>
5:14 pm - Friday April 20, 8181

ግልፅ ደብዳቤ ለኦሮምያ ክልል ፕሬዝዳንት  አቶ ለማ መገርሳ  (መስዑድ ሙስጠፋ)

ግልፅ ደብዳቤ ለኦሮምያ ክልል ፕሬዝዳንት  አቶ ለማ መገርሳ 
መስዑድ ሙስጠፋ
 
ዜጎች ተወልደው ባደጉበት ቦታ ሰፋሪ እና ” የሰፋሪ ልጆች”፤ “ወራሪዎች” እየተባሉ ሲሸማቀቁ እና ለጥቃት እንዲጋለጡ ሲሰራ የነበረ ሴራ ነው ዛሬ በተግባር የተገለጸው
<<የተጎጀዎችን በደል፤ የደረሰባቸውን ነውረኛ ግፍ በአካል ተገኝተው እንዲመለከቱ እና ከተበዳዮች ጎን እንዲቆሙ በአክብሮት እጠይቆታለው፡፡>>
ይህንን ግልፅ ደብዳቤ የምፅፈው በእርሶ ላይ ካለኝ ከፍተኛ እምነት እና ለእውነት እንደሚቆሙ ስለማምንቦት ነው፡፡ ክቡርነቶ እንደሚያውቁት ከትላንት ጀምሮ በቡራዩ ፤በአስኮ ፤በአሸዋ ሜዳ እና በአዲስ አበባ አጎራባች በሆኑ ኦሮምያ ከተሞች ላይ ዜጎች በማንነታቸው ፡ ኦሮምኛ ባለመናገራቸው ምክንያት በፍጹም አረመኔያዊት እና በድንጋይ ዘመን እንኳን ይፈፀማል በማይባል ጭካኔ  የዶረዜ፤ የጉራጌ፤ የስልጤ እና የሌሎች ብሄር ተወላጆች በዘር ጥላቻ በሰከሩ መንጋዎች ባደባባይ በሚስማር ገላቸው ተተልትሏል፤ እንደእባብ ተቀጥቅጠዋል፤ንብረታቸው ወድሞባቸዋል፤ በሴት አህቶቻችን ላይ ፍፁም ነውረኛ ድርጊት ተፈፅሞባቸዋል፡፡
ይህ ነውረኛ ተግባር መፈፀሙን ሲሰሙ እንደሚያዝኑ፤ እንደሚበሳጩ እና ልቦ እንደሚሰበር እገምታለው፡፡ ይህ ድርጊት እንዲፈፀም ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በተቀናጀ መልኩ ቅስቀሳ ሲደረግ ነበር፡፡ ዜጎች ተወልደው ባደጉበት ቦታ ሰፋሪ እና የሰፋሪ ልጆች፤ ወራሪዎች እተባሉ ሲሸማቀቁ እና ለጥቃት እንዲጋለጡ ሲሰራ ነበር፡፡ አሁንእተፈፀመ ያለው አረመኔያዊ ድርጊት እርሶ በሚያስተዳድሩት ክልል መፈፀሙ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ለእርሶ ከሚሰጠው ከፍተኛ ቦታ የተነሳ ልባችን ተሰብሯል፤ አዝነናልም፡፡
ድርጊቱን ለመቆጣጠር የኦሮምያ ፖሊስ ያሳየውን ፍጹም ቸልተኝነት እና ጥቃቱን ያደረሱትን የመንጋ ቡድኖች በህግ ጥላ ስር ለማዋል ያሳውን  ቸልተኝነት በጥልቀት እንደሚመረምሩት እና በሃገሪቱ በሚተላለፉ ሚድያዎች በግልፅ የሚደረገውን ለዘር ጥቃት የሚያነሳሳ ቅስቀሳ የክልሎ መንግስ እውቅና እንደማይሰጠው በአደባባይ እንዲያረጋግጡልኝ እጠይቃለው፡፡
የተጎጀዎችን በደል፤ የደረሰባቸውን ነውረኛ ግፍ በአካል ተገኝተው እንዲመለከቱ እና ከተበዳዮች ጎን እንዲቆሙ በአክብሮት እጠይቆታለው፡፡
Filed in: Amharic