ግርማ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)
ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ገጽታ ማስጠንቀቂያ
(When Intellectualism Gives Way to Cadre Politics: A Warning to the Ethiopian Political Landscape)
አንኳር ነጥቦች፤
የረጅም ዓመታት በማኅበራዊ ታታሪ አንቂነት እና በሰብአዊ መብት ተሟጋቾችነት ተሳትፎዬ፤ አንድ ጠቃሚ ነገር ተምሬአለሁ። አንድ የነፃነት ትግል፤ በገለልተኛ ምሁራዊ አስተሳሰብ ቦታ፤ የፖለቲካ ስምምነት የሚኖረው አካሄድ ሲመረጥ፤ እራሱን ወደፊት ሊያራምድ አይችልም። ሆኖም፣ ዛሬ፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ፤ ይህ አደጋ ነው ስጋቴን እየጨመረው የሄደ። በፖለቲካ ልሂቃን እና በፖለቲካ ታታሪ አንቂዎች መካከል ያለው ልዩነት፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ መጥቷል። የበለጠ የሚያስጨንቀው ደግሞ፤ የካድሬ አስተሳሰብ ተብሎ ሊገለጥ የሚችለው ግንዛቤ፤ተጽዕኖው እያደገ መምጣቱ ነው። ከገለልተኛ ግምገማ ይልቅ፤ የፖለቲካ ባህል ርዕዮተ ዓለም ታማኝነት የበላይነት ያገኘበት፣ የተለዬ ሃሳብ ማቅረብ፤ ታማኝነት እንደ ጎደለው ተደርጎ የሚወሰድበት፣ እና በተያዘው ዋና የፖለቲካ መስመር ላይ ጥያቄ ማቅረብ እንደ ክህደት ተደርጎ የሚተረጎምበት ጉዳይ!
በተለይ አሁን የዐማራ ህልውና ትግልን የጉዞ አቅጣጫ በሚመለከት በሚደረገው ውይይት፤ ይህ ጉዳይ በጣም አሳሳቢ ነው። የፖለቲካ ስልት ንድፍን፣ ጥምረትን፣ድርድርን፣ ወታደራዊ ትብብር፣ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ጋር ያለውን ግንኙነት፤ እና የኢትዮጵያ የወደፊት የፖለቲካ ሥርዓትን የሚመለከቱ ጥያቄዎች፤ እጅግ በጣም ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው። ስለሆኑም፤ በፖለቲካ ታማኝነት ወይም በቡድን ጫና ሊወሰኑ አይገባቸውም።እኒህ ጉዳዮች፤ አይነኬ ሳይሆኑ፤ ምንም እንኳን ፈታኝና የማይመቹ ቢሆኑም፤ ጥብቅ ምሁራዊ ምርመራ፣የአደባባይ ውይይቶች፣ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ አመክንዮ እና ተቀባይነት ያገኙ ሃሳቦችን በድፍረት መጋፈጥን ይጠይቃሉ። የፖለቲካ ልሂቅ ካድሬ አይደለም። የአንድ የፖለቲካ ልሂቅ ኃላፊነት፤ ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት፣ ለአንድ ቡድን፣ ለአንድ መሪ ወይንም ተቀባይነት ላገኘ የፖለቲካ መስመር፤ ጥብቅና መቆም አይደለም። ይልቁንም ሃሳቦችን መመርመር፣ማስረጃዎችን መፈተን፣ ተቃርኖዎች እንዳሉ ወይንም እንደሌሉ አገላብጦ ማየት፣ አማራጭ ዕይታዎችን ግምት ውስጥ ማስገባት እና ሊከሰቱ የሚችሉ ውጤቶችን ማጤን ነው። የፖለቲካ ታታሪ አንቂዎች እና ድርጅቶች፤ ሕዝቡን መቀስቀስና የፖለቲካ ግባቸውን ማሳካት መጣር፤ ሕጋዊ ሚናቸው ነው። ይሁን እንጂ፤የፖለቲካ ልሂቃን፤ ቀደም ሲል ለተደረጉ ውሳኔዎች፤ሕጋዊነት ለማስገኘት አስተናጋጅ መሆን የለባቸውም።