አርሲ፤ ወልቃይት እና ራያ እንደ ማሳያ…ታሪክ ራሱን ሲደጋግም
ሲሳይ ሙሉ
ኢህአዴግ የአራት ፓርቲዎች ግምባር ሆኖ ሀገር ሲመራ የአማራ “ወኪል” የተባለው ብአዴን የነበረው ሚና ከታዛዥነት እና የጸረ አማራ ፕሮጀክቱ ተባባሪ ከመሆን የዘለለ አልነበረም፡፡ ጥቂት ሁነቶችን እንደ ማሳያ እናንሳ፡፡ ከመጀመሪያዎቹ የብአዴን መስራቾች አንዱ ታምራት ላይኔ ወያኔ ስልጣኑን በያዘ ማግስት አማሮች በሀረርጌ እና አካባቢው በጅምላ ሲጨፈጨፉ “አማራ እዚህ ምን ሲሰራ መጣ፤ ይሄ እናንተን ሽርጣም እያለ ሲሰድባችሁ እና ሲያዋርዳችሁ የኖረ ነፍጠኛ ነው በሉት” ብሎ ለገዳዮች ኦነጎች እና የኢህአዴግ መስራች አንዱ ለሆነው ኦህዴድ የልብ ልብ ሰጥቶ ለአማራው መከታ ከመሆን ይልቅ በኢህአዴግ ጥላ ስር ሆኖ ከአማራው ገዳዮች ጋር ግንባሩን በአማራ ህዝብ መቃብር ላይ ለ27 ዓመታት እንዲቀጥል ሆነ፡፡ እንዲሁም በአንድ ወቅት አንድ ከወለጋ እየተሳደደ መጠጊያ ያጣ አማራ ለአገኘሁ ተሻገር ስልክ ይደውልና ጉዳዩን ሲያስረዳቸው የእሳቸው ምላሽ “እዛው ራስህን ቻል፡፡ እዛው አካባቢ ላሉት አመራሮች ተናገር እኛ ምንም ልናደርግልህ አንችልም” እንዳሉ የተቀዳ የስልክ ምልልስ አዳምጠናል፡፡
በተመሳሳይ የግጨው መሬት ለህወሃት በፊት ከተወሰደው ከወልቃይት ጠገዴ በተጨማሪ እንደምርቃት በይፋ የተሰጠበትን መንገድ ልብ ይሏል፡፡ ከአማራ ህዝብ ጥቅም እና ፍላጎት በተቃራኒ በመቆም ፤ ከ25 አመት በላይ በጉልበት የተወሰዱትንና በህዝበ ውሳኔ፣ በኮሚቴዎች እና በሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት ግጨው እና ጎቤ የአማራ መሬት መሆናቸው በተደጋጋሚ ተረጋግጦ የነበረም ቢሆንም በትግራዩ ፕሬዝዳንት አቶ አባይ ወልዱና በአማራው ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው የክልሎቹ አመራር ጠገዴ ወረዳ ላይ የተወሰኑና ህዝብ ያልመረጣቸውን ሰዎች በመሰብሰብ ስምምነት ደርሰናል ብለው ስምምነታቸውን በፊርማቸው አስቀመጡ፡፡ የብአዴን አመራሮች ባልተመረጡ ግለሰቦች በተቀነባበረ ስምምነት መሬቱን በፊርማ አሳልፈው ለህወሃት በመስጠት፣ የአማራዎችን መብት ነፍገው የአጋራቸውን የህወሃት ፍላጎት የይገባኛል ጥያቄ ለትግራይ ብለናል ብለው ነገሩን፡፡
ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ ግንቦት 6/2010 ዓ.ም “ብአዴን ሆይ ከእነ “እንቶኔ” የጡት ልጅነት መቼ ይሆን ነጻ የምትወጣው?” በሚል በጻፈው ጽሁፍ፤ ከግጨው ጋር በተያያዘ ሲያብራራ፡- “እኔ እስከማውቀው ድረስ አቶ በረከት ስምዖን የግጨው ጉዳይ ይነሳ በነበረበት መድረክ ሁሉ ለኩርማን መሬት ብላችሁ በየስብሰባው ይህን ጉዳይ እያነሳችሁ ታላዝናላችሁ እያለ የሰሜን ጎንደር ካድሬዎችን ያሸማቅቅ የነበረ መሆኑን ነው” ይላል፡፡ ከብዙ በትንሹ እንደማሳያ ይሆን ዘንድ እነዚህን ጥቂቶችን ጠቀስኩ እንጂ በዚህም ስራው ብአዴን ከአማራ ይልቅ ከጸረ አማራ ሀይሎች ጋር እንደሚቆም ያረጋገጠበት ሆኖ አልፏል፡፡
