>

ከአፈና ወደ ዴሞክራሲ ወይስ መልሶ ወደ አፈና? (በፈቃዱ ዘ ኃይሉ)

ከአፈና ወደ ዴሞክራሲ ወይስ መልሶ ወደ አፈና?

በፈቃዱ ዘ ኃይሉ 

DW 

በአመፅ እና ለውጥ ከዚያም መልሶ በአመፅ አዙሪት ውስጥ ለኖሩት ኢትዮጵያውያን የለውጥ ተስፋ እያዩ ማጣት አዲስ አይደለም፡፡ መስከረም በጠባ የመጀመሪያው ሳምንት ላይ የተከሰተው አመፅ እና የመንግሥት የተዝረከረከ ምላሽ እና ግልጽነት የጎደለው የእስር እርምጃ፣ ባለፉት ስድስት ወራት የታየው የለውጥ ተስፋ ሊያመልጥ እንደሚችል ጠቋሚ ምልክት ሆኗል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለአመፅ እና አፈና ሊዳርጉን ከሚችሉት ችግሮች አንደኛው ለውጡ የተበየነበት መንገድ ነው፡፡ ለውጡ በሕዝባዊ አመፅ የመጣ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከገዢው ቡድን ውስጥ ባለ መከፋፈል የለውጥ አቀንቃኝ የነበሩትን የሚደግፍ ቡድን ተከስቶ ወደ ሥልጣን ባይመጣ ኖሮ የበለጠ ቀውስ እና አፈና ይመጣ እንደነበር መገመት አይከብድም፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ባለመረዳት ወይም ለመረዳት ባለመፈለግ በለውጥ አቀንቃኞቹ ጥረት እና ጥረት ብቻ የመጣ በማስመሰል የሽግግር ጊዜውን መበየኑ፣ በለውጥ አቀንቃኞች ዘንድ “ምን ይሳነኛል” የሚል ስሜት ያዳበረ ይመስላል፡፡ ይህ ደግሞ ችግርን በዴሞክራሲያዊ መርሕ በመነጋገር እና በማመቻመች ለመፍታት በመሞከር ፈንታ “ኃይል ተጠቅሜ ወይም በአመፅ ችግሩን እፈታዋለሁ” የሚል ስሜት እንዲጎለብት አድርጓል፡፡ በዚያ ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች “የለውጡ ባለቤት እኔ ነኝ” ብለው በፉክክር በሚያስቡበት ሁኔታ፣ ተነጋግሮ ሁሉንም አስማሚ መፍትሔ መቀየስ እንዳይቻል ሆኗል፡፡

ለውጥ እና የሕግ የበላይነት ጉዳይ

ነባሩ የኢትዮጵያ ስርዓት ኃይልን እንደ አስተዳደራዊ መሣሪያ ሲጠቀም ነበር፡፡ የፍትሕ አካላቱ እና የዴሞክራሲ ተቋማቱ ደግሞ በኃይል አፋኝነቱን ሽፋን ሲሰጡ በመክረማቸው ሕዝባዊ ተአማኒነታቸውን አጥተዋል፡፡ በሌላ በኩል ገና መስተካከል ያለባቸው ኢ-ፍትሐዊ ሕጎች አሉ፡፡ አሁን በመከለስ ላይ ካሉት አፋኝ ሕግጋት (የፀረ ሽብርተኝነት፣ የሲቪል ማኅበራት… አዋጆች) እና መመሪያዎች ውጪ እንደምሳሌ የባንዲራ አዋጁን መጥቀስ ይቻላል፡፡

የኢፌዴሪ አርማ የሌለውን ባንዲራ በአደባባይ ይዞ መታየት አሁንም ድረስ በሕግ ተከልክሏል፡፡ ይሁን እንጂ በለውጡ ድባብ አዋጁ ኢፍትሐዊ ነው በሚል ይመስላል፣ ዜጎችም አርማ የሌለውን ባንዲራ በአደባባይ ይዘው ከመውጣት አልተቆጠቡም። መንግሥትም በዚህ ሰበብ ክስ አይመሠርትም፡፡ በዚህ መሐል የትኞቹ አዋጆች እንደሚከለሱ፣ የትኞቹ ተፈፃሚ እንደሚሆኑ ግልጽነት ጎድሏል፡፡ ይህም የሕግ የበላይነት ጉዳይ ከቁም ነገር የተቆጠረ አይመስልም፡፡ በጥቅሉ፣ የተቋማቱ ሕዝባዊ ተአማኒነት ማጣት እና በመከለስ ላይ ያሉ ወይም መከለስ በሚገባቸው ሕግጋት ስርዓትን ማስከበር ስለማይቻል ወደ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር የሚደረገው ጉዞ ሌላኛው አስቸጋሪ ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡

የቅድመ መከላከል ችግር

ኢትዮጵያ አሁን በአገር ውስጥ በተፈናቀሉት ዜጎቿ ቁጥር በጦርነት እየታመሱ ካሉ አገራት ሳይቀር እየበለጠች ነው፡፡ እነዚህ መፈናቀሎች የተከሰቱት በጦርነት ሳይሆን ማንነትን መሠረት ባደረጉ ጥቃቶች ነው፡፡ ጥቃቶቹ እና ግጭቶቹ ከተከሰቱ በኋላ ተፈናቃዮቹን በቀላሉ መልሶ ማቋቋም አዳጋች እንደሆነ ባለፉት ወራት ከጅግጅጋ እና ከጉጂ የተፈናቀሉትን ሰዎች ጉዳይ በማስታወስ ብቻ መረዳት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ከእነዚህ ግጭቶች ትምህርት በመውሰድ፣ መንግሥት ቀድሞ የመከላከል ሥራ ላይ ያተኮረ አይመስልም፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙዎች በነጻነት እና በሠላም መኖር እንደማይቻል፣ ይልቁንም ከሁለት አንዱን መምረጥ እንዳለባቸው እንዲሰማቸው ሆኗል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ትርክት የሚጋጩ ሕልሞች ያሏቸው ቡድኖችን ከመፍጠሩም ባሻገር፣ ታፍነው የነበሩ ጥያቄዎች የለውጡን ጭላንጭል ተከትለው ሁሉም በአንዴ እንዲመለሱ መፈለጋቸው ሐቅ ነው፡፡ ይህም ሆኖ መንግሥት በተለያዩ ቡድኖች መኃል ያሉ፣ በቁጥር አናሳ ነገር ግን በአመለካከት ወይም በማንነት የተለዩ ዜጎችን ደኅንነት በንቃት የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ አሁን ባለው አሠራር ግን ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት ቀርቶ ከተከሰቱ በኋላ እንኳን የሚሰጡት ምላሾች የዘገዩ ናቸው፡፡

የለውጡ ፍኖተ ካርታ ግልጽነት ማጣት

ከላይ ከተዘረዘሩት ችግሮች ሁሉ በላይ የለውጡን ተስፋ ወደ አፈና ሊቀለብሰው የሚችለው፣ ለውጡ ግልጽ መንገድ ያልተበጀለት የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ በደፈናው ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እየተሸጋገረች እንደሆነ ይነገራል፡፡ ነገር ግን እንዴት እና መቼ የታለመው ቦታ እንደምትደርስ ግልጽ አሰራር የለም፡፡ አፋኝ አዋጆችን ለመከለስ፣ ተቋማዊ ነጻነትን ለመገንባት እና ወቅቱ ሲደርስ ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሔድ ቃል ተገብቷል፡፡ ይሁን እንጂ አዋጆቹን በመከለሱም፣ ተቋማቱን ነጻ እና ገለልተኛ በማድረጉም ይሁን የቅድመ ምርጫ ሜዳውን ነጻ በማድረጉ ሒደት ውስጥ ግልጽነት የለም፡፡

ስለ ለውጥ ሒደቱም ይሁን ግብ ዜጎች አያውቁም፤ የፖለቲካ ልኂቃንም ወጥ አተያይ የላቸውም፤ የመንግሥት አመራሮች ደግሞ በቂ ማብራሪያ እየሰጡ አይደለም፡፡ ይህም ዜጎችን ለውዥንብር፣ የለውጥ አቀንቃኞችም የሚፈልጉትን አግኝተው ይሁን አይሁን ወይም ሊያገኙ እንደሚችሉ እርግጠኝነት እንዳይሰማቸው አድርጓል፡፡ ለውጡ ፍኖተ ካርታ (roadmap) ሳይዘጋጅለት ወደ ፊት መገስገስ የለውጥ አቀንቃኞችን ትግስት ከማሳጣቱም ባሻገር የመንግሥትንም ተአማኒነት ይሸረሽራል፡፡

እነዚህ እና ሌሎችም ተግዳሮቶች ላይ ኃላፊነት የማይሰማው የማኅበራዊ ሚድያ አጠቃቀም ሲጨመርበት አመፅ እና ብጥብጥ በቀላሉ ሊፈነዳ ይችላል። መንግሥት ደግሞ ይህንን ሰበብ በማድረግ ወደ ተለመደው የአፈና አዙሪት ሊወድቅ ይችላል፡፡ ስለሆነም፣ የለውጥ አቀንቃኞችም ይሁኑ መንግሥት የየግል ኃላፊነታቸውን በመወጣት ኢትዮጵያውያን ከኖሩበት የአመፅ እና የለውጥ አዙሪት እንዲወጡ የማድረግ ከፍተኛ ፈተና ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል፡፡

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ « DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።

Filed in: Amharic