በጽምዶ(ጥምረቱ)ትብብሩ ዙሪያ በአፋብን አባላት የተዘጋጀ የመወያያ ሰነድ

(ሰነድ 1)

መስከረም 2019 ዓ.ም።

መግቢያ—

ይህ ሰነድ በአሁኑ ሰዓት “አፋብን ከሌሎች ታጣቂ ኃይሎች ጋር እየተነጋገረ ስላለው የጽምዶ/ጥምረት/ትብብር ጉዳይ ፣ የትኛው የአፋብን አካል ነው የማፅደቅ ወይም የመወሰን መብት ያለው?” የሚለውን ጉዳይ መሰረታዊ በሆነ የአምክንዮ ተጠየቅ የጋራ መግባባት ላይ እንዲደረሰ እና የሂደትም ሆነ የአሰራር ግድፈት እንዳይፈጠር የተዘጋጀ የመወያያ ሰነድ ነው።

የቃላት ትርጓሜ :-

ምንም እንኳን “ጽምዶ” የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን ህዝቦች ለማቀራረብ ታስቦ የተጀመረ እንቅስቃሴ ቢሆንም፣ በሂደት በኢትዮጵያ ያሉ ታጣቂ ኃይሎችን በአንድ ጥላ ስር ለማሰባሰብ የተጀመረው ጥረትም መጠሪያ ሆኗል።

ይህ የመወያያ ሰነድ “ጽምዶ” የሚለውን ቃል የሚጠቀመው ድርጅቶቹን ለማሰባሰብ ከሚደረገው ጥረት ጋር በተገናኘ ብቻ ነው።

ጥያቄ—ይህ ሰነድ የሚዳስሳቸው የጽምዶ/የጥምረቱ /የትብብሩ ባለድርሻ አካላት እነማን ናቸው?

መልስ—

ጽምዶ/ጥምረቱ/ትብብሩ እንዲመሠረት ባለድርሻ አካላት ሆነው በንግግር ላይ የሚገኙት አፋብን፣ ሕወሓት፣ ኦነግ/ሸኔ፣ ጉምዝ፣ ወዘተ ናቸው።

በዚህ የመወያያ ሰነድ የሚዳሰሰው የአፋብን ጉዳይ ብቻ ነው።

ጥያቄ —- ወይይት የምናደርገው በምን ዓይነት ሥነ -ዘዴ እና አግባብ ነው?

መልስ :

ከከፍተኛ አመራር ጀምሮ በተዋራድ እስከ ተራ አባል ደረጃ ያሉ የአፋብን አባላት ይህን የውይይት ሰነድ በማንበብ፣ በግል ደረጃ የሃሳቡን ጭብጥ በመረዳት ግንዛቤ መጨበጥን ጨምሮ፣ በተለያዩ መድረኮች በሚደረጉ ውይይቶች ሃሳቦቹን በማንሳት እና በማንሸራሸር ይሆናል።

ውይይት ሲደረግ ይህ ሰነድ በተዘጋጀበት መልኩ፣ የጥያቄ እና መልስ (የሶክራተስ ዲያሎግ) ስነ ዘዴን መከተል ያስፈልጋል። ይህ ማለት የመወያያ መነሻ ጭብጡ በጥያቄ መልክ ይቀርብ እና በአመክኖያዊ መስፈርት ትክክኛ ነው ተብሎ የታመነበት መልስ ይቀመጣል።

በተሰጠው መልስ ላይ ተወያዮች ከአጠቃላይ የትግላችን ዓላማ እና አሰራር አኳያ እየመዘኑ ይወያያሉ፣ ይወስናሉ። በዚህ አግባብ እያንዳንዱ ጥያቄና መልስ ውይይት እየተደረገበት ወይ በስምምነት ይታለፋል ፣ወይ የሚጣለው ይጣላል፣ወይ አዳዲስ ሃሳቦች ከመጡ ይያዛሉ።

ጥያቄ — በአፋብን ከፖሊት ቢሮ እስከ ተራ አባላት ድረስ የተዘረጋ ድርጅታዊ መዋቅር ያለ በመሆኑ፣ በጽምዶ/ጥምረቱ/ትብብሩ ጉዳይ የትኛው የአፋብን አካል ነው የመወሰን መብት ያለው?”