ዛሬም ትብብር በሚባለው ኦነግ እና ህወሃትን ያካተተው ትብብር የሚባል ስብስብም ስማቸው ይለያይ፤ ዘመኑም ይለያይ፤ አሁን ያሉበት ሁኔታም ይለያይ እንጂ እስካሁን ባየነው እና በታዘብነው መሰረት ኢህአዴግ ከሚባለው ጸረ አማራ ግምባር የተለየ አቋም እያራመደ አይደለም፡፡ በተደጋጋሚ የትብብሩ መስራች አባላት የሆኑት ኦነግ እና ህወሃት ከአማራ ህዝብ ጥቅም ጋር የሚጋጭ መግለጫ ሲሰጡ አማራው በዝምታ እንዲያልፈው ተደርጓል፡፡ ጥያቄ የሚያነሱ ሁሉ ልክ በብአዴን/ኢህአዴግ ዘመን ጥያቄ ያነሱ የነበሩ ሰዎች ነፍጠኛ እና ተስፋፊ የሚል ማሸማቀቂያ ስም ይሰጣቸው እንደነበረው ሁሉ አሁንም ትብብር የሚባለው አካሄድ ላይ ጥያቄ የሚያነሱትን አማሮች የብልጽግና ደጋፊዎች ፤ ፖለቲካ ያልገባቸው ባህላዊ አማራዎች እያሉ ማሸማቀቅ ይታያል፡፡ ለምሳሌ የህወሃት ሀይሎች በተደጋጋሚ እዚህ ጦርነት ውስጥ የገቡት ወልቃይት እና ራያን ለማስመለስ እንደሆነ በከፍተኛ ጦር አዛዦቻቸው፤ በሚዲያ እና የፖለቲካ ወኪሎቻቸው በኩል ደጋግመው ነግረውናል፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን የትብብሩ አባል ብቻ ሳይሆን የሊቀመንበርነት ቦታውን የያዘው አፋብን ትንፍሽ ያለው ነገር የለም፡፡ በቅርብ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የትግራይ ሀይሎች በራያ አካባቢ አዲስ የትግራይ አስተዳደር ለማቋቋም እየሰሩ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ አሁን በትብብሩ ደጋፊዎችም ሆነ በትብብሩ አባል አፋብን ምንም አይነት የተቃውሞ ድምጽ አልሰማንም፡፡ ተቃውሞ አለማሰማት ብቻ ሳይሆን በዚህ ዙሪያ ጥያቄ የሚያነሱትን ማሸማቀቁ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
በወልቃይት ጉዳይ ከበረከት ስምዖን የጠገዴ ንግግር ጋር ያለው ተመሳሳይነት ቃል በቃል የሚመሳሰል ነው። ህወሓት በወልቃይት እና ራያ ላይ በተደጋጋሚ የሚያነሳው የይገባኛል ጥያቄ የአካባቢውን ህዝብ ህልውና እና ደህንነት በቀጥታ የሚፈታተን በመሆኑ፣ የአማራ ወኪል ነኝ ብሎ «ትብብር»ን ከሚመራ ድርጅት የማያሻማ ህዝባዊ ምላሽ ይጠበቃል። አፋብን ግን አጋሩን ከመሞገት ይልቅ ዝምታን ሲመርጥ፣ ተቺዎችን ጸጥ ለማሰኘት የቀድሞ የማሸማቀቂያ ቃላት ዳግም አገርሽተው በረከት ስምዖን በአንድ ወቅት የሰሜን ጎንደር ካድሬዎችን ለ«ኩርማን መሬት» ብላችሁ ታላዝናላችሁ እያለ ያሸማቅቅ እንደነበረው ሁሉ፣ ዛሬም የጥምረቱ ደጋፊዎች እና አባላት በዚህ ዙሪያ ጥያቄ የሚያነሳውን ሁሉ «ለቁራጭ መሬት» እና «ለሰሊጥ ንግድ» ብላችሁ እያሉ ያንቋሽሻሉ። የማሸማቀቅ ስልቱ ከኢህአዴግ ዘመን አልተለወጠም፡፡ ዛሬም ከአማራን ህዝብ ጥቅሞችን እና ፍላጎቶች በተጻራሪ የቆሙትን “አጋሮች” እንደአማራ ቆመው ሳይጋፈጡ…”ማንን ታሸንፋለህ ቢባል ሚስቴን” እንዳለው የወንድ ግማሽ የመሬት፣ የማንነት እና የደህንነት የህልውና ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ጥያቄ የሚያነሱ የአማራ ወገኖች ላይ ይዘምታሉ።
በራያም አካባቢ ደግሞ ይኸው አጋርን ያለመሞገት አቋም በጠገዴ ያልተመረጡ ሰዎች ስብሰባ የህዝብን ይሁንታ እንደተላለፈው ሁሉ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የትግራይ ኃይሎች በአካባቢው አዲስ የትግራይ አስተዳደር ለማቋቋም እየሰሩ ነው። በዚህም ጉዳይ አፋብንም ሆነ የ«ትብብር» ደጋፊዎች ምንም አይነት የተቃውሞ ድምጽ አላሰሙም። በዘመነ ህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን የነበረው ከጠገዴ እስከ ወልቃይት እና ራያ ያለው ሰንሰለት ዛሬም ድረስ ያልተበጠሰ ነው። በብአዴን ፊርማም ሆነ በአፋብን ስልታዊ ዝምታ፣ የአማራ ወኪል ነኝ የሚለው አካል የትግራይ አጋሩ አከራካሪ መሬቶችን ለመጠቅለል እና ለማስተዳደር ሲንቀሳቀስ በይፋ ለመከላከል ለመቃወምም ፈቃደኛ አልሆነም።
ህወሃት ለሚባለው የድሮ የብአዴን አጋር እና የአሁኑ አፋብን ተጣማሪ ወልቃይት እና ራያ ጠገዴን በተመለከተ የድሮው ብአዴን ተባባሪ የነበረውን ያህል፣ አርሲ የሀረርጌ እና የወለጋ ላይ አማራ ላይ የሚፈጸመውን የጅምላ ፍጅት በተመለከተም ብአዴን ለሌላኛው የኢህአዴግ አባል አጋሩ ኦህዴድ በተመሳሳይ ተባባሪው ነበር። የትብብሩ መስራች አባል የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) «ትብብር» በተመሰረተ በማግስቱ ኢትዮጵያን የማፍረስ አጀንዳውን እንዳልጣለ በተደጋጋሚ በይፋ አስታውቋል። ሰሞኑን ደግሞ በአርሲ በአማሮች እና በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በዘመነ ኢህአዴግ በኋላ በሀረርጌ አርሲ እና ባሌ የተፈጸመውን የጅምላ ጥቃት የሚያስተጋባ ጭፍጨፋ ሲፈጸም ኃላፊነቱን በይፋ እንደሚወስድ በመግለጫ ከማሳወቁም በላይ በቃል አቀባዩ በኩል ጥቃቱ እንደሚቀጥል እና ሟቾችም የትርፍ ጊዜ ታጣቂ እና ተዋጊዎች ናቸው ሲል ወንጅሏል።
