>

ሥጋት ሲያይል÷ተስፋ ሲመነምን (ከይኄይስ እውነቱ)

ሥጋት ሲያይል÷ተስፋ ሲመነምን

ከይኄይስ እውነቱ

በዚህ የግል አስተያየት የአገር ህልውና መሠረታዊ ጉዳይ እና ይህንንም በማረጋገጥ ጅምር የለውጡን ሂደት በፖሊሲ፣ በሕግ፣ በመዋቅር፣ በተቋማት ግንባታና ወዘተ. የተደገፈ የሥርዓት ለውጥ በማድረግ፤ የለውጡ ማረፊያ የሆኑትን መንግሥት ሕዝብ የማቆምና ኹለንተናዊ የአገር ግንባታ ተግባራትን ማእከል በማድረግ አገራዊ መረጋጋትን እና የዴሞክራሲ ተቋማት ተከላን ከወቅታዊ የአገራችን ምስቅልቅሎች ጋር በማያያዝ ለማየት እሞክራለሁ፡፡ ስለሆነም ምልከታው አንድ ወጥ ርእሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ አይደለም፡፡

1/ መግቢያ – ወቅታዊው ሁኔታ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጥቂት ዘረኞች አገዛዝ የሆነው የወያኔ ትግሬ ቡድን ግፍ፣ ጭቆናና ውርደት አንገፍግፎት በተባበረ ሕዝባዊ ዓመፃ በመነሳት አሁን የሚታየውን ጅምር የለውጥ ሂደት እንዲመጣ አድርጓል፡፡ በዚህ እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ በተለያየ ስም ተሰባስበው መሥዋዕትነት የከፈሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች ድርሻ ትልቅ ሥፍራ አለው፡፡ ባንፃሩም ብልሃትና ጥበብ በተመላበት ሁኔታ ራሳቸውን ለአደጋ በማጋለጥ ጭምር ትግሉን ፈር በማስያዝና በመምራት ረገድ የነ አቶ ለማ ቡድን አስተዋጽዖ ታላቅ ነው፡፡  አነሰም በዛም ወያኔ ሕወሓትን ለማስወገድ አገር ውስጥ ያለውና በስደት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በትግሉ ውስጥ ድርሻ አለው፡፡ ያም ሆነ ይህ ለውጡ የሚገኘው የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ነው፡፡ የዕውቅና ሽሚያው ዓላማ ምንድን ነው? እንደ ወያኔ ዘላለማዊ ገዥነት ይገባኛል ለማለት ነው? ወያኔ ትግራይን ነፃ አወጣለሁ ብሎ ታግሎ ለዚሁ ዓላማ እንዲሠዉ ያደረጋቸው ታጋዮችን ቊጥር እያነሳ ለኢትዮጵያ የታገሉ ይመስል የምንይልክን ቤተመንግሥት የዕድሜ ልክ ርስት ሊያደርግ ተመኝቶ ነበር፡፡ ነውረኛ!!! ይህን ዓይነቱን ሰይጣናዊ ክጀላ በተረፈ-ወያኔዎችም እያየን ነው፡፡ ነውረኞች!!!

የጠ/ሚር ዐቢይ አስተዳደር በሦስት ወራት ዕድሜ የወሰዳቸው አስደማሚና ለለውጥ መንገድ ጠራጊ ርምጃዎች ወያኔ ትግሬ ያጨለመብንን ሕይወት የተስፋ ወጋገን እንደፈነጠቀበት አብዛኛው  ሕዝባችን ይስማማል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለለውጡ አመራር ኃይሎች ከጅምሩ ድጋፍ የሰጠው እነዚህ ወንድሞቻችን በውስጥ ትግል አውሬው ወያኔን ክፉኛ አቁስለው ወደመጣበት እንዲያፈገፍግ በማድረጋቸው፣ ወያኔና መንደርተኛ ፖለቲከኞች ያንቋሸሹትን ኢትዮጵያዊነትንና አገራዊ አንድነትን ከፍ ከፍ ስላደረጉ፣ ቅንነት በተሞላበት ሁኔታ በተግባር የፖለቲካ እስረኞችን በገፍ በመፍታት÷ ቅድመ ዐቢይ የነበረው የወያኔ አገዛዝ መንግሥታዊ ሽብርን በኢትዮጵያ ላይ መፈጸሙን በጥቅል በማመንና ይቅርታ በመጠየቅ፣ ተወንጅለውና ተፈርዶባቸው የነበሩ በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶችን÷ የተቃውሞ ፖለቲካ ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦችን÷ የሰብአዊ መብት ታጋዮችን እንዲሁም የብዙኃን መገናኛ ተቋማትን ውንጀላና ፍርድ በማንሳት አገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ በር በመክፈታቸው፣ የታገዱ ገጸ ድሮችን በመክፈታቸው፣ የወያኔ ትግሬ የግል ንብረት የነበሩትን የወታደራዊና ደኅንነት ተቋማት ሕዝባዊ ለማድረግ ማሻሻያ መጀመራቸውን፣ እንደ ፀረ-ሽብር ያሉ ሕጎችን ለማሻሻል ግብረ ኃይል ማቋቋማቸውን፣ ባጠቃላይ የፖለቲካ ምሕዳሩን በመክፈት አንፃራዊ ነፃነት እንዲመጣ ላደረጉት ጥረት ወዘተ እንደሆነ ይታመናል፡፡

ከዚህ በላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሚከተሉት አንኳር ጉዳዮች ግን መዘንጋት የለባቸውም፡፡

ሀ/ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለለውጡ አመራር ያሳየው ድጋፍ ከአመራሮቹ ጎሣዊ/ነገዳዊ ማንነት ጋር ግንኙነት የሌለው መሆኑን፡፡

