>
1:51 am - Thursday July 7, 2022

"የጳጳሳት ስራ ሕዝብን ማጽናናት እንጂ ህዝብን ማሳዘን አይደለም" አቡነ መቃርዮስ (ሊቀጳጳስ)

“እረኛው በጎቹን መፈለግ ትቶ በጎቹ እረኛውን የሚፈልጉበት ግዜ መጣ” አቶ አስራት ተሾመ (የሰበካ ጉባኤው ሊቀመንበር)
ኣ.ተ. (ቫንኩቨር)
Abune Mekarios & Melake Stehay Afework
ለላፉት ሶስት አመታት በተለያዩ አለመግብባቶች ሲጓተት የነበረው የቫንኩቨር ጼዴንአ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤት በአቡነ መቃርዮስ፤ ሊቀጳጳስ ባራኪነት ተከበረ፤ የቫንኩቨር ምእመናን የደስታ እንባ አነቡ። ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ በተከበረው በዓል ላይ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቫንኩቨርና አካባቢው ምእመናን፤ ከአመታት ልፋትና ጸሎት በኋላ ሀሳባቸው ሰምሮ የመድሄኔዓለምና የቅድስት ማርያም ጽላት ስለገቡላቸው ደስታቸውን በዝማሬና በእንባ ገልጸዋል።

ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ የኩቤክና የአውስትራሊያ ሊቀጻጻስና የአውሮፓና የአፍሪካ ም/ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን ብጹእ አቡነ መቃሪዮስን ለመቀበል በቫንኩቨር አውሮፕላን ማረፊያ የተገኙት ምእመናን፤ ገሚሶቹ አዳራቸውን በቤተክርስቲያን በማድረግ፤ ከፊሎቹም በሌሊት ወደቤተክርስቲያን በመምጣት፤ ምስጋናቸውን በደስታና በዝማሬ ገልጸዋል።
የቫንኩቨር ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በ1990ዎቹ ውስጥ፤ በአሁኑ ሰዓት በሕይወት በሌሉት በአቡነ ዜናማርቆስ ቡራኬና በሊቀካህናት ምሳሌ ትብብር ተመስርታ፤ በ2006 አመተ ምህርት አካባቢ ወደ ህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት በሚያዘነብሉ ደጋፊዎች ከተጠለፈች በኋላ፤ እንደገና በማንሰራራት ምእመኑን ማሰባሰብ ብትችልም በርካታ ፈተናዎችን አልፋ በተቋቋመችው ቤተክርስቲያን ዘንድም አለመግባባት በመፈጠሩና የአገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ችግሩን በእንጭጩ ከመፍታት ይልቅ፤ ችላ በማለታቸውና በማጓተታቸው ልዩነቱ እስከመለያየት መድረሱ ይታወቃል። የጸዴንያ ማርያም ምእመናን ላለፉት አራት አመታት ሲያሰሙት የነበረው ጥሪና እውቅና ሰሚ ሳያገኝ ቆይቶ፤ በሀዘንና በተስፋ መቁረጥ ይኖሩ ዘንድ ተገደዱ።

እነሆ፤ የቫንኩቨር ምእመናን ጸሎት ተሰምቶ፤ በፈረንጆቹ ዘመን ዘመን አቆጣጠር፤ ቅዳሜ ጁን 28 ቀን 2014 ዓ.ም.፤ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ደግሞ ሰኔ 21 2006 ዓ.ም. በአውሮፓና በአውስትራሊያ፤ በተመሳሳይ ሀዋርያዊ ተልአኮዋቸው የሚታወቁት፤ አቡነ መቃርዮስ፤ የአውስትራሊያና የኩቤክ ሊቀጳጳስ፤ የአውሮፓና ምስራቅ አፍሪካ ረዳት ሊቀጳጳስ በተገኙበት የቤተክርሰቲያኗ ቅዳሴ ቤት ከብሯል።

ሊቀጳጳሱ፤ ከምእመናኑ የቀረበላቸውን ተደጋጋሚ ጥሪ በመቀበል፤ በአውሮፓ፤ በጀርመንና በአውስትራሊያ፤ እንዳደረጉት ሁሉ፤ ከአርብ ሰኔ 21 ቀን ጀምሮ በአካባቢው በመገኘት፤ የመድሀኔዓለምና የቅድስት ማርምን ታቦታት ወደ መቅደሱ አስገብተዋል። ሊቀጳጳሱም፤ በአካባቢው በወንድማማቾች መካከል ያለውን ውጥረት ያረግባል በሚል እሳቤ፤ ቤተክርስቲያኗን፤ የቫንኩቨር ምስካየ ሕዙናን መድኃኔዓለምና ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በማለት ሰይመዋል።Ethio Chanda 2
ሊቀጳጳሱ በአካባው በቆዩበት ወቅት ለምእመናን የወንጌል ትምህርት የሰጡ ሲሆን፤ ምአመናን አገራቸውን እንዲጠብቁና ለሰላምና ለነጻነት ከመታገል ወደኋላም እንዳይሉ አሳስበዋል። በቤተክርስቲያን በኩል ስለሚታዩ ድክመቶች አባቶች በየአካባቢው የሚነሱ ችግሮችን በጊዜ ያለመፍታታቸውን ምክንያት በተመለከተ ለተነሳባቸው ጥያቄ፤ ካህናትና ጳጳሳት የምአመናን እንባ ለማበስ እንጂ ምእመናንን ለማስለቀስ እንዳልተሾሙ ተናግረው፤ በሳቸው በኩል ዘወትርም ከምእናን ጋር እንደሚቆሙና በተለያዩ ምክንያት የተቀየሙም፣ የሸሹም ካሉ እነሱን ወደቤተክርስቲያን ለማምጣት እንደሚተጉ ገልጸዋል።

የጼዴንያ ቅድስት ድንግል ማሪያም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ሊቀመንበር አቶ አስራት ተሾመ ባደረጉት ንግግር፤ የአካባቢው ምእመናን እምነታቸውን ለማስጠበቅ ላለፉት 20 አመታት ያለፉበትን ፈተና አስታውሶ፤ በተለይ ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ በጎቹ ተሰብስበን በተለያየ መንገድ የእኛ እረኞች የሆኑትን አባቶቻችንን ለማግኘት ጥረት ስናደርግ፤ ያ ሳይሳካልን ቀርቶ በብዙው ተፈተንን ብለው፤ በመጨረሻ ጸሎታቸው ሰምሮ አቡነ መቃርዮስ፤ ሊቀጳጳስ፤ በቤተክርስቲያን ተገኝተው አመታት የፈጀ ችግሮችን በአንድ ቀን ስለፈቱላቸውና እንባቸውን ስላበሱላቸው ለሊቀጳጳሱና በስደት ለሚገኘው ህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

(የበአሉን አከባበር በተመከለተ የተዘጋጀውንና ከሊቀጳጳሱ ጋር የተደረገውን ቃለምመልልስ በቪዲዮ መልክ እንደደረሰ እናቀርባለን።)

Filed in: Amharic