>
4:50 pm - Sunday August 7, 2022

ከበረሃው  የሚነፍስ የጥበብ  እሥትንፋስ …!! (አሰፋ ሀይሉ)

ከበረሃው  ሚነፍስ የጥበብ  እሥትንፋስ …!!
አሰፋ ሀይሉ
«ከአዲስ አበባ አንድ ሺህ ኪሎሜትሮችን በደጋ በቆላ አቆራርጬ.. ‹‹ለምለሚቱ›› የሚል ቅፅል በስሟ ላይ በተቀጠለላት — እና የሚያውቃት በሚያውቃት — የማያውቃትም በሚያውቃት — አንዲት የምወዳት ኢትዮጵያዊት ከተማ ላይ፤ በአንድ የኢጣልያ ከተማ ስም በያዘ ሸግዬ ሆቴል፤ በሁለተኛው ፎቅ የበረንዳ ሠገነት ላይ.. ለበረሃው ንፋስ የሚስማማ.. የሐረሩ አጎቴ ሥጦታ የሆነችውን.. ቡራቡሬ ሀገርኛ ሽርጤን በወገቤ አገልድሜ.. ይኸው … ከወዳጄ ጋር በተጓዝን ቁጥር… ከጓዛችን ፈፅሞ በማንነጥላት… እና ‹‹እናት›› የሚል ስም ባወጣንላት… ሁነኛ ያገርቤት የሰሌን ምንጣፍ ላይ….  ጋለል-ዘንበል ብዬ … የአልጋ ትራሴን ከመኝታዬ ወደሰሌኔ አምጥቼ… ግራ ክንዴን ደገፍ አድርጌ…. ተቀምጫለሁ፡፡
«ʿበቀኝ እጄ… ዱልዱም እርሳሴን እያሻሸሁ.. እንደ ሰማዩ ወከክ ብሎ በደረቅ ፈገግታ ከሚያዋዛኝ ባዶ ወረቀቴ ጋር ተፋጥጫለሁ፡፡ የዘንባባው አረንጓዴ ቅጠሎችና… ቢጫ ፍሬዎች… ደግሞ እኔ ላይ በውበት በግርማ ተሞልተው ጉራቸውን ይነሰነሱብኛል፡፡ ቀይ ቆርኪ ያለውን ኮካዬን ከፍቼ ተጎነጨሁ፡፡ ቃጠሎዬ ቢበርድ ብዬ፡፡ አዎ፡፡ ነፋስ አለ፡፡ ግን ሕይወት የለም፡፡ ፀጥ፡፡ ረጭ፡፡ ዝም፡፡ ቁዝም፡፡ እንዴ!!? ኧረ ወጊድ!!?! ህይወትማ አለ፡፡ ግን ደንዝዤያለሁ፡፡ ማለት ነው፡፡ ደስታማ አለ፡፡ ግን ተክዤያለሁ ማለት ነው፡፡ እንደ ተከዜ፡፡… እንደ አባይ፡፡ እንደ አትባራ፡፡ እንደ ቦርከና፡፡ እንደ…. እንደ ትካዜ እንደራሱ፡፡ʾ
«የበረሃው ንፋስ «የምን ትካዜ..?!» እያለ በበረሃ.. በጠል.. በቋጥኝ ሳይበገር ያለማቋረጥ ከሚምዘገዘገው የዘመን ባተሌ ተጓዥ.. ከተከዜ ወንዝ.. ሽቅብ እየተነሳ በላዬ እያፏጫ በሞቃት የንፋስ አርጩሜው ፌቴን ይገርፈኛል፡፡ «ለምን አየኸኝ?» ብሎ የጨው አምድ ሊያደርገኝ እየተጋ ያስመስልበታል፡፡ አሊያ ግን ሳይሰስት ያለውን አየር ዘግኖ እየበተነልኝ ነው፡፡ ተከዜ፡፡