ለ/ ጠ/ሚሩ ወይም የአቶ ለማ ቡደን የሚገኙበት ‹ወያኔ/ኢሕአዴግ› የተባለው ግንባር አገርና ሕዝብ አጥፊ የሆነ የዘር ፖለቲካን እና በውሸት ፌዴራል ሥርዓት ስም ‹ክልል› የሚባል የአፓርታይድ አገዛዝ መዋቅርን ተክሎ እና በይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› ሕጋዊ ቅርፅ ሰጥቶ ለአእላፋት ሞት÷ እስር÷ እንግልት÷ ስደት÷ የመሬት ወረራ ከቤት ንብረት መፈናቀል፤ መጠነ ሰፊ የሆነ የአገር ሀብት ዝርፊያ፤ ዘርፈ ብዙ የሆነ ማኅበራዊ ምስቅልቅል/ማኅበራዊ ድቀት፤ ወዘተ. በመዳረግ በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በክብደታቸው የመጨረሻ የሚባሉ (በምህረትና ይቅርታ ሥርዓት የማይታለፉ) ወንጀሎችን የፈጸመ ወንጀለኛ ድርጅት በመሆኑ በጋራም ሆነ በተናጥል የሚኖር ተጠያቂነት ጥያቄ ውስጥ አስገብቶ አይደለም፡፡ በተለይም ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በጠላትነት ፈርጆ ለጥፋት ዓላማው የእጁ ሥራ የሆኑትን ሦስት የጎሣ ድርጅቶች አሠማርቶ ነውር የተባለን ኹሉ ንቅስ አድርጎ ሲፈጽምና ሲያስፈጽም የነበረውና ያለው ሕወሓት እንደ ድርጅት በጋራና አባላቱ በተጠናጥል ግንባር ቀደም ተጠያቂዎች ስለመሆናቸውና በፍርድ ተገቢውን ፍትሕ የማግኘት መብቱ ላይ ጽኑ አቋም በመያዝ ነው፡፡ ስለሆነም የነ አቶ ለማ ቡድን ተቀባይነት ከግለሰቦቹ ስብእናና በቀጣይ ሕወሓት ላይ ከሚወስዱት የማያዳግም ርምጃ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፤ ሕወሓትን አስወግዶ÷ ስሙንና ግብሩን ቀይሮ÷ ከዘር መሠረት ወጥቶ ባዲስ መልክ ካልተደራጀ በስተቀር ‹ወያኔ ኢሕአዴግን› እንደ ግንባር፣ 3ቱ የጎሣ ፖለቲካ ድርጅቶች በተናጥል ሕዝባችን ወደሚፈልገው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያሸጋግሩናል የሚል እምነት የለኝም፡፡  

ሐ/ የለውጡ አመራሮች በሚመሯቸው የጎሣ ፖለቲካ ድርጅቶችና ‹በግንባሩ› ደረጃ የሚያራምዷቸውን ርእዮተ ዓለም፣ አስተሳሰብ፣ በዘር የመደራጀት ፖለቲካ ወዘተ በሂደት እንደሚለወጡ ግምት ውስጥ በማስገባት እንጂ በመደገፍ አለመሆኑ፡፡ በሂደት አንድ የኢትዮጵያ መሪ በፖለቲካ ዓውድ አባል የሆነበትን ነገድ/ጎሣ በኦፊሴላዊ ተግባሩ የማያነሳበት ሥልጣኔ ላይ እንደርሳለን የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

መ/ በእስካሁኑ ሂደት በለውጡ አመራር ዘንድ በአሮጌ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ ለማኖር የሚደረገውን ሙከራ ደግፎም አይደለም፡፡ በመንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ ከካቢኔው ጀምሮ ከሙያዊ ብቃት እና ቅንነትንና ሞራላዊ ልዕልናን የተላበሰ ስብእና ይልቅ ድርጅታዊ አሠራር ሠልጥኖ ቀጥሏል፡፡ በተለይም ሥልጣንና ጥቅሙ የተነካበትና ለውጡን ለመቀልበስ እየታገለ ካለው የሕወሓት አባላት ቊጥራቸው ቀላል የማይባል ከቀድሞ የኃላፊነት ቦታ አለመነሳት ወይም አዲስ ሹመት መስጠት በየትኛውም መመዘኛ ራስን ከማጥፋት ተለይቶ አይታይም፡፡ አብዛኛው የፌዴራል አስፈጻሚ አካላት ውስጥ ከላይ እስከ ታችኛው ዕርከን ያሉ ኃላፊዎች፣ በተለይም በውጭ ጉዳይ መ/ቤት፣ የሰብአዊ መብቶቸ ጉባኤ ኃላፊ (በእኔ እምነት ይህ ተግባር በማኅበረሰብ ተቋማት እንጂ በመንግሥት አካል መከናወን የለበትም)፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወዘተ፡፡ በክፍላተ ሀገር ደረጃ ደግሞ ሕዝብን በጎሣ ግጭት እያመሱና እያተራመሱ ያሉ አብዛኛዎቹ የፖለቲካም ሆነ የአስተዳደር ኃላፊዎች አልተነኩም፡፡ ምን ተይዞ ጕዞ? በዚህ ዓይነቱ አሠራር ዐቢይ የሆነውንና ገና ያልተጀመረውን መሠረታዊ የለውጥ ተግባር – ነፃና ገለልተኛ (ተአማኒነት ያላቸው) የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባት እኩልነት፣ የሕግ የበላይነት እና ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት መንግሥተ ሕዝብ የማቆም – ማራመድ የሚቻል እንዳልሆነ የብዙዎች አቋምና እምነት ነው፡፡

