ለአፋብን ፖሊት ቢሮ።
ከእስክንድር ነጋ።
ጉዳዩ—ያለ አፋብን አባላት ተሳትፎ እና ውሳኔ ስለተቋቋመው “ትብብር”።
መስከረም 12፣ 2019።
አፋብን ከተመሠረተበት ጥር 9፣ 2018 አንስቶ እስካለንበት መስከረም 2019 ድረስ የአማራ ህልውና ትግል ትላልቅ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ ድሎች ያስመዘግባል ተብሎ በህዝብ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት እንደነበር ይታወሳል። ይህ ተስፋ ሁለቱ የፋኖ አደረጃጀቶች አንድ ከመሆናቸው በፊት በአፋህድ ላይ እንደ ድርጅት፣ በእኔ ላይ እንደግለሰብ የተፈፀሙ በደሎችን እንደ ፀጋ እንድቆጥራቸው እስከማድረግ የደረሰ ነበር። መስዋዕትነት እና ጨዋነት ለአፋህድ ድርጅታዊ ባህል፣ ለአባላቱ ደግሞ ግለሰባዊ ሱስ እንዲሆን በመጠኑም ቢሆን ስንጥር የቆየን በመሆናችን፣ የአፋህድ ድርጅታዊ ህልውና በዚያ መንፈስ መቋጨቱ ከፍተኛ የህሊና እርካታ ሰጥቶኛል።
ሆኖም፣ እንደ አፋብን ለመሰለ አዲስ ድርጅት የተስፋ፣ የብዙ ስራዎች እና የብዙ ውጤቶች ማስመዝገቢያ ግዜ በሆነው እና በተለምዶ “የጫጉላ ሽርሽር ወቅት” ተብሎ በሚታወቀው የመጀመሪያዎቹ 100 ቀናቶች፣ ለትግሉም ሆነ ለድርጅቱ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ወይም የለውጥ ተስፋ ሳይመዘገብ ቀርቷል።
በመላው ዓለም እንደሚታወቀው፣ “የ100 ቀናቶቹ የጫጉላ ሽርሽር ወቅት” የመንግሥት ወይም የድርጅት መሪ ብቃት ምን ያህል እንደሆነ የሚመዘንበት ወሳኝ ወቅት ነው። በጫጉላ ዘመኑ ውጤታማ ያልሆነ መሪ በቀጣይነት ውጤታማ የመሆን ዕድሉ በጣም ጠባብ ነው።
የአፋብን መሪ ወደሥልጣን የወጣበት ሂደት ብቃትን፣ ቅቡልነትን እና ዲሞክራሲያዊ ምርጫን ማዕከል ያደረገ ከመሆን ይልቅ፣ የፋኖ አንድነትን ለስልጣን ብለው ከአገቱት ለማስለቀቅ የተደረገ ድርድር ውጤት የነበረ መሆኑ ድርጅታችን በእውቀቱ የበሰለ፣ በመንፈሱ የተረጋጋ መሪ እንዳያገኝ አድርጎታል። በዚህ ሳቢያ የተከሰተው የአመራር ቀውስ (leadership crisis) ካስከተለብን ጉዳቶች መካከል፣ የሚሞትለትን ዓላማ በትክክል በሚያውቅ ታጣቂ ኃይል ውስጥ የህግ በላይነት ምን ያህል ወሳኝ እሴት መሆኑን የተረዳ መሪ አለመኖር በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው። ለዚህ እውነታ “በጽምዶ/ትብብሩ” ዙሪያ ከነበረው ሂደት የተሻለ ማሳያ የለም።
አሁን “ትብብር” በሚል መጠሪያ መቋጫ ያገኘው ሂደት፣ የአፍሪካ ቀንድ ህዝቦችን ለማቀራረብ ታስቦ “ጽምዶ” ተብሎ የሚታወቀው እንቅስቃሴ መነሻ እንደነበር ይታወቃል። ይህ ጉዳይ በወራት ሂደት አንዴ ጠበቅ አንዴ ላላ እያለ ሲገላበጥ የአፋብን አባላትም ሆኑ አብዛኛው አመራር በመገናኛ ብዙሃን ከሚሰሙት ባሻገር ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም። በመጨረሻ፣ አርበኛ ዘመኔ ካሴ ስዊዘርላንድ ከሚታተም ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ የትብብሩን ምስረታ ሲያበስሩ፣ በፋኖ አባላት ዘንድ በድጋፍም በተቃውሞም የተደበላለቀ ስሜት ለመፍጠር በቅቷል ። ይበልጥ ደግሞ፣ አባላት ሳያውቁ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ እንዴት ይተላለፋል? የሚል ጥያቄም አስነስቷል።