መልስ —

በአንድ ድርጅት ውስጥ 4 የስልጣን አካላት እና እርከኖች አሉ 
1ኛ– አባላት፣
2ኛ– ጉባኤ፣
3ኛ– ማዕከላዊ ኮሚቴ፣
4ኛ— ሥራ አስፈፃሚ ናቸው።

ከእነዚህ መካከል፣ ከፍተኛው የሥልጣን እርከን አባላት ናቸው– አባላት የድርጅቱ ባለቤት ናቸው። (ህዝብ የትግሉ ባለቤት ነው።) ከአባላት በታች ጉባኤ፣ ከጉባኤ በታች ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ከማዕከላዊ ኮሚቴው በታች ሥራ አስፈፃሚው ወይም ፖሊት ቢሮው ናቸው።

እንደ ጉዳዩ ክብደት ወይ በአባላት፣ ወይ በጉባኤ፣ ወይ በማዕከላዊ ኮሚቴ ወይ በሥራ አስፈፃሚው ይወሰናል።

ጥያቄ—የአንድን ጉዳይ ክበድት እንዴት ነው የምንወስነው?

መልስ—

1ኛ— የሚወሰነው ጉዳይ የድርጅቱን ዓላማ የሚያስቀይር ወይም የሚነካ ሆኖ ሲገኝ፣ በአባላት ይወሰናል።

2ኛ — የሚወሰነው ጉዳይ የድርጅቱን ፖሊሲ የሚያስቀይር ወይም የሚነካ ሆኖ ሲገኝ፣ በጉባዔ ይወሰናል።

3ኛ— የሚወሰነው ጉዳየ ዓላማም ሆነ ፖሊሲ የማይነካ ከሆነ፣ በሥራ አስፈፃሚው ወይም በማዕከላዊ ኮሚቴው ይወሰናል።

የጽምዶ/ጥምረት/ትብብር ጉዳይ እላይ በተቀመጡት መሥፈርቶች ስንመዝነው፣ እንደ አማራ ፋኖ የቆምንለትን ዓላማ እና ፖሊሲ የሚያስቀይር በመሆኑ በቀጥታ ለአባላት ወርዶ ውይይት ተደርጎበት ውሳኔ ሊያገኝ የሚገባው ጉዳይ ነው።

ጥያቄ— ለምንድን ነው ጽምዶ/ጥምረት/ትብብር የአማራ ፋኖ የቆምንለትን ዓላማ የሚያስቀይር ወይም የሚነካ ነው የሚባለው?

መልስ—

እንደ አማራ ፋኖ ከህዝብ የተቀበልነው ተልዕኮ እና ግብ በአማራ ህዝብ ላይ በተለይ ባለፉት 8 ዓመታት (ማለትም ብልፅግና መንግሥት ከሆነ ግዜ አንስቶ) የተከፈተውን የጅምላ የዘር ጭፍጨፋ ከምንጩ ማስቆም ነው።

ባለፉት 8 ዓመታት፣ በአማራ ላይ የጅምላ የዘር ጭፍጨፋ የፈፀሙት አካላት ማንነት በተለያዩ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ አካላት (የተባበሩት መንግስታት ጄኖሳይድ ቢሮ፣ ሂውመን ራይትስ ዋች፣ አመንስቲ ኢንተርናሽናል፣ጄኖሳይድ ዋች) በማስረጃ ተረጋግጧል። በአማራ ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ የፈፀመው የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት ብቻ አይደለም።

እነዚህን የጅምላ ጭፍጨፋዎች ፈፅመዋል ተብለው በዓለም አቀፍ ተቋማቱ በማስረጃ ከተለዩት መካከል የሚከተሉት አካላት ይገኙበታል:-

1ኛ— የኦህዴድ/ብልፅግና መንግስት።

የአማራ ፋኖ የትጥቅ ትግል ዋነኛ መነሻ ምክንያት እና የግቡ ዒላማ ኦህዴድ/ብልፅግና በአማራ ላይ የፈፀማቸው መንግስታዊ የጅምላ ጭፍጨፋዎች ናቸው።

ይባስ ብሎ፣ ኦህዴድ/ብልፅግና ከፈፀማቸው የጄኖሳይድ ጥቃቶች በላይ፣ ሥልጣኑ አደጋ ላይ ቢወድቅ ሊፈፅመው የሚችለው ጄኖሳይድ የሚያሰጋ ነው። የአማራ ፋኖ የትጥቅ ትግል የግድ በድል መጠናቀቅ ያለበት በዋናነት ይህን አደጋ ለመታደግ ነው።

2ኛ— ኦነግ/ሽኔ።

ከተመሠረተ ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ኦነግ ፅንፈኛ ክንፍ የሆነው ኦነግ/ሸኔ ድርጊቶች ብዙ ቢሆኑም፣ እንደ ምሳሌ፣ በ2014 በወለጋ በአንድ ቀን ብቻ ከ2000– 3000 የማያንሱ የአማራ ህፃናት፣ ሴቶች እና አረጋዊያንን በጅምላ የጨፈጨፈ የአል–ቃይዳ የመንፈስ ወንድም ነው።