2/ የጅምር ለውጡ ተግዳሮቶች፤ ጅምር የለውጡን ሂደት ለመቀልበስ ከመነሻውም ጀምሮ ፈተናዎች አጋጥመውታል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ፈተናዎች ከጊዜ ወደጊዜ አድማሳቸውን እያሰፉና እየተጠናከሩ አገራዊ አለመረጋጋቱን አሳሳቢ ደረጃ ላይ እያደረሱት እንደሆነ ታዝበናል፡፡ እዚህም እዚያም ሥርዓተ አልበኝነት ሲነግሥ እያስተዋልን ነው፡፡ ብዙዎቹ ፈተናዎች የሚጠበቁ ቢሆንም በመንግሥት በኩል ያለው የፈተናዎቹ አያያዝ፣ አመራርና አፈታት ባንድ ወገን ጥንቃቄና ብልሃት እንዳለ ሲያመለክት በሌላ ወገን ደግሞ ኹከት ፈጣሪ ወንጀለኞችን (በተለይም ግዙፍ የዝርፊያ ሀብትንና በአባሎቻቸው አማካይነት መንግሥታዊ መዋቅርን በመጠቀም ሌሎችን መሣሪያ በማድረግ በአሳብ በሎጂስቲክስ ድጋፍ የሚያደርጉ እንደ ሕወሓት ያሉ ኃይሎችን) ወደ ፍርድ በማምጣት፣ ምርመራውን በብቃት፣ በተአማኒነትና በፍጥነት በማከናወን ሕግን የማስከበሩ ዳተኝነት በስፋት እንደታየ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ በቅርቡ በቡራዩና አካባቢው የተፈጸመውን አረመኔያዊ ድርጊት ከማውገዝ ባለፈ ከድርጊቱ ቀደም ብሎ ራሳቸውን እንደ ሕዝብ መሪ ኮፍሰው በሙሉ የፈላጭ ቆራጭነት ሥልጣን የሚናገሩ ወይም ራሳቸውን ‹አክቲቪስት› ብለው በሰየሙ ግለሰቦች በአገር ውስጥና በውጭ የተደረጉ ዘርን መሠረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮችና ቅስቀሳዎች በቸልታ የታለፉበት ሁኔታ እና የጥቃት አድራሾቹን ማንነት የማድበስበሱ ድራማ፣ ድርጊቱ ከመፈጸሙ በፊት መወሰድ ስለሚገባው ርምጃ  በሚመለከተው የክ/ሃገሩ ፖሊስ አዛዥ በኩል የተሰጠው ተልካሻ ምክንያት የጥንቃቄ ሳይሆን የፖለቲካ ስሌት እንዳለበት ከጥርጣሬ በላይ መናገር ይቻላል፡፡ የአገር መሪ ስለ ይቅርታና ዕርቅ አጥብቆ ቢናገርም ከሽማግሌነቱና ሰባኪነቱ ይልቅ የፖለቲካ ስብእናውን መርሳት የለብንም፡፡ ፖለቲካውም የዘር መሆኑን እንደዚሁ፡፡ የዜግነትና የዘር ፖለቲካን ለማስተባበር መሞከር በጭራሽ ኅብረት የሌላቸውን ታቦትና ጣዖት ባንድነት እንደማኖር ይቆጠራል፡፡ ውጤቱ የታቦተ ጽዮንና የጣዖቱ ዳጎን ይሆናል ታላቁ መጽሐፍ እንደመዘገበው፡፡

3/ ነገደ ብዙ ኢትዮጵያ በዘርፈ ብዙ ታሪክ÷ባህል÷ ትውፊት÷ቋንቋ÷በጋራ መልካም እሴቶች የተሰናሰሉ ማኅበረሰቦች ባንድነትና ባብሮነት ለዘመናት የኖሩባት አገር ነች፡፡ ባለፉት 27 የወያኔ ትግሬ አገዛዝ ዓመታት ማኅበረሰባችን የተፈተለበትን ድርና ማግ ከመሠረቱ ተናግቷል፤ በዘመናት የተገነቡ የእሴት ሥርዓቶቻችን በማጥፋት ለከፋ ማኅበራዊ ድቀት ተዳርገናል፤ በወገን መካከል ሥር የሰደ የመለያየትና የጥላቻ እንክርዳድ በመዝራት አገራዊ ህልውና እና የሕዝብና ግዛታዊ አንድነት በተለይም ማኅበረሰባችን እምነትና ባህልን መሠረት አድርጎ ለዘመናት የገነባው ግብረ ገባዊ ሥርዓት  በአገራችን ታሪክ ተወዳዳሪ በሌለው ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በከፋ የመጨረሻ አደጋ ላይ እንዲገኝ አድርጎታል፡፡ ለዚህም ግዙፍ ጥፋት ከዚህ መንደርተኛ አሸባሪ ቡድን ጋር እጅና ጓንት ሆነው በቅንጅት በመሥራት ላይ የሚገኙ (ባገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ) ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች እንዲሁም ታሪካዊ ጠላቶች እንዳሉ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተሠወረ አይደለም፡፡