የፖለቲካ ልሂቃን፤ ምንም እንኳን ጠቅላላ የእንቅስቃሴውን ግብና ዓላማ የሚጋሩት ቢሆንም፤ ከዚህ አቀንቃኞች የተወሰነ ርቀት እንዲኖር፤ ሚናቸው ግድ ይላል። አብዛኛውን ጊዜ እራሳቸውን፤ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከመንግስት ሥልጣን እንደ “ነፃ ተንገዋላይ” አድርገው፤ ለይተው ያስቀምጣሉ። ሆኖም በተለምዶና በተመክሮ፤ ተጨባጩ ሀቅ የሚያመለክተው፤ ከዚህ የሚመኙት እውነታ የተለዬ መሆኑን ነው። የፖለቲካ ልሂቃን በተለያዩ ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ አውዶች ውስጥ፤ ሁልጊዜም ነፃ ነን ለሚሉት እውነታ፤ ተገዢ ሆነው አልተገኙም። ይልቁንም በየጊዜው የምሁራን ነፃነትን፣ የፖለቲካ ድጋፍን፣ የተቋም ፍላጎትን እና የማህበረሰቡን ኃላፊነት በሚመለከት፤ ጠንከር ያሉ ውጥረቶች ገጥሟቸዋል። በዚህ ጦማር፤በፖለቲካ ልሂቅነት ውስብስብ ህይወት ውስጥ ጠልቄ በመግባት፤ እነዚህን ውጥረቶች በጥልቀት መመርመር እፈልጋለሁ። የፖለቲካ ልሂቅ መሆን ማለት ምን ማለትነው? በፖለቲካ በተወጠረ መድረክ ዙሪያ፤ እንዴት ነው የፖለቲካ ልሂቅ ነፃነትን ሊጠበቅ የሚቻለው? እናስ የፖለቲካ ልሂቃን ሊፈትሿቸው ከሚጠበቅባቸው ድርጅቶች፣ እንቅስቃሴዎች ወይም የሥልጣን አካላት ጋር ተቆራኝተው ሲገኙ ምን ይሆናል? እነዚህ ትልልቅ እና ውስብስብ ጥያቄዎች ናቸው፤ እናም እዚህ ላይ ያለኝ ቦታ በዝርዝር እንድሄድባቸው አያስችለኝም። በዚያ ፈንታ፤ በፖለቲካ ልሂቅ ህይወት ማዕከላዊ ማጠንጠኛ የሰፈሩትን ውጥረቶችና ጭንቀቶች ላይ፤ የራሴን አንዳንድ ግንዛቤዎች አቀርባለሁ።
የፖለቲካ ልሂቃን፤የፖለቲካ ድርጅቶች አስተናጋጅ ቀኝ እጆች ሲሆኑ፤የፖለቲካ ልሂቅነት ነፃነት ይበረዛል። የተለዬ ሃሳብ ይዞ መገኘት ታማኝነት እንዳጎደለ ሲወሰድ፤ እውነተኛውይይት አስቸጋሪነቱ እየጨመረ ይሄዳል። እናም፤ በኃላፊነት ለተቀመጡት የፖለቲካ ተስማሚነት ማሳየት ገምጋሚ አስተሳሰብን ሲተካ፣ አንድ የነጻነት ንቅናቄ፤እኒያኑ አቸንፎ ሊያስወግዳቸው የተነሳውን አምባገነናዊ ባህሪያት እና የፖለቲካ ባህሎች፤ እንደገና የማባዛት ሂደት ያጋጥመዋል። ይህ የየፖለቲካ ልሂቅነት ችግር ብቻ አይደለም፤ የፖለቲካ እና የዕቅድ ቅንብርም ችግር ነው።
የዐማራ ህልውና ትግል፤ አስቸጋሪ እና ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችን የሚያስከትሉ ምርጫዎች ባጋጠሙበት ወቅት፤ ትችቶችን የሚያቀርቡ ድምፆችን ማፈን አያዋጣውም። ወታደራዊ ጥምረቶች፣ የፖለቲካ አጋርነቶች፣ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወገኖች ጋር የሚፈጠሩ ግንኙነቶች፣ እና የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በሚመለከት የሚቀርቡ የተለያዩ ዕይታዎች፤ ለጥልቅና ጥብቅ ምርምር በራቸው ክፍት መሆን አለበት። ማንም ድርጅት፣ መሪ፣ የፖለቲካ ልሂቅ፣ ወይንም የፖለቲካ ቡድን፤ የትክክለኛ ፖለቲካ መስመርን በብቸኝነት ያዥ መሆን የለበትም። አንድ የነፃነት ትግል፤ እውነትም የነፃነት ትግል እስከሆነ ድረስ፤ የተለያዩ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ ክፍት ቦታ መፍጠር ይገባዋል።