የዛሬ 52 ዓመት

‘’የ60 ሰዎች አስክሬን ደረሰኝ’’

ምሽቱን በትዕዛዙ መሰረት ሰዎቹ ተገደሉ። የወሕኒ ቤቱ አባል ሻምበል ነጋሽ ማሞ የ60 ሰዎችን አስክሬን ተረክቦ ደረሰኝ ሰጠ። 60ኛው በዛው ዕለት ከደርጉ ጋር ተዋግተው እራሳቸውን የገደሉት የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የመጀመሪያው ሊቀመንበር የነበሩት የሌ/ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም አስክሬን ነበር።በግድያው ወቅት በተባራሪ ጥይት የቆሰሉ የደርግ ወገኖች ማንነት ተረጋግጦ በደርጉ የሕክምና መኮንን በመ አለቃ እንዳለ ገላን በኩል ሕክምና ተደረገላቸው።

ባለ ሥልጣናቱ ላይ እነማን ተኮሱ?

ለደርጉ ሃላፊዎች አዲስ አበባ ወህኒ ቤት ግቢ ውስጥ በአካል ተገኝተው የአፄ ኃይለስላሴን ጄኔራሎችና ሚኒስትሮች ተኩሰው የገደሉ የደርግ አባላት ስም ዝርዝርና የተኮሱት ጥይት መጠን በሻለቃ ጌታቸው ሺበሺ ሪፖርት ተደረገ። በዚሁ መሠረት፣

ሻለቃ ጌታቸው ሺበሺ- 43 ጥይት

ሻምበል ተፈራ- 32 ጥይት

ሻምበል ኃይሌ መለስ- 25 ጥይት

ባሻ ተፈራ ጅፋር- 60 ጥይት

፶/አለቃ በቀለ ደጉ- 32 ጥይት

ፒ/ኦ ሚካኤል- 25 ጥይት

፶/አ ዳምጤ- 16 ጥይት

ወታደር ደጀኔ አ/አገኘሁ- 40 ጥይት

ወታደር ገ/ጊ ብርሃኑ- 50 ጥይት

ሻለቃ ባሻ ለማ ኩምሳ- 7 ጥይት

ም/፲/አ ግርማ አየለ-3 ጥይት

(በፌ.ከ.ፍ.ቤት ወነጀል መዝገብ ቁጥር 1/87(401/85) ውስጥ የ ልዩ አቃቤ ህግ ማስረጃ ድ.1.9.3)

በግድያው ላይ በጠቅላላው 393 ጥይቶች መተኮሳቸው ተረጋገጠ። ይህ ቁጥር በደርግ አባላቱ ብቻ የተተኮሰውን የሚያካትት እንጂ በሌሎች ወታደሮች የተተኮሰውን አይጨምርም።

የመጨረሻዋ ሰዓት ምን ትመስል ነበር?

ግድያው ሲፈፀም የነበረው የዓይን እማኝ ይናገራል

“ሥራ ጨርሼ ከቀኑ አስር ሰዓት ስወጣ በር ላይ ትዝ እንደሚለኝ አስር አለቃ ገረመው እንዳትወጡ ተብለናል አለኝና ቆየሁ። አስራ አንድ ሰዓት ተኩል በሚሆንበት ጊዜ አስር አለቃው ከመሣሪያ ግምጃ ቤት ካቴና አውጡ አለንና አወጣን። ከዚህ በኋላ ሻምበል ባሻ ደጀኔ የሚያሽከረክረው እስረኛ ማጓጓዢያ ከባድ መኪና ውስጥ ግቡ ተባልንና ከገረመው ጋር ገባን።

ሌሎች እነ እከሌ የማልላቸው ሁለት ወይም ሦስት የጦር ሠራዊት አባላት ጭምር ያሉባቸዉ መኪናዎች እየመሩን በግምት ከ12፡30 እስከ አንድ ሰዓት መካከል አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ገባን እንደገባን ቤተ መንግሥት ግቢ ዉስጥ ፎቅና ምድር ቤት ያለዉ ሕንፃ ፊት ለፊት አዙሩና አቁሙ አሉን። መኪናዉ ቆመ ወረድን። አካባቢዉን ስናይ ባዉዛ ይበራል ፣ ፀሀይ ሆኗል። ዙሪያዉ በታንክ ተከቧል። ሚሊታሪ ፖሊስ በብዛት አለ።

