“ምሁራን ወይስ እ ውራን…?”
ፋኖና ጋዜጠኛ ወግደረስ ጤናው
በዋናነት “ፕሮፌሰር፣ዶክተር፣ኢንጂኔር…” ወዘተ.. የሚል መጠሪያ ከፊት ተሸክማችሁ “ምሁራን” እየተባላችሁ የምትጠሩ በውጭም በውስጥም ያላችሁ ግለሰቦች (በአማራ የሕልውና ትግል ውስጥ)
“ምሁር” ማለት ምን ማለት ነው?
– በአውራጃ፣በሰፈርና በጎጥ ተወሽቆ የአማራ የሕልውና ትግልን መከፋፈል ነው እንዴ?
-ፖለቲካዊ ሴራው ገብቶት ሳይሆን በተግባር የሚፈፀምበት አካላዊ ጥቃት አስገድዶት ራሱን ከመጥፋት ለመከላከል አንድያ ሕይወቱን የሚሰጠውን አርሶ አደር፣ ባልተገራ ፖለቲካዊ ሴራ፣በአካባቢና በመንደር ከፋፍሎ ማገዳደል ነው እንዴ?
– ሁሉን ነገር ትተው፣ መሬት ላይ ከአገዛዙ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ጥቃት፣ከድሮን፣ ከእባብና ጊንጥ ጋር እየታገሉ፤ማንነትን፣እምነትንና ባህልን ለማቆየት ዋጋ የሚከፍሉ የፋኖ መሪዎችን ሌት ከቀን መስደብ፣ማዋረድ፣መከፋፈልና ማጋጨት ነው እንዴ?
– ለአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል የሚጠቅመውን ሐቅ ትቶ፣ የግል ፖለቲካዊም ይሁን ኢኮኖሚያው ጥቅማችሁን ብቻ ሊያሳካ ይችላል የምትሉትን ግምታዊ መሰመር እርስ በእርስ እያገዳደሉ መከተል ነው እንዴ? አይመስለኝም።
ይልቁንስ፦
– ምሁርነት፦ በየዘርፉ ጥናትና ምርምሮችን በማድርግ ሕቀኛ፣የተፈተነና ለውጥ ሊያመጣ የሚችልና የሚያመጣ ስራ መስራት ነው። ይህንን ትርጓሜ ወደ ትግላችን ስንለውጠው የሕልውና ትግሉ አሁን ያሉበትን መሰረታዊ ችግሮች ምሁራዊና ሙያዊ( ፖለቲካዊና ወታደራዊ) በሆነ መንገድ በጥናትና ምርምር ነቅሶ በማውጣት በቅንነት ችግሮቹን ፈትቶ ለግብ እንዲበቃ መስራት ማለት ነው።
– በጥናትና ምርምር ላይ በመመርኮዝ የጋራ መግባቢያ የትግል ሰነዶችን፣ ምክረሐሳቦችን፣ ፍኖተ መርኆችንና ሌሎች ለፋኖ የሕልውና ትግል ጠቃሚ ሰነዶችን ማዘጋጀት፣በተዘጋጁት ሰነዶች ዙሪያ እንደያመችነቱ በጋራ፣በተናጥልም ሆነ በቡድን ስልጠናዎችን መስጠት፣ክትትልና ድጋፍ ማድረግ፣የትግል ሂደቱንና ለውጡን እየተከታተሉና አየገመገሙ ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ… ወዘተ..እንጂ…
-ምሁርነት፦ በተለይ በሕልውና ትግል መንደሬነትን፣አካባቢያዊነትን፣ ጎጠኝነትንና በሰፈር መርመጥመጥን አብዝቶ ይጠላል። ቧልተኝነትን፣አድር ባይነትን፣አስመሳይነትንና ሆዳምነትን ይፀየፋል።የኀሊናና የሆድ እስረኝነትን አያዎድም። ቅጥፍናንም ይታገላል።