በትችትና በክህደት፣ በገለልተኛ ትንተና እና በፖለቲካ ጥብቅና፣ እና በየፖለቲካ ልሂቅ ኃላፊነትና በፖለቲካ አቀንቃኝነት መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ አለበት።በአምባገነን የፖለቲካ ስርዓቶች ታሪክ ውስጥ ጥልቅ ትምህርት አለ። የፖለቲካ ታማኝነት፤ የፖለቲካ ልሂቅነት ሕጋዊነት ዋና መለኪያ ተብሎ በሚወሰድበት ጊዜ፤ገለልተኛ አስተሳሰብ ጥሎ መሸሽ ይጀምራል። ገለልተኛ አስተሳሰብ ሲዳከም ደግሞ፤ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ለስልታዊ ስህተቶች፣ ለውስጥ አምባገነንነት፣ ለቡድን አስተሳሰብ እና ጉዳዮችን ለሚፈልጉት ግብ ማገልገያ አድርጎ ለመውሰድ መጓተት ተጋላጭ ይሆናሉ። ስለዚህ፤ዓላማው፤ በአንድ የተወሰነ የፖለቲካ ሰፈር ውስጥ፤ክርክሮችን ከማሸነፍ የበለጠ መሆን አለበት። ለሀቀኛ የነጻነት ትግል፣ ለዴሞክራሲ፣ የክብር እና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ትግል አስፈላጊ የሆነውን የፖለቲካ ልሂቅነት እና የፖለቲካ ጉዳዮች መወያያ መድረክ ቦታን መጠበቅ መሆን አለበት። የዐማራ ትግል ድርጅት ያስፈልገዋል፤ በአኳያውም ነፃ የሆኑ አስተሳሰብ አራማጆችም ያስፈልጉታል። የፖለቲካ ታታሪ አንቂዎች ያስፈልጉታል፤ ነገር ግን የፖለቲካ ልሂቃንን ካድሬዎቹ ማድረግ የለበትም። አንድነት ያስፈልገዋል፣ አንድነት ግን አንድ ዓይነት ሃሳብ ያላቸው ብቻ የተሰበሰቡበት ማለት አይደለም። የዐማራ የህልውና ትግል የወደፊት ዕጣ ፈንታ፤ እና በተስፋም የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ፤በእኔ እምነት ይህንን ልዩነት በመጠበቅ ላይ የተመሠረተነው።
ስለራሴ አቋምም ግልጽ መሆን እፈልጋለሁ።ኢትዮጵያ መሠረታዊ የፖለቲካ ለውጥ ያስፈልጋታል ብዬ አምናለሁ፣ እናም የበለጠ ዴሞክራሲያዊ፣ ተጠያቂነት፣ሁሉን አቀፍ እና ፍትሃዊ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲኖር አስተዋፅዖ የሚያደርጉ የፖለቲካ ሂደቶችን እደግፋለሁ።ቢሆንም ግን፤ የፖለቲካ ለውጥ እንዲኖር መፈለጌ፤ ለውጡን እደግፋለሁ ብሎ የቀረበውን እያንዳንዱን የፖለቲካ ወይም ወታደራዊ ተዋናይ፣ ጥምረት፣ስትራቴጂ ወይም የይገባኛል ጥያቄ እንድደግፍ አይጠበቅብኝም። የፖለቲካ ለውጥ እና በፖለቲካ አመለካከት አንድ ወጥነት አንድ አይደሉም። አሁን በቅርቡ፤ በዐማራ ፋኖ እና በሌሎች የታጠቁ ቡድኖች መካከል ባለው ጥምረት ዙሪያ ያለውን ፈታኝ ውጥረትና መከፋፈል እየተገነዘብኩ መጥቻለሁ። ስለእነዚህ የመጣመር ሂደቶች በቂ እውቀት አለኝ አልልም።