>
5:13 pm - Tuesday April 20, 9097

ለእነ ኮሌኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ይቅርታ ወይም ምህረት ማድረግ አይቻልምን? (ዉብሸት ሙላት)

ለእነ ኮሌኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ይቅርታ ወይም ምህረት ማድረግ አይቻልምን?
ዉብሸት ሙላት
በደርግ ዘመን የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኮሌኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በፈጸሙት የዘር ማጥፋት ወንጀል በሌሉበት የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡ እንደሳቸው ሁሉ በሌሉበት የተፈረደባቸው በጣሊያን ኤምባሲ ዉሥጥ የተጠለሉ የደርግ ባለሥልጣናት መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡
 ብዙ ባለሥልጣናት ቅጣታቸውን ፈጽመው በአመክሮ ቢለቀቁም በሌሉበት የተፈረደባቸው ግን ቅጣታቸውን አለመፈጸማቸው ይታወቃል፡፡ ባለመፈጸማቸውም አሁንም ያው ፍርደኛ ሆነው መንግሥቱ ኃይለማርያምም እዚያው ዚምባብዌ እነ ብርሃኑ ባይህም ጣሊያን ኤምባሲ ዉስጥ በጥገኝነት ኑሯቸውን በመግፋት ላይ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አሕመድ አገሪቱ መሪ ከሆኑ በኋላ መንግሥቱ ኃይለማርያምንም ይሁን እነ ብርሃኑ ባይህን በይቅርታ ከዚምባብዌ ቢመጡ ከጣሊያን ኤምባሲም ቢወጡ ፍላጎታቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ ደግሞ ጥፋተኛ የተባሉበት ወንጀል ዓይነት የዘር ማጥፋት በመሆኑ በዚህ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሰው ይቅርታም ይሁን ምህረት እንደማይደረግለት ሕገ መንግሥቱ ላይ ስለተገለጸ የሕገ መንግሥት ጉዳይ እንደሆነ የሚመስል ይዘት ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ መንግሥቱ ኃይለማርያምና እነ ብርሃኑ ባይህና ሀዲስ ተድላን ይቅርታ ወይም ምህረት ማድረግ መቻል አለመቻሉን   መፈተሸ ነው፡፡ ፍተሻ የሚደረገውም ከሕገ መንግሥቱና ከሌሎች ሕግጋት አንጻር ነው፡፡ ስለሆነም መንግሥቱ ኃይለማርያም ወደ ኢትዮጵያ ይመለሱ ወይም አይመለሱ፣እነ ብርሃኑ ባይህ ከኢምባሲ መውጣት አለባቸው ወይም የለባቸው የሚል ሙግት ለማቅረብ አይደለም፡፡
የእነ መንግሥቱ ጉዳይ በምህረት ወይስ በይቅርታ?
ምሕረት የሚሰጠው ላልተከሰሱና በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ላልተባሉ ግለሰቦች ነው፡፡ የተፈረደባቸው ከሆነ ግን ምሕረት ሳይሆን ይቅርታ ነው የሚሰጠው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ምሕረቱ በወንጀል የተፈረደባቸውንም ጭምር ሊያካተት ይችላል፡፡ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 230 ላይም የተገለጸው በዚሁ መርሕ ቅኝት ነው፡፡ መርሑን ንዑስ ቁጥር 1 ላይ ሲያስቀምጥ “ለአንድ ዓይነት ወንጀሎች ወይም በአንድ ደረጃ ለሚገኙ ወንጀለኞች”  በማለት ነው፡፡
ይህ አገላለጽ የሚያመለክተው ምሕረት የሚደረገው ክስ ያልቀረበባቸውን የሆነ የወንጀል  ዓይነት ፈጽመዋል የተባሉን እንጂ የተፈረደባቸውን አይደለም፡፡ ይህንን ሐሳብ የሚያጠናክረው ስለይቅርታ የሚደነግገው አንቀጽ 229 ነው፡፡ አንቀጹ “በፍርድ የተወሰነ ቅጣት ሥልጣን በተሰጠው አካል  ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በይቅርታ ሊቀር … ይችላል” በማለት ያስቀምጣል፡፡ ይቅርታ ለፍርደኞች የሚሰጥ መሆኑን በግልጽ ሲያሳይ ምሕረት ግን በዚህ መልኩ አልተገለጸም፡፡
