>

ይህንንም እውነታ ተጋፈጡት!!! (አቡበከር አህመድ)

ይህንንም እውነታ ተጋፈጡት!!!
አቡበከር አህመድ
ማንኛውም የማህበራዊም ይሁን የብሄርተኝነት ንቅናቄ ከእንቅስቃሴው ውጪ ባሉ አካላቶች ላይ በጥርጣሬ መታየት የተለመደና የሚጠበቅ ነው ። እንደ አገራችን የሚቃረኑ የፖለቲካ ህልዩት በበዛበትና የተለያየ ተቃራኒ ፍላጎቶች በሚናፀባረቁበት ማህበረሰብ ደግሞ ገዝፎ መታየቱ በጣም የሚጠበቅ ነው ።
የኦሮሞ ብሄርተኝነት ንቅናቄ ከብሄሩ ተወላጆች ውጪ ባሉ ኢትዮጵያዊያን ለረዥም ግዜ የተሳለበት አሉታዊ የሆነን ምስል የኦሮሞ ኤሊት የማያውቀው ጉዳይ አይደለም። ይህ አሉታዊ ምስል በተገቢው ሁኔታ ሳይቀረፍ የኦሮሞ ህዝብ የአገሪቱ የስልጣን ማማ ላይ ወጥቷል። የኦሮሞ ኤሊቶችና ፖለቲከኞች በዚህ ወቅት መስራት ከሚገባው ስራዎች ውስጥ አንዱ የነበረውን “የኦሮሞ ወደ ስልጣን መውጣት ስጋት አይደለም ። እንዲያውም ከፍተኛ አገራዊ ጥሩ አጋጣሚ ነው ” የሚለው ላይ ነበር ። ይህን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በተግባር (እደግመዋለሁ በተግባር) ማሳየት አለመጀመራቸው በከፍተኛ ፍጥነት  ከብሄሩ ተወላጆች ውጪ ለኦሮሞ ብሄርተኝነት መልካም እይታ የነበረንን ሳይቀር አመለካከታችንን ደግመን እንድናስብ የሚያደርግ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ናቸው ።
የድምፃችን ይሰማ እንቅስቃሴ በሚጀመርበት ወቅቱ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የሚሳልበትን የተጠርጣሪነት አመለካከት መግፈፍ ላይ ያተኮረን ስራ መስራት የህልውና ጉዳይ እንደሆነ አምኖ ተንቀሳቅሷል። በዚህም ምክንያት ብዙ የአገሪቷንም ይሁን የውጪ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብን ስጋት መግፈፍ ብቻ ሳይሆን አጋሩም አድርጎ አልፏል። ይህን እንቅስቃሴ በቅርብ የሚያውቁ የኦሮሞ ብሄርተኝነት አራማጆች ግን ከድምፃችን ይሰማ በላይ ትልቅ ጥንቃቄን የሚፈልገውን አገራዊ ሃላፊነታቸውን አለመወጣታቸው አስገራሚ ሆኗል።የኦሮሞ ብሄርተኝነት ላይ ለሚነሱ ትችቶች ሁሉ ኦሮሞ ፎቢያነት እንደሆነ ማሰብ ከስህተታችሁ ላለመታረም ትልቅ እክል እንዳይሆንባችሁ እሰጋለሁ።
የዚህ መልስ ንግግር ሳይሆን የተግባር ምላሽ ነው የሚያስፈልገው ። የኦሮሚያ ክልል የሌሎች ብሔረሰብ አባላት አለምንም ስጋት ሰርተው የሚኖሩባት ፣ አግብተው የሚወልዱባት ፣ በሰላም ተኝተው የሚያድሩባት እንዲሁም ልጆቻቸውን ት/ት ቤት ልከው ያለሃሳብ የሚቀመጡባት ምድር ስታደርጉ ብቻ ነው ።
Filed in: Amharic