“ሳይደግስ አይጣላም” እንዲሉ ግን፣ የአርበኛ ዘመነ ቃለ ምልልስ የአባላት መብት እንዲከበር ለጠየቁ አባላት እንቅስቃሴ መነሻ ምክንያት ለመሆን በቅቷል። በዚህም መሠረት፣ ነሃሴ 12፣ 2019 ዓ.ም የአፋብን አባላት በአፋብን ፅ/ቤት በኩል ለፖሊት ቢሮው ባስገቡት ህጋዊ አቤቱታ፣ ፖሊት ቢሮው ወይም ሥራ አስፈፃሚው ለትግላችን ሰኬት ተብሎ ከድርጅታችን ጋር በአጋርነት ቢተሳሰሩ ጥሩ ነው ብሎ ከሚያምንባቸው ኃይሎች ጋር ግንኙነት ማድረግ እና የመግባቢያ ሰነድ እስከ መፈራረም መድረስ እንደሚችል ከህግም ከመርህም አኳያ ተቀባይነት እንዳለው ገልፀው፣ በተጀመረው ጥረት ላይ ቅሬታ እንደሌላቸው አሳውቀዋል።
ሆኖም፣ ከአፋብን ጋር የትብብር ስምምነት አድርገዋል የተባሉት ሕወሓት፣ ኦነግ/ሸኔ እና ጉምዝ ነፃ አውጪ በጀርባ ታሪካቸው በፀረ–አማርነታቸው እና በፀረ–ኢትዮጵያዊነታቸው ከመታወቃቸው ባሻገር፣ ባለፉት 8 ዓመታት ከኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት በተጨማሪ በቀጥታ በአማራ ህዝብ ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ የፈፀሙ የታጠቁ ኃይሎች መሆናቸው በገለልተኛ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት የተረጋገጠባቸው እና በዚህ ሳቢያ የህግ እና የሞራል ተጠያቂነት ያለባቸው መሆናቸውን አቤቱታ አቅራቢዎቹ ጠቅሰዋል።ከዚህ አኳያ፣ በመርህም በህግም ከእነዚህ ኃይሎች ጋር የሚደረግ ስምምነት በድርጅት ደረጃ ሊፀድቅ የሚችለው ለሠራዊቱ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት ቦኃላ የብዙሃኑ ድጋፍ ሲኖረው ብቻ መሆኑን አሳስበዋል።
በተጨማሪም፣ የአፋብን አመራር በድርጅታዊ ጉባኤ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ያልተመረጠ እና በዋናነት የፋኖ አንድነትን ለማሳለጥ በግዚያዊነት የተደለደለ እንደ መሆኑ መጠን፣ በእንደዚህ ዓይነት መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ለመወሰን የሚያስችል ህጋዊም ሆነ ሞራላዊ ቁመና እንደሌለው አስምረውበታል።
በመጨረሻም፣ አርበኛ ዘመኔ ካሴ በአደባባይ የሰጡት መግለጫ በዝምታ ቢታለፍ ከታሪክም ከህዝብም አኳያ እያንዳንዱን አባል የሚያስጠይቅ በመሆኑም፣ አቤቱታቸውን ህዝብ እና ታሪክ እንዲያውቅላቸው ለመገናኛ ብዙሃን እንደሚያሰራጩትም አሳውቀዋል። ባሉት ልክም ሄደዋል። በቀጣይነትም ከአቤቱታ አቅራቢዎቹ አንዱ በመሆኔ በጉዳዩ ዙሪያ በጀርመን ድምፅ ላይ ማብራሪያ ሰጥቼበታለኹ።