ይሁን እንጂ፣ አንዳንዴ ደግሞ የተፈረደባቸውንም ሊጨምር እንደሚችል አንቀጽ 230 ንዑስ ቁጥር 2 ላይ ከተቀመጠው መረዳት የሚቻለው “ምሕረት በሚሰጥበት ጉዳይ ቅጣት ተወስኖ እንደሆነ” በማለት የተገለጸው አንዳንድ ጊዜ ፍርደኛንም ሊያካትት መቻሉን ነው፡፡
ይህ የሚሆነውም ከተፈረደባቸው በኋላ በምሕረት ለመልቀቅ ሳይሆን ምሕረት በተደረገበት የወንጀል ጉዳይ ላይ ምሕረት ከመደረጉ በፊት ቅጣት የተላለፈባቸው ሰዎች ካሉ እነሱን ላለመለየት ነው፡፡ ልዩነት ማድረጉ የአድልኦ ድርጊት ስለሚሆን ነው፡፡
በመሆኑም፣ ጥፋተኛ ለተባለው ሰው በመርሕ ደረጃ ይቅርታ እንጂ ምሕረት አይደረግም፡፡ በልዩ ሁኔታ ግን ምሕረት በተሰጠበት ጉዳይ ጥፋተኛ የተባሉ  ካሉ እንደ ይቅርታ ሁሉ የተፈረደባቸው ሰዎችንም ይጨምራል፡፡ በመርህ ደረጃ በእነመንግሥቱ ጉዳይ ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደባቸው በመሆኑ ምህረት አይመስልም፡፡
በሌላ አገላለጽ እነ መንግሥቱ የተፈረደባቸው ስለሆነ ከምሕረት ጽንሰ ሐሳብ ጋር አብሮ አይሔድም፡፡ ለይቅርታ ደግሞ ጥፋተኛ የተባለው ሰው ቅጣቱን በመፈጸም ላይ መሆን አለበት፡፡ በጥፋቱም መጸጸት አለበት፡፡ከዚህ አንጻር ሲታይ እነመንግሥቱ ጥፋተኛ ቢባሉም እንደፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅጣቱን በመፈጸም ላይ አይደሉም፡፡ ስለሆነም በፈጸሙት ወንጀል አልተጸጸቱም፡፡ ለይቅርታ ፍርደኛ የሆነ ሰው መጸጸቱን መግልጽ ይጠበቅበታል፡፡
ምሕረት፣ አንዲት አገር በሉዓላዊነት ሥልጣኗ ልታደርገው የምትችለውም ድርጊት ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ አንዳንድ የወንጀል ድርጊቶች ላይ ምሕረት ማድረግ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት በማጣቱ፣ በሰብኣዊነት ላይ የተፈጸሙ ዘግናኝ ወንጀሎችን ምሕረት ማድረግ እየቀረ መጥቷል፡፡ ጉዳዩም በአንዲት ሉዓላዊት አገር ሥልጣን ሥር መወሰኑ ቀርቶ ዓለም አቀፋዊ ሆኗል፡፡ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ምሕረት የማይሰጥባቸውን የወንጀል ዓይነቶች ለይተው አስቀምጠዋል፡፡
እንግዲህ ከላይ እንዳየነው በመርህ ደረጃ እነመንግሥቱ ጉዳይ በምህረትም በይቅርታም የሚሸፈን አይመስልም፡፡ ይቅርታም ለማድረግ ምህረትም ለመስጠት ትንሽ ግራ የሚያጋባ ከአጀን መጀን የወጣ ጉዳይ ይመስላል፡፡ ይህንን መደምደሚያ እውነት ነው ብሎ ከመቀበል አስቀድሞ ለሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
የመጀመሪያው እነመንግሥቱ ጥፋተኛ የተባሉበት ወንጀል በራሱ ምህረት ወይም ይቅርታ ያሰጣልን? ምህረት ወይም ይቅርታ ማሰጠት ወይም አለማሰጠቱ የሚወሰነው በየትኛው ሕግ ነው የሚሉት ናቸው፡፡ ሁለቱንም ጥያቄዎች ተራ በተራ እንመልከታቸው፡፡
የዘር ማጥፋት ወንጀል ይቅርታና ምሕረት ባይኖረውም
በመሆኑም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 1 ኢትዮጵያ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣በጦርነት ጊዜ በቆሰሉና በተማረኩ ወታደሮች፣ በሲቪል ሕዝብና በሲቪል ተቋሞች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚደነግጉት የጄነቫ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ፕሮቶኮሎችና ሌሎች ስምምነቶች እና በኢትዮጵያ ሕግ በወንጀልነት የተደነገጉት የወንጀል ሕጉ የይርጋ የጊዜ ገደብ የማይገድባቸውና ማንኛውም አካል በምህረት ወይም በይቅርታ ሊያልፏቸው የማይችሉ እንደሆኑ ደንግጓል፡፡
