ለአቶ ልደቱ አያሌው፣ — ከእስክንድር ነጋ፣

 ለአቶ ልደቱ አያሌው፣

ከእስክንድር ነጋ፣

ጉዳዩ—ስለ ትግራይ እና ኦሮሞ ወገኖቻችን እና ስለእኔ ስለተናገሩት።

በቅድሚያ፣ የከበረ እና ልባዊ ሰላምታዬን አቀርብልዎታለኹ። ስለ እኔ የተናገሯቸው መልካም ነገሮች ከእኔ ይልቅ ለእርስዎ የሚገቡ እንደሆኑ ሳልጠቅስ ባልፍ እውነትን መበደል ይሆንብኛል። እነዚህ በጎ ነገሮች ሁሉ በምድር ብቻ ሳይሆን በሰማይም እንዲታሰቡ የፈጣሪ መልካም ፍቃድ ይሁንልዎ።

ከ40 ደቂቃ በላይ በፈጀው የቪዲዮ መልዕክትዎ በርካታ ጉዳዮችን አንስተዋል። የተቃኘው ረዥም ዘመን መሆኑን ግምት ውስጥ ስናስገባ፣ እውነታዎች እና ህፀፆች መደባለቃቸው የሚገርም አይደለም። ሕፀፆቹ ሆን ብለው የተፈበረኩ ናቸው አልልም። መስተካከል እንዳለባቸው ግን ይሰማኛል። ይህንን የምለው “መልካም ስሜን” ለመከላከል ሸንጦኝ አይደለም። በሕፀፆቹ ውስጥ ያሉት ሃሳቦች በመንታ መንገድ ላይ በቆመው በአማራ የህልውና ትግል ውስጥም የሚገላበጡ ናቸውና፣ ከጀርባ ታሪካችን ብንማር መልካም መስሎ ስለታየኝ ነው። ከታሪክ የማይማር ስህተቶቹን ይደጋግማል፣ ወደኋላ እንጂ ወደፊትም አይጓዝም።

ሕፀፆቹን በሁለት ከፍያቸዋለኹ። ቀዳሚው የእኔን የፖለቲካ ታሪክ እና እምነት በሚመለከት የታባሉት ናቸው። እነዚህን በፅሁፍ ምላሽ ከምሰጥባቸው፣ ገለልተኛ አወያይ ባለበት እና በቀጥታ ስርጭት ፊት ለፊት ብንነጋገርባቸው ደስ ይለኛል።በተለይ፣ “በብሄር ፖለቲካ ላይ የተካሄደ ህዝበ–ውሳኔ (ሬፈረንደም) ነበር” ልንለው ስለምንችለው ምርጫ 97 ብዙ የምንዳስሳቸው ነገሮች እንዳሉ ይሰማኛል። ምርጫ 97 ስለ “ትብብሩ” ፋይዳም እጣ ፋንታም ብዙ የሚያመላክተን ነገሮች አሉ።

በፖለቲካ እምነቴ ላይ እርስዎ ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ግን፣ በይደር ላስቀምጠው የማልችለውም የማልፈልገውም ጉዳይ አለ። የዚህ ፅሁፍ ዓላማም በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በአጭሩ የሚያጠነጥን ነው። ይኸውም፣ በትግራይ እና ኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ “የጥላቻ ፖለቲካ” እንደማራምድ፣ ወይም የግል ጥላቻ እንዳለኝ በሚያስመስል መልኩ የተናገሩት ነው።

በሁለት ምክንያቶች ይህ ፈፅሞ ሐሰት ነው። ትልቁ እና ቀዳሚው ኃይማኖታዊ ነው። በትውልዴም፣ በአስተዳደጌም፣ በኑሮዬም አብዛኛውን ህይወቴን ባህላዊ ክርስቲያን ሆኜ ነው ያሳለፍኹት። በእስር ቤት ቆይታዎቼ ግን፣ ክርስትና ምን እንደሆነ እንዳውቅ እድል ያገኘኹበት አጋጣሚ ሆኖልኛል። ለዚህ ነው በረዥሙ ዓመታት የእስር ቆይታዎቼ የማልማረረው።

