የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (OLA) ዋና አዛዥ አቶ ኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) ቃለ ምልልስ የአፋብን ጥቂት ከፍተኛ አመራሮችን በአማራ ሕዝብ፣ በአፋብን አመራርና በአፋብን ሰራዊት ላይ ሲፈጽሙት የነበረውን ታላቅ ቅጥፈት ቁልጭ አድርጎ አጋለጠ-!
“…በአዲስ አበባ፣ በወለጋ፣ በደራ፣ አንደራደርም…የኦሮሚያ ምድር ቀይ መስመራችን ነው…” ኩምሳ ድሪባጃል መሮ
አፋብን በተንበርካኪና ጥገኛ ጥቂት አመራሮቹ የአማራንና የኢትዮጶያን ሕዝብ ህልውና ለአደጋ እየዳረገ ነው!
ጋዜጠኛ ወንድወሰን ተክሉ
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (OLA) ዋና አዛዥ የሆነው አቶ ኩምሳ ድሪካ በትግል ሜዳ ስሙ ጃል መሮ ዓርብ መስከረም 8 ቀን 2019 “Dhangaa Torbanii” ( የሳምንቱ እንግዳ) ከሚል ከራሳቸው የትግል ሚዲያ ጋር 1 :28 ደቂቃ የፈጀ ቃለ ምልልስ አድርጋል። በቃለ ምልልሱ አቶ ኩምሳ ድሪባ በወቅታዊው የኦነስ (OLA ) እንቅስቃሴ ላይ በተለይም ስለጽምዶ፣ ጥምረት፣ አጋርና ትብብር እየተባሉ ስለሚጠሩ አሰላለፎች ዙሪያ የሚመራውን ድርጅትን አቋም ያንጸባረቀበትን ውይይት አድርጋል። ከአደረጃጀትም አልፎ ስለአማራ ፋኖ፣ ስለበወለጋ ያለው ቢዛሞ ፋኖ ጉዳይ ጃል መሮ ከአወያዪ ጃል ዳንዱ ጋር ሀሳብ የተለዋወጠ ሲሆን የአፋብን ቃለ አቀባይ የሆነውና ይህ ጸሀፊ ደግሞ ደጋግሞ እየዋሸ ነው እያለ ሲገልጸው የነበረን አስረስ ማረ ዳምጤን ጭልጥ ያለን ቅጥፈት አጋልጣል።
የኦነጉ ዋና መሪ ጃል ኩምሳ ድሪባ “…እኛ የምናካሂደው ትግል አላማ የሚታወቅ ነው። ትግላችን ኦሮሞ የራሱን እድል በራሱ መወሰን ላይ የተመሰረተ ነው። እኛ ደግሞ ታጥቀን ከቤት የወጣነው እና ስንወድቅ እና ስንጥል የቆየነው ሉዓላዊነታ የተጠበቀና ራሷን የቻለች ኦሮሚያን ለመመስረት ነው። አብረን ትብብር የፈጠርናቸው አካላት በዚህ ተስማምተው ነው አብረውን ለመስራት የፈለጉት ….” በማለት በትብብሩ ውስጥ ካልታቀፍን ገመድ በአንገቴ እያሉን ያሉት የአፋብን ጥቂት ከፍተኛ አመራሮች እነ አርበኛ ዘመነ ካሴ በሰሜን የወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ሁመራ፣ ራያና አላማጣን ለህወት በመስጠትና በደቡብ ደግሞ ልክ በመተከል አማራ ላይ እንደፈረዱት በወለጋ፣ በደራ፣ በአዲስ አበባና በአጠቃላይ በኦሮሚያ ክልል ባለው የአማራ ሕዝብ ህልውና እና የሀገረ ኢትዮጲያ ሉዓላዊ አንድነት ላይ በመፍረድ ያላቻ ጋብቻ የሆነውን ፖለቲካዊ ጥምረት ካልፈጠርን እያሉ መሆናቸውን ከኦቦ ኩምሳ ድሪባ ግልጥልጥ ያለ ቃለ ምልልስ መረዳግ ችለናል።