በሁሉም የፖለቲካ እና ወታደራዊ ተለዋዋጮች ውስጥ ራሴን አስገብቼ በበቂ አልተከታተልኩም። እናም በነኚህ ጥምረቶች ዙሪያ በያንዳንዱ ጉዳይ ላይ አቋም መያዝ ያስቸግረኛል። ከተለያዩ በዓለም ዙሪያ ካሉ ሰዎች፤ ለምን ግልጥ የሆነ አቋም እንድልወሰድኩና ባደባባይም ያንኑ እንዳላቀነቀንኩ ጠይቀውኛል። ምን ጊዜም ቢሆን የኔ መልስ፤ ሁኔታውን በጥንቃቄ እየተመለከትኩ ነው! የሚል ነው። መረጃዎች ያልተሟሉ በሆኑበት ሀቅ፣የሚሠጡ ትንተናዎች በጥልቅ ወገንተኛ ሲሆኑ፣ እናም የተለያዩ ፍላጎቶችን፣ ግቦችን እና የዕቅድ ንድፎችን የያዙ ተዋናኞች ሲበዙ፤ አቋም መያዝ ያስቸግራል። ውጤቱ፤ ከፍ ባለ ደረጃ እርግጠኛ አለመሆን እና ግራ መጋባት ነው።
ቸኩዬ አቋም ለመውሰድ ፈቃደኛ ለመሆን አለመጣደፌ፤ ለፖለቲካ ለውጡ ግድየለሽነት ተደርጎ ሊተረጎም አይገባውም። በተገላቢጦሹ፣ እንደዚህ ዓይነት ታሪካዊ ክብደት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ያሉ አቋሞች፤በፖለቲካ ጫና ወይም በቡድን ታማኝነት ሳይሆን፤በትክክለኛ መረጃዎች፣ በዐውደ–ጽሑፍ፣ ጥንቃቄ በተሞላበት ትንተና እና በምሁሯዊ እውነተኝነት እንዲሆን አጥብቄ መቆሜን ያሳያል። በተለይ እኔን ያሳስቡኝ፤ በእነዚህ የመወያያ ጉዳዮች ዙሪያ፤ የስም መቀባባት፣ የግለሰብ መጠቃቃቶች፣ እና የአስከፊ ቃላት ውርጅብኞች ናቸው። ሰዎች ትክክለኛ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ወይም አለመግባባቶችን በይፋ ለመግለጽ ሲፈሩ፤ የፖለቲካ ውይይት ሂደቱ ጥራት፤ ይታመማል።እንዲህ ዓይነቱ ድባብ፤ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ ሽግግርን ለማስከተል የሚፈልግ ማንኛውም እንቅስቃሴ፤ አደጋ ነው። ይህንን ስጋት የሚደግፉ ተጨባጭ ምልከታዎች አሉኝ። የጓደኞች ወይም የሚግባቡ ሰዎች ስብስብ በመሆን የተጀመረ የዋትስአፕ ቡድን ውስጥ፤ለጥያቄዎች ወይም ለዐማራጭ አመለካከቶች የሚሠጡ ምላሾች፤ እየጠነከሩ ሲሄዱና አልፎ ተርፎም ወደ ጠንካራ ጥላቻ ሲያድጉ ተገንዝቤአለሁ። ማሸማቀቅ ብዬ የምገልጠው – አንድን ሀሳብ ወዲያውኑ ማሳነስ፣ውድቅ ማድረግ፣ ማጣጣል ወይም አለመቀበል፤በሂደቱም ጠያቂውን ወይም ጥያቄውን እራሱን፤መወገድ ያለበት እንቅፋት አድርጎ መሰየም – እያደገ መምጣቱ ታይቷል። የግለ ሰብ ተክለ ሰውነትን ማግዘፍን የሚመስል እንካ ስላንትያ፤ በጥልቅ አሳሳቢ እና አንዳንዴም አሳፋሪ በሆነ መልክ ሲቀነቀን ተገንዝቤአለሁ። ቀደም ሲል ታልፈዋል የተባሉት የፖለቲካ አምልኮ እና ፍጹም ታማኝነት/ተገዢነት እንደገና ሲያቆጠቁጡ ማየት ግራ ያጋባል። ምናልባትም፤የዚህ ዓይነቱን የፖለቲካ ባህል፤ ከብዙ አሥርተ ዓመታት በፊት አልፈናል ብለን አምነን ነበር።
እኔ እንግዲህ፤ለፖለቲካ ለውጥ ድጋፍ እና ለተወሰኑ የፖለቲካ ተዋናዮች ትችት የሌለው ድጋፍ ማድረግን በግልጥ እለያለሁ። ገለልተኛ አስተሳሰብን፣ ሂሳዊ ጥያቄን እና የውስጥ አለመግባባትን መታገስ የማይችል እንቅስቃሴ፤እፈልጋለሁ የሚለውን እውነተኛ ነፃ ማህበረሰብ ለመገንባት ተግዳሮት ያጋጥሙታል። የፖለቲካ ሽግግር ማድረግ፤ ከመንግስት ወይም ከፖለቲካ አመራር ለውጥ በላይ ይጠይቃል። የሃሳብ ልዩነት፣ ጥብቅ ፍተሻ፣ተጠያቂነት እና ገለልተኛ አስተሳሰብ የሚጠብቅ የፖለቲካ ባህልንም ይጠይቃል። ኢትዮጵያ ጥንቃቄን በሚጠይቅ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። የዐማራ ሕዝብ የወደፊት ዕጣ ፈንታም፤ ውጤታቸው የሚያናጋ ሊሆን በሚችል ሂደቶች እየተቀረጸ ነው። ይህ በበኩሉ፤የበለጠ ግልጥነትን፣ የፖለቲካ ልሂቅነት እውነተኛነትን እና በጥንቃቄ የታሰበበት የወደፊት መሄጃን ይጠይቃል።