ክርስትና ብርሃን ነው፣ ጨለማም አያሸንፈውም። ብርሃኑ ፍቅር፣ ጨለማው ጥላቻ ነው። ስለዚህም፣ የክርስትና ወርቃማ ህግ “ጎረቤትህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” የሚለው ትዕዛዝ ነው። ማን ነው ጎረቤቴ? ትግራይም ኦሮሞም ናቸው ። በምንም ምክንያት ጎረቤቱን የሚጠላ (ጨለማ) ክርስቲያን (ብርሃን) መሆን አይችልም። የክርስትና ጥልቀት እና ፈተና የሚጀምረውም የሚያበቃውም ጎረቤት ላይ ነው።

ኃይማኖቴን በዚህ ልክ የማውቅ፣ የምረዳ፣የማምን እና በዚያ ልክ ለመኖር የምታትር ነኝ።ለብርሃን እንጂ ለጨለማ ቦታ እንዳይኖረኝ ሁሌም በትግል ላይ ነኝ። እንደ ሰው ከሁላችንም የሚጠበቀውም የምንችለውም በዚህ ልክ እንድሆን ነው። ልብን የሚያነበው ፈጣሪ ይህን ያውቅልኛል።ሌላውም ቢያውቅልኝ ደስ ይለኛል።

ወደ ሁለተኛው እና ፖለቲካዊው ምክንያት ደግሞ ልሂድ። ጥላቻ “ፓኬጅ” ነው። ብዙ ነገሮችን ያዘለ ጉዳይ እንጂ፣ በነጠላ ነገር ላይ የሚንጠለጠል ስሜት አይደለም።
እንደማሳያ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሽታ(the disease of Ethiopian poltics) የሆነውን የአማራ ጥላቻ (Amhara Phobia) እንመልከተው።

የአማራ ጥላቻ “ፓኬጅ” የሚጀምረው ፋሺስት ጣሊያን ስሪት ከሆነው የፈጠራ ታሪክ ነው። በዚህ የፈጠራ ታሪክ ወራሪ ብሄር እና ተወራሪ ሉዓላዊ ብሄር ብሄረሰቦች አሉ። በወረራው የተፈፀመ የፈጠራ እልቂት አለ፣ ወረራው ያጠፋው ምናባዊ “በጎ ዘመን” አለ፣ ከወረራው ቦኃላ “የተናቀ” ባህል አለ፣ “እየተዳከመ” ያለ ቋንቋ አለ፣ “ገዢ መንግሥት እና ተገዢ ህዝብ” አለ፣”በዝባዥ መደብ እና ተበዝባዥ ህዝብ” አለ። የዚህ ሁሉ መቋጫ ሆኖ ደግሞ፣ በወራሪ እና ተወራሪ መካከል የሚደረግ የ”ነፃነት” እና የ”ፀረ–ነፃነት” ትግል አለ። ትርክቱ መነሻ፣ መሃል እና መቋጫ አለው። የጥላቻ ፖለቲካ በዚህ ልክ የተቀመጠ ፓኬጅ ነው።

ታዲያ፣ የእኔ ጥያቄ፣ የትኛውን ፓኬጅ ይዤ ነው እኔ በትግራይ እና ኦሮሞ ላይ ወደ ፖለቲካ የሚመነዘር “ጥላቻ፣” ወይም “የጥላቻ ፖለቲካ” የሚኖረኝ? የሚል ነው። ለአማራ የተፈበረከለት “የጥላቻ ፓኬጅ” የለም። አማራ “በዚህ ዘመን ተወረሬ የተቀማኹት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት አለ” የሚለው ነገር የለም። “ባህሌ ተናቀ፣ ቋንቋዬ ተዳከመ፣ ነፍጠኛ ሰፈረብኝ” ብሎ አያውቅም። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ “አማራ ሉዓላዊ ብሄር ነው” የሚል ተረት–ተረት የለውም ።ለዚህም ነው ሕወሓት በስልጣን ዘመኑ አማራን ሲከስ የኖረው “በትምክህት” እንጂ በጥላቻ ያልነበረው።

በመጨረሻም፣ ጥላቻ ያለው “ሉዓላዊነታችንን ተገፈፍን” ከሚሉት የብሄርተኞች ሰፈር እንጂ፣ ራሱን ለመከላከል ሲል ብቻ በማንነቱ ለመደራጀት እና ለመታገል ከተገደደው አማራ ሰፈር አይደለም። ሀገራዊው እውነታ ይህ ነው። የእኔም ቁመና ከዚህ ውጭ አይደለም፣ ሊሆንም አይችልም።

ፈጣሪ ሀገራችንን ይጠብቅልን !!!

ህዳር 2፣ 2019 ዓ.ም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.