“…እኛ የጽምዶም ሆነ የትብብሩ አካልና አባል አይደለንም። የትብብሩ ግን አካል ለመሆን እየሰራንበት ነው..” ሲል የገለጸው የኦነስ (OLA) ዋና አዛዥ ኦቦ ኩምሳ ድሪባ ካደረገው 1:28 ደቃቂ ውይይት ውስጥ የሚከተለው አንኳር ነጥብ ጨምቀን ይዘናል።
♦️ በጃል መሮ በኩል የተላለፉ ነጥቦች:-
📌 ወለጋ፣ አዲስ አበባ፣ ደራ እና ድፍን ኦሮሚያ ቀይ መስመራችን ነው።
📌 በጽምዶና ጥምረት ውስጥ የለንበትም። በትብብሩ ውስጥ አለንበት። ሆኖም እስካሁን ድረስ የተስማማንበት አንድም የፖለቲካ ውሳኔ የለም።
📌 ግንኙነት ከአንድ አመት በፊት ጀምሮ ቢያንስ ለ21 ግዜ ያህል ከእነዚህ ኃይሎች (የአማራ ፋኖ እና የትግራዩ ህወሃት ) ጋር በአካል እየተገናኘን ውይይት አድርገናል። በዚህም ሂደት እስካሁን የተግባባንባቸው ነጥቦች ሶስት ናቸው:-
📌 1ኛ- የአሰበርስ የጎኒዮሽ ጦርነት አለማድረግ
📌 2ኛ- በጋራ የብልጽግናን አገዛዝ መጣል
📌 3ኛ- የአቢይን አገዛዝ ከገረሰስን በኃላ በሕዝባችን ቀጥተኛ ውሳኔ የሀገሪቱን ቀጣይ አቅጣጫ መወሰን በሚሉ ነጥቦች ላይ የጋራ ስምምነት ላይ ደርሰናል።
📌 ይህ ሆኖ ሳለም በትብብሩ ጉዳይ ገና ብዙ የሚቀር ስራ አለ። ገና አልበሰለም። ንግግርና ውይይት የሚፈልጉ ጉዳዮች አሁንም አሉ። ስምምነት ደረጃ ላይ መድረስ ከቻልን ትብብሩን ይፋ ማድረግ ደረጃ ላይ እንደርሳለን ፣ እናም ንግግሩ እንደቀጠለ ነው
📌 እኛ ለትብብሩ ብለን ስንዝር ታህል የኦሮሞን መሬት ለማንም አሳልፈን አንሰጥም። የትብብሩ አባል የሆነና በደራ፣ በወለጋ፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሳብን ካለ ምንም እንካን በድርጊቱ ብልጽግና ተጠቃሚ የሚሆን ቢሆንም በእኛ በኩል አፈሙዛችንን አዙረን ከመግጠም ወደ ሃላ አንልም።
📌 – በወለጋ ያለውና እራሱን ፋኖ እያለ የሚጠራው ቡድን የ OLA ከህወሃት ጋር አጋር ሆኖ ብልጽግናን በሚወጋበት ወቅት ከአምስት አመት በፊት አገዛዙ OLA ን ለማጥቃት ሲል ያቃቃመው የብልጽግና ታጣቂ ኃይል ነው። ከአባይ ማዶ ላሉት ፋኖዎች በዚህ ቡድን ጉዳይ ላይ ያለንን ግልጽ አቃም አሳውቀናቸዋል። ያላቸውንም ግንኙነት በአስቸካይ እንዲያቃርጡ ነግረናል። ምርጫቸው የየወለጋውን ታጣቂ ቡድን ካደረጉ የምንታገላቸው ጠላታችን እንጂ አብረን ትብብር የምናደርግ አይሆንም። ምርጫና ውሳኔው ግን የእነሱ ነው።
📌 ስለዚህ በወለጋ ስላለው ታጣቂ ቡድን በጃዋር መሀመድ በኩል የተነገረው እጅግ ትንሹ 5% ያህሉ ብቻ ቢሆንም እውነት ነው። እኛ የተቀረውን 95 % ብንናገር እጅግ ብዙ ነው።