በጅ ያሉ ማስረጃዎችን መመርመር ያስፈልጋል።ተፎካካሪ ትርጓሜዎችን መመልከት ያስፈልጋል።የፖለቲካ ግኝቶችን ከርዕዮተ ዓለም አቋሞች፤ እና በተጨባጩ ሀቅ ላይ የተመሠረተ ትንታኔን መለየት አለብን። መደምደሚያዬ ቀጥተኛ ነው፤ የፖለቲካ ለውጥን እደግፋለሁ፣ ነገር ግን የፖለቲካ ለውጥ የፖለቲካዊ ልሂቅና የሃሳብ አንድነትን ይጠይቃል ብዬ አላምንም። የፖለቲካ ልሂቃን፣ ተመራማሪዎች፣ጋዜጠኞች እና ሌሎች ገለልተኛ አሳቢዎች፤ ከማስረጃ፣ከታሪካዊ አውድ፣ ከተፎካካሪ አመለካከቶች እና ከአስቸጋሪ ጥያቄዎች ጋር በግልጥ እንዲከራከሩባቸው ይለቀቅ። የፖለቲካ ታታሪ አቀንቃኞች እና የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የራሳቸው የሆነ ሕጋዊ ሚና አላቸው። ነገርግን፤ እነዚያ ሚናዎች፣ ገለልተኛ የፖለቲካ ልሂቃን ጥያቄን መተካት የለባቸውም። ይህ ልዩነት ወሳኝ ነው።አንድ ሰው፤ ጥንቃቄ በተመላበት መንገድ፣ ሁኔትውን እየመረመረ፣ ያንን ለውጥ እንወክላለን ከሚሉት ተዋናዮች በልሂቅና ግንዛቤ ነፃ ሆኖ፣ የፖለቲካ ለውጥን አስፈላጊነት ሊደግፍ ይችላል። ለእኔ ይህ ገለልተኛነትም ሆነ ፖለቲካዊ ግዴለሽነት አይደለም። ይልቁንስ፤ በተለይ ነፃ የሆነ ገለልተኛ አስተሳሰብ አስፈላጊ በሆነበት ወቅት፤ለምሁራዊ ገለልተኝነት ጥብቅና መቆም ነው። ዘላቂ ድርጅታዊ እድገት እና እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ሽግግር እንዲካሄድ፣ የነጻነት እንቅስቃሴዎች ግብረመልስን፣ መቻቻልን እና ትህትናን በንቃት ማዳበር አለባቸው። አንድ ጤናማ የፖለቲካ ባህል፤ ጭፍን ታማኝነትን ወይም የርዕዮተ ዓለም አጎብዳጅነትን ከመጠየቅ ይልቅ፤ ገንቢ ትችትን ማበረታታት፣ለውስጣዊ የሃሳብ ልዩነት በር መክፈት፣ እና አንድም አንጃ በእውነት ላይ ሙሉ ባለቤትነት እንደሌለው ለመገንዘብ፤ የፖለቲካ ልሂቅነት ትህትናን ማዳበር አለበት። አንድ ንቅናቄ፤ ትክክለኛ መረጃን በማስቀደም፣ገለልተኛ አስተሳሰብን በመጠበቅ እና ለሃሳብ ልዩነት ቦታ በመሥጠት፤ የውስጥ አምባገነንነት እንዳይነሳ መከላከል ይችላል። በሂደቱም ሊገነባ ለሚፈልገው ነፃ ኅብረተሰብ የፖለቲካ ልሂቅና እና ዲሞክራሲያዊ መሠረት ሊጥል ይረዳዋል። እውነተኛ የነጻነት ትግል፤ በራሱ የውስጥ መዋቅር ውስጥ፣ የሃሳብ ልዩነቶችን ማስተናገድ መቻል አለበት። ጥያቄዎችን በትዕግስት ለማስተናገድ የሚያስችል ጥንካሬ፤ የሚቀርቡ ትችቶችን ለመጋፈጥ ብቁነትን፣ እና የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶችን በማፈን የፖለቲካ አንድነት ሊገነባ እንደማይችል የመገንዘብ ችሎታ ሊኖረው ይገባል።
ትግሉ ቆርጠው የሚቆሙለት ሰዎችን ይፈልጋል – ከዚያ ላይ ግን፤ ለማሰብ ነፃ የሆኑ ሰዎችንም ይፈልጋል።