እነዚህም  በሰብኣዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች (Crimes Against Humanity)፣  የሰው ዘር የማጥፋት ወንጀል (Genocide)፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ መውሰድ/ (Summary Execution)፣ በአስገዳጅ ሁኔታ ሰውን መሰወር (Forced Disappearance) እና ኢሰብዓዊ የሆኑ የማሰቃየትና የድብደባ ድርጊቶች (Torture) ተብለው የተጠቀሱትን የወንጀል ድርጊቶችን ፈጽመው የሚገኙ ሰዎች ላይ የሚቀርብ የወንጀል ክስ በማናቸውም አካል ውሳኔ በምሕረት ወይም በይቅርታ አይታለፉም፡፡ በይርጋም አይታገዱም፡፡  ሕገ መንግሥቱ በዚህ መልኩ በመደንገግ ለእነዚህ ወንጀሎች ከሌሎች ወንጀሎች በተለየ ሁኔታ ጥብቅ የወንጀል ተጠያቂነትን በሚያስከትል አኳኋን ደንግጓል፡፡
ከዚህ አንፃር በወንጀል ሕግ አማካኝነት ስለ ወንጀል ክስ የይርጋ ጊዜ ገደብ፣ ስለ ምሕረትና ይቅርታ የተደነገጉት ድንጋጌዎችና ሕገ መንግሥቱ ጸድቆ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የወጡና የሚወጡ የይቅርታና የምህረት አዋጆችና ደንቦች ከእነዚህ ወንጀሎች አንዱን ፈጽሞ በተገኘው ሰው ላይ ተፈጻሚነት የማይኖራቸው መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
የወንጀል የፍትሕ ስርዓቱ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሕግጋትና በሕገ መንግሥቱ ጥብቅ ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ መሆናቸው የተደነገጉት ወንጀሎች ከመፈጸማቸው በፊት ለመከላከል ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠበቅባቸው ዘንድ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ የወንጀል ድርጊቶች ሲፈጸሙ ሕገ መንግሥቱ የደነገገውን ጥብቅ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥተው ተግባርና ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡
ስለሆነም እነ መንግሥቱ ኃይለማርያም ጥፋተኛ የተባሉባቸው ክሶች በምሕረትም አይታለፉም፡፡ በይቅርታም ቅጣቱ ቀሪ አይሆንም፡፡ ነገር ግን ምሕረት እንደማያሰጡም ይቅርታም እንደሌላቸው የሚገልጽ ሕግ ወንጀሉ በተፈጸመበት ወቅት መኖር አለበት፡፡
እነመንግሥቱ ኃይለማርያም ወንጀል በፈጸሙበት ጊዜ ሥራ ላይ የነበረው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስለይቅርታና ምህረት ሲደነግግ ይቅርታ የሌላቸውና ምህረት የማያሰጡ ወንጀሎችን አልዘረዘረም፡፡ እንዳሉም አላመለከተም፡፡ በመሆኑም ወንጀሉ ሲፈጸም ይቅርታ አልባና ምህረት የለሸ ወንጀሎች እንዳሉ በሕግ እስካልተገለጸ ድረስ ለሁሉም ዓይነት ወንጀሎች ምህረት ማድረግም ይቅርታ መሠጠትም ይቻላል ማለት ነው፡፡
ምህረትና ይቅርታን ለዘር ማጥፋት ወንጀል የነፈገው አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥትና ዓለም አቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ናቸው፡፡ ስምምነቱንም ኢትዮጵያ ተቀብላ ሥራ ላይ የዋለው ደርግ ከወደቀ በኋላ ከመስከረም 1 ቀን 1986 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡
የወንጀል ሕግ ወደ ኋላላ ተመልሶ የማይሠራ ስለመሆኑ፤
በወንጀል ሕግ አስተምህሮ ከሚታወቁት ዋነኛ መርሆች አንዱ ከሕጋዊነት መርህ ነው፡፡ በዚህ መርህ ሥር ከሚጠቃለሉት አንዱ ወይም ተያያዥነት ያለው ሌላው መርህ የወንጀል ሕግ ወደ ኋላ ተመልሶ ሕጉ ከመውጣቱና ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ሊሠራ አይገባውም የሚለው ነው፡፡ ይኸ መርህ የወንጀል ሕግ በመሠረቱ ሕግ ሆኖ ከወጣ በኋላ በሚፈጽሙ ድርጊቶች ላይ ብቻ ተጠቃሽና ተፈፃሚ ሊሆን እንደሚገባ የሚገልጽ ነው፡፡
