>
5:13 pm - Sunday April 19, 5401

በነተበ ጨርቅ ላይ አዲስ ዕራፊ መጣፍ (ከይኄይስ እውነቱ)

በነተበ ጨርቅ ላይ አዲስ ዕራፊ መጣፍ

ከይኄይስ እውነቱ

የዶ/ር ዐቢይ ‹አስተዳደር› ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያዳርሰናል ብሎ አብዛኛው ተስፋ የሚያደርግበትን የሽግግር ሂደት እንደሚመራና የዚህም መቋጫው በ2012 ዓ.ም. የሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ እንደሆነ ግልጽ አድርጓል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ የሚመሩት ‹ግንባር› ወያኔ (ሕወሓት) የተባለ የአገር ነቀርሳ እንደያዘ ነው የሚያሸጋግረን? ወይስ አንድ ወጥ ‹ፓርቲ› ሲሆን ይህንን የማጅራት መቺዎች ቡድን ለማስወገድ አቅዶ ነው? ወይስ ለውጡን ተቀብለዋል በሚል በአገርና በሕዝብ ላይ የመጨረሻ የሚባሉ ወንጀሎችን ንቅስ አድርገው የፈጸሙ ወሮበሎችን እንደ አህያ ጆሮ ሁሉም እንደፈለገ በሚጎትተው ‹መደመር› በሚል ቋንቋ ይዟቸው ሊዘልቅ አስቧል? ባንፃሩም የምርጫውን ሂደት ነፃ፣ ገለልተኛና ተአማኒ የሚያደርገው ወያኔ ለራሱ ጥቅም ሲል ያቋቋማቸውን ‹ኩባንያዎች› (ተቋማት ለሚለው ስያሜ ስላልበቁ) እና ለዚሁ አስፈጻሚነት የመለመላቸውን ሎሌዎች በመያዝ ይሆን?

ከፍ ብዬ በጥያቄ መልክ ላቀርብኳቸው ሥጋቶች መሠረት የሆነኝ ጉዳይ በቅርቡ ‹በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን› ሲተላለፍ በመስማቴ ነው፡፡ ይኸውም ወያኔ ያቋቋመውና የኢትዮጵያን ሕዝብ ድምጽ ሲያሰርቅ የኖረው÷ ለወያኔ በመሸጦነት ሲያገለግል የኖረው÷ ሕዝብን በመክዳትና በዚህም ምክንያት ለብዙዎች እልቂት ምክንያት የሆነው የይስሙላ ‹የምርጫ ቦርድ› የወቅቱ ሰብሳቢ የሆኑት ወ/ሮ ሳሚያ ዘካርያ የሰጡት አስተያየት ነው፡፡ ወይዘሮዋ ከመጪው ሀገር አቀፍ ምርጫ ጋር በተያያዘ ምርጫውን ስለሚያስፈጽመው ‹ምርጫ ቦርድ› አስመልክተው ሲናገሩ፣ ቦርዱም አገራዊው የለውጥ ሂደት አካል እንደሆነ፣ የማሻሻያ ሃሳቦችን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቀብለው ለማስተናገድ ዝግጁ እንደሆኑ፣ በአገሪቱ ለሚካሄደው ምርጫ የመጨረሻውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ እንደሚውል ገልጸው በእስካሁኑ ሂደት ወደ አገር ውስጥ ከገቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማናቸውም መጥተው እንዳልተመዘገቡ ተናግረዋል፡፡

እንዴት ነው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብድግ ብለው የሚመዘገቡት? ማን ጋ ነው የሚመዘገቡት? ይህ ወያኔ ያዋቀረው ‹የምርጫ ቦርድ› ጋ ነው? ሕዝብ ሳያውቀውና ሳይሰማው የተደረገ ለውጥ ይኖር ይሆን?

ይህ አስተያየት ቸኮለ ካልተባለ በቀር የወ/ሮዋ ንግግር በእጅጉ ገርሞኛል፤ መግረም ብቻ ሳይሆን ሥጋት ውስጥ ከቶኛል፡፡ ምርጫ ቦርድንም ሆነ ሌሎች ተቋማትን ነፃ÷ገለልተኛና ተአማኒ ለማድረግ የታሰበው ከመዋቅራዊ ለውጥ ውጭ ነው እንዴ? እንደሚታወቀው ወይዘሮዋ የወያኔ ተሿሚ ናቸው፡፡ ከወያኔ ተሞክሮ እንደምንረዳው በአምባሳደርነትም ሆነ በመንግሥት የአስተዳደር መ/ቤቶች ተሿሚ የሚሆነው እርሱ በፈጠረው ‹ግንባር› ወይም ‹አጋር› ባላቸው የ‹ፖለቲካ ድርጅቶች› ውስጥ አባል የሆነ ግለሰብ በመሆኑ ወይዘሮዋ ከዚህ ነፃ እንዳልሆኑ እገምታለሁ፡፡ የ‹ምርጫ ቦርድ› ኃላፊ ሆነው ከመሰየማቸው በፊት የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዲሬክተር ነበሩ፡፡ የግለሰቧን አቋም ለጊዜው ወደ ጎን አድርገን በመርህ ደረጃ ስንነጋገር፤

