>
5:14 pm - Friday April 20, 7427

የሶስተኛውን እጅ  ያለ ይሉኝታ በአደባባይ የመዋጋት፤ ወቅቱ አሁን ነው (አቢይ...)  

የሶስተኛውን እጅ :-
 ያለይሉኝታ በአደባባይ የመዋጋት፤ ወቅቱ አሁን ነው  

አቢይ ኢትዮጵያዊ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ

 
ሁለት የተለያዩ ዓላማዎች ያሏቸው አካላት በአንድ ጉዳይ ላይ በሃሳብ ሲፋጩ፣ሲወያዩ እና ሲታገሉ፤ሶስተኛ አካል ሆኖ በስውር የሚያጠቃ መኖሩ  ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው።እናም ቅንነት፣በጎ አስተሳሰብና መልካም ሥነ-ምግባር ለፍቅር ጉዞ የሕይወት ማጣፈጫዎች ቢሆኑም፤በፖለቲካ ሕይወት ውስጥ፣እነዚህ ማጣፈጫዎች ግን እጅግ ጥንቃቄ የሚሹ ሆነው እናገኛቸዋለን።
በተለይም ኢትዮጵያ በለውጥ ማዕበል ወዴት እየተጓዘች እንደሆነ ሁላችንም የምናየውና ያረጋገጥነው ዕውነት ስለሆነ፤በፍቅር እና በይቅርታ ከባርነት ወደ ነፃነት ለመሸጋገር መጓዛችንን እርግጠኞች መሆን አለብን።ነጻነትን የምንሻ ሁሉ በጣም ጥንቃቄ የሚየስፈልገንም ፍቅርና ይቅርታ፤ ያለትግል በፍፁም እንደማይመጡ ሳንዘነጋ መሆን አለበት።ይህም ማለት ፍቅርን መዘመርም ሆነ ይቅርታ ማድረግ ትግል ቢያስፈልጋቸውም፤ያለቂም-በቀል መጪውን ዘመን ለኢትዮጵያ በጋራ ተባብረን በመሥራት ላይ የሚመሠረት መሆን ይኖርበታል።
ይሁንና በማጭበርበር፣ በደባ፣ በተንኮል፣ በማስመሰልና ዋናው ደግሞ በገንዘብ እና በሚችሉት ሴራ ሁሉ ወደቀድሞው የባርነት ዘመን ሕዝቡን ለማስገባት ሌት-ተቀን የተደራጁ አሉ።እነዚህ ፣እየተሽሎከሎኩ ሊያጠፉን የሚፍጨርጨሩ:-ሕዝብን በጅምላ መግደል ቀጥለዋል። በዚህም የጥፋት ተንኮል፣ሰበቦቹ እና ምክንያቶቹ ተለይተው እንዳይታወቁ ፖለቲከኞች ነን ከሚሉት ተንኮለኞቹ ካድሬዎች ጋር እና ከአጭበርባሪው የሶስተኛው አካል  ጋር ሆነው ገና ብዙ ሕይወት ሊያስገብሩን ታጥቀዋል።
የዶክተር አቢይን እግር እየጠበቁ ችግሮችን መፍጠር እና ሆን ብለው በአራጋቢዎቻቸው በድብቅ ለሰላም የምንሠራውን ማፍረሱ:-ሰበብና ምክንያቶቹን እንዳናይ  አድርጎናል።ዋናው ምክንያት ግን አጭበርባሪው እና የሶስተኛው አካል  እጆች ?፤የእነዚህም ሦስተኛው እጆች:-ባለቤታቸው ደግሞ ሕውሃት ለመሆኑ ፊትለፊት ሳይሆን፣(*ጡን ገልቦ) እየነገረን ነው።በመረጃ ለማስደገፍ በምሳሌ፦ እነዚህን አመላካችና ተንታኝ ጦማሮች ይመልከቱ፤የቄሮውን ዓይነትና ትግል፣ https:// www.zehabesha.com/ mharic/archives/94261 እንዲሁም https://ecadforum.com/Amharic/archives/19303/ እናhttp://www.ethioreference.com/archives/13911  የጉጅሌ-ወያኔን ሴራ http://quatero.net/amharic1/archives/30762  እንዲሁም https://www.zehabesha.com/amharic/archives/94255 ናቸው።https://www.zehabesha.com/amharic/archives/94326 እና ብዙ ጥፋቶችን የማይጠብቁት ዶክተር አቢይ የትኛውን ምክንያት ማስቀደም እንዳለባቸው ቢያውቁም https://amharic.borkena.com/2018/09/17/የኢትዮጵያ-ክፍላተሃገር-ሕብረት-መግለጫ  እና http://ethioforum.org/amharic/ቄሮ፣-ፋኖ-እና-ዘርማ-አሮጌ-ጋሪ-የሚጎትቱ ፤ የሚሉት ዋና ዋና ሰበቦች ናቸው።