የሕጋዊነት መርህ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሊሆንና ተፈጻሚነት ሊኖረው የሚችለው መሠረታዊ የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች ከመውጣታቸው በፊት በተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ ተፈፃሚ እንዳይሆኑ የሚከለክል የሕግ ገደብ ነው፡፡
የዚህ መርህ ይዘትና ተግባራዊ ተፈጻሚነት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ሥር እንደ አንድ መርህ ተደንግጎ እናገኛዋለን፡፡ የወንጀል ሕጉ መርህ አንድ የወንጀል ድርጊት የፈጸመ ሰው ወንጀሉን በፈጸመበት ጊዜ የነበረው የወንጀል ሕግ ከሚደነግገው ቅጣት የከበደ ቅጣት የሚደነግግ አዲስ የወንጀል ሕግ ወይም ሌላ አዋጅ ወይም ደንብ ወጥቶ ሥራ ላይ በዋለበት ጊዜ ተከስሶ ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝም እንኳ ወንጀሉን በፈጸመበት ጊዜ ሥራ ላይ የነበረው የወንጀል ሕግ ከሚደነግገው ቅጣት በላይ ሊቀጣ እንደማይገባው በመደንገግ የመንግሥትን ሥልጣን የሚገድብ ነው፡፡
በመጀመሪያው ንዑስ አንቀጽ ላይ  “እንዲሁም ወንጀሉ በተፈጸመበት ጊዜ ለወንጀሉ ተፈጻሚ ከነበረው ቅጣት ጣሪያ በላይ የከበደ ቅጣት በማንኛውም ሰው ላይ አይወስንም” በሚል አገላለጽ የወንጀል ሕግ ወደኋላ ተመልሶ የማይሥራ መሆኑን አሻሚነት በሌለው ሁኔታ ገልጾታል፡፡
የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ በመጀመሪያ ህግ አውጭው የወንጀል ኃላፊነትና ቅጣት የሚያስከትሉ አዋጆችን ሲያውጅ ሕጉ ከመጽደቁ በፊት ለተፈጸሙ ድርጊቶች ተፈጻሚነት ያላቸው መሆኑን በመደንገግ አዋጆቹን ከመውጣታቸው በፊት ለተፈጸሙ ጉዳዮች ተፈጻሚ ማድረግ የማይቻል መሆኑን ግልፅ የሚያደርግና የሕግ አውጭውን ሥልጣን የሚገደብ ድንጋጌ ነው፡፡
ነገሩ በሕግ አውጭው ብቻ ሳይወሰን የወንጀል ክስ የማቅረብና የመሟገት እንዲሁም የፍርድ ሂደትን የመስማት፣ ፍርድ የመስጠትና የመሳሰሉት ስልጣን ያላቸው የፍትህ አካላት በልዩ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር አንድ የወንጀል ሕግ ከመውጣቱ በፊት በተፈፀሙ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን መጥቀስና ውሳኔ መስጠት የማይችሉ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው፡፡
 የወንጀል ሕግ ወደ ኋላ ተመልሶ መሥራት የለበትም የሚለው መሠረታዊ የወንጀል ሕግ መርህ ዓቢይ ግቡ የሕጋዊነት መርህ እንዲከበር ማድረግና ተከሳሾች ወንጀሉን ከፈጸሙ በኋላ በሚወጡ የሕግ ማዕቀፎች በሚደነገጉ ከባድ ቅጣቶች እንዳይቀጡ መከላከልና መጠበቅ ነው፡፡
ስለዚህ መርሁ የተከሳሾችን መብትና ጥቅም ለማስከበርና የመንግሥትን ሥልጣን ለመገደብ ታስቦ የተፀነሰና በብዙ አገሮች የወንጀል ሕግ ማዕቀፎችም ተካትቶ ሥራ ላይ የዋለና በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋት በተለይም በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሁሉ አቀፍ መግለጫና በዓለም አቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ላይ ጭምር የተደነገገ መርህ ነው፡፡ በመሆኑም እነመንግሥቱ ኃይለማርያም ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡
