>

በባንዲራው ጎበዝ! በባንዲራው ጀግና!!! (አሰፋ ሀይሉ)

በባንዲራው  ጎበዝ!   በባንዲራው  ጀግና!!!
አሰፋ ሀይሉ
* ይድረስ ባንዲራህን የማዋረድ ጀብድህን – እንደጀግንነት ለቆጠርክ ኢትዮጵያዊ ወጣት!
۞ ሀገርህን አክብር! ሕዝብህን አክብር! ባንዲራህን አክብረው!
 ۞ ባንዲራህ – መንግሥት ሲበድልህ እሪ የምትልባት – የምትሳደብባት፣ የምትፎክርባት፣ የሀገርህ ዋልታ ናት!
۞  አስታውስ! ለዚህች ባንዲራ – እንዳንተ በንፁህ ወገን ላይ ሣይሆን – በወራሪ ጠላት ላይ – የጀገኑ፣ የተዋደቁ፣ የሞቱ፣ የተነሡ ጀግኖች እንዳሉ!
۞ አክብር ስትጮህ የሚሰማህን – ስትራብ የሚያጎርስህን ህዝብ!
۞ አክብር የሚራራልህን ህዝብ! አክብረው በባንዲራው ሥር ተጠልሎ ስላንተ ጥቃት እርር የሚለውን ሕዝብ!
۞ አክብር ከጉልበተኛ፣ ከቀማኛ፣ ከሽፍታ፣ ከወራሪ የሚጠብቅህን ህዝብና ሀገርህን!
۞ ያዋጣኛል ያልከውን ፖለቲካህን እንዳሻህ አድርገው! ባንዲራህን ግን አክብር!
۞ ባንዲራህን ስታከብር አንተ ትከበራለህ! ሀገርህን ባንዲራህን ስታከብር ነው አንተ የምትከበረው!
۞ ሀገርህ ነው አክብረው! ህዝቦችህ ወገኖችህ ነን አክብረን!
۞ አክብር – ስታከብር ላንተም ለወገኖችህም ክብር ይሆንልሃል!
۞ አክባሪያችን ብሔር አይደለም! አዋራጃችንም ብሔር አይደለም! ሰው ነው!! ሰው ነው ጀግና! ሰው ነው ኮሣሣ!
۞ ሀገሩን ያከበረን ሰው – ባንዲራውን ያከበረን ጀግና – ባንዲራው ያስከብረዋል – ትውልድ ያከብረዋል! እናከብረዋለን!
۞ ራስህን አዋርደህ – የጀግኖቹን የእነ አበበ ቢቂላን ታላቅ የተከበረ መንፈስ አታዋርድ!
۞ ባንዲራህን አዋርደህ – የብዙ ጀግኖችን ዋልታ – የአቧራ ክምር ላይ አትጣል!
۞ አርማህን እንደወደድኽ አድርገው! ባንዲራህን ግን አክብር!
۞ በባንዲራው ስትል እንሰማሀለን! በባንዲራው ስንልህ ስማን!
۞ እናት ኢትዮጵያችን ለሁላችን ትበቃለች! ባንዲራችን እንኳን እኛን መፈጠሪያዋን – አፍሪካን አህጉሩን ያለበሰች ባንዲራ ነች!
۞ የሁላችን እናት እምዬ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
۞ አረንጓዴ! ቢጫ! ቀይ! የክብር ባንዲራችን – ለዘለዓለም ከፍ ብላ ስትውለበለብ ትኑር!
۞ ኢትዮጵያችን – በልጆቿ የተባበረ ክንድ – ለዘለዓለም ፀንታ ትኑር!
۞ ባንዲራችን – የልጆቿ የክብር ሰንደቅ ሆና – ለዘለዓለም ባለም ላይ ትንቦግቦግ!
۞ እምዬ ኢትዮጵያ – ባንዲራዋን በክብር የሚያነሱላትን ልጆች – መንታ መንታውን ይስጣት!!
۞ እምዬ እናት ሀገር – ባንዲራዋን በውርደት የሚያራክሱ ልጆቿን ከምታይ – የወላድ መካን ያድርጋት!
۞ ሀገሩን ያላከበረ – ባንዲራውን ያላከበረ – ህዝቡን ወገኑን ያላከበረ – ወገናችን አይደለም!
۞ የብዙሃን እናት – እምዬ ኢትዮጵያ – በክብር ባንዲራዋ ተውባ – በልጆቿ ፍቅር ኅብረት ደምቃ – ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic