“.. የእስክንድር ደህንነት ያሳስበኛል ..”
ልደቱ አያሌው
የልደቱ አያሌው የሞተቺዋን ህወሃት ለመታደግ በሚያደርገው ትንቅንቅ ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ በጽምዶ ላይ የያዘውን አቋም ምክንያት በማድረግ በአርበኛው ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የቅስቀሳ ፕሮግራም እስከመስራት ደረሰ
ጋዜጠኛ ወንድወሰን ተክሉ
የእድሜ ልክ የህወሃት ታማኝ አገልጋይና በህወሃት ፍቅር ልቡ እስኪቀልጥ ድረስ ህወሃት ወይም ሞት እያለ ያለው ልደቱ አያሌው ህወሃት መራሹን ጽምዶ ያልተቀበለ ሁሉ የብልጽግናው አገዛዝ አገልጋይና ደጋፊ ነው እያለ በመፈረጅ ተግባር ላይ በመጠመድ ለዚሁ ስራ ብሎ በጀመረው የግል ዩቲውብ፣ቲክቶክና ፌስ ቡኮችን በመክፈት ዘመቻውን እያሳለጠ ባለበት ሁኔታ ዛሬ ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋን አጀንዳው በማድረግ 47 ደቂቃ የፈጀ ፕሮግራም ሰርታል።
“እስክንድር ነጋና የፖለቲካ አቋሙ [ የእስክንድር ደህንነት ያሳስበኛል ]..” በሚል ርእስ ስር ባሰራጨው ባለ 47 ደቂቃ ቪዲዮ ልደቱ አያሌው የታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ ደህንነት ያሰበ በመምሰል ህይወቱ አደጋ ላይ ነው በሚል “መፍትሄ” ብሎ ያሰበውን በማር የተለወሰ መርዛማ መልእክት አስተላልፋል።
እንደ ልደቱ አያሌው አገላለጽ ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ ከህወሃት፣ኦነግና ጉምዝ ታጣቂ ጋር መስራት አይቻልም ብሎ ጽምዶን ያለመቀበሉና በዚህም ምክንያት እራሱን ከአፋብን አባልነት ያገለለበትን ውሳኔውን ፍጹም ስህተት በማለት ከገለጸ በኃላ ዘመነ ካሴ ለአርበኛው በጻፈው ደብዳቤ “… በድርጅታችን መተዳደሪያ ደምብ መሰረት ተጠያቂ እንደሚሆኑ አሳስባለሁ ..” ብሎ የገለጸውን ቃል አፋብን በእስክንድር ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ስላለ መወሰድ ያለበት እርምጃ ይህን መሆን አለበት በማለት ለአርበኛው ያሰበ በመምሰል ሀሳብ ሲያቀርብ ተደምጣል።
የአዲስ ኮምፓሱ ኤርሚያስ ለገሰ ደግሞ ዲያስፖራ ያሉ ሶስትና አራት ግለሰቦች ለህወሃት አመራሮች በጻፉት ደብዳቤ በታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ እርምጃ እንዲወሰድ ብለው በጠየቁት መሰረት ህወሃት በዘመነ ካሴ በኩል በአርበኛው ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የሚል ውሳኔ ማስተላለፋን የገለጸ ሲሆን በዲያስፖራ ሆነው በአርበኛው ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ለህወሃት ደብዳቤ ከጻፉት ውስጥ አንዱ ልደቱ አያሌ መሆኑን በመጥቀስ በውስጥ ለውስጥ እርምጃ ይወሰድበት እያለ ደብዳቤ ይጽፋል አደባባይ ወጥቶ የእስክንድር ደህንነት ያሳስበኛል በሚል አርእስት ፕሮግራም ይሰራል ሲል የልደቱን ፕሮግራም አላማና ግብ በውስጥ ያሴረውን ሴራ የመደበቂያ ቅድመ ፕሮግራም አድርጎ ሲገልጸው ተደምጣል።
የአዲስ ኮምፓሱ ኤርሚያስ ለገሰ “..የእስክንድር ርሸና..” በሚል ርእስ ስር እና የለደቱ አያሌ አያሌው “.. የእስክንድር ነጋ ደህንነት ያሳስበኛል ” በሚል አርእስት በአንድ ቀን እና በአንድ ሰዓት ልዪነት በታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ ላይ የታቀደ እቅድ ስለመኖሩ ፍንጭ የሚሰጥ ሆኖ እናየዋለን። የኤርሚያስ ለገሰ ፕሮግራም ከተጀመረ በኃላ ልደቱ በተመሳሳይ አርእስት ላይ ፕሮግራም መጀመሩን ስንመለከት ምናልባትም ልደቱ የኤርሚያስን ፕሮግራም አይቶ የጀመረ ነው ብለን ከመገመት የዘለለ የምንገልጸው ነገር ባይኖርም የኤርሚያስን ወደ ጎን አድርገን ወደ ልደቱ ፕሮግራም ስንመለስ የሚከተሉትን አንካር ነጥቦችን ማውጣት እንችላለን።