አሁን በሥራ ላይ ካለው ሕገ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ሕግጋት አንጻር የሚጠቅማቸው ሳይሆን የሚጎዳቸው ነው፡፡ የሚጎዳቸው ከሆነ ደግሞ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ የሚፈጸመው ወይም እነሱን በሚመለከት ተፈጻሚነት የሚኖረው በወቅቱ የነበሩት ሕግጋት ናቸው፡፡ በወቅቱ የነበሩት ሕግጋት ይቅርታና ምህረትን የማያሰጡ ወንጀሎችን አልያዙም፡፡ ስለሆነም እነመንግሥቱን አሁን ባሉት ሕግጋት ሳይሆን በቀድሞው ሕግ ይቅርታም ይሁን ምህረት ማድረግ ይቻላል፡፡
የበለጠ ለማብራራት ያህል የወንጀል ሕግ ወደ ኋላ ተመልሶ አይሠራም የሚለው መርህ ግብና ሊጠብቀው እና ሊከላከለው ከሚገባው መብትና ጥቅም በመነሳት መርሁ ተፈጻሚ የማይሆንበት አንድ ልዩ ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ይኸውም የወንጀል ሕግ ወደ ኋላ ተመልሶ መሥራት የለበትም የሚለው ጠቅላላ መርህ እንደተጠበቀ ሆኖ መርሁ ተፈጻሚ የማይሆንበት ልዩ ሁኔታ የተከሳሹን መብትና ጥቅም ማዕከል ያደረገ መሆኑ ነው፡፡
ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ የወጣ ሕግ ለተከሳሹ ጠቀሚ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ የወጣው ወንጀል ሕግ የሚደነግገው ቅጣት ዝቅተኛ ከሆነ ፍርድ ቤቱ ለተከሳሹ የሚጠቅመውን እና ዝቅተኛ ቅጣት የሚያስከትለውን ሕግ ተፈጻሚ የማድረግ ግዴታና ኃላፊነት ያለበት መሆኑን የሚደነግግ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የወንጀል ህጉ አንቀፅ 6 የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 22 ንዑስ አንቀፅ 2 ተፈፃሚነት የወንጀል ህጉ እንዲፀና ከተደረገ በኋላ አድራጊው የወንጀል ሕጉ ከመውጣቱ በፊት ላደረገው ወንጀል ሲፈረድበት ወንጀሉን በፈፀመበት ጊዜ ሥራ ላይ ከነበረው ሕግ ይልቅ አዲሱ የወንጀል ሕግ ቅጣት የሚያቀልለት ሲሆን በአዲሱ የወንጀል ህግ የተመለከተው ቅጣት ይፈፀምበታል፡፡
ፍርድ ቤቱ ይኽ ሕግ የተሻለ መሆኑን የሚወስነው በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ አግባብነት ያላቸውን የሕግ ድንጋጌዎች በመመዘንና በውል በመመርመር ነው በማለትም በግልጽ ደንግጓል፡፡ በእነመንግሥቱ ስንመለስ ምንም እንኳን የፍርድ ቤት ጉዳይ ባይሆንም በአስፈጻሚው ወይም በሕግ አውጭውም ቢሆን መርሁ ተመሳሳይ ነው፡፡ በፍርድ ቤት ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም ዘንድ ተፈጻሚነት አለው፡፡
ለማጠቃለል ያህል እነመንግሥቱን በሚመለከት ጥፋተኛ የተባሉበት ወንጀል የተፈጸመው አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ከመውጣቱም ዓለም አቀፉን የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ከመቀበላችን በፊት በመሆኑ እንዲሁም በወቅቱ ምህረትና ይቅርታ እንደሌላቸው የሚገልጽ ሕግ ስለሌለ ይቅርታ ወይም ምህረት ማድረግ ይቻላል፡፡
አስቸጋሪው ነገር ምህረት እንዳይደረግላቸው ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ ይቅርታ እንዳይባሉ የተፈረደባቸውን እየፈጸሙ አይደለም፤መጸጸታቸውንም በመግለጽ ይቅርታ የሚጠይቁበት አሠራርን የሚፈቅድ ሕግ አለመኖሩ ነው፡፡ አንድም እራሳቸውን አሳልፈው በመሥጠት እስረኛ በመሆን ይቅርታ መጠየቅ (ነገሩ የይስሙላ ይሆናል እንጂ)፤ አንድም ፓርላማው ሕግ በማውጣት ለጉዳዩ እልባት መስጠት መቋጨት ነው፡፡ እነሱን ብቻ የሚመለት አዋጅ በማውጣት ለጉዳዩ የመጨረሻ ውሳኔ መሥጠትን የሚከለክል ሕግ የለም፡፡
መልካም አዲስ ዓመት!
Filed in: Amharic