እነዚህ ወገኖች ጥፍጣፊ የሰውነት ጠባይ በውስጣቸው ቢገኝ ኖሮ በተፈጥሮ ወንድምና እህታቸው፤ ባንድ አገር ልጅነት ደግሞ ወገናቸውና ዘመዳቸው የሆነውን ኢትዮጵያዊ፣ ፋሽስት ጣልያንን ማረኝ በሚያስብልና መፈጠርን በሚያስጠላ የጭካኔና ግፍ መጨረሻ ባልጨፈጨፉና ከቤት ንብረታቸው ባላፈናቀሉ ነበር፡፡ ለጽንፈኛ የዘር ፖለቲከኞች ከእነሱ ነገድ/ጎሣ ውጭ ያለ ወገን ላይ የሚፈጸም ጥላቻ፣ ግፍ፣ በደልና እልቂት ሆን ተብሎ የሚደረግ በመሆኑ ከጸጸት ‹ነፃ› ናቸው፡፡ መሠረታቸው ሐሰት በመሆኑ  አረመኔያዊ ድርጊታቸውን በሌላ ሐሰት ለመሸፈን የፈጠራ/ሕዝብን የሚያሳስትና የሚያስቆጡ መረጃዎችን በመልቀቅ የሌባ ዓይነ ደረቅ ይሆኑብናል፡፡ ጎሣን መሠረት ያደረገው የቡራዩው ጥቃት በተጠቂዎችና በአካባቢው ነዋሪ ምስክርነት እንደተረጋገጠው ራሱን ቄሮ ብሎ የሰየመው ስብስብ አካል መሆናቸው የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ እነዚህ ወጣቶች ቄሮን ይወክላሉ/አይወክሉም የሚለው የማይረባ ጥያቄ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው የዐቢይ አስተዳደር የፖለቲካ መሠረቴ (constituency) ወያኔ የፈጠረው ‹ኦሮሚያ› የሚባል ክ/ሃገር ነው በሚል ለማስተባበል መሞከሩ የሚጠቅመው ሳይሆን ተአማኒነቱን የሚያወርደው ነው፡፡ ከሠለጠነ ዓለም መጥቶ ፊደል ቆጥሬአለሁ ከሚልና የቄሮ መሪ ነኝ እያለ የሚደነፋ ዕኩይና ዕቡይ የሱ ብጤ በስሜት የሚነዱ አውሬዎች አሰማርቶ በወገን ላይ ሽብር ከመፈጸም አልፎ አሁንም የሽብር ቅስቀሳዎችን፣ ዘርን መሠረት ያደረጉና ወደ የርስበርስ ግጭት የሚመሩ የጥላቻ ንግግሮችን ያለማንም ሀይ ባይነት ሲያሰማና በአገሪቱ ሥራ ላይ ባሉ ሕጎች የሚያስጠይቅ ወንጀል ሲፈጽም በዝምታ ማለፍ ሕግና ሥርዓት አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ በዚህ አካሄድ የዐቢይ አስተዳደር በመነሻው ላይ በወሰዳቸው አበጀህ! ይበል! ያሰኘው አበረታችና ተስፋ ሰጭ ጅምር የለውጥ ርምጃዎችን ተከትሎ በውስጥም በውጭም ያገኘው የፖለቲካ ካፒታል እየተሸረሸረ እንዳይሄድ ሥጋት አለኝ፡፡ አያያዙን ካላወቁበት የፖለቲካ ጥሪት ሲሰበሰብ እንጂ ከእጅ ሲሾልክ አይታወቅም፡፡ የፖለቲካ ካፒታል እንደማኅበራዊውና ኢኮኖሚያዊው ካፒታል ጊዜ አይሰጥም፡፡ ባንድ ጀምበር ብን ብሎ ሊጠፋ ይችላል፡፡

4/ በመርህ ደረጃ ማንኛውም ግለሰብ፣ ማናቸውም ሕጋዊ ዕውቅና ያለው ማኅበር/ድርጅት በወንጀል ድርጊት ከተጠረጠረ አግባብ ያለው የሕግ ሥርዓትን ተከትሎ መጠየቅ እንዳለበት ኹሉንም ያስማማል፡፡ ይህ ሕግና አፈጻጸሙ የዜጎችን ማንነት መሠረት አድርጎ ወይም ፖለቲካዊ ጥቅምን መሠረት አድርጎ በአድልዎ ከተፈጸመ ግን በመንግሥትነት የተሰየመው አካልም ሆነ አንባቢው ቆም ብሎ ማስተዋል ይገባዋል፡፡ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ፖሊስ የዜጋን ቤት የሚበረብርበት አግባብ ሕግ ወጥና ወያኔያዊ አካሄድ ነው፡፡ ዜጎች ተጠርጥረው ሲታሠሩ ምክንያቱን በይፋና ወዲያውኑ አለመግለጽ ወያኔያዊ ተግባር ነው፡፡ (ጠ/ሚሩ አስቀድመን አጣርተን ነው በቁጥጥር ሥር የምናውለው ከሚለው ቃላቸው ጋር ይጣረሳል) ሥራ አጥነትን እንደ ወንጀል ቆጥሮ ዜጎች ጥፋታቸው በፍ/ቤት ሳይረጋገጥ ‹አደገኛ ቦዘኔ› የሚል ባለሥልጣን የአገር ውርደት ምልክት ከሆነው መለስ ዜናዊ በምን ይለያል? በትንሹ ያልታመነ ለትልቁ ጉዳይ ማን ይሾመዋል? አገር ተረጋግቶ ሕዝብ ለተዋደቀለት ዓላማ በጋራ ለመንቀሳቀስ እንዳይቻል በማድረጉ አፍራሽ ተግባር መለ በመሸገው ጠላት ብቻ የሚሳበብ ሳይሆን የርሱን አሠረ ፍኖት የተከተሉ ጽንፈኛ መንደርተኞች (ተረፈ-ወያኔዎች) በአፋጣኝ በሕግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ ለዶ/ር ዐቢይ ያለ የሌለ ምክንያት እየፈለግን፣ የሥጋት ‹ቢሆኖችን› እየፈጠርን የሕግ ማስከበር ዳተኝነትን ማበረታታት ያለብን አይመስለኝም፡፡ ለጠ/ሚር ዐቢይ አጠገቡ ያሉ አፍራሽ ኃይሎች ታላቅ ተግዳሮት እንደሚሆኑት ‹‹ተረፈ ወያኔዎች›› በሚል በጻፍኩት አስተያየት ቀደም ብዬ ለማሳሰብ ሞክሬአለሁ፡፡ (https://www.ethioreference.com/archives/13090) የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ራሱን የማስተዳደር መብት የለውም በማለት ባደባባይ በንቀት የተናገረው የዐቢይ አስተዳደር ባለሥልጣን አሁን ደግሞ አዲስ ስም የተሰጠው ኦዴፓ ፖሊት ቢሮ አባልነት ከፍ የተደረገው አዲሱ አረጋ ለአብነት ይጠቀሳል፡፡  

