>
5:13 pm - Saturday April 20, 7202

በተበላሸ መሰረት ላይ ቆሞ የመታደስ ፈተና!! (በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ - ዶይቼቬሌ)

በተበላሸ መሰረት ላይ ቆሞ የመታደስ ፈተና!!
በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ D.W
* ኢሕአዴግ ውስጣዊም ይሁን ውጪያዊ ፈተና በገጠመው ቁጥር “ተሐድሶ” የማወጅ ልምድ አዳብሯል። ከተሐድሶ ተነስቶ ‘ጥልቅ ተሐድሶ’ የሚለው ላይ የደረሰው በዚህ መንገድ ነው። (ተሐድሶ የሚለው ቃል የእንግሊዝኛውን ‘reform’ ለመተካት ከግዕዝ የተወረሰ ነው።)
አሁን ያለው ተሐድሶ ከቀድሞዎቹ ለየት የሚለው ‘ከጥገናዊ ለውጥ’ ይልቅ ‘ሥር ነቀል ለውጥ’ ለማምጣት ፈቃደኛ ስለሚመስል ነው። ይሁን እንጂ ሥሩ ላይ ቆሞ ሥሩን መንቀል ቀላል ነገር እንዳልሆነ አሁን አሁን እየታየ ያለው ሁኔታ እያስመሰከረ ይመስላል።

በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ተቋማትን እና ሕግጋትን ለማደስ ደፋ ቀናው ተጀምሯል። ከፀጥታ ተቋማት እስከ ፍትሕ አካላት ድረስ ለተሐድሶ ተዘጋጅተዋል። ተሐድሶውን ለማካሔድ የአመራር አካላቱ ይሁንታ ቢኖርም የነባሩ ስርዓት ሰበቃ ግን እንቅፋት ሆኖ ቆሟል።

ለተሐድሶ ከታጩት ዘርፎች መካከል የፍትሕ ስርዓቱ አንዱ ነው። ይህንን ለማስፈፀም 13 አባላት ያሉት ጉባዔ መቋቋሙ ይታወሳል። ጉባዔው አምስት አማካሪ ቡድኖችን በሥሩ ፈጥሯል። እነዚህ አማካሪ ቡድኖች እንዲያጠኑ በተወሰነላቸው ዘርፍ የተስተዋሉ ችግሮችን ነቅሰውና የተነሱ ቅሬታዎችን በማጥናት የመፍትሔ ሐሳቦችን ይጠቁማሉ። በዚሁ መሠረት ሕዝባዊ ምክክሮች ተደርገው በጉባዔው አማካይነት ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ከዚያም ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ፣ ማሻሻያው ወይም ተሐድሶው ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህ ሒደት ውስጥ ከተስተዋሉት ችግሮች ዋነኛው የችግሮቹን መንስዔ እንደመነሻ አድርጎ ለማሻሻል መሞከር ነው። እንደሚታወቀው፣ ድኅረ ምርጫ 97 አፋኝ አዋጆች እና አፋኝ አተገባበሮች የተስተዋሉበት ነበር። ከነዚህ አፋኝ አዋጆች ውስጥ የፀረ ሽብርተኝነቱ ዐዋጅ እና የሲቪል ማኅበራቱ ዐዋጅ ተጠቃሽ ናቸው። የአማካሪ ቡድኖቹ በፍጥነት ጥናት ሠርተውባቸው ለሕዝባዊ ውይይት በቅድሚያ የበቁትም እነዚህ ሁለቱ ናቸው። አጥኚዎቹ ለሕገ መንግሥታዊ መብቶች እና ዓለምዐቀፍ ድንጋጌዎች ቅድሚያ ሰጥተው የመፍትሔ ሐሳቦችን ለማመላከት የሞከሩ ቢሆንም ያለፈው ሁኔታ እየፈተናቸው ይገኛል።

እንደምሳሌ ለመጥቀስ ያህል የሲቪል ማኅበራት የገቢ ምንጭ ከውጪ 10 በመቶ፣ ከአገር ውስጥ ደግሞ 90 በመቶ መሆኑ ዋነኛው የሲቪል ማኅበራት ገዳይ ነው። ይሁን እንጂ አሁን ዐዋጁን የማሻሻል ነገር ሲነሳ፣ ቀድሞ ገደብ በመቀመጡ የገደቡን ምጥጥን ማሻሻል ቀድሞ ይመጣል እንጂ የመደራጀት ነፃነትን ላለማደናቀፍ ሲባል ገደብ አለማስቀመጥ የሚለው ማራኪ ሐሳብ አልሆነም። አጥኚ ቡድኑ ምንም ዓይነት ገደብ መኖር የለበትም ቢልም ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል፣ በተለይም ደግሞ ከቀድሞዎቹ እና አሁንም ድረስ በሲቪል ማኅበራት ማደራጃ ኤጀንሲ  ሠራተኞች በኩል ከፍተኛ ቅሬታ እየተሰማ ነው።

ስርዓቱ፣ ምንም እንኳን ከላይ ያሉ አመራሮቹ በሐሳብም በሰው ኃይልም እየተቀየሩ ቢሆንም በመካከለኛ ኃላፊነት እና በዝቅተኛ መደብ ያሉ ሠራተኞች አንድ ዓይነት በመሆናቸው ከበፊቱ የተለየ አሠራር በሙሉ ይጎረብጣቸዋል። ለለውጥ ተቋቋሚነትም ይታይባቸዋል። ከዚህም በላይ የአፋኝ ዐዋጆችን እና አሠራሮችን ገመና ለመሸፋፈን ለዓመታት የዘለቀ ፕሮፓጋንዳ ሲደረግ ከመክረሙ የተነሳ ቀድሞ ከተጣለው መሠረት አፈንግጦ ማሰብ ከባድ እየሆነ ይመስላል።

በተበላሸ መሠረት ላይ ሆኖ የተሻለ ስርዓት መገንባት በጣም አስቸጋሪ ነው። ‘የችግሩ ፈጣሪ የሆነው አስተሳሰብ መፍትሔውን ማምጣት አይቻልም’ የሚለው አባባል ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ይዛመዳል። የማሻሻያ/የተሐድሶ ሒደቱ ማነፃፀሪያ መሥፈርቱ (the benchmark) የቀድሞው አፋኝ ሁኔታ ከሆነ ምናልባትም ዘላቂ ለውጥ ማምጣት ላይሳካ ይችላል። ይህም ትልቁ ፈተና ሆኖ ይቀጥላል። እንደመፍትሔ በተለይ የፍትሕ ስርዓቱን እና አፋኝ ዐዋጆችን ለማሻሻል መነሻችን የቀድሞው አሠራር ከሚሆን ይልቅ ሕገ መንግሥታዊ እና ዓለምዐቀፍ መርሖዎች ቢሆኑ መልካም ነው።

Filed in: Amharic