>

የኦሮሞና የአዲስ አበባ ወጣቶች ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ቁርሾ ትታችሁ አትለፉ!!! (ፋሲል የኔአለም)

የኦሮሞና የአዲስ አበባ ወጣቶች ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ቁርሾ ትታችሁ አትለፉ!!!
ፋሲል የኔአለም
በእውቀት የተነጠቀውን ስልጣን በግጭት መልሶ የሚያገኘው  የሚመስለው ህወሃት ፣ ግጭት በተነሳ ቁጥር ስጋ እንዳየ ውሻ ምራቁን ሲያዝረከርክ ስናይ ስለእሱ እኛ እናፍራለን። እንዴው ፖለቲከኞች መስማማት አቅቷቸው በአገሪቱ የስልጣን ክፍተት ቢፈጠር እንኳን፣   ህወሃት ከእንግዲህ ወደ ስልጣን ተመልሶ እንደማይመጣ፣ ተዓምር ተፈጥሮ ቢመጣ እንኳ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለአንድም ቀን እንደማያስደረው በምን በጥብጠን ብንግተው ሊገባው እንደሚችል አላውቅም፡፡ ትናንት 20 ሺ ሰራዊቱን ካምፕ አስገብቶ ከአገር ያባረረውን ኦነግ፣ ፍሪዳ ጥሎ ቢያበላው፣ አገር ላገር ቢያንሸራሽረው፣ የፈለገውን ሜዳሊያ ቢሸልመው፣ በትከሻው ላይ አስቀምጦ እምበር ተጋዳላይን  ቢዘፍንለት፣ ኦነግ የጀርባውን ጠባሳ ይረሳል ብሎ ማሰቡ በራሱ የህወሃትን የአስተሳብ ደረጃ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። እንዲህ በሚያስቡ ሰዎች የሚመራ ድርጅት ስልጣኑን እውቀትና ጥበብ ባላቸው ሰዎች ቢቀማ አይገርምም። ህወሃት ያደገበትንና የኖረበትን ባህሪ በዚህ በፍቅር ዘመን እንኳን ለመተው ተስኖት አሁንም ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት  ቤንዚን ሲያርከፈክፍ ስናይ፣ ህወሃትን ይበልጥ እንድንጠላው ብቻ ሳይሆን፣ ህወሃት ካልጠፋ ሰላምና መረጋጋት እንደማይኖር እንድናምን እያደረገን ነው። በአዲስ አበባ የተፈጠረው አሳዛኝ ድርጊትና የህወሃት ምላሽ ለእነ አብይ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው- ህወሃትን በኪስ ይዞ መዞር ትርፉ መነደፍ ነው።
ለህወሃት ሰዎች የመጨረሻው ምክሬ ይህ ነው፦
 “አርኩም ይሄድና፣ ሶልዲውም ያልቅና
ሰላም ይመጣና፣ ያስተዛዝበናል ይኸ ቀን ያልፍና”
የኦሮሞና የአዲስ አበባ ወጣቶች ደግሞ ከሴራ ፖለቲካ ተጠበቁ። ቤንዚን ከሚያርከፈክፉት ሰዎች እራቁ።  ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ቁርሾ ትታችሁ እንዳታልፉ ሁሉንም በትዕግስት አሳልፉ።
Filed in: Amharic