>
5:14 pm - Thursday April 20, 6305

ወዴት ወዴት አቶ በረከት ምን እያሉ ነው? (አያሌው መንበር)

ወዴት ወዴት አቶ በረከት ምን እያሉ ነው?
አያሌው መንበር
<<እኔ አማራ ክልል ያለው ነገር አይጥመኝም፣አንድም በፖሊሲ የሚሞግትህ የለም!!!>>.
ሲሉ – ለታዲያስ አዲስ ተናገዋል።
እንግዲህ ይህንን ንግግራቸውን እንበትነው ከተባለ ብዙ ጥያቄ ያስነሳል።ወደ ታች ደግሞ እኔ ራሴ በአንድ ወቅት ከበረከት ስምኦን ጋር ስለነበረኝ የፖሊሲ ክርክር ለመዳደስ እሞክራለው።
አቶ በረከት ከላይ ካለው ንግግራቸው አማራ ክልል እየሆነ ያለው ነገር እንደማይጥማቸው ገለፀዋል።አማራ ክልልን ለ27 ዓመት የመሩት እርሳቸውና የእርሳቸው ፓርቲ ጭምር ነው።ያውም አቶ በረከት ፈላጭ ቆራጭ ሁነው እንጅ እንደ አንድ ተራ ሰው ሁነው አይደለም።ስለዚህ በለማውም በጠፋውም ቀጥተኛ ተጠያቂ እንጅ ተችና ሀሜተኛ ሆነው መቅረብ አለባቸው ብየ አላምንም።ስለሆነም የአማራ “ክልሉ” ጉዳይ አልጣመኝም ሲሉ ማንን እንድንጠይቀው ነው እየመከሩን ያለው?ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን።
ሌላኛው ጉዳይ የፖሊሲ ክርክር ጉዳይ ነው።አቶ በረከት እዚህ ላይም ዋሸተዋል።ላልፋት 27 ዓመታት የፖሊሲ ክርክር የተደረገበት አንድ ጊዜ ብቻ በ1997 ዓ.ም ነው።ለዚያውም ምርጫ ወቅት ስለነበር።ከዚያ ውጭ ምሁራንም ይሁኑ ሌሎች የፖለቲካ ሳይንስ ልሂቃን በፖሊሲ ጉዳይ እንዳይወያዩ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ውጭ አቋም የያዘን ሁሉ ፀረ ልማትና ፀረ ሰላም፣ህገመንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል፣ አብሮበትን የሚሸረሽር ንግግር የተናገረ እየተባለ እውቀት ያለው ሁሉ ማረፊያው ዝዋይ፣ ቂሊንጦ፣ ማዕከላዊ፣ ሸዋሮቢት በሆነበት አገር ውስጥ ማን ነው ታድያ የፖሊሲ ክርክር እንዲያደርግ የሚጠበቀው? ዛሬ እኮ ከእስር የተረፉ ምሁራን ራሳቸውን ከጠያቂነት ለማገድ ብለው ይመስለኛል ብዙዎች ወደሱስኛነት ቀይረዋል።የብዙ ምሁራን ጫት ቃሚነትና ጠጭናትን የማየው ስርዓቱ እውቀታቸውን እንዳያበረክቱ ስላደረጋቸው ብስጭት ውስጥ ስለሚገቡ ነው ብየ አስባለው።
የሆነው ሁኖ የፖሊሲ ክርክር ያልተደረገበት ምክንያት እነበረከት ምሁራንን ሲያሳድዱ ስለኖሩ እና የክርክር መድረክ ማዘጋጀትም ስለማይቻል ነው።ይህ ደግሞ ተመልሶ እርሳቸውን በረከትን ነው ተጠያቂ የሚያደርግ።በመንግስት ኮምንኬሽን ሰበብ የዜጎችን የመናገር ነፃነት አፍነው ኑረው ዛሬ ማንን ነው ለመክሰስ የሚታትሩት? ማንስ ነው እንዲናርገ የሚፈለገው?አቶ በረከት ወደተሳሳተ መንገድ እያመሩ ነው።በነገራችን ላይ ሰይፉ ፋንታሁንም መጠየቅ ነበረበት።ማዕዛ ብሩ ብታቀርባቸው እመክር ነበር።
ከበረከት ጋር ስለነበረኝ የፖሊሲ ክርክር ላምራ
ወቅቱ 20005/06 ዓ.ም ይመስለኛል። የአማራ ብዙሃን መገናኛ ጋዜጠኞች ስልጠና ወቅት (አለምነው መኮነን የአማራን ህዝብ ልሃጫም ያለበት መሆኑ ነው) እንደ አጋጣሚ ሁኖ ለስልጠና የተመደብኩበት ቡድን ግሩም ቡድን ነበር።እነ ተስፋየ ወ/ ሳላሴ፣ እነ ጌታቸው (ደባርቅ)፣ እኔና ሌሎችም ትልልቅ አጀንዴዎችን ነበር የምናነሳው።ጌችና ተስፍሽ በመረጃ ከፍ ያሉ ነበሩ።ከበረከት ጋር የተከራከርንበት አንዱ ጉዳይ ታድያ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ልማታዊ መንግስት እሳቤና ለኢትዮጵያ በብቸኛ አማርምጭነት መቅረብ ኣዋጭ ነው አይደለም የሚል ነበር።