ከአርሲው ጭፍጨፋ በኋላ የታየው ምላሽ «ትብብር» ከተጠቁ አማሮች ይልቅ የጥምረት አጋሮችን ስሜት እና ፍላጎት የመጠበቅ የብአዴንን መንፈስ እንዴት እንደወረሰ የሚያሳይ ነው። በመጀመሪያ አንዳንድ የ«ትብብር» ደጋፊዎች ጥምረቱን ከትችት ለመከላከል ሲሉ ለጭፍጨፋው ያለውን ኃላፊነት ለማስተባበል ሞክረው ነበር። ሆኖም የኦነግ ቃል አቀባይ በአደባባይ በሚዲያ ወጥቶ ጭፍጨፋውን የፈጸሙት እነሱ መሆናቸውንና ጥቃቱንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት ሲያውጅ እነዚያ ማስተባበያዎች በአሳፋሪ መልኩ ፈራረሱ። የትብብሩ አባል ኦነሰ በይፋ በአደባባይ መግለጫ ሰጥቶ እንኳ፣ በዘመነ ካሴ የሚመራው «ትብብር» በሀረርጌ እና በወለጋ ብአዴንን ያሳየው አይነት ተቋማዊ ሽባነት በሚያንጸብርው መልኩ እስካሁን ምንም ሳይል ዝምታን መርጧል። በአጠቃላይ፣ ሶስቱ የኢህአዴግ ሁነቶች እና ሶስቱ የ«ትብብር» አቻዎቻቸው አንድ ወጥ መስመር ይፈጥራሉ። ሀረርጌ እና ወለጋ በብ አዴን ዘምን የታዘብነውን ዛሬ በአርሲ ተንጸባርቋል፤ በጠገዴ በወልቃይት እና በራያ በኢሃዴግ ዘመን የታዘብነውን አሁን በአፍብን እና ብትብብሩ ዘመን እየኖርነው ነው። በሁለቱም ዘመናት ቀውሱ ከክልል ውጭ ያለን አካላዊ ህልውናው ፈተና ውስጥ ለግባውም ሆነ በክልሉ ውስጥ እየኖረ አማራ አይደለህም ተብሎ ለሚሳደደው ወገን የአማራ ወኪል ነኝ የሚለው አካል ከህዝባዊ መከላከያ ይልቅ ዝምታን እና አጋርን እና ተባባሪን ማስደሰትን መርጧል።
እንደ መውጫ…
በታሪክ ምዕራፎች ውስጥ ቅርጽ እና ስያሜ ቢለዋወጥም፣ የአማራን ህልውና እና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት የተሰጣቸው ወገኖች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከህዝቡ ይልቅ ለጥምረት አጋሮቻቸው ቅድሚያ ሲሰጡ የቆዩበት መንገድ በግልጽ አይተናል። በኢህአዴግ ዘመን የብአዴን ታዛዥነት እና የአጋሮችን ፍላጎት የማስጠበቅ አካሄድ በሀረርጌ፣ በወለጋ እና በጠገዴ ያስከተለውን መዘዝ አይተናል። ዛሬም በ«ትብብር» ስም በተዋቀረው ጥምረት ውስጥ የአፋብን ዝምታ እና የአጋር ኃይሎችን እንቅስቃሴ ያለመሞገት አዝማሚያ በአርሲ፣ በወልቃይት እና በራያ ተመሳሳይ ስጋቶችን እና ቀውሶችን እያስከተለ ይገኛል። የጥያቄዎችን ማፈን እና ተቺዎችን በስም ማሸማቀቅም ከትላንቱ የማይለይ ሆኖ ቀጥሏል።
በመጨረሻም፣ ዋነኛ አጀንዳቸውን እና የቆሙለትን ጸረ አማራ ዓላማ በግልጽ ካሳወቁና ከቀደሙት ፍትሃዊ ጥያቄዎች ጋር የሚጋጩ አቋሞችን ከሚያራምዱ ተጻራሪ ወይም ጠላት ኃይሎች ጋር ጥምረት መፍጠር፣ የህዝብን ጥቅም ከማስጠበቅ ይልቅ የአማርን ንየህውና ትግል የሚያዳክም እና በአንጻሩም የብልጽግናን አገዛዝ እድሜ ሚያራዝም መሆኑን ብዙዎች አስቀድመው አስጠንቅቀዋል። ዛሬ እየታዩ ያሉት ክስተቶችም በተለይም የአጋር ኃይሎች በግልጽ የሚወስዷቸው እርምጃዎች እና በ«ትብብር» በኩል የሚታየው ምላሽ አልባነት ብዙዎች አስቀድመው እንደተነበዩትና እንደተናገሩት ይህ ትብብር ለአማራ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን እያረጋገጠ ይገኛል።”
@amorawwub


















