ያሬድ ሃይለማርያም
የቆዩና ታሪካዊ የሆኑ ስብራቶችን፣ ፖለቲካዊ ቁርሾዎችን፣ የተፈጸሙ በደሎችን፣ ግፎችንና የመብት ጥሰቶችን፣ በማህበረሰቡ መካከል የተፈጠሩ ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ ነገሮችን ለማከምና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በሚል ለአራት አመት የተደከመበት የብሔራዊ ምክክር አዳዲስ ቁርሾዎችንና የፖለቲካ ሽኩቻዎችን መፍጠሪያ መድረክ ሆኗል።
ከሁለት ቀን በፊት እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ ላይ ተሳታፊ የሆኑ አምስት ሰዎችን በተናጠል ሰፋ ያለ ጊዜ ወስጄ ማውራት ችዬ ነበር። ከአምስቱ ሁለቱ የቆዩ የብልጽግና አባላት ሲሆኑ በመንግስት ሽፋን የኦሮሚያ ብልጽግና አባላት በምክክሩ ላይ እየፈጸሙት ባለው ፍጹም ሕገወጥ፣ መረን የለቀቀና አይን ያወጣ የአጀንዳ ነጠቃ ሥራ አንጀታቸው ያረሩ ካድሬዎች ሲሆኑ አንዱ ለብልጽግና ካለው ስስ ልብና ጭፍን ድጋፍ የተነሳ ዲያስፖራውን ወክለዋል በሚል ከውጭ ከገቡት ሰዎች ነው።
ለማንኛውም በነበረኝ ሰፊ ውይይት ከዚህ የሚከተሉት መረጃዎች ደርሰውኛል።
1ኛ/ በዚህ ምክክር ላይ ሁሉም የብልጽግና አባላት ለብቻቸው ተጠርተው በመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና በተለይም በደህንነት ሰዎች በተሰጣቸው ጥብቅ ማሳሰቢያ ብልጽግና ከሚፈልጋቸው አጀንዳዎች ውጪ የመንግስትን ገጽታ የሚጎዱ ምንም አይነት አጀንዳዎች እንዳይጸድቁ እንዲረባረቡ፣
2ኛ/ ከኦሮሚያ ክልል የመጡ የብልጽግና አባላት ደግሞ ለብቻቸው በየቀኑ ከምክክሩ በኋላ በየአጀንዳው ላይ ከደህንነትና ከክልሉ ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር እንደሚወያዩና ትዕዛዝ እየተቀበሉ ሌሎች ተሳታፊዎችን (ኦሮሞ ያልሆኑ የብልጽግና አባላትን ጨምሮ) በተናጠል እንዲያስፈራሩና በስብሰባዎቹም ላይ ቁጣቸውን እንዲገልጹ፣ አጀንዳ እንዲያስቀይሩ፣
3ኛ/ በተወሰኑና እጅግ አወዛጋቢ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ፤ በተለይም የአዲስ አበባና የድሬደዋ ከተሞች እጣፈንታ፣ በኦሮሚያ ክልል በተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች፣ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ ስለሚደርሰው ተደጋጋሚ ጥቃት፣ በኦሮሚያ ክልል ስለሚገደሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች፣ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በተነሱ የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎች፣ ውዝግቦችና ሌሎች ከኦሮሚያ ክልል ጥቅም ጋር ተያይዘው በተነሱ ጉዳዬች ላይ በተደረጉ ውይይቶች ላይ ጠንካራ አቋም ይዘው እውነቱንና ትክክለኛ ያሉትን ነገር የተናገሩ፣ የተከራከሩና አጀንዳ ያስያዙ ሰዎች በስም ተለይተው በተናጠል በደህንነት አባላትና በካድሬዎቹ በኩል ክትትል እንዲደረግባቸውና ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ ተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ የደረሰባቸው መሆኑን።
