ስንታየሁ ሀይሉ
ዛሬም በተድበሰበሰ ምርመራ እና በተርበተበተ አንደበት ስለኢንጅነሩ አሟሟት እርስበርሱ የተጣረሰ እና በምርመራ ተቋም ደረጃ ወጥ ያልሆነና ተዓማኒነት የጎደለው የምርመራ ውጤት ላይ ኢንጅነሩ ራሳቸውን እንዳጠፉ በድፍረት ተገልፇል።
በግሌ የኢ/ር ስመኘው ራስን የማጥፋት ተግባርን ለመቀበል ቢከብደኝም ከዚያ ተያይዞ ያሉት ምርመራዎች ሁሉ አሳፋሪ እና የተቀነባበረ ውሸት እንደሆነ መግለጫው ያሳብቃል።
– ኢ/ር ስመኘው ከመሞቱ በፊት የበተነው እና በመኪናው ውስጥ የተገኘው የፖስታ መልዕክት ይፋ አለመደረጉ ወይም “ለመሞት ያደረሰው ምክንያት አልተገለፀም ” ተብሎ መነገሩ በትልቅ ውሸት ትልቅ መረጃ መደበቁ ግልፅ ነው።
– ኢ/ር ስመኘው ከመሞቱ ሁለት ቀናት በፊት በቢቢሲ በሠጠው ቃለመጠይቅ በመልካም ሁኔታ ግንባታው እየተካሄደ እንደሆነ ተናግሮ እያለ በውስን ቀናት ውስጥ ራስን እስከማጥፋት የሚያደርስ መረበሽ አያደርሰውም።
– ኢ/ር ስመኘው ከሜቴክ ጋር ባለው ጫና እንዳይሆን የሜቴክ ዝርፊያ የአደባባይ ወሬ እና የሌሎች ተቋራጮች፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና በመዝገብ ደረጃ ሁሉም የሚያውቁት እንደመሆኑ ለኢ/ሩ ራስን ማጥፋት የግል ድርሻም ሆነ ምክንያት አይሆንም።
– ኢ/ር ስመኘው በተገደለበት እለት ለጋዜጣዊ መግለጫ በቢሮው እንግዶች እንደተጋበዙ ተገልፆ በዛሬው እለት ደግሞ እንደ ጦስ ዶሮ ቢሮ እና ሽንት ቤት ሲመላለስ ነው ያረፈደው የሚል ምርመራ ጉንጭ አልፋ ወሬ ነው።
– በመጨረሻም የሶስት ልጆች አባት የሆነው ኢ/ር ስመኘው በስንብት መልዕክቱ ላይ የአንዱን ልጅ ብቻ አደራ ለፀሀፊው እና ለራሱ እንዳስቀመጠ ሲናገሩ ለውሸት ውጤት እንኳን እንዳልተዘጋጁበት እና አሁንም የተደበቀ ሴራ በዙርያችን እንዳለ ውልል ብሎ ይታያል።