ኤርትራ ከመግባታችሁ በፊት እንድታስቡበት!

ኤርትራ እውነተኛ ትግል ያለ መስሎን ከ11ዓመት በፊት “ለእናት ሀገሬ ልሰዋ ደሜም እንደ ጅረት ይፍሰስ” እያልን በማዜም በወቅቱ የነበረውን የህውሓት/ኢህአዴግ ዘመን የመረጃ ሰንሰለቶችን አልፈን በሞትና ህይዎት መካከል ተረማምደን ኤርትራ ስንገባ የገጠመንን ለታሪክ ይሆን ዘንድ “የተሰለለው ሰላይ” በሚለው መጽሐፌ ላይ እጅግ በጣም በጥቂቱ ለመዳሰስ ሞክሬአለሁ። ታሪክ ራሱን ደገመ ለማለት በሚያስችል መልኩ ለ50ዓመታት ከፋቲክ ጀምሮ ራሱን ያልቀየረው ሻቢያ፤ ለለውጥ እንታገላለን የሚሉ ወንድሞቻችንን በመሬቱ ተቀብሎ ከ1992 ዓ.ም ውጊያ ሽንፈት በኋላ በየ አቅጣጫው ተቃዋሚ አደራጅቶ ወደ ግዛቱ በማቅረብ የራሱን አላማ ብቻ ያስፈጽም እንደነበር ታሪክ ምስክር ነው።

ይህም ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ የተረጋጋ ሀገርና ህዝብ እንዳይኖር ለማድረግ ከህዝብ ጥቅምና ክብር ይልቅ በስልጣን ጥም ያበዱ ሁለትም ሶስትም ሰዎችን ሰብስቦ ድርጅት ናችሁ ይል የነበረበትን ጊዜ አሁን ደግሞታል።

ቀደም ሲል “እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ ታገሉ” በሚል አቋም አንድም ታጣቂ (ከአመራሮች ውጭ) ወደ መሬቱ አላስገባም ነበር። አሁን ግን ከወያኔ ጋር ወደኋላ ሲያፈገፍጉ ራሳቸውን ኤርትራ ያገኙት ወንድሞቻችን ቁጥራቸው ቀላል የሚባል ባለመሆኑና ሌላውንም ወደ ኤርትራ የመጥራት ፍላጎቶች ስለሚኖሩ በተለይም ጀግና አዋጊዎችን “ኤርትራ ገብታችሁ ስልጠና ካልወሰዳችሁ ስልጣን አንሰጣችሁም” በሚል ሊሰበስቧቸውና እንደኛ አስረው ሊያስቀምጧቸው መሆኑን ሳልናገር ማለፍ ስለሌለብኝ ነው የምጽፈው።

ኤርትራ የቅቤ ቅል ትመስል ከነበር በሶስት ወራት ውስጥ የርሃብ ማስታወቂያ የምትሰራ መስለህ ከአመራሩ ውጭ ያለው ሰራዊት መልኩ ተመሳሳይ እስኪሆን ድረስ መጠውለግህ እንደማይቀር ከወዲሁ ልነግርህ እፈልጋለሁ። ይህንን ስል ” ብንከሳ ብንጠወልግ ትግል ውስጥ ነው ያለነው” ልትል ትችላለህ። እዚያ መሬት ውስጥ እየታገልክ ሳይሆን ድንጋይ ተንተርሰህ ከጠላትህ ይልቅ እባብና ጊንጥ እንዳይነድፍህ የምትጨነቅበት ቦታ ነው። ከዛሬ ነገ ገብቸ እዋጋለሁ ስትል ከወራት አመታትን አስቆጥረህ መልክህ ከመልከ ዓምድሩ ጋር ይመሳሰላል እያልኩህ ነው።

ሌላው ፤ ያለ ሻቢያ ፍቃድ አንድም ቦታ ገብተህ ልትዋጋ አትችልም። እያንዳንዱ እቅድህን ለሻቢያ አሳውቀህ ነው የምትንቀሳቀሰው። እነሱ ካልፈቀዱ የምታደርገው ምንም ነገር የለም።
ዛሬ በትግል ላይ እያለህ እየደወልኽ ሚስትና ልጆችህን ታገኛለህ። ለመረጃም ቅርብ ነህ። ኤርትራ መሬት ግን ስልክ ሁሉም ይሰበሰብና ዜናዎችን የምትሰማው በዶቼቬሌ እና ቪኦኤ VOA&DW ብቻ ይሆናል። ወደ ድሮው ዘመን ወደኋላ ተመልሰህ ትኖራለህ።

ተከትለሃቸው የገባሃቸው አመራሮችህ በሻቢያ ዘንድ ቋሚ የወር ደመወዝ ክፍያ ያላቸው ሲሆንና እዚያው ኤርትራ ውስጥ የመንቀሳቀስ ፍቃድ ስለሚሰጣቸው አንተ በርሃብ አለንጋ ስትገረፍ በወደሓከር አሳር ስትበላ፤ እነሱ በየቀኑ ፍየል ምግባቸው ነው። አንተ በርሃብ እያለቅህ መሪዎችህ በጥጋብ ሊፈርጡ ከደረሱ ያልኩህን አስታውስ! ሻቢያ ከአመራር እስከ ሰራዊቱ ቦርጫም ሰው ፈልገህ የማታገኝ ሲሆን ” አንተን ነጻ ለማውጣት ነው የምታገልልህ” የሚሉ ሰዎች ጉማሬ መስለው ስታይ እንዳትደነግጥ ከወዲሁ እየነገርኩህ ነው።

በተግባር የነበረውን ትግል ወደ ፕሮፖጋንዳ ብቻ ይዛወርና ኤርትራ ውስጥ የተከማቸ 300ሺህ ጦር አለ ስትባል አምነህ ለመግባት እንዳትቸኩል። ሻቢያ ይህንን ያህል ጦር ለመመገብ አቅም የለውም። ያም ብቻ አይደለም የዚህን ያህል ቁጥር ይዘህ በመሬቱ እንድትደራጅ አይፈቅድልህም።

ከላይ ያለው እጅግ በጣም በጥቂቱ ነው የነገርኩህ። በቀጣይ ሰፋና ዘርዘር አድርጌ ትግሉን ለሻቢያና ወያኔ ለማስረከብ ለምን ተፈለገ? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ከ11 ዓመት በፊት የነበረ አሁንም በዚያ መንገድ እየተሄደ በመሆኑ ኑሬበት በማውቀው የትግል ታሪክ ውስጥ ለአዲስ ታጋዮች ንቃት እንዲሆን በማሰብ ተከታታይ ጹሁፎችን አደርሳለሁ።

  1. ምስል
    ከኤርትራ ከወጣሁ በኋላ ወደ ሱዳን የስደተኛ ካምፕ (ሸገራብ) በገባሁ ጊዜ ከርሃብ ማስታወቂያነት የተወሰነ አገግሜ ለማስታወሻ የተነሳሁት ነው📷
    ———————————–
    ከ @ስንታየሁ_ታከለ የፌስቡክ ገፅ የተወሰደ ✅
    ኤርትራ ከመግባታችሁ በፊት እንድታስቡበት!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.