>

ድልን ማስጠበቅ ድል ከማድረግ በላይ ዋጋ ያስከፍላል!!! (ዳንኤል ክብረት)

ድልን ማስጠበቅ ድል ከማድረግ በላይ ዋጋ ያስከፍላል!!!

ዳንኤል ክብረት

ሰውዬው አንበሳ ሊያድን ጫካ ይገባል፡፡ እየተሽሎከለከ ዛፍ ለዛፍ ሲያነጣጥር፣ የአንበሳውንም ዱካ እያዳመጠ ሲከተል፣ ቆየና አንድ የአንበሳ ደቦል በቀስቱ አነጣጥሮ ጣለ፡፡

 ገና ደስታውን ሳያጣጥም የሰውነት ክፍሎቹ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፡፡ 

* እጁ አንበሳውን አነጣጥሮ የጣለው እርሱ መሆኑን በማስረዳት የተለየ ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ ተናገረ፡፡

 * ይህንን የሰማው እግሩም ‹መጀመሪያውኑ ማን ተሸክሞህ መጥተህ ነው ወጋሁት፣ መታሁት የምትለው› ብሎ ክብሩ የእርሱ መሆኑን ገለጠ፡፡ 

* ነገሩን የታዘበው ዓይንም ‹በምን ዓይተህ ነው ያነጣጠርከው› አለና ክብሩ የእርሱ መሆኑን በኩራት ደሰኮረ፡፡

 * ጆሮም የአንበሳውን ዱካ እኔ በጽሞና ባልከተል የት ታገኙት ነበር? ሲል ቀዳሚው ባለ ድል እርሱ መሆኑን ደነፋ፡፡ 

* አፍና ሆድም ‹ባልተበላ ምግብ በባዶ ሆድ እንኳን ማደን መታደን አይቻልም› ሲሉ ተከራከሩ፡፡

እንዲህ የሰውነት ክፍሎች ሁሉ እየተነሡ ‹ተኳሹ፣ መራዡ፣ አነጣጣሪው፣ እኔ ነኝ› እያሉ ሲከራከሩ ሰውዬው ወደ ግዳዩ ሳይሄድ ዘገየ፡፡ በዚህ መካከል ዓይን ቀና ቢል አንበሳው ሲሞት ያሰማውን ድምጽ የሰሙ ሌሎች አንበሶች ዙሪያቸውን ከበዋቸዋል፡፡ ዓይን በድንጋጤ ሲፈጥ ያስተዋለው እጅም ለሌሎች አካላት መከባባቸውን ጠቆመ፡፡ ይህን የተመለከተው እግር እሮጣለሁ ብሎ ሲያስብ እንኳን መሮጫ መሹለኪያ ቀዳዳ አላገኘም፡፡ ቅድም እኔ ነኝ እኔ ነኝ እሉ ሲፎክሩ የነበሩት ሁሉ ለየብቻ ሮጠው ማምለጥ አልተቻላቸውም፡፡ አንበሶቹ ግን የግዳይ ቀለበታቸውን እያጠበቡ እያጠበቡ ተጠጉ፡፡ ፍጻሜውም መበላት ሆነ፡፡

ዛሬም በኢትዮጵያ የሚታየው ይሄ ነው፡፡ ባለ ድሉ እኔ ነኝ፣ ታጋዩ እኔ ነኝ፣ ለውጡን ያመጣሁት እኔ ነኝ፣ የዚህ ሁሉ ፊታውራሪ እኔ ብቻ ነኝ፣ ሠሪ ፈጣሪው፣ ያዡ ገናዡ እኔ ነኝ፤ የቅድምና ሩጫ የክብር እሽድድም፡፡ ከአንባሰው ሞት በኋላ ምን እናድርግ? ብለው ከመወያት ይልቅ አንበሳውን የገደለው ማነው? በሚል ውዝግብ ውስጥ እንደገቡት የሰውነት ክፍሎች፣ዛሬም ከተፈጠረው ለውጥ በኋላ ምን እናድርግ? ችግሩ ተመልሶ እንዳይመጣ፣ የተሻለ ቀንም እንዲፈጠር ምን እናድርግ? ከማለት ይልቅ ‹የዚህ ሁሉ ጫጩት አውራው እኔ ነኝ› የሚል በሽታ ውስጥ ገብተናል፡፡ የአንድ ሰውነት አካላት መሆናችን ረስተናል፡፡ የሚና ልዩነት የአስተዋጽዖ ተዋረድ ፈጥሮብናል፡፡ አሁንም ከትናንት ሳንወጣ በትናንት አዙሪት ውስጥ እየገባን ነው፡፡