የልደቱ አያሌው አንኳር ነጥብ
ልደቱ አያሌው የአርበኛ እስክንድር ነጋን ከህወሃት ጋር መስራት ያለመቻል ጉዳይ ለማስረዳት አርበኛው በነጻ ፕረስ ጀምሮ በጸረ ህወሃት አቋሙ ጸንቶ የዘለቀ ነው ሲል ይገልጸዋል። የ1997ቱን ምርጫ በማንሳትም እስክንድር ወደ ፓርላማ እንዳንገባ ባደረገብን ተጽእኖ ቅንጅት ፓርላማ ሳይገባ ቢቀርም እኛ ግን ፓርላማ ገብተን በፍርሃት መቀመጫቸውን ጥለው የቀሩ አባላቶች ነበሩን በማለት ታላቁን አርበኛ ሲከስ ተደምጣል።
እጅግ የገረመኝ ነገር እስክንድር በወቅቱ በሳምንት በሚታተሙ ሶስት ጋዜጦች ምንሊክ፣ አስካል እና ገናናው በእኛ ላይ ይዘምት ነበር ብሎ የገለጸበት ሲሆን ገናናው ጋዜጣ የእስክንድር ሳይሆን የጋዜጠኛ ዘገዬ አየለ መሆኑን እንካን የማያውቅ ሆኖ ነው። ( በነገራችን ላይ ልደቱ አያሌው ስለመአህመድ እና በእስክንድር ሲታተሙ በነበሩ ጋዜጦች ጉዳይ ላይ የጠቀሳቸው ሁሉ የተዛቡና እውነትነት የሌላቸው መሆናቸውን በቅደም ተከተል በሌላ ጽሁፍ እመለስበታለሁ)
እንደ ልደቱ አያሌው አገላለጽ የታላቁ አርበኛ እስክንድር ጸረ ህወሃት አቋም እድሜ ልኩን የዘለቀ ነው ይልና ዛሬ ላይ የአማራ ፋኖ ከህወሃት፣ ኦነግና ጉምዝ ታጣቂ ጋር መጣመር አለመቀበሉ የማያስገርም ነው ይልና ውሳኔው ግን ትክክል ያልሆነ ጸረ ፋኖ ነው በማለት ሲወነጅለው ይደመጣል።
የእድሜ ልክ የህወሃት አፍቃሪ እና ታማኝ አገልጋይ የሆነው ልደቱ አያሌው ለምን እና እንዴት ህወሃትን እድሜ ልኩን ለማገልገል እንደፈለገ ፈጽሞ ሳይነግረን ህወሃትን ይቃወማል፣ ህወሃትን አይቀበልም ያለንን አርበኛ ጽምዶን ያለመቀበሉ ውሳኔ ትክክል አይደለም በማለት ሲገልጽ ይሰማል።
ይህንንም መሰረት አድርጎ ታላቁ አርበኛ ከአፋብን አባልነት ለቆ በመውጣቱ ዘመነ ካሴ በጻፈለት ደብዳቤ እርምጃ እንወስድብሀለን ሳላለው እርምጃው መሆን ያለበትን እስክንድርን ከትግሉና ከሀገር እንዲወጣ ማድረግ ነው በማለት ለታላቁ አርበኛ ደህንነት ያሰበ በመምሰል አቅጣጫ ሲያመላክት ተደምጣል።
ከህወሃት ጋር ባለኝ ያልተገባ ድብቅ ፍቅር እስክንድርና ሲሳይ አጌና እጅግ ያወግዙኝና ይጽፉብኝ ነበር ብሎ የተበዳይነትን ስሜት ያስተጋባው ልደቱ አያሌው መለስ ብሎ ለታላቁ አርበኛ ደህንነት አሳቢና ተቆርቃሮ በመምሰል በማር የተለወሰ መርዝ ሲያቀብል ነው ያመሻው።
ለመሆኑ ከጸረ አማራዎቹ ህወሃት፣ ኦነግና የጉምዝ ታጣቂ ጋር የአማራ ፋኖ አብሮ መጣመር የለበትም የሚለው አቃም በምን ስሌት ነው ጥፋት ሆኖ የሚገኘው ብላችሁ ልደቱን ብትጠይቁት የሚመልስላችሁ መልስ ጭፍን ባለ ሁኔታ ከብላሉግና እና ከህወሃት መካከል አንዱን ምረጥ፣ ጽምዶን ያልተቀበለ ሁሉ ብልጽግናን መደገፍ ማለት ነው ብሎ የፍረጃ መልስ ከመስጠት የዘለለ የሚሰጠው አጥጋቢ ምላሽ የለውም።
ሆኖም ግን ህወሃት ሲኦል ብትወርድ ከህወሃት ጋር ሲኦል ወርዶ ድጋፉን ለመስጠት የማያመነታው የእድሜ ልክ የህወሃት አገልጋይና አፍቃሬ ህወሃት የሆነው ልደቱ አያሌው በታላቁ አርበኛ ላይ ይዞት የከረመውን ቂም በቀል ለመወጣት ወቅቱ አሁን ነው በማለት የአቅሙን የጥቃት ፍላጻውን ለመወርወር ሞክራል።
ሆኖም ግን 47 ደቂቃ በፈጀው ፕሮግራሙ ልደቱ አያሌው በአርበኛው ላይ ዘመን ተሻጋሪ ቂም ያለው እና ለህወሃት የእድሜ ልክ ፍቅር እንዳለው ሰው የሁለቱ ስሜት ድምር ውጤት ይዘቱ ከፊሉ ጥቂት እውነት አብዛኛው ፍጹም መሰረተ ቢስ ውሸት የተሞላበትን መልእክት በማስተላለፍ ታላቁን አርበኛ ለመበቀል ሲጋጋጥ የሰማነውን ፕሮግራም ለመስራት እንደቻለ ነው መረዳት የቻልኩት።
በቀጣይ ስለ ጋዜጦች በገለጸበት ሁኔታ ላይ ምን ያህል የተዛባ መረጃ እንዳስተላለፈ በቅደም ተከተል በማቅረብ ምላሹን አቀርባለሁ።
ልደቱ አያሌው ህወሃትን ለመታደግ የሚያደርገው መጋጋጥ ህወሃትን ከመካነ መቃብር ፈጽሞ አይታደጋትም። አበቃሁ።


















