አንዋር አንዋር
ማታ ሰልፍ እና የታክሲ አድማ እየተባለ ፌስቡክ ላይ ሲሰራጭ፣ ሰልፉን መገደብ ባይቻልም የታክሲው አድማ ግን መደረግ እንደሌለበት ፅፌ ነበር። ሆኖም ሰው ስሜቱ ስለተነካ የሚመራውም ስለሌለ በስሜቱ ተነሳስቶ ሰልፍ እንደሚወጣ ጠብቄ ነበር። ጠዋት ከቤቴ ስወጣ ሰልፍ ይጀመራል ብዪ ግን አልገመትኩም ነበር። ሆኖም ገና አንዋር መስጂድ ስደርስ ጎርፍ የሆነ ህዝብ መፈክር እያሰማ ከወደ አውቶብስ ተራ ሲመጣ ተመለከትኩ፣ በቃ ቁር መንገድ እቀምሳለው ብዪ ሰልፉን ተቀላቀልኩ፣ ሰው እራሱን እያሰተባበረ፣ እራሱ ሰላሙን እያስከበረ፣ እራሱን እየመራ ጉዞ መዘጋጃ አርጎ ወደ ጊዮርጊስ ተጓዘ።
በየመንገዱ የሚገኙ ፖሊሶች እንደማንኛውም ሰው ከማየት ውጭ ምንም አይተናኮሉም ነበር፣ ከዛም በፒያሳ አርገን ቸርቸርን ተያያዝነው፣ አንዳንድ ሰው በመሃል የተከፈቱ ሱቆችን ሲያይ ዝጉ! እያለ ሲጮህ ከመሃል የወጡ ወጣቶች ነበር ለማረጋጋት የምንሞክረው። ወጣቱ እርስ በእርሱ መደማጡ ያስደስት ነበር። ፖሊስም ሆነ ፌደራል በህዝቡ መሃል እያቆራረጡ በመኪናቸው ሲያልፉ ወጣቱ ”ፌደራል እኛ ነው!” የሚል መፈክር ያሰማ ነበር። እነሱም በፈገግታ ነበር የሚያልፉት፣ በዚህ አይነተ ሆኔታ ቸርቸርን ጨርሰን EBC ህንፃ ጋር ደረስን። ፊት ለፊት አድማ በታኝ ፖሊሶች ቆመዋል። ሰው ከእነሱ ጋር እንዳይጋጭ እዛው የነበርን ወጣቶች እጅ ለእጅ ተያይዘን ሰው ወደ አምባሳደር አቅጣጫ እንዲሄድ አደረግነው። ወደ እዛ አቅጣጫ መስመር መያዙን ስናረጋግጥ ወደ ሰልፉ ገባን።