>
4:42 pm - Monday January 18, 1221

ብአዴን ስሙን ሲቀይር… (ዉብሸት ሙላት)

ንቅናቄ ፣ ግንባር፣ ፓርቲ (ድርጅት)?
 
(ብአዴን ስሙን ሲቀይር…)
ዉብሸት ሙላት
የተቃዋሚ (የተፎካካሪ) ፓርቲዎችን ትተን አገሪቱን በክልልም ሆነ በፌደራል ደረጃ እያስተዳሩ ያሉትን ፓርቲዎች አደረጃጀት ስናጤን አንድ ግር የሚል ነገር ማስተዋላችን አይቀርም፡፡ እሱም የተወሰኑት ግንባር (ሕወሃት/TPLF፣ኢሐአዴግ)፣ሌሎቹ ንቅናቄ (ብአዴን፣ደሕዴን፣ጋህዴን) ፣ የተወሰኑት ፓርቲ (አብዴፓ፣ ሶሕዴፓ፣ ቤጉደፓ)፣ቀሪዎቹ ደግሞ ድርጅት (አህዴድ) የሚል ገላጭ ወይም አመላካች መጠቀማቸው ነው፡፡
ሕወሃት (TPLF)አንድ ድርጅት ብቻ ሆኖ ሳለ በግንባርነት መጠራቱ ወይም መመዝገቡ፣ ብአዴን፣ ደሕዴን፣ ጋሕዴን ደግሞ ገዥ ፓርቲዎች ሆነው ሳለ ንቅናቄ የሚል ቅጽል ይዘው መጓዘቸው ብዥታን ሳይፈጥር አይቀርም፡፡ ንቅናቄ፣ግንባር እና ፓርቲ  ወይም ድርጅት ሲባል ምን ማለት ነው? ልዩነታቸው ምንድን ነው?
ንቅናቄ (Movement) 
ንቅናቄዎች አንደኛ፡- በአብዝኃኛው ማኅበራዊ ድርጅቶች ናቸው፡፡ አንድ ግብ አስቀምጠው እሱን ለማሳካት የሚጥሩ ናቸው፡፡ ንቅናቃዌች በግልጽ የተቃዋሚ ፓርቲነት ሚና ባይኖራቸውም ከፖለቲካ ግን ገለልተኛ ላይሆኑ ይችላሉ፤አይደሉምም፡፡  (ስለዚህ ጉዳይ ይህንን ጽሑፍ ይመልከቱ፡፡ Paul G. Lewis (2000) Political Parties in Post-Communist Eastern Europe, London, Rutledge  በታተመው መጽሐፍ ላይ ምእራፍ ሁለትን ልብ ይሏል፡፡ የምእራፉና በሥሩ ያለው ንዑስ ርእስ ይህ ነው፡፡ “Party Origins and Party Development: Parties and Movements in the Founding Elections” ጸሐፊው ከሶቭየት ኅብረትና ከዩጎዝላቪያ መፈራረስ በኋላ ምሥራቅ አውሮፓ ላይ በምን ሁኔታና ምን ምን ዓይነት ድርጅቶች ወደ ፖለቲካ ፓርቲ ተሸጋግረው ምርጫ ውስጥ እንደገቡ ብሎም ሥልጣን እንደያዙ ሰፊ ትንተና አቅርቧል፡፡)
ከላይ በስርዋጽ ከገባው ወደ ዋናው ቁምነገር ስንመለስ ንቅናቄዎች የተቋቋሙበትን ዓላማና ግብ ለማሳካት ሲሉ የሚንቀሳቀሱ ስለሚሆኑ፡፡ ወደ ፓቲነትም ሊቀየሩ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ንቅናቄዎች ሊመደቡ የሚችሉት ከብዙኃን ማኅበራት (Civil Societies/Civic Organizations) ጎራ ነው፡፡
ሁለተኛ፡- በሌላ በኩል ደግሞ የትጥቅ ትግል የመረጡ ድርጅቶችም በንቅናቄ መልክ ይደራጃሉ፡፡ ማስወገድ የሚፈልጉትን የአገዛዝ ሥርዓት እስከሚያስወግዱ ድረስ በዚሁ አኳኋን ይጠራሉ፡፡ ሥልጣን ሲይዙ ግን ወደ ፓርቲ ይቀየራሉ፡፡ ከአደረጃጀት አንጻር ሲታዩም ንቅናቄዎች ላላ ያለ ሞደል ይከተላሉ፡፡ በእርግጥ የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ድርጅቶች በሰላማዊ ትግል ከሚታገል ፓርቲም የበለጠ ጥብቅ ተዋረዳዊ ዲስፕሊን እንደሚከተል ይታወቃል፡፡ (ለዝርዝር ማብራሪያ የሚከተለው መጽሐፍ፣በተለይም የመጀመሪያውን ምእራፍ፣ ይመለከቷል፡፡ Kalowatie Deonandan et al (2007) From Revolutionary Movements to Political Parties : Cases from Latin America and Africa, Palgrave,Macmillan,NewYork.)
 በመሆኑም ንቅናቄዎች የሆነ ግብ ለማሳካት ሲባል የሚቋቋሙ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በአፍሪካም ሆነ በሌላ ክፍለ ዓለም ከቅኝ ግዛት ነጻ ለመውጣት የተቋቋሙ በርካታ ንቅናቄዎች ነበሩ፡፡ ስማቸው ግን በዚያው አልቀጠለም፡፡
በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጁ ቁጥር 573/2000 ላይ ስለንቅናቄ ምንነት አልተገለጸም፡፡ በኢትዮጵያ፣ገዥ ፓርቲም ሆነው ንቅናቄ የሚለውን ስያሜ የያዙ አሉ፡፡ ብአዴን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን ኢሕዴን ሲወርስ ንቅናቄ የሚለውን ግን አልተወም፡፡ ደሕዴንም እንደ ብአዴን ሁሉ ንቅናቄ ነው፡፡
 እዚህ ላይ በምሥረታ ላይ ያለውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብንን) በምሳሌነት ብናነሳ የአማራ ሕዝብን ብሔራዊ ንቃት በመጨመር እንዲደራጅ፣ለመብትና ጥቅሙ ዘብ እንዲቆም ማንቃት እስከሆነ ድረስ ንቅናቃኔ የሚለው ገላጭ ነው፤አብሮ ይሄዳል፡፡ ለምርጫ ሲወዳደር ግን ከንቅናቃኔ ይልቅ ወደ ፓርቲ ቢቀየር ከላይ ከቀረበው ጋር ይስማማል፡፡
ግንባር
ግንባር (Front) ማለት፡- ለጋራ ዓላማ በአንድ አመራር ሥር ተሰባስበው ወይም ተጠቃልለው የሚታገሉ ወይም የሚሠሩ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚመሠርቱት አልያም የሚሰባሰቡበት መድረክ ነው፡፡አባል ድርጅቶች ባንድ ዘላቂ ፕሮግራም የመተሳሰር ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡
‘ግንባር’ የሆነ ግብ ለማሳካት ሲባል ነው የሚፈጠረው፡፡ የግንባር አባል ድርጅቶች በተወሰነ ፕሮግራም ላይ የዓላማ እንድነት ይፈጥሩና በአንድ አመራር ሥር ሆነው ይታገላሉ፡፡ ‘ግንባር’ በመፍጠር የሚታገሉለት ዓላማ ሲሳካ ይፈርሳሉ፡፡ ካልሆነም ወደ ሌላ ቅርጽ ይለወጣሉ፡፡
ስለሆነም ‘ግንባር’ ጊዜያዊ ነው ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በብዙ አገራት እንደተስተዋለው ሕዝባዊ ግንባር በመሆን የተወሰነ ዓላማን ከማሳካትም አልፈው ቀጣይነት እንዲኖረው በማሰብ የተመሠረቱ ድርጅትች አሉ፡፡ አሁንም በብዙ አገራት አሉ፡፡ አንድ የጋራ ዓለማን እስከሚሳኩበት ጊዜ ድረስ ብቻም ይሁን ቀጣይነት ባለው መልኩ ይቋቋሙ ዞሮ ዞሮ ግን ሁለትና እና ከእዚያ በላይ የሆኑ ፓርቲዎችን ወይም ድርጅቶች በሌሉበት ግንባር መሆን አይቻልም፡፡
የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጁ ቁጥር 573/2000ም ስለግንባር ከዚሁ ጋር የተቀራረበና የሚስማማ ትርጓሜ ሰጥቶታል፡፡  አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ራሱን የቻለ ፖለቲካ ፓርቲ ወይም ደግሞ ሁለትና ከእዚያ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅንጅት ወይም በግንባር መልክ ሊመሠርቱትይችላሉ፡፡
‘ቅንጅት’ ና ‘ግንባር’ ሁለትና ከእዚያ በላይ የሆኑ ፓርቲዎችን ይፈልጋል፡፡ በግንባር መልክ ሲደራጁ እያንዳንዱ ፓርቲ የተናጠል ኅልውናው እንደተጠበቀ ይቀጥላል፡፡ ይሁን እንጂ የጋራ ፕሮግራምና አመራርም ይኖራቸዋል፡፡ ‘ቅንጅት’ ሲሆን ለአንድ ጊዜያዊ ዓለማ ስኬት ሲባል የሚቋቋም ነው፡፡ ከዚያም በቅንጅት መልክ የተፈጠረው ድርጅት ይፈርሳል፡፡
 
የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ድርጅት
የፖለቲካ ፓርቲ እና የፖለቲካ ድርጅት ትርጉማቸው አንድ ዓይነት ነው፡፡ ፓርቲ ወይም ድርጅት የሚል ቅጽል ወይም ገላጭ ቢጠቀሙም ትርጓሜው ግን አንድ ነው፡፡  የተወሰኑ አባላት እስካለው፣የፖለቲካ እምቱንና ፍላጎቱን ሕ በሚፈቅደው ማእቀፍ ውስጥ ሆኖ ለማራመድ የተመዘገበ ማኅበራዊ ተቋም ሁሉ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡ ብአዴን ስሙን ሲቀይር ከምርጫ ማውጣት ያለበት “ንቅናቄ” የሚለውን ነው፡፡
Filed in: Amharic