ለቀረበው ህጋዊ ጥያቄ ፖሊት ቢሮው የሰጠው ምላሽ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከሚንቀሳቀስ የበሰለ ታጣቂ ኃይል እና የህግ በላይነትን በውስጡ ካሰፈነ ተቋም የሚጠበቅ አልነበረም። ከሁሉ አስቀድሞ፣ የቀረበው ህጋዊ አቤቱታ እንደ አጀንዳ ተይዞ ለውይይት አልቀረበም። እንዲያውም፣ በአባላት አቤቱታ መቅረቡም ለፖሊት ቢሮው አልተነገረውም።
ይህ ማለት ግን፣ ጉዳዩ ፈፅሞ ታልፎ ነበር ማለት አይደለም። በጀርመን ድምፅ ላይ የሰጠኹት ቃለ ምልልስ አጀንዳ ሆኖ ከቀረበ ቦኃላ፣ ምንም እንኳን በቃለ ምልልሱ ህገ ወጥ ነገርም ሆነ ውሸት ስለመናገሬ የቀረበ ማስረጃ ያልቀረበ እና ባነሳዃቸው የመብት ጥያቄዎች ዙሪያ ምንም ውይይት ያልተደረገ ቢሆንም፣ በጭፍን እንድታሰር ተወስኖ ትዕዛዙ ለበታች አካላት ተላልፏል። ከበታች የተሰጠው ምላሽ የአማራ የህልውና ትግል የህግ የበላይነት የሰፈነበት እንዲሆን ብዙሃኑ ታጋይ እንደሚፈልግ በተጨባጭ አሳይቶናል።
ይህን ሁሉ ወዳኋላ ሄጄ ማስታወስ ያስፈለገኝ፣ በአንድ በኩል፣ በአፋብን አናት ላይ የሰፈነውን የተዛባ እሳቤ እና አሰራር የሚያሳይ ተጨባጭ ማሳያ ስለሆነና፣ በሌላ በኩል፣ የአባላት መብት እንዲከበር ጥያቄ በማቅረባችን የተሰጠን ምላሽ በአጋጣሚ የተፈጠረ ስህተት እንዳልሆነ አፅእኖት ለመስጠት ነው። ይህ የተዛባ እሳቤ እና አሰራር ግለሰቦችን ሊጎዳ ይችላል። ይበልጥ የሚጎዳው ግን ድርጅትን እና ዓላማን ነው። ግለሰብን ማሰርም መግደልም ይቻላል። እውነትን ማሰር እና መግደል ግን አይቻልም።
ያቀረብነው የአባላት መብት ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ አግኝቶ ቢሆን ኖሮ፣ ውሳኔያቸው ቀኝም ይሁን ግራ በአለት ድንጋይ ላይ እንደቆመ ቤት ወጀብን የሚቋቋም ይሆን ነበር። ያ ሳይሆን ግን ቀርቷል።
አሁን ያለአባላት ተሳትፎ እና ውሳኔ ተቋቁሟል የተባለው “ጽምዶ/ትብብር” በአሽዋ ላይ እንደቆመ ቤት ወጀብን መቋቋም የማይችል ነው።ይህ በአማራ የህልውና ትግል ላይ የተፈፀመ ታላቅ በደል ነው። በዚህ ልክ ነገሮችን ማመዛዘን የሚችል መሪ የሌለን በመሆኑ ከልብ ባዝንም፣ በእግዚአብሔር እመካለኹና በትግሉ ተስፋ አልቆርጥም። ፈጣሪ በዚህ ትግል ውስጥ ብዙ ተዓምራትን አሳይቶናል። ወደፊትም ያሳየናል።
አፋብን የህግ በላይነት የተከበረበት ቤት እንዲሆን የተጀመረው ህጋዊ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ፈጥኖም ሆኖ ረፍዶ፣ በጽምዶ/ትብብሩ ዙሪያ የአባላት ድምፅ ወሳኝ ይሆናል። በዚህ ሂደት እስር እና ግድያ ያጠናክረናል እንጂ አይበግረንም።
እስክንድር ነጋ፣
የአፋብን አባል።
መስከረም 12፣ 2019 ዓ.ም
—
ግልባጭ :-
— ለአፋብን አባላት እና ደጋፊዎች
— ለመገናኛ ብዙሃን (ለህዝብ)
— ለማህበራዊ ሚዲያ (ለህዝብ)


















