>

የእትጌ ጣይቱ ሃውልት ጉዳይ፡ “ጥያቄ ማጋነን መልስ ያቀጭጫል!” (ስዩም ተሾመ)

ሰሞኑን “አዲስ አበባ ውስጥ ለእትጌ ጣይቱ መታሰቢያ የሚሆን ሃውልት ሊገነባ ነው” በሚለው ዙሪያ ተቃራኒ ፅንፍ የረገጡ ሃሳብና አስተያየቶች ከዚያና ከዚህ ይሰነዘራሉ። በአንድ ወገን ሃውልት ሊቆም ነው የሚል ደብዳቤ ከከተማ መስተዳደሩ ወጥቷል ይባላል። በሌላ በኩል ደብዳቤው በሚመለከተው አካል ወጪ የተደረገ አይደለም የሚል የአፀፋ ምላሽ ይሰጣል። ቀጥሎ ደግሞ በአንድ አደባባይ ላይ የመሰረት ድንጋይ መጣሉን የሚያሳይ ምስል ይፋ ይደረጋል። አንድ የከተማ መስተዳደሩ ኃላፊ ደግሞ በተጠቀሰው ቦታ ተገኝቶ የመሰረት ድንጋይ መቆሙን የሚያሳይ ምልክት የለም ብሎ ይከራከራል።

ከውዝግቡ በስተጀርባ ደግሞ የሃውልቱን መገንባት የሚደግፉና በሚቃወሙ ወገኖች መካከል ንትርኩ ጦፏል። የሚሰነዘረው ሃሳብና አስተያየት በሁለቱ ወገኖች መካከል በምክንያት ላይ የተመሰረተ ውይይት በማድረግ መግባባት እንዳይፈጠር የታለመ ይመስላል። ለዚህ ደግሞ መሰረታዊው ምክንያት ሁለቱም ወገኖች ጥያቄ ማጋነናቸው ነው። አንደኛው ወገን አዲስ አበባ ውስጥ ለእትጌ ጣይቱ ሃውልት ተገነባ ማለት በኦሮሞ ህዝብ ላይ ከፍተኛ በደል መፈፀም እንደሆነ አድርጎ ያቀርባል። ሌላኛው ወገን ደግሞ “የከተማ መስተዳደሩ ለእትጌ ጣይቱ ሃውልት ለመገንባት ወስኗል ወይ?” ብሎ መጠየቅ በአዲስ አበባ ሕዝብና ታሪክ ላይ የተቃጣ ጥቃት እንደሆነ አድርጎ ያቀርባል።

አዲስ አበባ ውስጥ ለእትጌ ጣይቱ መታሰቢያ የሚሆን ሃውልት “መገንባት አለበት ወይ?” እና “ለመገንባት ታቅዷል ወይ?” ብሎ መጠየቅ በማንም ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ሆነ ስጋት ሊፈጥር አይችልም። ጥያቄውን ተክትሎ በጉዳዩ አግባብነትና አስፈላጊነት ዙሪያ በምክንያት ላይ የተመሰረተ የሰከነ ወይይት ማድረግ ይቻላል። በእርግጥ ሁሉም ሰው በጉዳዩ ላይ ሊስማማ አይችልም። ነገር ግን በሰለጠነ መልኩ ውይይት እስከተደረገ ድረስ ብዙሃኑ በጉዳዩ ዙሪያ የጋራ አቋምና አመለካከት ይይዛል። ይህን መሰረት በማድረግ ሃውልቱ መገንባት አለበት ወይም የለበትም በሚለው ላይ መወሰን ይቻላል።

በዚህ መልኩ የሰከነ ውይይት እንዳይደረግ ዋናው እንቅፋት ጥያቄ የማጋነን አጉል ልማዳችን ነው። “እያዩ ፈንገስ” የተሰኘው ቲያትር ደራሲ በረከት በላይነህ እንዳለው “ጥያቄ ማጋነን መልስ ያቀጭጫል”። አዲስ አበባ ውስጥ ለእትጌ ጣይቱ መታሰቢያ የሚሆን ሃውልት “መገንባት አለበት ወይ?” እና “ለመገንባት ታቅዷል ወይ?” የሚሉት ጥያቄዎች ያለቅጥ በመጋነናቸው ምክንያት ነገሩ ወደየሚያስጠላ ጎጠኝነትና ዘረኝነት ወርዷል። በእንዲህ ያለ ሁኔታ መግባባት ቀርቶ መወያየት እንኳን አይቻልም። ስለዚህ መፍትሄው በቅድሜያ ጥያቄ ከማጋነን አባዜ እንውጣ። በመጨረሻ ለግንዛቤ ይረዳን ዘንድ “እያዩ ፈንገስ” ከተሰኘው ቲያትር የሚከተለውን የቪዲዮ ምስል ቀንጭበን በመውሰድ አቅርበናል

Filed in: Amharic