በዚህ ድርጊት የሞቱት ንፁሃን ቁጥር፣ ከሩዋንዳ ጄኖሳይድ ቦኃላ በአንድ ቀን በተፈፀመ የማንነት ጭፍጨፋ በዓለም የአንድኝነትን ደረጃ የያዘ ነው።

3ኛ— ሕወሓት።

ሕወሓት ከስልጣን ከወረደ ቦኃላ በማይካድራ በአማራ ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ የፈፀመ ነው።

ይህ አልበቃ ብሎ፣ የጅምላ ጭፍጨፋውን በማይካድራ የፈፀመውን “ሳምሪ” ብሎ በሥልጣን ዘመኑ ያደራጀውን የጄኖሳይድ ቡድን በአሁኑ ግዜ በሱዳን ትልቅ ወታደራዊ ኃይል አድርጎ የገነባ እና ይኸው የጄኖሳይድ ኃይል ወልቃይትን በኃይል እንዲይዝ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ዝግጅት እያደረገ የሚገኝ ነው።

በተጨማሪም፣ ስልጣን ላይ በነበረ ግዜ በወሊድ ቁጥጥር ሽፋን በዓለማችን የመጀመሪያውን ሰኬት “ድምፅ አልባ ጄኖሳይድ” በአማራ ህዝብ ላይ የፈፀመ ነው።

4ኛ—ጉሙዝ ነፃ አውጪ።

የአማራ ህፃናትን መርዝ በተቀባ ቀስት በመግደል በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በማስረጃ የተደገፈ “ልዩ ዝና” ያተረፈው “የጉምዝ ነፃ አውጪ” ተብዬው፣ አማራን በቁጥር የአንደኝነት ቦታ ካለው መተከል ዞን ለማጥፋት ካለው የአደባባይ ቅዠት ባሻገር፣ ከፖለቲካ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውን የአባይ ግድብን ወታደራዊ ዒላማ አድርጎ በመንቀሳቀስ የሚታወቅ ነው።

አፋብን ከእነዚህ አራት ኃይሎች ጋር የሚያደርገው ስምምነት ወይም ስምምነቶች፣ የአማራ ፋኖ ከህዝብ በተቀበለው “ጄኖሳይድን ከስር መሠረቱ የማድረቅ” ዓላማ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪም የሚያስቀይር ወይም ተፅእኖ የሚያሳድር መሆኑ ግልፅ ነው። ስለዚህም፣ የድርጅቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ለሆነው መላው አባል ቀርቦ መፅደቁ ከሞራልም፣ ከህግም፣ ከፖለቲካም፣ ከታሪክም አኳያ ግድ ነው።

ጥያቄ — አባላት ሳይወያዩ እና ሳይፈቅዱ ከሕወሓት፣ ኦነግ/ሸኔ እና ጉምዝ ነፃ አውጪ ጋር በአመራሩ ውሳኔ ብቻ ስምምነት ቢደረግ፣ ምን ችግር አለው?

መልስ —

1ኛ —የአፋብን አባላት ሳይወያዩ እና ሳይፈቅዱ ከሕወሓት፣ ኦነግ/ሸኔ እና ጉምዝ ነፃ አውጪ ጋር ዛሬ የሚደረግ ስምምነት፣ ነገ እና ተነጎዲያ የአፋብን አባላት ሳይወያዩ እና ሳይፈቅዱ ከብልፅግና ጋር የሚደረግ ስምምነት እንዲኖር ሁኔታዎችን የሚያመቻች ነው።

2ኛ —-3ኛ—-4ኛ ብለን ሊዘረዘሩ የሚችሉ ተጨማሪ ከበባድ ችግሮች አሉ። እነሱን ግን ለግዜው እንለፋቸው።

ጥያቄ–-ምን ቢደረግ ነው ጥሩ የሚሆነው?

መልስ —

1ኛ — ሥራ አስፈፃሚው ከጽምዶ/ጥምረት/ትብብር ከሚላቸው ድርጅቶች ጋር የጀመረውን ድርድር ይጨርስ። ጥሩ ናቸው ባላቸው የስምምነት ነጥቦች ላይም የአባላት ውሳኔ የሚያስፈልገው የመግባቢያ ሰነድ ያዘጋጅ።

2ኛ — እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሰ ቦኃላ ግን፣ የመግባቢያ ሰነዱን በአባላት ለማፀደቅ ወደ ሠራዊቱ ይውረዱ እና ውይይት ይደረግባቸው።

3ኛ— ከውይይት ቦኃላ ድምፅ ይሰጥ እና የብዙሃኑ አባላት ድምፅ የድርጅቱ አቋም ይሁን።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.