>
5:13 pm - Wednesday April 18, 6829

ይድረስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ "ባለቤቴ የራሱን ሕይወት ያጠፋል ለማለት እቸገራለሁ" (የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ባለቤት)

ይድረስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ
“ባለቤቴ የራሱን ሕይወት ያጠፋል ለማለት እቸገራለሁ”
የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ባለቤት ወ/ሮ እሙን ማዘንጊያሽ  – ከካናዳ ቶሮንቶ
የተከበራችሁ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ፤
ወ/ሮ እሙን ማዘንጊያ እባላለሁ፡፡ የአቶ ስመኘው በቀለ ባለቤትና የልጆቹ፤ የበእምነት ስመኝው፤ አሜን ስመኘውና ጽናት ስመኝው እናት ነኝ፡፡ በአሁኑ ወቅት ነዋሪነቴ፤ በቶሮንቶ ካናዳ ነው፡፡
ዛሬ ከፊታችሁ ተገኝቼ ይህንን መግለጫ የምሰጥበት ምክንያት ከሁላችሁም የተሰወረ አይደለም፡፡ የባለቤቴን፤ የአቶ ስመኘው በቀለን ድንገተኛ ምስጢራዊ ሞት ይመለከታል፡፡
ሀሙስ፤ ሀምሌ 19 ቀን፤ 2010 ዓ.ም. ለኔና ለቤተሰቦቼ፤ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ህዝብ አሳዛኝ ቀን ነበር፡፡ በመገናኛ ብዙሀን የተለቀቀው፤ ባለቤቴ፤ ስመኝው በቀለ፤ ጠዋት በመስቅል አደባባይ፤ ሞቶ ተገኘ፤ የሚለው ዜና፤ ቅስም ሰባሪና አስደንጋጭ ነበር፡፡ ባለቤቴን እስከማውቀው ድረስ፤ ፈሪሀ እግዚአብሄር ያለው፤ ታታሪ፤ አገሩንና ቤተሰቡን የሚወድ፤ በምንም አይነት መልኩ ልጆቹን፤ አገሩንና ቤተሰቡን ጥሎ፤ የራሱን ሕይወት ያጠፋል ብዬ የማላስበው ሰው ነው፡፡ ስለዚህ ባለቤቴ ራሱን አጠፋ ለማለት እቸገራለሁ፡፡
በዚህ በስደት በምኖርበት ካናዳ፤ የባለቤቴን ድንገተኛ ሞት በሰማሁ ግዜ፤ ሀዘኔ መሪር ሆኗል፡፡ የስደትን አስከፊ ገጽታ የተረዳሁበት ክስተትና ዜና ነው፡፡ ስለዚህም ላለፉት 4 ሳምንታት በአደባባይ ወጥቼ፤ ሀዘኔን መግለጽ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ማመስገን አልቻልኩም፡፡
በባለቤቴ ሞት መሪርና የማይቆርጥ ሀዘን ቢሰማኛም፤ የባለቤቴን ሞት ተከትሎ የኢትዮጵያ ህዝብ ያሳየው ፍቅር፤ ድጋፍና፤ የሀዘን መግለጫ፤ መጽናኛ ሆኖኛል፡፡ ባለቤት ለሀገሩ ካለው ጽኑእ ፍቅር የተነሳ፤ የራሱንና የልጆቹን ህይወት በድሎ ለህዳሴው ግድብ ግንባታም ይሁን ለሌሎች ታላላቅ ግድቦች ግንባታ መስዋእትነት ከፍሏል፡፡ ሞቱን ተከትሎም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ያሳየው ፍቅር፤ ባለቤቴ እንዳልሞተና፤ በስራው ሕያው ሆኖ እንደሚኖር አሳይቶኛል፡፡
በዚህ አሳዛኝና አስቸጋሪ ወቅት፤ ከጎኔ በመሆን ላጽናናችሁኝ፤ የቶሮንቶና አካባቢው ኢትዮጵያውያንና ኤርትራዊያን፤ እንዲሁም በአገርቤት ልጆቼን የተንከባከባችሁልኝ ወገኖቼ፤ ፈጣሪ ብረድራችሁን ይክፈል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት፤ የባለቤቴን አሟሟት አጣርቶ፤ እውነታውን ለኢትዮጵያ ህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ወደፊት፤ ጊዜና ሁኔታዎች ሲፈቅዱ፤ የማውቀውንና የሚሰማኝን በሰፊው እስክገልጽ ድረስ፤ ልክ እንደእስካሁኑ ሁሉ; በአርምሞና በጸሎት; ግዜዬን እንዳሳልፍ እንደምትፈቅዱልኝ አምናለሁ፡፡  አመሰግናለሁ፡፡
ወ/ሮ እሙን ማዘንጊያሽ  ከካናዳ ቶሮንቶ
ምንጭ:- ሄቨን ዮሀንስ
Filed in: Amharic