Bourdieu, P. (1988). Homo academicus (P. Collier, Trans.). Stanford University Press. (Original work published 1984)
Gregg, A. P., Mahadevan, N., & Sedikides, C. (2017). Intellectual arrogance and intellectual humility: Correlational evidence for an evolutionary-embodied-epistemological account. The Journal of Positive Psychology, 12(1), 59–73. https://doi.org/10.1080/17439760.2016.1167942
Hendriks, F., Kienhues, D., & Bromme, R. (2016). Disclose your flaws! Admission positively affects the perceived trustworthiness of an expert science blogger. Studies in Communication and Media, 16, 124–131.
Jensen, J. D. (2008). Scientific uncertainty in news coverage of cancer research: Effects of hedging on scientists’ and journalists’ credibility. Human Communication Research, 34(3), 347–369. https://doi.org/10.1111/j.1468-2958.2008.00324.
Konrád, G., & Szelényi, I. (1979). The intellectuals on the road to class power. Harcourt Brace Jovanovich.
Osman, M., Heath, A. J., & Löfstedt, R. (2018). The problems of increasing transparency on uncertainty. Public Understanding of Science, 27(2), 131–138. https://doi.org/10.1177/0963662517711058
Petersen, M. B. (2021). COVID lesson: Trust the public with hard truths. Nature, 598, 237. https://doi.org/10.1038/d41586-021-02758-2
Porter, T., Elnakouri, A., Meyers, E. A., Shibayama, T., Jayawickreme, E., & Grossmann, I. (2022). Predictors and consequences of intellectual humility. Nature Reviews Psychology, 1(9), 524–536.
Preston, J. L., & Shin, F. (2017). Spiritual experiences evoke awe through the small self in both religious and non-religious individuals. Journal of Experimental Social Psychology, 70, 212–221. https://doi.org/10.1016/j.jesp.2016.11.00

