ምክንያቶቹ ግን ሕውሃቶች እንደ እሥስት መልካቸውን እየቀያየሩ ማሸበራቸው ነው፤ልክ”ቅማሏ ተይዛ ስትገደል ሁሉም ቦታ የሚያሳክከን እና ሰላም የሚነሳን ሕመም ሁሉ እንደሚቆመው።” ቅማሏን (ትኋን)መግደል ኅጢያት ከሆነም ፤አቀራረቤን የተስተዋለ ላድርገውና በጠርሙስ ውስጥ ተደርጋ ትጣላለች። 
ሕዝብና መንግሥት፤ባልና ሚስት፤አሊያም ሌሎች ሁለት የተለያዩ ወይም ተቃራኒ ሃሳቦችን በውሳኔ የሚያስተላልፉ አካላት፣ ለበጎ እና መልካም ነገር ብለው፤ፊት ለፊት ሲፋጠጡ፣ሲሟገቱ፣ ሲታገሉና፣ ሲፋጩ፣ እናያለን።እንገት ውሉን ስተው ደግሞ ሲዘባርቁ፣ሲነታረኩ፣ዱላ ቀረሽ ፀብ ሊፈጥሩ ሲተናነቃቸው፤እንደገናም ሊስማሙ ብለው ሰከን ሲሉ፤አንዱ ሌላውን ለማሳመን ሲዳክር፣ሌላው ነገሩን እንደገና ወደ ኋላ ተመልሶ ሲጀምር፤ሊስማሙ ጥቂት ሲቀራቸው፤ የሶስተኛው አካል  እጆች   የሆኑት ድንገት ጥልቅ ለማለት ደካማ ጎኖችን ሲፈልጉ አይተናል።
የሦስተኛው አካል ተምሳሌት መነሻ ምክንያቴ ያገራችንን ሁኔታ  ብቻ ሳይሆን፤በግል የሚደርስብንን ችግር ሳይቀር እንኳ ጠንቅቀን እንድናይ ስለሚያመላከተን ነው።የሦስተኛው አካል በአደባባይ ለዕይታ እና ለመዝናኛነት ሲቀርብ ግን አስማት ነው ያስብላል፤ምክንያቱም ሦስተኛውን እጅ የሚጠቀሙት ሰዎች ሥመ-አምላክ አንብበው ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች ስላሉ ነው።ይሁን እንጂ፣ወደ አገር ጉዳይ ስንመጣ ሦስተኛውን እጅ የመዝናኛ ወይም የቀልድ ሆኖ አይቀርብም፤ በጥንቃቄ ይመረመራል፣ይጠናል ይጋለጣል።”ለምን?” ቢባል ሦስተኛው አካላት ጣልቃ የሚገቡት ሳይጋበዙ፣አድብተው አጭበርብረውና ሆን ብለው ጠብቀው፤ ቢቻልም ተደብቀው ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ነው።ሌላው ተጎዳ አልተጎዳ ፤ሳይሉ ደንታ ቢስ ሆነው፣አስበውና ገምተው ችግር የሚያቃልሉ መስለው ሌላ ስውር ችግር በጥያቄ መልክ በመፍጠር ነው ጣልቃ የሚገቡት። ልክ ሰይጣን አዳምን ለማሳሳት፣በላይ በላዩ ላይ ጠያይቆ እና ሆን ብሎ መልስ ሳይጠብቅ፣”ጠያቂው ጥያቄው ተጠያቂውን ጠያቂ አድርጎ የተንኮል ጥያቄ” ልቡ ውስጥ እንደጫረው ማለት ነው(ኦሪት ዘፍጥረት ም ፫ ቁ ፬)።
እነዚህን ዕውነታዎች ከመሠረቱ ሶሥቱንም በምድር ላይ ካሉት ተጨባጭ ሁኔታዎች አንፃር በንፅጽር  እንመልከታቸው፤
1ኛ/በቤተሰብ፣
2ኛ/በማሕበረ-ሰብ እና 
3ኛ/በመንግሥት መካከል ያሉትን ሁሉ ይጠቀልላል።
 1ኛ/የመጀመሪያው በአባት እና በእናት ወይም በሌሎች ዝምድናዎች ባሉበት ቤተሰብ መካከል ውስጥ ችግር መፈጠሩ ሲታወቅ በሁለት አካላት ብቻ የተፈጠረ ሆኖ በግልፅ ይታያል። ጉዳዩን እየጠለቅን ማየት ስንጀምር፤ ሦስተኛውን አካል እና ዋናውን ምክንያት እናገኛለን። ለዚህም ነው ሰበብ እና ምክንያቱን በጥንቃቄ መለየት የሚያስፈልገው።ይህም ማለት ችግሩ እንዲፈጠር ያደረገው፣ችግሩን የፈጠረው እና ችግሩን የተገበረው መለያየት አሉባቸው። ለምሳሌ ሚስት ሆን ብላ፤በቅናት እና በጥርጣሬ መንፈስ ሆን ብላ ወሬ ማዛመት የሚችለውን ሰው መርጣ እንደቀልድ አድርጋ በተለያዩ ሰዎች ላይ በመሞከር በጥያቄ መልክ ታሰራጫለች።እርሷ ታዲያ ችግሩ እንዲፈጠር ያደረገች ሲሆን ችግሩን ፈጣሪዋ ግን ፈፃሚ ወይም ተግባሪ(የሚተገብርላት) ያስፈልጋታል።በእነዚህ እንቅስቃሴዎች የሚሳተፉት ሰዎች ሁሉ የጋራ ምክንያት ኖሯቸው ሳይሆን ችግሩ እንዲፈጠር ያደረገችበት ምክንያት የተሳሳተም ይሁንም ወይም ትክክለኛ፣ከውጤቱ የተጠቃሚነት ዓላማ ስላላት ብቻ ነው፤እናም ችግሩን ለመፍታት ሦስተኛውን አካል ለማግኘት ምን ያህል ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ እንገነዘባለን።
