>
5:13 pm - Wednesday November 30, 2022

የጃዋር እና የታማኝ ሀሳብ እውነት አይደለምን?  (ሞሀመድ እድሪስ)

የጃዋር እና የታማኝ ሀሳብ እውነት አይደለምን? 
(ሞሀመድ እድሪስ)
ከመንግስት መዋቅር እና ከተደራጁ ተቃዋሚዎች ይልቅ የፖለቲካችንን መዘውሩን ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንደያዙት ነው። የታማኝ እና የጃዋር የሀሳብ ልውውጥም የሚያሳየን ይሄንኑ ነው።
ጃዋር Oromo First ብሎ በአለምአቀፍ ሚዲያ ላይ ሲያውጅ አምኖበት፣ ኮርቶበት እና ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች ትልቁ ብሎ የሚያምነውን በመቅረፍ ለኢትዮጵያ መስራትን እንደ ስልት መርጦ ነው። ያ ስልቱ ደግሞ ውጤታማ አድርጎት ማንም ተንጠራርቶ ሊያወርደው በማይችልበት ደረጃ ስሙን ሰቅሎታል። ከዚህ አንፃር ካየነው ታማኝ በየነ የጀዋርን ስኬት አድንቆ የመፈክር ለውጥ እንዲያመጣ መጠየቅ ጀዋር እንዳለውም ከቅንነት የመጣ የቀጣይ ጉዞ የትብብር ጥያቄ እንጂ የመካሪና ተመካሪ ጉዳይ አይደለም።
በተለምዶ የአንድነት ሀይል ተብሎ የሚታወቀው እራሱን ከተግባራዊ ትግሉ ይልቅ ቅስቀሳዋ ላይ ትኩረት አድርጎ መቆየቱ ይታወቃል። የተናጠል ትግሎችንም በተለያየ መልኩ ሲነቅፍም ቆይቷል። ጀዋር በተጋጋሚ ትግል በአጀንዳ ማንሸራሸር ብቻ የሚመጣ እንዳልሆነ እና ሁሉም አካል አለኝ የሚለውን ጠንካራ ማህበረሰባዊ መሰረት ( Social Base) በተግባር ቢያነቃንቅ ለውጡ ፈጣን እንደሆነ ሲጣራ ቆይቷል። አዲስ አበባ እና አንዳንድ ክልሎች ጠንካራ ይዞታ አለን የሚሉ የፖለቲካ ሀይሎችም በሚዲያ ግነት የታጀበ ተደጋጋሚ የህዝባዊ ተቃውሞ ሙከራ ቢያደርጉም እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ስኬታማ መሆን አልቻሉም ነበር። ከዚህ አንፃር ካየነው የተቃውሞ ዘመን ላይ ሁላችንም ሀይላችንን ብናሰባስብ ኢትዮጵያን ነፃ እናወጣታለን ለሚለው ለተግባራዊ ስራ የተደረገው ጥሪ መልስ ሳያገኝ ዛሬ ወደ “አስተዳደራዊ ፖለቲካ” ከተሻገርን በሁዋላ የሚቀርብ ጥሪ የዘገየ ነው ቢባል ግዜው የሚጠይቀውን ትግል እናድርግ የሚል ጥሪ እንጂ ምፀት ሆኖ ሊታይ አይችልም።
እውነታው መሬት ላይ አለ። ሀቁ ከዋናዎቹ ባለድርሻዎች የተደበቀ አይደለም። የደጋፊ ነን ባዮች የታሪክ ሽሚያና የቆርጦ ቀጥል ፖለቲካ ያልተገባ ትኩረት ተሰጥቶት እውነታው ላይ ያልተመሰረተና ከመንገድ የሚቀር የለውጥ ሂደት እንዳይኖር   ስክነት እና አርቆ አሳቢነት ከተፅእኖ አሳዳሪ ሰዎቻችን ይጠበቃል።
Filed in: Amharic