>

ዓውዳመት እና ቀልብ ...!  (አሰፋ ሀይሉ)

ዓውዳመት እና ቀልብ . . . !
 አሰፋ ሀይሉ
 
«በፍየል ዘመን ፤ በግ አትሁን…?!»
እናቴ ምንድን ነበር የምትለው? አዎ … ትዝ አለኝ አሁን፡፡ በግ፣ ዶሮ፣ ፍየል፣ ወዘተ.. የመለየት ጥበብ ነበራት!!! እሷም ከአያቷ ነው የተማረችው፡፡ ወይም ይመሥለኛል፡፡ እና ያ ጥበቧ ደሞ – «ቀልብ» ይባላል!! አዎ – ቀልብ!!! ከበጎች መሐል – የቱን እንደምትመርጥ – ሁሉ ዓይን አዋጅ ሆኖብህ ግራ ስትጋባ – ሌላ ምንም መዳኛ የለህም – ከቀልብህ በቀር!!! እና ቀልብ – በቃ – ሀገር-በቀል የ«ቾይስ ሲስተም» ናት፡፡ ሲስተሟም – ሁሌ ከእናቴ አፍ ስትነገር እንዲህ ተደርጋ ነው፦
«የፈለገ ይሁን – በቃ ልክ እንዳየኸው – ቀልብህ
እርፍ ያለበትን ነው – ይዘህ መመለስ ያለብህ!»
– ነው የምትልህ እሷ፡፡ ቀልብ ነው ዋናው መዳኛ! እኔ ደሞ – ሲፈጥረኝ – ቀልብ የለኝም፡፡ እና ይኸው የጠፋ ቀልቤን ሳፈላልግ – ይኸው እንዳለሁ አለሁ!! እሺ እኛ ቀልባችን የማይደነግጥብንስ – በምን እንለይ?!!! አወይ ቀልብ!?
… እና በቃ ቆይ – ስለእናቴ የጀመርኩልህን መች ጨረስኩ?!! አንዱ በግ ላይ – በቃ – እናቴ – ልቧ ድንግጥ ይልባታል አይደል? … እና ቀልቧ ካረፈበት ደሞ – ሻጩም በዋጋው ቀልቧን ይገፈዋል አይደል? – እንዲያ ሲሆንባት እናቴ – ቀልቧን በቆረጣ አሸጋግራ እየመነጠረች – ገበያውን ሁሉ ሌላ በግ እየተደራደረች ታስሳለች፡፡ ነገር ግን – ሁሌም – ውጤቱ አንድ ነው፡፡ ለምደነዋል፡፡ ወደ መጀመሪያው ቀልቧ ነው የምትመለሰው፡፡ ተመልሳ – ተከራክራ – ተጨቃጭቃ – ያንኑ!!! እና እኛ ልጆቿ – ያን የእናታችንን ቀልብ ስለምናውቅ – ልክ አንዱን ለይታ ዋጋውን ስትጠይቅ – እርስ በእርስ እንተያያለን! ድንገት የማዘር ቀልብ ትልቅ በግ ላይ ካረፈ – ወዮለት ገዢው ስፖንሰር!
አንዴ – እህቴ በግ እንግዛ ብላ ወደ ገበያ ሄድን፡፡ እናታችን ደሞ – ገና እንደደረሰች ቀልቧ – የሆነ የሚገርም ሙክት ላይ አረፈ፡፡ እና እናቴ ያኛውን አየሽው? – ትላታለች እህቴን – ወደሙክቱ እየጠቆመች፡፡ እህቴ ደሞ – የቱን ነው የምትዪው? – አይታየኝም!! እንዴ – ያኛውን?!! – መልስ፡- እኔ የምትዪኝን ልለየው አልቻልኩም – በቃ ሌላ ቦታ ዞር ዞር እንበልና እንይ!! (የምን ዞር ዞር!!! እንዲያውም ይቅርብኝ! በግ አልፈልግም!!) ኡውውውይይ!!! (Loool!!!)