እኛ ከጠሪዎች ሶስት እርምጃ እርቀን እስረኞቹ ከምድር ቤቱ በየተራ በየስማቸዉ እየተጠሩ ወጥተዉ እኛ ዘንድ ሲደርሱ በተሰጠን ትዕዛዝ መሠረት የአንዱን እስረኛ ግራ እጅና የሌላኛውን እስረኛ ቀኝ እጅ አንድ ላይ በማድረግ በካቴና እናቆራኛቸዋለን። ከዚያ በኋላ መኪና ላይ ሚሊታሪ ፖሊሶች ያሳፍራሉ። በዚኽ አይት በግምት ከሃምሳ በላይ ሰዎች ተቆራኝተዉ መኪና ላይ ተጫኑ፣ መኪና ዉስጥ ገባንና ጉዞ ተጀመረ።”

የሟቾቹ ሚኒስትሮች እና ጄኔራሎች የመጨረሻ ቃል ምን ነበር?

“በጉዞ ላይ እስረኞቹ የትነዉ የሚወስዱን ወቴ ሲሉኝ እኔም አላወኩም አልኳቸው። ሜክሲኮ አደባባይ ደርሰን ወደ ወህኒ ቤት መስመር መኪናዉ ሲጠመዘዝ ደስታ ተሰማቸዉና ወሕኒ ቤት ከገባን ጥሩ ነዉ ቤተ ሰቦቻችንም ይጠይቁናል ብለዉ ተወያዩ። ጉዞ ቀጠለና የአዲስ አበባ ወሕኒ ቤት ግቢ በር ተከፍቶ መኪናው እስረኞቹን እንደያዘ ሲገባ በመኪናው መብራት ሳንጃ ያለው መሳሪያ ይዘው የተደረደሩትን ወታደሮች እስረኞቹ ሲያዩ በመደናገጥ ተንጫጩ። ራስ መስፍንተንጫጩ፣ “ይህ ባርያ ሊፈጀን ነው› “ለፍርድ ሳንቀርብ፣ ፍርድ ይታይልን” እያሉ ጮኹ። ሌሎቹም ተንጫጩ አስተጋቡ። መኪናው ወደፊት ሄደና አዙሮ ቆመ።

እስረኞች ወርደው በሰልፍ መደዳ የሕንጻው ግንብ ከኋላቸው ሆኖ ቆሙ። የመኪና መብራት ይበራባቸዋል። ፊሽካ ድምጽ ተሰማ፡፤ ማን እንደነፋው አላውቅም። ሁለት ጊዜ እንደተነፋ ተኩስ ተከፈተ። ተኩስ የተከፈተው በተደረደሩት እስረኞች ላይ ነው። በርቀት ግቢ ውስጥ ምንም መሣሪያ ሳንይዝ በማናውቀው ኹኔታ በተፈጠረው ተኩስ ተደናግጠን እያለን በጥይት ጭንቅላቴን ተመታሁ። ሆስፒታል ገባሁ ከዚህ በኋላ የሆነውን አላውቅም።”

“መጀመሪያ እኔን ግደሉኝ” -ኮሎኔል ያለም ዘውድ ተሰማ

ስለ ግድያው አፈፃፀም ኮሎኔል ተስፋዬ ወ/ስላሴ ሰብሳቢው አጠገብ ሆኖ ሂደቱን በመገናኝ ሬዲዮ ይከታተል ነበር። በስተመጨረሻም የግድያው ዋና አስፈፃሚ ሻለቃ ጌታቸው ሺበሺ ከተገዳዮቹ መካከል ኮሎኔል ያለም ዘውድ ተሰማ እየፎከሩ “መጀመሪያ እኔን ግደሉኝ” እንዳሉ ጄኔራል አሰፋ አየነ “እጠቅማችኋለሁ አትግደሉኝ” እንዳሉ ከርሸናው በሁዋላም ቀብራቸው መፈፀሙን ሪፖርቱን ለጉባኤው አቀረበ። ታሪክም እያንዳንዷን መዝግቦ እንዲህ አኖረ።

ምንጭ:- ፍኖተ አበው ዘ ኦርቶዶክስ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.