በወቅቱ እኔ ይህ እሳቤ አዋጭ አይደለም።ከጫካ በአብዮት ስልጣን የያዘ መንግስት ቤተመንግስትም ቁጭ ብሎ ስለአብዮት ከሚያወራ ስለሰላምና ዴሞክራሲ በማሰብ ርዕዬታለሙን ቢያስተካክል በሚል የሶሻል ዴሞክራሲን እሳቤ በአማራጭነት ይዠ ቀርቤ ነበር።ሙያየ ፖለቲካል ሳይንስ ባይሆንም ቅሉ ለእኔ ካነበብኩት ሶሻል ዴክራሲ እንደ እኛ ላለ ማህበራዊ ትስስሩ ጠንካራ ለሆነና በኢኮኖሚ ለደቀቀ ህዝብ ይህ ፍልስፍና የተሻለ ነው የሚል ነበር።ይህ የፖለቲካ ርዕዬታለም ወደፊትም ለእኛ ሀገር ጠቃሚ ነው ብየ አስባለው።በለውጥ አቀንቃኞች አማካኝነት እየተመራ ዲሞክራሲያዊ የሆነ ማህበረሰብ የመፍጠር እሳቤ ሲሆን በካፒታሊዝም ኢኮኖሚ ውስጥ የአጠቃላይ የሀገርንና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ስልት ነው።በህግ የበላይነት እየተመራ የተለያዩ ቡድኖችን የእኩልነት፣ ፍትሃዊነትና የጭቆና ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብቶ ይህንን ለማስወገድ የሚቀረፅ የዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እሳቤ ነው።የሰው ልጅ አለማቀፍ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ እንዲከበሩ እና ዜጎች የህዝብ አገልግሎቶችን (ትምህርት፣ ጤና፣የጡረታና ክፍያ…) ያለ ልዩነት በመንግስት  እንዲያገኙ የሚያደርግ ሲሆን እንደ እኛ ሀገር የተጨቆነና ድሃ እንዲሁም የሀብት ልዩነቱ ጣራ የነካ ህዝብ ባለበት ሀገር ፍትሃዊ ተጠቃሚ ለማድረግ ሶሻል ዲሞክራሲ አዋጭ ነው።ይህ ፍልስና ወደ ሊበራል ዲሞክራሲ ለመሸጋገር ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል የአጭር ጊዜ አመራር ስልት ነው።የማህበራዊ ለውጥ በግለሰቦች የነፃ አስተሳሰብ እና አስተዋፅኦ እንደሚመጣ ያምናል።ለእድገት በር ከፋች ዘርፍም ነው።ወደፊትም በስፋት የማቀነቅነው ይህ ፍልስፍና ነው።
የሆነው ሁኖ ከበረከት ጋር በዚህ ሀሳብ ብዙ ተከራክረናል።በረከት የዚህ ፍልስና ደጋፊ የሚመስል አቋም ቢያሳይም አብዮታዊ ዲምክራሲ ግን ከ20 እስከ 30 ዓመት ማምራት ያለበት ይመስለኛል ነበር ያለው።እኔ በአማራጭነት ያቀረብኩትን ይህንን ዘርፍ ከ20 ወይም 30 ዓመት በኋላ አዋጭ ሊሆን እንደሚችል አሁን ግን ከእነርሱ ፍስፍና ውጭ አይንን መግለጥ የሚያስችል እንደሌለ ነበር የተናገረው።
ታድያ በዚህ በጭፍን አስተሳሰብ ላይ ያለው አቶ በረከት የፖሊሲ ጥያቄ የሚያነሳ አላገኘውም ዱቄት ናቸው የሚላቸው አመራሮች ከቶ በረከት እያለ እንዴትስ የፖሊሲ ጥያቄ ያንሱ? በመሰረቱ እኮ አማራጭ ባያቀርቡ እንኳን ሀገሪቱ ውስጥ አሁን እየታየ ያለው ቀውስ የእነ በረከት ፖሊሲ ያመጣው ውድቀት መሆኑን ለመናገር ነብይ መሆን አያስፈልግም።
እናም አቶ በረከት ለመድረክ ፍጆታ ብለው በየሚዲያው የሚሰጡት መግለጫ ራሳቸውንም ያስገምታል፣ ከማስገመት አልፎም የሚያስጠይቅ ይመስለኛል።አንዳንድ ሀሳቦቻቸው ጫፍ የወጡ ናቸው።በነገራችን ላይ በሀገር ደረጃ ለመጣው በጎም ይሁን መጥፎ ነገር ከበረከት የበለጠ ተጠያቂም ተወዳሽም አይኖርም።በረከት ሁሉንም ነውና
 
((ውይይቱን አያይዠዋለው ብዙ ነገር አለው።አድምጣችሁ ፍረዱ))
Filed in: Amharic