5/ የወያኔ ትግሬ ዕጣ ፈንታ፤ ዶ/ር ዐቢይ የሚመራው ኦሕዴድ በቅርቡ ስሙን ቀይሯል፡፡ ከወያኔ ትግሬ የመፋታት አንድ ርምጃ ይመስላል፡፡ ወያኔ የፈጠረው ግንባር ‹ኢሕአዴግ› ፈርሶ ከግንባሩም ሕወሓትን አስወጥቶ ፍቺውን የተሟላ ያደርገው እንደሆነ በሂደት የምንመለከተው ይሆናል፡፡ እውነቱን ለመናገር አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ይህንን የግንባሩን ስም ከነግብሩ መጥራትም መስማትም አይፈልግም፡፡ የጠ/ሚር ዐቢይ አስተዳደር ወያኔ ትግሬን ይዞ ለመጪው ምርጫም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሰሶ የሆኑትን ተቋማት በመገንባት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግረን ማለት ዘበት ነው፡፡ ለሞት የሚያደርስ ነቀርሳ ይዞ አገርን ለመታደግ እንዴት ይቻላል? ተረፈ-ወያኔዎቹም በጀመሩበት የጥፋት መንገድ ከቀጠሉ ውለው አድረው ወደ ነቀርሳነት ላለመሸጋገራቸው ምን ዋስትና አለ? ስለሆነም ወያኔ ትግሬ/ሕወሓት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን ለማጥፋት የተነሳ ፋሺስት ቡድን በመሆኑ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት ላንዴና ለመጨረሻ መታገድ ይኖርበታል፡፡ በስም መቀየር ሽፋንም እንዲንቀሳቀስ በጭራሽ መፍቀድ የለብንም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብና የዐቢይ አስተዳደር ይህን ማድረግ ከቻሉ ኢትዮጵያም አካሏ የሆነችውም ትግራይ ነፃ ይወጣሉ፡፡

6/ የሕግ የበላይነት – ሕግን የማስከበር ተግባር፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ የእኔ የሚላቸውና የሚተማመንባቸው ሰላሙንና ደኅንነቱን የሚያስጠብቁለት የፀጥታና ሕግ አስከባሪ ኃይሎች የሉትም የሚል የግል እምነት አለኝ፡፡ ይህም የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣም ወዲህ በተግባር ታይቷል፡፡ ዘርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችና መፈናቀሎች በተፈጸሙበት ቦታ ኹሉ በነዚህ ኃይሎች የታየው ዳተኝነትና አንዳንዴም ከአጥፊዎች ጋር ማበር ብዙዎች ምስክር የሆኑበት እውነታ ነው፡፡ የአገር ውስጡን ለጊዜው አቆይተን አርሶ አደር ወገኖቻችን ከሱዳን ሠርጎ ገቦች ጋር ባደረጉት ትንቅንቅ ጊዜ በገሃድ ታይቷል፡፡ በጎሣ የተደራጀ ሠራዊት ብሔራዊ ጦር ነው ብሎ ለመቀበል እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡  ጥያቄው የጎሣ ተዋጽዖ ይጨምር አይደለም፡፡ ከመነሻው እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የተሳሳትና ለአገር የማይበጅ ነው፡፡ ቊጥራቸው ቀላል የማይባል የሠራዊቱ አባላት የአገር ፍቅር÷ የሕዝብ አለኝታነትና የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ክብር የገባቸውና ያላቸው አይመስሉም፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ሥራ የሚጠበቅብን ይመስለኛል፡፡ ወያኔ ትግሬ በሕግ የበላይነት ስለማያምን ሠራዊቱና ደኅንነቱን ጨምሮ የሕግ አስከባሪ አካላት የሕዝብና የአገር ሳይሆኑ የወያኔን ሥልጣንና ጥቅም አስጠባቂዎች መሆናቸው ባለፉት 27 ዓመታት በወህኒ ቤቶች የተፈጸመው መጠነ ሰፊ ዘግናኝ ስቃዮችና የዚህ አስነዋሪ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ንጹሐን ወገኖቻችን ሕያው ምስክር ናቸው፡፡

ለመሆኑ ፖሊስ የዜጎችን ሰላማዊ ኑሮና ደኅንነት መጠበቅና ማስከበሩ ዋና ተልእኮው መሆኑ ቀርቶ፤በጠላት ወረዳ ያለ ይመስል በድብደባ ልክፍት ተይዞ የዕለት ተዕለት ተግባሩ ዜጎችን መቀጥቀጥ÷አካል ማጉደል÷ማስፈራራትና ማሸማቀቅ አልፎም ተመጣጣኝ ባልሆነ ርምጃ መግደል የተንሠራፋበት የኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ በቂ ትምህርትና ሥልጠና አላገኘም የሚለው ምክንያት ለአውሬነት ጠባይ ማስተባበያ አይሆንም፡፡ ፖሊስ ለሚፈጽመው ሕገ ወጥ ድርጊት በሕግ የሚጠየቅበት አግባብ ቢኖርም ቅድመ ዐቢይ በነበረውም ሆነ በዘመነ ዐቢይ መረን የለቀቁ የፖሊስ አባላት ክስ ተመሥርቶባቸውና ተጠያቂ የሆኑበትን አግባብ አላስተዋልንም፡፡ ክቡር የሆነው የፖሊስነት ሙያ ዝንባሌ የሌለው÷ዓላማው ያልገባውና ዓመሉን ያላረቅ ጋጠወጥ ኹሉ የሚፈንጭበት ሥራ አይደለም፡፡ ባለፉት ሁለትና ሦስት ወራት ውስጥ በወገን ላይ የተፈጸሙ ፋሺስታዊ ድርጊቶች ወያኔና ተረፈ-ወያኔዎች መርዘኛ በሆነው የዘር ፖለቲካ አማካይነት ግብረገብነትን በማጥፋት ከሰብአዊነት የወጡ ‹አውሬዎችን› ለማፍራት መቻላቸውን የተጋፈጥንበት መራር እውነታ ነው፡፡ የፖሊስ ድርሻ ምን ነበር? በዚህ ዕኩይ ድርጊት ውስጥ በሠለጠነው ዓለም ኖረናል÷ፊደል ቆጥረናል÷አንዳንዶችም እስከ ሦስተኛ ‹ድግሪ› ይዘናል የሚሉ ‹ደናቁርት› ድርጊቱን በአሳብና በዕቅድ የሚያስተባብሩ መሆናቸው የመንደርተኝነት ፖለቲካ ምን ያህል አዘቅት እንደሚወርድ ምስክር ነው፡፡ ትምህርትና ዕውቀት ራስን በበጎ ምግባር አንፆ÷ ለበጎ ለውጥ ካላነሳሳ÷ ትሩፋቱ ለአገር ለወገን በቊዔት ከሌለው ምን ረብ አለው? እንደነዚህ ዓይነቶቹ ጉዶች ለአገርና ሕዝብ ታላቅ ሸክም/ዕዳ ናቸው፡፡ በክራቫት የታነቀ አሸባሪ የሚከበርበት፣ ጭርንቁስ የለበሰ ነገር ግን በሥነምግባር ያጌጠ ዜጋ አደገኛ ቦዘኔ የሚባልበት የአስተሳሰብ ድህነት ውስጥ ነው እኮ ያለንው፡፡