ግን እናታችን – ራሷም ብትሆን ገዢዋ ማን – በቃ ቀልቧን አዳማጭ ነች ሁሌም፡፡ ከሁሉ ነገር በፊት – ቀልብ!!!! ቀልቧ ያረፈበት ካልሆነ የተገዛው – በቃ – ይሄኛው «ቀልበ-ቢስ» በግ – ታርዶ እየተበላ እንኳ – በቃ – የሆነ እንከን ይፈለግለታል!!!! ይሄ ስጋው «የጎፈየ» ነው!!! ወይ መጎፍየት???!!! (Loool!!!)  ለመጀመሪያ ጊዜ ጎፈየ የሚለውን ቃል የሰማሁት – በአንድ ጦሰኛ በግ ሰበብ ነው!!!
እናማ በቃ – እናት – በእኛ ቤት – በቀልብ ነው የምትመራው፡፡ በሌላውም ቤት ግን ያው ነው መሠል፡፡ በቃ – የሀበሻ እናቶች እንደዚያ ናቸው፡፡ ቀልብ – ዋናው ነገራቸው ነው፡፡ መታመምህን – ቀልቤ አላማረኝም – ምን ሆነሃል? – ብለው ያውቁብሃል፡፡ በግም፣ ዶሮም፣ ፍየልም – ሲገዙ – በቃ – ቀልባቸው አትርቃቸውም፡፡ እና ያው የኔም እናት እንደዚያው ናታ!! ለምን ጥንቅር አይልም?! – ምንም ነገር አርጋት – ብቻ ቀልቧን አትደውክባት !!!
እና አሁን – እኔም – ከትንሿ እህቴ ጋር ሄድኩ፡፡ እኔ ቀልብ ስለሌለኝ – በሰው ቀልብ ነው የምመራው፡፡ ዓይኗን አድንቄዋለሁ የእህቴን፡፡ ቁርጠኝነቱም አላት፡፡ እሷም ቀልቧ – «ሃርድ» ነው – የዋዛ አይደለችም፡፡ በምርጫም – በድርድርም – አትምጣባት!!! እኔማ ምን አውቄ?! – ሲፈጥረኝ የእግዜር በግ!!! (Loool!!!)፡፡
[ግን ግን .. ሰው ሁሉ… ራሱን ምስኪን አርጎ ለማቅረብ ሲፈልግ – ለምንድነው ግን – በግ በምሳሌነት የምትመጣበት?! በግ ነኝ – በግ ነው – የእግዜር በግ ናት – ይልሃል ሀበሻ፡፡ ከበግ የበለጠ –  ሌላ ምሳሌ የምትሆን እንስሳ ጠፍቶ ነው ግን?! … አይ… አንድ እንስሳ አለች መሠለኝ – አህያ፡፡ እሷ ግን ሸኮናዋ ድፍን ነው፡፡ አትበላም፡፡ እና አትረባም፡፡ ደሞ እሷን ብሎ ምሳሌ!!! ስለተንጎማለለች ነው?!! ኧረ በግ ይግደለኝ!!!? አባቴ ይሙት – በሥነሥርዓት!!!! በግ – እና – የተማረ – ይግደለኝ – ነው የምልህ!!!! (Loool!!!)]