ይህ አፋብን በሸዋም በተመሳሳይ ታጣቂ አለኝ እያለ ቢሆንም የሸዋውም ታጣቂ እንደወለጋው ብልጽግና ያስታጠቀው የአገዛዙ ታጣቂ ቡድን ነው።
📌 በወለጋ ያለውን ፋኖ ማጽዳት ያልተቻለው በሁለት ተከፍሎ የሚንቀሳቀስ ስለሆነ ነው። ታጥቆና ሸፍቶ ያለው በሽምቅ ውጊያ ላይ ያለ ነው ማጥፋት ይከብዳል። ሁለተኛው ደግሞ ስታየው አርሶ አደር የምትለው ሲያርስ፣ ሲዘራ፣ ሲያጭድ የምታየው አርሶ አደር ሲሆን ቀረብ ስትለው ግን ሁሉም የታጠቀ ሆኖ ነው ያለው። ስለዚህም ስለዚህም ወለጋን ማጽዳት አልተቻለም።
📌 በኦሮሞ ሕዝብ በኩል ከጠላታችን አማራ ፋኖ ጋር እንዴት ሄዳችሁ ትብብር ትፈጥራላችሁ ለሚለው ቅሬታና ስጋት የምሰጠው መልስ እነሱ መጡብን እንጂ እኛ አልሄድንባቸውም። ወደ እኛ ሲመጡ ግን እኛ የምንታገልለትን የኦሮሞን ሕዝብ አላማ፣ ጥያቄ፣ ጥቅምና መብት አክብረው እና ተቀብለው አቢይን በመጣል ደረጃ ላይ እንተባበር ካሉ ለእኛ የሚጠቅም ስለሆነ እሺ ብለን ተቀበልናቸው እንጂ ሕዝባችን እንደሚያስበው ከፋኖ ጋር የምንተባበረው የኦሮሞን መብት፣ ጥቅምና የሚታገልለትን አላማ በመተው አይደለም።
📌 – አሁን በለንበት ሁኔታ እነዚህ የትግሬና የአማራ ኃይሎች እኛ ባንፈልግም በራሳቸው ትግል ወደፊት ተጉዘው እኛ ያለንበት መድረሳቸው አይቀርም። ይህንን ደግሞ እኛ ስለማናስቆመው ማድረግ የሚገባን የእኛን አላማ ተቀብለው እንዲጋዙ ማድረግ ስለሆነ ይህን መሰረት ያደረገ ነው ትብብራችን እንጂ የእኛን ጥቅምና አላማን አሳልፎ በመስጠት ሁኔታ አይደለም።
📌 – አቢይ አህመድ የሚመራውን ብልጽግናን ከጣልን በኃል የኦሮሞ ሕዝብ ላለፉት 50 ዓመታት የታገለለትን ትግል ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ በሕዝበ ውሳንል በመወሰን እልባት ላይ እንዱያደርሰው እናደርጋለን። የአማራና የትግራይም ሕዝብ ስለራሳቸው ጉዳይ ሕዝቡ እንዲወስን እናደርጋለን።
📌 በአሁኑ ሰዓት የኦሮሞ ሕዝብ በሁለት ተከፍሎ ይገኛል። እድንደኛው ከአቢይ መራሹ ብልጽግና ጋር የተሰለፈ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (OLA) ጋር የተሰለፈ ነው። ከዚህ ውጪ ያለ ኦሮሞ የለም ….እና መሰል የሆኑትን ነጥቦች አስተላልፋል።
♦️ በጸረ ብልጽግና የትብብር ማእቀፍ ውስጥ ለመካተት ከቻሉ የትብብሩን የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት የሶስቱ ኃይሎች የአማራ ፋኖ፣ የኦሮሞው ኦነሰ እና የትግራዪ ህወሃት የመተባበሪያ ፎርም ምንድነው ???