ከዚሁ የሕግ ማስከበር ጉዳይ ሳልወጣ ማንሳት የምፈልገው ሌላው ነጥብ መንግሥት መደበኛ ፖሊስና ጦር ሠራዊት አለኝ የሚል እምነት ካለው እንደ አግአዚ ያሉ በየክፍላተ ሃገሩ ‹‹ልዩ ኃይል›› የሚል ሌላ ‹ሽብር› ፈጣሪ ለምን አስፈለገ? ዓላማውና ተልእኮውስ ምንድን ነው? የሕግ መሠረቱስ ምንድን ነው? በይስሙላ ‹ሕገ መንግሥቱ› አግባብ ብናየው እንኳን ኢ-ሕገመንግሥታዊ ነው፡፡ በእኔ አመለካከት አግአዚን ጨምሮ እንዲህ ዓይነቱ ኃይል በኦጋዴን እንደታየው ለአገር ደኅንነትና መረጋጋት አደገኛ ኃይል በመሆኑ ባስቸኳይ በመበተን ‹‹ጤናማዎቹን›› መርጦና አስተምሮ እንደ ፍላጎታቸው በመደበኛ ፖሊስ ኃይል ወይም ጦር ሠራዊቱ ውስጥ እንዲቀላቀሉ፤ የተቀሩትም እንደየዝንባሌአቸው የማገገሚያ ትምህርት ሰጥቶ መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲመሩ ማድረግ፤ በወንጀል የሚጠረጠሩትን ደግሞ ለፍርድ ማቅረብ ይገባል፡፡

7/ ስለ ዴሞክራሲ ተቋማት – የምርጫ ቦርድ ጉዳይ፤ ነፃ፣ገለልተኛና ተአማኒነት ያለው ሆኖ እንደ አዲስ መዋቀር ከሚገባቸው የዴሞክራሲ ተቋማት አንዱ የምርጫ ቦርድ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ እስካሁን ባለው ‹‹የወያኔ ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ›› የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት 27 ዓመታት ለደረሰበት ግፍና መከራ አባሪ ተባባሪ በመሆን የሚጠየቅ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ኹሉ በሚሳተፉበት ሕጉን ጨምሮ በአዲስ መልክ መደራጀት ይኖርበታል፡፡ በጽ/ቤቱ ከላይኛው እስከ ታችኛው ዕርከን የሚገኙ ኃላፊዎችም ሆኑ ተራ ሠራተኞች በሙሉ መቀየር ይኖርባቸዋል፡፡ ወያኔ ቢሮክራሲው ውስጥ ካደረገው ተሞክሮ ተነስተን የጽዳት ሠራተኛ ሳይቀር (በወሬ አቀባይነት) በሕግ አግባብ ሳይሆን በዘር ቋጠሮ ሲሰበስብ እንደኖረ ሂደቱን የተከታተልነው ምስክሮች ነን፡፡

የምርጫ ቦርድን በሚመለከት ‹‹በነተበ ጨርቅ ላይ አዲስ ዕራፊ መጣፍ›› በሚል ርእስ ያቀረብኹት አስተያየት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ (https://www.ethioreference.com/archives/13541) በቅርቡ የቦርዱ ጽ/ቤት ወደአገር ቤት ለገቡት የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች በድጋሚ የምዝገባ ጥሪ ማድረጉን ስሰማ እነዚህ ሰዎች ጤነኞች አይደሉም ወይ አሰኝቶኛል፡፡ አማርኛ ቋንቋ የሚገባቸው ከሆነ እየተናገርን ያለነው አሁን ያለው ወያኔ ትግሬ ያደራጀውና የወያኔን ፈቃድ ለመፈጸም ሲተጋ የኖረው፣ ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት የሚል ሎሌዎች ስብስብ በመሆኑ እንኳን ምርጫ ለመምራት የምዝገባ ጥሪ ለማድረግም ብቃትም ተአማኒነትም የለውም ነው፡፡ ነገሩ የደንቆሮ ልቅሶ ዓይነት ሆነብን እኮ ጎበዝ፡፡ ይህ ጅምር የዐቢይ አስተዳደር ዴሞክራቲክ ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ በሆነ መልኩ ለማዋቀር በይፋ የገባውን ቃልና ያሳየውን ቁርጠኝነት እንድንጠራጠር የሚያደርግ ነው፡፡

በሌላ በኩል የወያኔን የጊዜ ሰሌዳ ተከትሎ በአሁኑ ሰዓት ምርጫ ለማድረግ መጣደፉ ተገቢ አይደለም የሚል እምነት አለኝ፡፡ የአገር አለመረጋጋት ዋናው ምክንያት ሆኖ፣ በሽብር ስትናጥ በቆየች አገር ውስጥ በትክክል መሥራት የሚችሉ ተቋማት የሉንም፡፡ ወያኔ ለራሱ የጥፋት ዓላማ ያደራጃቸው አካላት እና በነዚህ አካላት ውስጥ የተሰገሰጉ በዘር የተቧደኑ ኃላፊዎች ወያኔ ትግሬ ከዘረጋው የዘረኝነት ስካር (hangover) የተላቀቁ አይደሉም፡፡ አልፎ አልፎ ‹ባዲስነት› የተሰየሙትም ከዚህ ቅኝት ውጭ ስለመሆናቸው ዋስትና የለም፡፡ አገርን የምናስቀድም ከሆነ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ምርጫ ማካሄድ ብልህነት/አስተዋይነትም አይመስለኝም፡፡ ምርጫው ሕጋዊ ተቀባይነትና ተአማኒነት (electoral legitmacy) ይኖረዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ጠ/ሚር ዐቢይ ምርጫው ድርጅታቸው ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲካሄድ አጥብቀው ለመግፋታቸው የሰጡት ምክንያት አገር ካለችበት አጠቃላይ ዓውድ አኳያ ሳየው አሳማኝ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡

8/ ብዙኃን መገናኛ፤ የነአቶ ለማን ቡድን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ገርበብ ብሎ የተከፈተው የብዙኃን መገናኛ ህዋ እና አንፃራዊ ነፃነት ወያኔ ተቆጣጥሮት የነበረውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከ15 ዓመታት በኋላ እንድከፍት አድርጎኛል፡፡ ይሁን እንጂ ‹የጫጉላው ጊዜ› አበቃ መሰለኝ አገርሽቶበት ወደ ወያኔያዊ ቅኝቱ ተመልሷል፡፡ ለነገሩ ከአብዛኛው ሆድ አደር ‹ጋዜጠኞቹም› ሆነ ከድርጅቱ እምብዛም የጠበቅኩት ነገር የለም፡፡ ከመጣው ጋር አጨብጫቢዎችና ወረተኞች መሆናቸውን አውቃለኹ፡፡ ከፊሉም በዘር ቋጠሮ የተሰባሰበ ነው፡፡

ስልታዊ ደፈጣና ማፈግፈግ ካደረጉ፣ ለጊዜው ተመሳስለው ለማደር ከመረጡና የወያኔ ትግሬ ፕሮፓጋንዳ መሣሪያ የሆኑት ዋልታ÷ ፋና እና ሪፖርተር የሚፈነጩበትን ‹የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ሆነ ራዲዮ ለማየትና ለመስማት እምብዛም ፍላጎቱ የለኝም፡፡ አገዛዝን በማገልገል የተጠመዱ፣‹ባርነትን› የለመዱ፣ የራሳቸውን ነፃ አስተሳሰብ የሌላቸው ‹ብዙኀን መገናኛዎች› እንኳን ‹‹አራተኛው የመንግሥት ክንድ›› ሆነው በመንግሥታዊ ተጠያቂነትና ግልጽነት ላይ የማኅበረሰባችን ዓይንና ጆሮ ሆነው ቊጥጥር በማድረግ ሊያገለግሉ ቀርቶ ለለውጥም ሆነ ለዴሞክራሲ ግንባታ ፋይዳ ይኖራቸዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በዚህ ላይ ሙያዊ ብቃትና ሥነ ምግባር አለመኖር ሲታከልበት በጨለማ ላይ ገደልና የዛፍ ጥላ መጨመር ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሚታየውን ታላቅ ክፍተት ሙያዊ ብቃትን ከመርህ ሰውነት ጋር፣ አገር መውደድን ከመልካም ሥነ ምግባር ጋር ገንዘብ ያደረጋችሁ የግሉ ዘርፍ ባለሙያዎች (ካላችሁ) ተግታችሁ ሕዝባችሁን የምታገለግሉበት ወቅት አሁን ነው፡፡  

በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉና በኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት የሚንቀሳቀሱ ብዙኃን መገናኛዎች አገዛዝን ወይም ሥልጣን ላይ ያለን ገዢ ፓርቲ እያገለገሉ የሚቀጥሉበት አሠራር ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቆም እንዳለበት የምንስማማ ከሆነ፣ ‹ሞተሩ› እንዳለ ወርዶ ሙሉ ቅያሬና እድሳት (overhaul መደረግ) ከሚያስፈልጋቸው የዴሞክራሲ ተቋማት አንዱና ዋነኛው መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን ነው፡፡ ይህ አስተያየት የመንግሥት ዓምድ ለሆነው የፍትሕ አስተዳደር እና አካላቱ፤ለማኅበረሰብ ተቋማት (ሲቪል ሶሳይቲ)፤ የመንግሥት አስተዳደር (ሲቪል ሰርቪስ/ቢሮክራሲው)፤ እነ ሌሎች የዴሞክራቲክ ተቋማት ግንባታም በእኩል ተፈጻሚነት አለው፡፡ እነዚህን ተቋማት መገንባት ጊዜ ወሳጅ ነው በሚል ምክንያት ለማንወጣው የቀውስ አዙሪት የሚዳርገን ሆያ ሆዬ ውስጥ ሳንገባ ሰከን ብለን ሁለት ሦስቴ አውለን አሳድረን ብናስብበት መልካም ይመስለኛል፡፡ ዴሞክራሲ ዘላቂ የሚሆነው ተቋማዊ ሲሆን፣ በሕግ ሲደገፍ፣ የዴሞክራቲክ እሴቶች በተግባር ሲገለጹና ዴሞክራሲያዊ ባህል ሥር ሲሰድ ነው፡፡ ለዚህ መድከሙ የዐቢይን አስተዳደር፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ የማኅበረሰብ ተቋማትንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላትን ትውልድን አሻግሮ የሚያዩ አርቆ አሳቢዎች ያደርጋቸዋል፡፡  