አንድ ሯጭ ምን ያህል ኪሎ ሜትር እንደሮጠ ከማሰብ ይልቅ ምን ያህል ከፊቱ እንደሚቀረው ማሰቡ ነው የሚጠቅመው፡፡ የሮጠው ያለቀ ጉዳይ ነው፡፡ የሚሮጠው ግን ገና የሚቀርና የሚፎካከርበት መድረክ ነው፡፡ ምንም ያህል እየመራ ቢሆን ገመዱን በጥሶ እስካልፈጸመ ድሉ ተጠናቅቋል ማለት አይቻልም፡፡ አንደኛ ሆኖ መቅደም አንደኛ ሆኖ ለመውጣት ብቸኛው ዋስትና አይደለም፡፡ ድሉን እስከ መጨረሻው ካላስጠበቀ በቀር፡፡

በአንድ ሀገር ታሪክ ውስጥ አንድ ሰው፣ ቡድን፣ ፓርቲ፣ ማኅበረሰብ ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ለውጥ የሂደት ውጤት ነውና፡፡ ነገር ግን የሚታዩና የማይታዩ ለውጥ አምጭዎች አሉ፡፡ መቼም የሰው መታወቂያ ላይ የሆድ ዕቃው ፎቶ አይወጣም፡፡ የፊቱ ጉርድ ፎቶ እንጂ፡፡ ያ ማለት ግን ሰውዬው ፊቱ ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ ለውጥና ትግልም እንደዚያው ነው፡፡ ከፊት የሚታዩት ፊታውራሪዎች የማይታዩት ውጤቶች መሆናቸውን ከረሱ አንገትን የዘነጋ ጭንቅላት ይሆናሉ፡፡ ዝናብ እንዲመጣ የተፈጥሮ ኃይሎች ሁሉ የተባበረ አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉ ሁሉ ለውጥ እንዲመጣም ማኅበራዊ ኃይሎች ሁሉ የሚታይና የማይታይ አስተዋጽዖ አላቸው፡፡

የተሻለውና የሚጠቅመው ነገር ‹እኔ ብቻ ነኝ‹ ና ‹ለእኔ ብቻ ነው› የሚለውን ስሜት አጥፍቶ ‹እኛ ነንና ለእኛ ለሁላችን ነው› የሚለውን እውነታ መቀበልና ማስፈን ነው፡፡ ድልን ማስጠበቅ ድል ከማድረግ በላይ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ለአንድ የእግር ኳስ ቡድን ግብ ከማስቆጠር በላይ የማሸነፊያ ነጥቡን አስጠብቆ መውጣቱ እጅግ አድካሚና የበሰለ ታክቲክ የሚጠይቀው ነው፡፡ ያንን ለማድረግ የሚችለው ደግሞ አሥራ አንዱም ተጨዋቾች ‹ግቡ የአጥቂው፣ ድሉ የቡድኑ ነው› ብለው ሲሠሩ ብቻ ነው፡፡ ግብ አግቢው ድሉ የኔ ብቻ ነው ብሎ ካሰበ ኳስ የሚያቀብለው አያገኝም፡፡

እኛ ‹ለውጡ የማን ነው?› እያልን ስንጨቃጨቅ ድል ያደረግናቸው ችግሮች መልሰው እንዳይከቡንና ከፈንጠዝያው ሳንወርድ ወደ ሽንፈቱ ቀለበት እንዳይከቱን ‹መከራው የጋራችን እንደነበረው ሁሉ፣ ድሉም የጋራ፣ የድሉ ፊታውራሪ ጀግኖችም የጋራ፣ የሚመጣውም ለውጥ የጋራ› ብለን ማመን አለብን፡፡ የጎጥ ጀግኖች ዘመን ይብቃ፡፡

Filed in: Amharic