እስቲ መጀመሪያ ትብብር Cooperation ምን እንደሆነ እንመልከት:-
📌 ፖለቲካዊ ትብብር (Political Cooperation / Alliance)
በሁለትና ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ የተለያዩ ኃይሎች መካከል ለጊዜው እርሰበርስ ያላቸውን ጠላትነትም ይሁን የጥቅምና የፖለቲካን ባላንጣነትን ትተው፣ ለአንድ የጋራ ጠላት ወይም የጋራ ጥቅም ብለው አብረው ለመስራት የሚስማሙ ሀይሎች ትብብር ተብሎ ይጠራል።
ትብብር በይዘቱ ረጅም ጊዜ የሚቆይ ሳይሆን እጅግ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ በመሆኑ ትብብሩ ፍቅር ፣ ጋብቻም ወይም ጥምረት አይነት ሳይሆን ዛሬ አብረን እንስራና ነገ እንለያለን በሚል ስምምነት የሚፈጠር የጥቅም ትብብር (Business Cooperation) ይሆናል።
📌 ምን አይነት ኃይሎች ናቸው የሚተባበሩት???
በፖለቲካ 5 አይነት ኃይሎች አብረው ይሰራሉ ወይም እርሰበርስ ለመተባበር ይፈልጋሉ-
📌 1ኛ. የይድዮሎጂ ትብብር (Ideological Allies)
– ተመሳሳይ የፖለቲካ እምነትና አይዲኦሎጂ ያላቸው፣ ምሳሌ: በዓለም ላይ የግራ ፓርቲዎች (ሶሻሊስቶች) አብረው ይሰራሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ መሃል-ቀኝ ፓርቲዎች አብረው በትብብር መስራት ይችላሉ።
– ጠንካራነቱ: – ረጅም ጊዜ ይቆያል
– ድክመቱ: በአይድዮሎጂ ክርክር ትብብሩ ለውጤት ሳይበቃ ይበጣጠሳል ወይም ብዙም ሳይገፋ ይበታተናል።
📌 2.ኛ በጋራ ጠላት ላይ የሚደረጉ ትብብሮች (Enemy of my enemy is my friend)
– ይህ በኢትዮጲያና በአፍሪካ በጣም የተለመደ እና በብዛት የተሰራበት ነው። በሀገራችን በ1980ዎቹ ጸረ ደረግ ትብብር፣ በ2010 ጸረ ህወሃት ትብብር በ2013ቱ አሁንም ጸረ ህወሃት ትብብር ትልቅ ኃይል ፈጥሮ ታላቅ ለውጥ ማምጣቱን እናስታውሳለን።
– ሁለት እርሰበርስ ጠላታሞች የሆኑ ኃይሎች አንድ የጋራ ጠላት ሲኖራቸው ትብብር መፍጠር የሚችሉበት ሁኔታም አለ።
– ምሳሌ ያህል ፋኖ፣ ኦነግና ህወሃት እርሰበርስ በጠላትነት የሚተያዩ ናቸው ሆኖም የሶስቱም ኃይሎች አንድ ጠላት ካጋጠማቸው ያላቸውን የእርሰበርስ ጠላትነት ለጊዜው በመተው ትልቁ ጠላታችን ባሉት ላይ ትብብር ለማድረግ የሚችሉበት ሁኔታን እናያለን።
ፋኖ፣ ህወሃትና ኦነግ Against ብልጽግና ማለት ነው።
ሆኖም ይህ አይነቱ በጋራ ጠላት ላይ ብቻ ለመዝመት ተብሎ የሚደረግ ትብብር ትልቅ ኃይል፣ ጉልበትና አቅም ፈጥሮ የተባበሩበትን ጠላት ማሸነፍ የሚያስችል ሁኔታን መፍጠር የሚችል ቢሆንም ከተባበሩበት ጠላት ሽንፈት ማግስት የሚያስከትለው አደጋ እጅግ ከባድ ነው።