1ኛ/ የተሻሻለው የምርጫ ሕግ ዓዋጅ ቊ.532/1999ዓ.ም. በአመዛኙ ሊያሠራ የሚችል ቢመስልም መሻሻል የሚገባቸው ድንጋጌዎች በመኖራቸው በዚህ ረገድ ጥናት ያደረጉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የማኅበረሰብ ተቋማት፣ የሕግ ባለሙያዎች ወዘተ የማሻሻያ ሃሳቦቻቸውን ለውይይት እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል ፤ ለምሳሌ ያህል ስለ ቦርዱ አባላት አሰያየም የሚደነግገው አንቀጽ 6 በንዑስ አንቀጽ (2) ጠቅላይ ሚኒስትሩ እጩ የቦርድ አባላትን ለተወካዮች ም/ቤት ከማቅረቡ በፊት በም/ቤቱ መቀመጫ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች እጩ አባላቱ ነፃና ገለልተኝነት መሆናቸውን በማረጋገጥ ረገድ በማማከር ደረጃ ተሳትፎ እንደሚኖራቸው ይገልጻል፡፡ እንደምናውቀው ወያኔ ላለፉት 27 ዓመታት ሲያደርጋቸው የነበሩ ምርጫዎች ኹሉ ለይስሙላ የሚደረጉ መሆናቸው (በቅንጅት ከተረታበት ከ1997ቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ በስተቀር፤ ያንንም ቢሆን ኮረጆ በመዝረፍና የለመደውን ብረት በመጠቀም አክሽፎታል) የአደባባይ ምሥጢር በመሆኑና ም/ቤት የተባለውም አካል በ‹ሕግ አስፈጻሚው› (ወያኔ) የሚቀርብለትን ማናቸውም የሕግ ረቂቅ ላይ ማኅተም ከማሳረፍ የዘለለ ሚና ስላልነበረው፤ ከኹሉም በላይ በም/ቤት ተብዬው ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲ የሚባል ኖሮ ስለማያውቅ ይህ ድንጋጌ ትርጕም አልባና እውነተኛ ተቃዋሚዎችን የሚያገልል ነው፡፡

2ኛ/ ቦርዱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች በሚያደርጉት ስምምነት መሠረት ሰብሳቢውና አባላቱን ጨምሮ ባዲስ መልክ መዋቀር ይኖርበታል፡፡

3ኛ/ በምርጫ ሕጉ መሠረት ሰብሳቢውም ሆነ አባላቱ ከማናቸውም የፖለቲካ ድርጅቶች ወገንተኝነት ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡

ለአብነት ያህል ከፍ ብለን የጠቀስናቸውንና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ የሚነሱ አሳሳቢ አሠራሮችን ግምት ውስጥ በማስገባት እንደገና የሚዋቀረው ምርጫ ቦርድ በቅርፅም ሆነ በይዘት ተአማኒነቱ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ይህ አካሄድ መጪውን ምርጫ ነፃ÷ ገለልተኛ÷ ፍትሐዊና ተአማኒ ለማድረግ ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ላይ በእኩል ተፈጻሚነት ሊኖረው ይገባል የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ አለበለዚያ ነገራችን ኹሉ የእምቧይ ካብ ይሆናል፡፡ በሌላ አገላለጽ ወያኔ ዘላለማዊ ገዥ ለመሆን ያዋቀራቸው የግል ‹ኩባንያዎቹን› መሠረት አድርገን ነፃና ገለልተኛ እንዲሁም ተአማኒ የሆነ የምርጫ ሥርዓት እንዲኖር ማለም በነተበው የወያኔ ቡትቶ ላይ አዲስ ዕራፊ ለመጣፍ ከመሞከር ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ውጤቱም ግልጽ ነው የነተበው ጨርቅና አዲሱ ዕራፊ እርስ በርስ ስለማይጠባበቁ ዕጣ ፈንታቸው ሁለቱም በመቀዳደድ ከጥቅም ውጭ  መሆን ነው፡፡

ስለሆነም ታሪክ የሰጠንን ዕድል በይድረስ ይድረስ አጉል ነካክተን እንዳናበላሸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ እንደ ዶ/ር ዐቢይ ፍላጎት ምርጫው ድርጅታው ባስቀመጠው መርሐ ግብር መሠረት በ2012 ዓ.ም እንዲከናወን ነው፡፡ ለዚህም የሰጡት ምክንያት እሳቸውም ሆኑ ሌላ የኢትዮጵያን መንበረ ሥልጣን የሚይዝ አካል በሕጋዊ ምርጫ የሕዝብን ይሁንታ አግኝቶ መምራት  እንዳለበት ካለቸው እምነት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የሰጡት ምክንያት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ጊዜውን ማራዘም ለአገር መረጋጋትም ሆነ የምንፈልጋቸውን ተቋማት መልሶ በማዋቀር ተአማኒነትና ተቀባይነት እንዲኖራቸው የሚያግዝ ከሆነ ጊዜውን ማራዘሙ በጥሞና ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ከዚህ ወዲያ በእያንዳንዱ አገራዊ ጉዳይ ላይ የምናሳርፈው ውሳኔ ከአገር ህልውና ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን ደግሞ ደጋግሞ ማስተዋል ይጠይቃል፡፡

Filed in: Amharic