«ተከዜ — የሁለት ወንድማማች ህዝቦችን ገመገሞች የሚከፍለው እርሱ ነው ይሉለታል፡፡ እውነቱ ግን ‹‹ሁለቱን የሚከፍለው›› ከሚሰኝ.. ለማንም ሳይወግን.. ሁለቱንም ህዝቦች.. በግራና ቀኝ ትክሻው እየታከከ.. ሁለቱንም እየታቀፈ.. እያሰናኘ.. በማይሰማ ድምፁ.. የሰላም መልዕክቱን.. እንደ ሰጎን እንቁላሎች በአሸዋው ዳር ዳር በሚበትናቸው በሚያማምሩ ህብረቀለማት ባሸበረቁ አልማዛዊ የድንጋይ ፈርጦች እየገለጸ.. ሰጥ ለጥ በሎ ያልፋል፡፡ ያም አልበቃ ሲለው፤ ድምፅ አውጥቶ.. በልስልስ ዜማ እየዘመረ.. እየተንሿሿ ሲገሰግስ.. ይህ ሁሉ ወጉ.. እንኳን ለጎረቤታሞች.. ለኔቢጤ አልፎ ሂያጅ ባይን በጆሮ ይገባል፡፡
«ባይን በጆሮዬ የገባ – ግን ያልተናገርኩት – አንድ ነገር ቀረኝ፡፡ ካለሁበት ሰገነት ቁልቁል በጎረቤት ግቢ አሁንም አሁንም እይታዬን የሰረቁብኝ.. አሁንም አሁንም ድሪያቸውን የሚያጧጡፉ.. አፍ ለአፍ የሚጎራረሱ.. ሁለት.. ነጫጭ.. ሰልካካ እርግቦች፡፡ በተቀለሰላቸው የእንጨት ጎጆ ደጃፍ ላይ.. እየተውረገረጉ ዓለማቸውን ይቀጫሉ፡፡ እነርሱ ዘንድ ያለው ፍቅር ብቻ ነው፡፡ ፍቅር፤ ሠላም፤ ፍቅር፤ ፍቅር፡፡ እርግብ ባረገኝ ያስብሉሃል፡፡ ክንፍ የለህ ነገር ሃሳብህን ወደሩቅ ታሸሸዋለህ፡፡
«እና ማንን ታገኛለህ?… ዕድሜ ጠገብ የበረሃ ግራሮች፣ አረንጓዴ የበረሃ ዘንባባዎች፣ እና ደግሞ የበረታ የበረሃ አውሎ ንፋስ.. ሁሉም እንደ ጨዋታ.. እንደ ወግ ተመስለው ባይኔ መግባታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በመጨረሻ.. ሁሉም እየተጋገዙ የሚያነሆልሉህ.. የሆነ ለሆሳሳዊ አፍዝ-አደንግዝ አላቸው፡፡ እንደ በረሃ አቧራ ዝም ብለህ ያለጥያቄ ወግ ወጉን የምትምገው ነገር ሁሉ.. ተጠራቅሞ እንደአንዳች የፍቅር መንፈስ.. የሰራ አከላትህን ሲወርህ ይታወቅሃል፡፡ ፍቅር ፍቅር ያሰኝሃል፡፡
«ቅርብህን ስትሸሸው… ከሩቅ ሆኖ.. ከሰማይ ጋር የተሰፋ ከሚመስልህ አውላላ መካከል.. የጥበብ እስትንፋስ.. እንደ ኤፍራጥስ ንፋሳት… እንደ ቢሾፍቱ ቆሪጦች ተመስላ… እየተጣራች… ና እያለች… በላይህ ላይ ትሰፍርብሃለች፡፡ ይህ አልበቃ ብሎት… ልክ ቅናት የያዘው ይመስል.. ደሞ በተራው.. ሃገር አቆራርጦ የሚያልፍ ኃይለኛ የጥበብ ዛር.. በበረሃ አውሎ ንፋስ እየተጓጓዘ.. በህልምህ ይሁን በእውንህ ሳታውቀው.. በላይህ ላይ አንዳች መንፈሱን ይነዛብሃል፡፡ ከዚያ አንተ የጥበብ ታዛዧ ትሆናለህ፡፡ ያልኖርክበት የጥንት ዘመን ባለሟሉ ያደርግሃል፡፡ በጥንት ልሳናት በልሃ ልበልሃ መግጠም ያሰኝሃል፡፡