4ኛ/ ካናገርኳቸው የብልጽግና አባላት አንደኛው በሦስት የኦሮሚያ ብልጽግና አባላት እዛው ስብሰባው ላይ ‘አርፈህ ተቀመጥ፣ በመንግስት ደህንነቶች አይን ውስጥ ገብተሃል፣ እያንዳንዱ ንግግርህ ተቀርጿል፣ እንደ በጥባጭ ነው የተቆጠርከው፣ ትላንት ማታ የኦሮሚያ ብልጽግና አባላት ከደህንነት ሰዎች ጋር በነበረን ውይይት ያንተም ስም ከበርካታ ሌሎች ተቀናቃኝ ሰዎች ጋር ተካቶ ስምህ ሲነሳ ነበር፣ እርምጃ ሊወሰድብህ ይችላል፣ አርፈህ ልጆችህን አሳድግ’ የሚሉ ምክር የመሰሉ ማስጠንቀቂያዎችና ማስፈራሪያዎች ከኦሮሚያ ክልል በመጡ ተሳታፊዎች የተሰጠው መሆኑን ገልጾልኛል።
5ኛ/ ሁሉም የምክክሩ ውይይቶች በቪዲዬ የሚቀዱ ሲሆን ኮሚሽኑ ለታሪካዊ ሰነድነት የሚቀመጥ ነው ቢልም ውይይቶቹ በሚካሄዱባቸው ሰዓት እዛው በሕንጻው ውስጥ የተለየ ክፍል ተዘጋጅቶላቸው ወሩን ሙሉ የእያንዳንዱን ስብሰባ ሂደት በእስክሪን እንዲከታተሉ የተመደቡ የብሔራዊ ደህንነት አባላት በምን አጀንዳ ላይ ማን ምን ተናገረ የሚለውን እየመረመሩ ግለሰቦቹ ላይ ክትትል እንደሚያደርጉና አስፈላጊም ሲሆን ግለሰቡ የያዘውን አቋም እንዲቀይር ውስጥ ባሉ የኦሮሞ ተሳታፊዎች መልዕክት እንደሚላክበት፣ ግለሰቡ አቋሜን አልቀይርም ካለም ደህንነቶቹ በቀጥታ እንደሚያናግሩትና እንደሚያስፈራረት በደሉ የደረሰበት ተሳታፊ አጫውቶኛል።
6ኛ/ እጅግ አሳፋሪ የሆነው ጉዳይ ደግሞ ከላይ በጠቀስኳቸው የኦሮሚያ ክልልን የሚመለከቱ ጉዳዬች ላይ ውይይት ተደርጎ በአብላጫው ድምጽ የጸደቁና በቃለ ጉባኤ የሰፈሩ የውይይት ሃሳቦች ለፊርማ ተዘጋጅተው ሲመጡ በደህንነትና በኦሮሚያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ውሳኔ ተቀይረውና ከስምምነቱ ውጪ ተዘጋጅተው ለፊርማ እንደሚቀርቡ፣ አንፈርምም ባሉ ሰዎች ላይም ክትትል፣ ወከባ፣ የግድያ ዛቻ፣ ማስፈራሪያና እንደሁኔታው መደለያዎችም እንደሚቀርቡ፤
7ኛ/ ውይይት ተደርጎባቸው በተሰብሳቢው የጸደቁ ነገር ግን የኦሮሚያ ክልልን የሚመለከቱ ጉዳዬች ሁነው የክልሉን ካድሬዎች የማያስደስቱ ጉዳዮች ውይይቱ ካለቀም በኋላ ከሰነዶቹ ላይ ተለይተው እንዳይካተቱ መደረጉን እና ይሄንንም የተቃወሙ ግለሰቦች ላይ ተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ እየተሰነዘረ መሆኑን፣
8ኛ/ በእያንዳንዱ ውይይት በሚካሄድበት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ለውይይት ከተመደቡት ሰዎች ውጭ አስተባባሪ፣ አስተናባሪ መስለው እያንዳንዱን ተወያይ የሚቆጣጠሩ ሲቪል የለበሱ የደህንነት ሰዎች መኖራቸውና በተወያዬቹ መካከል እርስ በርስ የሚደረጉ ምክክሮችን ጭምሮ ለመስማትና ለመቆጣጠር የሚጥሩ መሆኑን።
በአጠቃላይ ይህ የምክክር ሂደት ከምክክር ኮሚሽኑ እጅና ቁጥጥር ሙሉ በሙሉ መውጣቱንና ምክክሩን ከጀርባ ሆኑ አቅጣጫ እያሲያዘ ያለው የኦሮሚያ ብልጽግና ካድሬዎችና የብሔራዊ ደህንነት ቢሮ መሆናቸውን ያነጋገርኳቸው የብልጽግና አባላት ብዙ ማሳያዎችን እያቀረቡ አረጋግጠውልኛል።





