9/ ማኅበራዊ ድቀት/የሞራል ልሽቀት፤ በዚህ አስተያየት ደጋግሜ እንደገለጽኩት እና በትውፊታዊው ‹የየኔታ ትምህርት ቤት› አልፈን፣ ለሠፈር/ለጎረቤት ታዘን፣ ታላላቆቻችንን ታዘንና አክብርን፣ በሽማግሎች ተመክረን÷ ተገሥፀንና ተመርቀን፣ በሃይማኖት አባቶች ትምህርት÷ዕዝናትና ቡራኬ ተኮትኮትኩተን፣ ያገር ፍቅር÷ የወገን ፍቅር÷የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ክብር ገብቶን፣በዘመናት የዘለቀ የጋራ ታሪካችንን÷ባህላችንና ትውፊታችንን ገንዘብ አድርገን ወዘተ ላደግን ኢትዮጵያውያን አሁን ላለፉት 27 ዓመታት (ችግሩ ከደርግ ዘመን የጀመረ ይመስላል – በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ያለፈው አብዛኛው ወጣትና የደርግ አባላት ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና እምነት ፍጹም ባፈነገጠ መልኩ ያሳዩት ዕብደትና የትውልዱ በደም አበላ ተጠራርጎ ማለቅ) ባገራችን ሆን ተብሎ በዕቅድ እየተፈጸመ ያለውንና የመልካም እሴቶች ጥፋት/የሞራል ልልነት በዚህም የታየው አስደንጋጭ የለጋ ወጣቶች ‹አውሬነት› በዚህ ትውልድ መገኘትን እንድንጠላ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን ምነው ባልተፈጠርኹ የሚያሰኝ ሆኖ አግቼዋለሁ፡፡ በወጣቶቹ ላይ ጣት ለመቀሰር አይደለም፡፡ ጥፋቱ በወያኔና ተረፈ-ወያኔዎች (ጥላቻን የሚሰብኩ ጽንፈኛ የዘር ፖለቲከኞች) ብቻ የመጣ አይደለም፡፡ ኹላችንም የመጠን ጉዳይ ካልሆነ በቀር ኃላፊነት መውሰድ አለብን፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ ትምህርት ቤት፣የእምነት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የማኅበረሰብ ተቋማት ውድቀት ነው፡፡ ይህ አዝማሚያ ከቀጠለ አገርም አይኖረንም፤ እንደ አንድ ሕዝብም መቀጠል አንችልም፡፡ ጊዜ ሳንሰጥ ከቤተሰብ ጀምረን ይህንን የአገር ሕማም ለማዳን በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ጊዜና ቦታ ሳንመርጥ መደበኛ ባልሆነ መልኩ የኛው ልጆች የሆኑ ወጣቶቻችንን እናስተምር፣ እንምከር፣ እንገሥፅ፡፡  በዝርዝር የጠቀሰናቸው ተቋማት ደግሞ በተጠና ሁኔታ ዕቅድና መርሐ ግብር በማዘጋጀት መደበኛና ተከታታይነት ባለው መልኩ ወጣቶችን ማስተማርና ማነፅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግሥት ፖለቲካውን ከዘረኝነት አስተሳሰብ፣ ከጥላቻ ንግግርና ቅስቀሳ ነፃ ያድርግልን፡፡ በዚህ ዓይነቱ ነውረኛ ድርጊት የተሠማሩትንም ሆነ የሚሠማሩትን በሕግ አደብ እንዲያስገዛልን አበክረን እንጠይቃለን፡፡

10/ መሠረታዊ አገልግሎትን በሚመለከት፤ ዛሬ በአዲስ አበባ የተለያዩ ክ/ከተሞች የውኃና መብራት አገልግሎቶች ቅንጦት ሆነዋል፡፡ ሲለቀቁም በምሽት ወይም በሌሊት በመሆኑ ከድጡ ወደ ማጡ እየሄድን ይመስላል፡፡ አቅም ያላቸው የታሸገ ውኃ ገዝተው ሲጠቀሙ፤ በኤሌክትሪኩ ኃይል ረገድ ነጋዴዎች ወይም አንዳንድ ከዝርፊያ ጋር ንክኪ ያላቸው ግለሰቦች በጄኔሬተር ይጠቀማሉ፡፡ ቀሪው አዲስ አበቤ እንደለመደው ኑሮውን በአጃቢነት ቀጥሏል፡፡ በነዚህ አገልግሎቶች መስተጓጎል የመለዎቹ ሽፍቶች እጅ ካለበት ይነገረን፡፡ ቅድመ ዐቢይ ያለጥርጥር ነበረበት፡፡ የአሁኑን የምታውቁ አሳውቁን፡፡

በመጨረሻም መንግሥትና ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በናንተ የጋራ ጥንቃቄ ጉድለት አደጋ በተከሠተ ቊጥር ተሰባስቦ የማውገዝ ፖለቲካችሁ የትም ፈቅ አያደርገንም፡፡ ከፍ ብዬ ለማንሳት እንደሞከርኹት ጊዜው በምርጫ ለሚገኝ ሥልጣን ግርግር የሚፈጠርበት ሳይሆን አገር የማረጋጋትና ለመንግሥተ ሕዝብ የሚያበቃንን ዴሞክራሲን ተቋማዊ የማድረጉ ፈታኝ ተግባር ላይ ጊዜ ሳንሰጥ በጋራ ለመሥራት በቁምነገር የምንመክርበት ወሳኝ ሰዓት ላይ እንዳለን ይሰማኛል፡፡ የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር ጅምር ለውጡ የመጣው ነፃነት በጠማቸው ኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት ነው የሚል እምነት እንዳለው በተደጋጋሚ ስለገለጸ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃ÷ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ የሚመራውን ግለሰብና የፖለቲካ ማኅበር እስኪመርጥ ድረስ፣ የዐቢይ አስተዳደርና ተቃዋሚዎች ባንድነት የሽግግር አካል መሆናችሁን በማመን÷አንዱ የበላይ አንዱ የበታች ሳይሆን÷ ለሕዝብ አርዓያ በሚያደርጋችሁ የእኩልነትና የመከባበር መንፈስ አገር የማረጋጋቱንና ለኹላችን እኩል የምትሆን ኢትዮጵያን በዴሞክራሲያዊ ዓለት ላይ ለመገንባት የዴሞክራሲያው ሥርዓት ጡቦችን በጥንቃቄ ማስቀመጥን እንጀምር እላለሁ፡፡

አምላከ ኢትዮጵያ ፈተናውን በትእግስት አልፈን ኢትዮጵያችንን በተራራ ላይ ያለች ብርሃኗ ለአፍሪቃ የሚተርፍ ቅድስት ከተማ ያድርግልን፡፡

 

Filed in: Amharic