ለማንኛውም – ብቻ – ሁላችንን – ቀልብ አይራቀን፡፡ አንድዬ ቀልባችንን ይሰብስብልን፡፡ «ጠላታችንን ቀልቡን ይንሣው!» የሚለው ማን ነበር? – አዎ – ጋሽ ስብሃት ለአብ ገብረእግዚአብሔር ነበር፡፡ እናንተን ክፉ አይንካችሁ – ብሎ ይመርቅና – አስከትሎ ደሞ – ጠላታችሁ ቀልቡ ይገፈፍ – ይል ነበር ጋሽ ስብሃት፡፡ ወንድሜ – እንደኔ ቀልበ-ቢስ አርጎ የፈጠረህ ቀን – ቀልብ – ከቀለብ እራሱ እንደሚበልጥ – ያን ጊዜ ይገባሃል፡፡
ቀልብ ከሚነሳህ – እና ቅስምህ ከሚሰበር?! – ወንድሜ – የተሰበረ ቅስም – ብዙ ነገር ቀስሞ – ይጠገናል፣ ያገግማል፣ ይሽራል፡፡ የተበተነ ቀልብ ግን – በቀላሉ አይሰበሰብም፡፡ የተነሣ ቀልብ – እንዲህ በቀላሉ ተሰብስቦ ቁጭ ሊል?!! – ምን ነክቶሃል?!! ቀልብ – ዕቁብ መሠለህ እንዴ – እንዲህ በቀላሉ – እገሌንና እገሌን ብለህ የምትሰበስበው??!!!! (Loool!!!) አባቴ ይሙት – በሥነሥርዓት!!!!
የዘንድሮ ምክርማ – «በፍየል ዘመን ፤ በግ አትሁን!» – የሚል ሆኗል!! አትሞኝ ለማለት መሰለኝ፡፡ ወይም የዋህነቱን አታብዛው!!! (አንዳንዴ እኮ ሀበሻ እንዲህ ብሎ የሚሸረድደው – ከይሲውን ሁሉ እኮ ነው – አንተ ግን – ይለዋል – የዋህነቱን ታበዛዋለህ!!!) (Loool!!!)
እኔ ግን አገላብጬ እላችኋለሁ፡- «በበግ ዘመንም ፤ ፍየል አትሁን!»፡፡ «አጉል» አትሁን፡፡ ማለቴ – አጉል ብልጥ፣ አጉል አራዳ፣ አጉል አወቅኩኝ ባይ፣ አጉል ተናጋሪ፣ አጉል ተረበኛ፣ አጉል ችኩል፣ አጉል ተራቃቂ፣ አጉል አለቅላቂ፣ አጉል ሞዛዛ፣ አጉል .. ሁሉንም!!! በቃ አጉል ፍየልም አትሁን፡፡ እና ደሞ – ጨምርልኝ ካልከኝ – ምናልባት – «ባንበሣ ዘመን – ጅብ አትሁን!» – ብልህስ – ቅር ይልሃል??!!! – ነው የምልህ፡፡ («አውቀህ ሞተሃል!!» – ያልከው…. ሰምተሃል…!! Loool!!!)
ለማንኛውም አሁን – ከበጎች መሐል ገብቶ – አጉል ብትን ብሎብኝ የቀረውን ቀልቤን – አሁን እንደምንም እየሰበሰብኩት ነው፡፡ እና ወደ ቀልቤ ስመለስ – ለካንስ – ይሄ በግ – ገና እንዳየሁት – ቀልቤን ግፍፍ አርጎት ነበር!! ቀልቤን ለማስመለስ – የእህቴን እርዳታ መጠየቅ ነበረብኝ፡፡ እና ወደቀልቤ ስመለስ – ከበጉ ጋር – ልክ እንደጠፋ ዘመድ – አንላቀቅ አልን (ወይም እንዲያ መሠለኝ! Loool!)፡፡ ሻጩ ደሞ — ሰፍፍ ያለውን ቀልባችንን ተመልክቶ — ባንዲት ቃል – የሰበሰብኩትን ቀልቤን – መልሶ ከላዬ ገፈፈው፡፡ ቆዳውን አይግፈፍና – የእኔን ቀልብ ይግፈፍ እንጂ – ምን ያድርግ! – በበጎች መሐል የተገኘ – ሌላ በግ – እንዲህ ከፊቱ በነፃ ቆሞለት – ሲያገኝ!! (Loool!!!)