«በላይህ ላይ አንዳች ሀገራዊ የጥበብ መንፈሱን እንዲህ ሲነዛብህ. . . ከአክሱም የጥበብ ማማ ላይ…፣ ከላሊበላ ውቅር ቤተስኪያኖች ሥር..፣ ከፋሲል ታላላቅ ግንቦች ጀርባ..፣ ከሶፍ-ኦመር የውሃ ዋሻዎች ውስጥ…፣ ከየሃ ቤተመቅደሶች ግርጌ…፣ ከጀጎል ጥምዝምዝ ግንቦች ዘንድ…፣.. በቃ.. ከነዚያ እና ከነዚያ ሁሉ.. እንደ ሰናዖር ግንብ ከፊትህ ተሰትረው ከሚታዩህ ቢዛቁ የማያልቁ ያገርህ የጥንታዊ ጥበብ አውድማዎች.. የጥበብ መናፍስትና የጥበብ አድባራት ጋር… ኖረህ መሞትን ትመኛለህ፡፡
«አንተ አገር ምድሩን እየዞረ ያሰሰው የታላቁ የሄኖክ ዘር..፤ አንተ ከበረሃ ዛፎች የሚነሱ ዕጣኖች በመዓዛቸው የሚያውዱህ የበረሃ መፃተኛ፤… አንተ እንደ ዕድለኛ ንቦች በበረሃ የበቀሉ የሣሮን ፅጌረዳዎችን የምትቀስም የኢትዮጵያ መንፈስ ሆይ… አንተ ባሸበረቁ የብር ጌጦች መካከል በክብር የተቀመጥህ የሰርዲዮን አልማዝ ሆይ… ወደየት አለህ… ???!! — ይልሃል.. አንዳቹ.. አንተ በውል የማታውቀው.. እርሱ ግን ባገርኛ ቃናው በላይህ የሚያስገመግምብህ… አንዳች ጥበበ-እስትንፋስ!!! አንዳች  ነጎድጓዳማ ጥ በ በ – ድ ም ጽ !!!
«እናም በቃ… ዕድሉ ተሰጥቶሃልና… ትጠይቃለህ.. ትሞግታለህ.. ትማፀናለህ…፡፡ እርሱም… በዘመናት ሠጋር በቅሎ እየጋለበ.. በአውሎ ነፋሳት አምሳል ይለመንሃል.. ይዘከርሃል.. ይዋስሃል… የያዘህ የጥበብ ውቃቢ… ቆሌው ተገፍፎ…. ከላይህ ውልቅ ብሎ… እስኪለቅህ… ለቆህ ካጠገብህ እስኪፈረጥጥ ድረስ!! የጥበብ ዛር.. እንዲህ ነዋ!!! ምን ታረገዋለህ??!!
«*(በነገራችን ላይ፡- ‹‹የጥበብ እስትንፋስ…!!›› የሚለው ስም በሃገር ፍቅር ትያትር ቤት አዳራሽ መግቢያ ላይ.. ከጋሽ ስዩም የመስተዋት ስዕሎች ግርጌ.. በስተቀኝ በኩል… በቀራፂ አርቲስት ተስፋዬ ገብሬ ተሠርታ የቆመች… የአንዲት አስደማሚ ኃውልት ስያሜ ነው፡፡)»
አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክለ፡፡ የፍቅርን ዛር ይዝራብን፡፡ እምዬ ኢትዮጵያ – ለዘለዓለም – በፍቅር – በጥበብ – ትኑር፡፡ አሜን፡፡
Filed in: Amharic