– የዚህ አይነቱ ትብብር ጠንካራነቱ: በጣም ፈጣን እና ኃይለኛ ሲሆን…
– የዚህ አይነቱ ትብብር ትልቁና ዋናው ድክመቱ ግን የጋራ ጠላቱ ሲጠፋ የተባበሩት ኃይሎች ትብብር ወዲያው ከመበታተን አልፎ ደም አፋሳሽ የእርሰበርስ ጦርነትን ይፈጥራል። በተለይ ትብብሩን ያደረጉት ኃይሎች ከተባበሩበት ጠላታቸው መጥፋት ማግስት አንድ የሚያደርጋቸው አላማ የሌላቸውና ሁሉም የየራሳቸው የሆነ የግል አላማ ያላቸው ኃይሎች ከሆኑ ከፍተኛ የሆነ ደም አፋሳሽ የእርሰበርስ ጦርነት ውስጥ ይገባሉ።
ለምሳሌ በ1991 የሱማሊያውን ዘያድ ባሬን ለመጣል ትብብር አድርገው ወደ ሞቃዲሾ የገቡ አራት የሱማሌ ጄኔራሎች ዘያድባሬን ካስወገዱ በኃላ ወደ እርሰበርስ ጦርነት ውስጥ ስለገቡ ሱማሊያ ልትፈርስ ችላለች።
📌 3ኛ. በጥቅም ላይ የሚተደረግ ትብብር (Interest-Based Cooperation )
የጥቅም ልውውጥን መሰረት ያደረገው ትብብር ሶስተኛው አይነት ትብብር ሲሆን ለአብነት ያህልም በአሜሪካና በሳኡዲ አረቢያ መካከል ሳኡዲ ዘይት ልታቀርብ አሜሪካ ጥበቃና የጦር መሳሪያ በማቅረብ ሁለት የተለያያ አይዲኦሎጂ አራማጆች ሆነው ትብብር ማድረግ ችለዋል።
ዛሬ ፋኖ፣ ህወሃትና ኦነግ ለማድረግ ለሚያስቡት ትብብር ፈጽሞ አይሆንም።
📌 4ኛ . የትብብር አይነት በጂኦግራፊ የሚደረግ ትብብር (Regional Blocs) የሚባለው አይነት ትብብር ሲሆን ለምሳሌ IGAD , GCC ወዘተ አይነት በሀገራት መካከል የሚደረግ ቀጠናዊ የትብብር አይነት ነው።
– ይህን አይነቱን ትብብር በዛሬይቱ ኢትዮጲያ ለመጠቀም ከታሰበ በአማራ እና በትግራይ ህዝብ መካከል፣ በአማራ እና በኦሮሞ ሕዝብ መካከል፣ በትግራይና በኤርትራ ሕዝብ መካከልና በአማራ እና በኤርትራ ሕዝብ መካከል የህዝብ ለህዝብ ትብብር ማድረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ቢኖሩም ለሶስትና አራት አስርተ አመታት ፖሎራይዝ በሆነ የፖለቲካ ትርክት ውስጥ ተዘፍቀው ያሉ ሕዝቦች እንደመሆናቸው መጠንና እንዲሁም እነዚህ ሕዝቦች ከፖለቲከኞች ነጻ የሆነ የቀጥታ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማድረግ የማይችሉ በሆኑበት ሁኔታ ፍሬያማ የሚሆን ትብብር መፍጠር አዳጋች ሆኖ ነው የሚታየው።
📌 5ኛ- ጊዜያዊና ታክቲካዊ ጥምረት (Tactical Coalition) የሚባለው ትብብር ነው።
ይህ አይነቱ ትብብር በምርጫ ወቅት ለአንድ ግዜ ብቻ የሚደረግ ትብብር ነው።