– ምሁርነት ከተለመደው ዘፈቀዳዊ ሁናቴ እራስን መለየት ነው። ፊት ለፊት ሁሉም የሚያየውን ሳይሆን ከመጋረጃው በስተጀርባ የማይታየውን የሚያይ ነው።
– ምሁርነት ከድንቁርና አይጣባም። ጨለማ ከብርሃን ሕብረት እንደሌለው ሁሉ ምሁርነትም ከድንቁርና አይተዋዎቅም።
-ምሁርነት በየ ድግስ ቤቱ እንደ ወደላ ዝንብ ድንኳን ሰባሪነት አይደለም። “…ፋርፋሪ ጣሉልኝና፣ለውሸት ኀሊናዬን ላከራያችሁ”ነትም አይደለም። ቀና የሆነ ኩራት፣ቁጥበነትና እጅግ አርቆ አስተዋይነት እንጂ።
ይህንን መነሻ በማድረግ አሁን ላይ በተለይም በውጭ የሚኖሩ “አማራ ነን” የሚሉ ባለ ማዕረግተኞችን ስንፈትሽ ግን በተቃራኒው ሆነው አግኝተናቸዋል።
በአማራ ፋኖ የሕልውና ትግል ውስጥ መፍትሔ ከመሆን ይልቅ በሽታ ሆነዋል።
የአማራ ፋኖ አንድነት ችግሩን ለይተው መውጫ መንገዱን ከማሳየት ይለቅ ራሳቸው ዋነኛ ችግሮች ሆነዋል።
ሙያዊ ስነምግባራቸውም ሆነ ምሁራዊ ስሪታቸው ባይፈቅደውም መንደራቸው ውስጥ ገብተው ይርመጠመጣሉ። እንደተራው መደዴ ቧልት ሲያመላልሱ፣ ሲሳደቡ፣ትግል ሲከፋፈሉ፣የፋኖ መሪዎችን ሲያብጠለጥሉና በየ ድድ ማስጫው ተሰልፈው ሌላው(ተራው) የሚችለውንና የሚያውቀውን አብረው ሲያቀረሹ ይውላሉ።
ምሁር ሆኖ ቧልት ማመላለስ? ኧረ! እንዴት ይቀፋል። ምሁር ሆኖ ከድንቁርና መጣባት፣ ኧረ! እንዴት ይሆናል? ምሁር ሆኖ የሕልውና ታጋዩን፣ፋኖን፣አርሶ አደሩንና ሌሎችን በተሳሳተ መንገድ በመምራት ማገዳደል፣ተስፋ ማስቆረጥና እንዲበተኑ መስራት ለምን? ምሁር ሆነ ለግል ጥቅምና ዝና በማይሆን መንገድ መራኮት እንጂ በየቀኑ በድሮንና በአገዛዙ ቅጥረኛ ሰራዊት ለሚያልቀው አማራ ኬሬዳሽነት፤ለምን? አሁን እናንተን “የአማራ ምሁራን” ወይስ “የአማራ እውራን” እንበላችሁ?
አደብ ግዙ። ከቻላችሁ ስለ እውነት፣ ሙያችሁና ብቃታችሁ የሚፈቅደውን በሕልውና አደጋ ውስጥ ላለው አርሶ አደር አበርክቱ። ካልሆነ ግን እንደ ልማዳችሁ ሕሊናችሁን ለከርሳችሁ ገርዳችሁ ኑሩ።እኛን ተውን። ይህንን ስጽፍ ግን ሐቀኛ ምሁራንን ባለመዘንጋትና በማመስገንም ጭምር ነው።
በነገራችን ላይ “ፋኖ ግቡን እንዲመታ..! የሚለውን ምክረሐሳቤን ለእነዚህ “ምሁር ነን” ባይ እ ውራን አድርሱልኝ እና ከዛ ይማሩ።
እየታበይኩ እንዳለሆነ መቼም የሚያውቅ ያውቀዋል።
የሕልውና ትግሉ ባለቤት የአማራ ሕዝብ ነው!!!
ድል ለሰፊው ሕዝባችን!!
ኢትዮ ሪፈረንስ
ለአብነት ይህንን ቪዲዮ አጋርተናችኋል።
ምሁርነት ወይስ እውርነት?

