እግሬ አውጭኝ ማለት ነበር – መጨረሻዬ!!! ቀልቡ የተበተነ – ምን አቁሞ ያስጠብቀዋል? – መሄድ ነው እንጂ – የባከነበትን ቀልብ ፍለጋ – ራሱን ማባከን – መሮጥ – ብን ማለት ነው እንጂ!!! እና እኔም – መቼም አንዴ እንደምንም የሰበሰብኩትን ቀልቤን – ይሄ ዋዘኛ በትኖብኛልና – ዋጋም የለኝ – የሚል ሃሳብ መጣብኝ፡፡ እና – በሻጩ ድንጋጤ – ብርርርርር ብዬ ብፈተለክ ደግሞ – ዳግመኛ ደብዛዬም እንደማይገኝ – መመለሻም አንጀት አይተርፈኝም – አውቅ ነበር፡፡
እና – «በግ ከበረረ ፤ ሞኝ ካመረረ» – እንደሚባለው – እኔም – በርሬም ይሁን አምርሬ – ብቻ ግን – ልፈተለክ… ስሰናዳ – ለካንስ – እህቴ – ከጎኔ ነበረች!! እና – አፍሬ ተመለስኩ፡፡ አይ የበግ ነገር!! አይ ዓውዳመት!! አይ በዓል!! አይ እናት!! አይ ቀልብ!! አይ እህት!! አይ ገበያ!!! አይ 2011..!!! አይ የበግ ነገር!!!!
 ብቻ ግን – እንዲያም ሆነ – እንዲህም ሆነ – ጎደለም ሞላም – ብቻ ግን – ለዓውዳመቱ – ለቀኑ – ለዕለቱ – ለተስፋው – ለአዲስ ዓመቱ – ለዘመነ ሉቃሱ – ለቅዱስ ዮሐንሱ – ለሣሩ – ለቄጠማው – ለዕጣኑ – ለቡናው – ለምኑ – ለምኑ – ለሁሉ ነገሩ ብቻ – አምላካችንን ተመስገን እንበለው፡፡ ያም ሆነ ይህም ሆነ – ስለመኖራችን – ስለቅንጣት ደስታችን – ስላለን እና ስላልሆነብን ነገር ሁሉ – የተመሰገነ ይሁን ብቻ – እርሱ አንድዬ – የኢትዮጵያ አምላክ!!
ተመስገን አምላካችን!! አዲሱን ዓመት – የአዲስ ዘመን ብሥራት የምንሰማበት – በደስታ የምንቦርቅበት – በፍየል ዘመን፣ በግ ለመሆን የምንፈቅድበት – ልባችንን በየዋህ ፍቅር የምትባርክበት – የተባረከ ዓመት አድርግልን!  መልካም አዲስ ዓመት፡፡ መጪው – ፪ሺ፲፩ – ለሁላችን – የምህረት ዓመት ይሁንልን፡፡
መልካም ፈረሰኛ — መልካም ሻኛ — ከመልካም አዱኛ ጋር — ለሁላችን ተመኘሁ፡፡ መልካም እንቁጣጣሽ!! አበቃሁ፡፡ ቻው፡፡
«ይህንም ፡ ምሳሌ ፡ ነገራቸው ፡ እንዲህ ፡ ሲል ፦መቶ ፡ በግ ፡ ያለው ፡ ከነርሱም ፡ አንዱ ፡ ቢጠፋ ፥ ዘጠና ፡ ዘጠኙን ፡ በበረሓ ፡ ትቶ ፡ የጠፋውን ፡ እስኪያገኘው ፡ ድረስ ፡ ሊፈልገው ፡ የማይኼድ ፡ ከእናንተ ፡ ማን ፡ ነው ? ባገኘውም ፡ ጊዜ ፡ ደስ ፡ ብሎት ፡ በጫንቃው ፡ ይሸከመዋል ፤ ወደ ፡ ቤትም ፡ በመጣ ፡ ጊዜ ፡ ወዳጆቹንና ፡ ጎረቤቶቹን ፡ ጠርቶ ፦ የጠፋውን ፡ በጌን ፡ አግኝቼዋለኹና ፡ ከእኔ ፡ ጋራ ፡ ደስ ፡ ይበላችኹ ፡ ይላቸዋል ፡፡» — ሉቃስ ፲፭ ፥ ፩—፮
Filed in: Amharic