-ምሳሌ: በ 1997 ቅንጅት የተፈጠረበት፣ በ2013 ባልደራስ፣ አብንና መኢአድ Just ለምርጫው ሲሉ ያደረጉት አይነት ትብብር ማለት ሲሆን የዚህ አይነቱ ትብብር እድሜ በጣም አጭር ከመሆኑ የተነሳ ትብብሩ ከምርጫ በኋላ የሚበተን ይሆናል።
♦️ ማንኛውም አይነት ትብብር ስኬታማ ለመሆን 3 ሕግጋቶችን መከተልና መፈጸም አለበት
📌 1ኛ- ግልጽ የሆነ የጋራ ጠላት እና የጋራ ግብ የመኖር አስፈላጊነት።
የትብብሩ ባለቤቶች ለምንድነው አብረን የምንሰራው የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ ቁልጭ አድርጎ የሚመልስ የጋራ ጠላትና የጋራ አላማ ቁልጭ ብሎ መገለጽና መቀመጥ ይጠይቃል።
አላማው የማይታወቅ ጥምረት በ1 ሳምንት ይፈርሳል።
.📌2ኛ ፍጹማዊ እኩልነት
በሚፈጠረው ማንኛውም አይነት ትብብር ውስጥ የትብብሩ ውስጣዊ ህግና ደንብ ፍጹማዊ እኩልነት ላይ የተመሰረተ መሆንን ይጠይቃል።
ለምሳሌ ያህል – አንዱ “እኔ አለቃ ነኝ” ካለ እና ሌላኛውን እንደ ታዛዥ ሎሌ የሚያይ ከሆነ የተፈጠረው ጥምረት ወዲያው ይፈርሳል።
የትብብር ማጣበቂያ ሙጫ ፍጹማዊ እኩልነት ነው።
📌3ኛ – የመውጫ በር (Exit Strategy ወይም Plan B
የትኛውም ትብብር ከጅምሩ ትብብሩ መቼ እንደሚያበቃ እና እንዴትስ እንደሚያበቃ የሚገልጽ እቅድና ውሳኔን በቅድሚያና በግልጽ ማስቀመጥን ይፈልጋል።
መሰባሰቢያ እና መለያያ ነጥብና አድራሻ የሌለው ትብብር – ማለትም የማይለያይ ጥምረትና ትብብር የእርሰበርስ ጦርነት ይፈጥራል።
ከዚህ አንጻር የአማራ ፋኖን፣ የኦሮሞውን ኦነስ OLA እና የትግራዩን ህወሃት በአንድነት የሚያቅፍ የትብብር ፍሬምወርክ ለማየት ስንፈልግ እጅግ ብዙ መንገድ እንደሚቀር እንረዳለን።
የትብብሩን ፕሮጄክት ያስተጋቡ ዘንድ የተቀጠሩት 16ቱ የጽምዶ ሚዲያዎችን የእለት ተእለት ዘገባን ከሰማችሁ ግን ገና በሀሳብ ደረጃ ተጸንሶ ያለውን የትብብር ሀሳብ ቅርጽና ይዘት ኖሮት የተወለደ ድርጅት ያህል አድርገው ሲያስተዋውቁ ልትሰሙ ትችላላችሁና ፕሮፖጋንዳውን ፈጽሞ አትስሙት።
በቀጣይ – የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ንቅናቄ ቃለ አቀባይ አስረስ ማረ ዳምጤ የተዋረደበትን፣ እንደ ድርጅት አፋብን፣ እንደ ሕዝብ የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል በአመራር እጦት እና በአመራር ቀውስ ምክንያት የተጋረጠበትን ከፍተኛን አደጋ ከእነስ OLA ዋና አዛዥ ኦቦ ኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) ቃልና ከህወሃት አቋም አንጻር ምን እንደሚመስል ይዤ እቀርባለሁ፣ አበቃሁ።

