በ2ኛ/ሁለተኛው ምሳሌ ውስጥ የምንመለከተው የማሕበረ ሰቡን ትሥስር ሲሆን፣ከቤተሰብም የሚለየው በስፋትም ሆነ በዓይነት፣በጣም የበዛ እና ችግሩን ለመፍታት ቢያንስ በሥጋም ሆነ በዝምድና ወደ ራስ ገብቶ እንዲቀር ባለማስቻሉ ነው።በዚህም ምክንያት በመንግሥት እና በሕግ የተቋቋሙ የመሐበራት ድርጅቶች አሊያም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ካነሰም ባሕላዊ ተቋማት ድርሻቸውን እንዲወጡ ይደረጋል።ለምሳሌ የቀበሌ እና የፍርድ ቤቶች በግምባር ቀደምትነት ሲጠቀሱ፤የአገር ሽማግሌዎችና የዕምነት ተቋማት ጣልቃ-ገብነት ተቀባይነት ያላቸው ናቸው።
 3ኛ/ ሦስተኛውና የመጨረሻው በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል የሚፈጠረው ችግር ሲሆን፣ከሁለቱም የሚፈጠሩት ችግሮች የሚለዩትም በብዛት እና በመጠን በጣም የተራራቁ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የራሳቸው የአፈታት ዘዴ ስላላቸው ነው።ሲጀምር ከመሠረቱ ዳኝነትን የሚይዘው ሕዝብ ሲሆን፤ችግሮቹ በዓይነት፤የፖለቲካ፣የኢኮኖሚ ወይም የምጣኔ ሀብት እና የማሕበራዊ እየተባሉ በየመፍትሄአቸው ይፈረጃሉ።እነዚህን ለማስፈፀም ደግሞ አሁን ያሉትን ተቋማት ሳይሆኑ ዶክተር አቢይ አህመድ ሙሉ ሥልጣን ሲጨብጡ የሚያቋቁሟቸው እና ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው ሲያደራጇቸው በአዲስ መልክ መዘጋጀት ሲያደርጉ ችግሮችን መፍታት ይችላሉ።የሚያሳዝነው ግን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ለዚህ መፍትሄ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማ በአጋጣሚ በኢሳት ላይ የሰጡትን የምክር https://www.youtube.com/watch?v=KwfQ_rYzQhs አገልግሎን አለመቀበል እና ለሕዝብ አገልግሎት ላለመሥራት የሕዝብን ዳኝነት ክደው የሚያደርጓቸው አሻጥሮች ወደ አምባገነን ሥርዓት እንድንጓዝ የሚመሩን ሆነው እናያቸዋለን።ይህም የጥፋት ገመድ በግድያ፣በሽብር፣በተንኮል እና በተለያዩ አሻጥሮች፤የገንዘብ ብተናን ጨምሮ ለቅጥር አጥፊዎች ሚሊዮን በማደል ሦስተኛው እጅ በፍጥነት በትዕቢት እና በንቀት በአደባባይ የለውጥ ጉዞውን እየተዋጋ ይገኛል።    
እናም ዶክተር አቢይ አህመድም ለተጨማሪ የኢትዮጵያ ሥራ እግራቸው ወደውጭ አገር ወጣ ባሉ ቁጥር፤ በኅላፊነት ሥልጣን ላይ ሆነው ለውጡን ወደው ደገፉም ወይም አልደገፉም ሁለት ገፅታዎችን ይዘው ሲያመቻቸው ችግር እንደሚፈጥሩ የታወቁ እንዳሉ ሆኖ፤የሦስተኛው እጆች ባለቤቶች ሕውሃቶች ናቸው ስለዚህም ሐቁ በመረጃ ተደግፎ፣ያለምንም ይሉኝታ ባደባባይ መነገር  አለበት።የሕዝብ ጉዳይን አውቆ እንዳላወቀ መሆን ሳይሆን ለዓላማውና ለበጎ ሥራው ፍፃሜ የግዴታ የሶስተኛውን እጅ ያለይሉኝታ በግልፅ ለሕዝብ ማሳወቅና የሥርዓት ለውጥ በፍጥነት ለማምጣት በሃሳብ ለመዋጋት፤ወቅቱ አሁን ነው።
Filed in: Amharic