት ውስጥ እጅ ተዎርች ይዞ የራሱን ፍልስፍናዊ ወግ ዓለም ላይ ለማስረፅ መንቀሳቀስ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥሯል።
 ይህ አንቅስቃሴ ተሳክቶለት በተለያዩ አገሮች የአገር ሉዋላዊነት ከገዢዎች ጋር በመሞዳመድ የብዙ አገሮችን ጓዳቸው ውስጥ በመግባት” ሾላ በድፍን “ብለው የያዙትን የአገራቸውን ሚስጥር በእርሱ መዳፍ አጅ ውስጥ በማስገባት በአገራቱ የሚካሔዱትን አጠቃላይ የፖሊሲ ለውጥ እና የመዋቅር ማሻሻያዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሬ በመግባት በሚረቁ ፖሊሲዎች እና መዋቅሮች አጁን በማስገባት የእዝ ቀለበት ሰንሰልት ውስጥ በማስገባት አሉታዊ ተፅህኖ ያሳድራል።
 የዚህ የሉል-አቀፋዊነት የሀሳብ ወረራ ማሸነፍ የሚቻለው ጦርን በማዝመት ወደር ያላቸውን መሳሬያ ከአፍ እስከ ገደፍ በመታጠቅ አልያም የሰራዊት ጋጋታ በመደርደር አይደለም ይልቅስ ትልቁ ወደር የሌለው መሳሬያ በሃሳብ በለጦ መገኘት የዕዝ ሰንሰለቱን በጣጥሶ መጣል ይቻላል። ይህንን ካልን ዘንዳ ሉል-አቀፋዊነት (ግሎባላይዜሽንን) በአገራችን ኢትዮጵያ በትምህርቱ መስክ ምን አይነት ጥላውን እያጠላ ነው፤ ምንስ አሉታዊ ተፅህኖ እያሰደረ ነው የሚለውን ስንመለከት። ከዚህ በላይ ባየነው የሉል-አቀፋዊነት ሁለንተናዊ የዘመናዊ ቅኝ አገዛዝ አጀንዳ ወጥ ባህልን ለመፍጠር ካለው ፍላጎት የተነሳ ትምህርት ዋነኛ የአላማው ማስፈፀሚያ መሳሬያ አድርጎ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።
 አገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ በተመለከትናቸው ሁለት መንግስታት ማለትም የአፄ ሃይለ ስላሴን እና የወታደረዊውን መንግስት ደርግን ለምህራብ መጤ ትምህርት በራቸውን በመዝጋት እዛው በፀበልህ ብለው ቆይተዋል፤ አገሬቷን እየመራ ያለው ኢህአዴግ ግን ለውጭ ምህራባዊያን መንገስታት አዲስ መጤ ለሆነ ባህል እና ትምህርት ተገዶም ይሁን በሌላ መንገድ በሩን ወለል አድርጎ በመክፈት ቀዳሚ ነው፤ ለዚህ ይመስላል ኢህአዴግ ባለፈው ሕዳር ለ17 ቀናት አደረኩት ባለው ጥልቅ ግምገማ ላይ መግላጫ በሰጠበት ግዜ አገሬቷ ለውጭ ተጋልጭነት የተዳረገች መሆኑን ያመነው። በዚህ የሉል-አቀፋዊነት ተጋላጭየታችን ትናንት የነበሩንን መልካም ስነ-ምግባር አስጠብቀው ማቆየት የሚችሉ ትምህርቶችን:- ኑሮ በዘዴን፣ እርሻን፣ የእጅ ስራን፣ ስነ-ጥበብ ፣ ዕደ-ጥበብን፣ የታሬክን ትምህርትን ወደጎን በማለት(በነገራችን በዩንቨርስቲ ደረጃ የሚሰጠውን የታሬክ ትምህርት እንዲቆም ተደርጓል)፣ ግብረ-ገብ ወዘተ… ተረፈ ትምህርቶችን ወደ ኃላ ሽምጥ እንዲጋልቡ በማድረግ ዛሬ የደረስንበት የባህዳን ዕቡያን እጆች ሰለባ በመሆን መረን የለቀቀበእራሱ የማይተማመን መንፈሰ ደካማ የሆነ ትውልድ እንዲፈጠር ሉል-አቀፋዊነት እና አገሬቷን እየመራ ያለው ኢህአዴግ የበኩሉን ተጫውቷል። በዚህ 27 ዓመታት በጎ አመለካከት ያለው፣ በእውቀት እና በክሎት የዳበራ አገራዊ ፍቅር ያለው የተማረ ወጣት ማፍረት ተስኖት ከእነ ዕፀፁ የቆየው የ1986ቱ ዓ.ም የትምህርት ፖሊሲ ከ24 ዓመታት በኃላ እንዲሻሻል እና አዲስ ፍኖተ-ካርታ እንደሚያስፈልግ ጠ/ሚ አብይ አህመድ(ዶ/ር) በማመን ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ይመለከተናል ከሚላቸው ግለሰቦችጋ በተገኙበት የመክፈቻ ንግግር ተናግረዋል  ።
በመጨረሻም:-
ይህ ብቁ ዜጋ ማፍራት ተስኖት ለእሩቡ ክፍለ-ዘመን የላሸቀ ትውልድ እና እንዲፈጠር ያደረገውን አሮጊ የትምህርት ፖሊሲ አዲስ በሚተካው ፍኖተ-ካርታ  ከውጭ ሕቡያን  ጣልቃ ገብነት  በሆነ ሁኔታ በአገራችን ባህል ጋር የተዛመደ ወግና ስርሃቱን የጠበቀ አዲስ ፍኖተ-ካርታ በመቅረፅ ረገድ እና በሉል-አቀፋዊነት እጅ ተጠፍሮ የተያዘውን አሮጊውን የትምህርት ፖሊሲ ከስጋት ወደ ተስፋ የጠ/ሚ አብይ አህመድ(ዶ/ር) አስተዳደር ይቀይሩታል፤ የሚል ተስፋ በብዙዎች ዘነድ ቢኖረም፤ በተቃራኒው ደግሞ በዚህ አሳብ የማይስማሙ ሌሎች ምሁራን ደግሞ ለዚህ አዲስ የትምህርት ፖሊስ ፍኖተ ካርታ አሁንም በምህራብዊያን አጅ የሚዘወሩ መሆኑን  ሲገልፁ ይደመጣሉ። መልካም ቀን!
Filed in: Amharic